ዓይን እያየ ወደገደል? ምን ይባላል!

መስፍን ወልደ ማርያም
ነሐሴ 2008

በአገዛዙ ወንበር ላይ ተጣብበው የተቀመጡት ሰዎች ሁሉ ብዙ ቢሆኑ ይነጋገሩ ነበር፤ ቢነጋገሩ ሁሉም በየፊናውና በየአቅጣጫው በራሱ ዓይኖች ያየውንና በራሱ ጆሮዎች የሰማውን፣ በራሱ አእምሮ አብሰልስሎ እያቀረበ ክርክር ይፈጠር ነበር፤ ከክርክሩ የሚፈልቀው እሳት ከተለያዩ ሰዎች የሚወረወሩትን ሀሳቦች እያቀለጠ አዲስ መመሪያ ያወጣ ነበር፤ ነገር ግን ተጣብበው የተቀመጡት ተጣብቀው አንድ በመሆናቸው ዓይን የሚያየውና ጆሮ የሚሰማው አንድ ነው፤ አእምሮ ሲጨፈለቅና ሲጣበቅ ሕይወቱን ያጣል፤ ስለዚህም የታየውና የተሰማው ጎዳ ሆኖ ሲቀርብ ውጤቱም ጎዳ በመሆኑ ክርክር የለም፤ ክርክር አለመኖሩ የመካንነት ምልክት ነው፡፡
አገር ተረብሽዋል፤ ሥርዓት ጠፍቷል፤ መደማመጥ ተስኖናል፤ የገነፈለው ስሜት እያቀለጠ ወደሞት ጅረት እየወሰደን እንደሆነ ወንበሩ ላይ ተጣብቀው የተቀመጡት ገና አልተገነዘቡም፤ የዓለም ሕዝብ በሙሉ ተገንዝቦታል፤ በወንበሩ ላይ ተጣብቀው የተቀመጡት በሚገነዘቡበት ጊዜ የሞት ጅረት አጥለቅልቆናል፤ መድኅን የሚመጣው ከሞት በፊት ነው፤ የዱሮ አዝማሪ እንዳለችው፡–

አንጀቴ ተቆርጦ ከሆዴ ከወጣ፣
እንግዲህ ሀኪሙ ምን ሊቀጥል መጣ!

ሳምሶን ‹‹ውጽዒ ነፍስየ ምስለ ነፍሶሙ፤›› ብሎ ምሰሶውን ገፍቶ እንደጣለው ዛሬም በወንበሩ ላይ የተጣበቁት ምሰሶውን ገፍቶ የመጣልና የሦስት ሺህ ዓመታት የኢትዮጵያን ታሪክ ለማፈራረስ ጉልበቱ እንዳላቸው ያምኑ ይሆናል፤ ‹‹ውጽዒ ነፍስየ ምስለ ነፍሶሙ›› ለማለትና ውጤቱንም ለመቀበል ከቆረጡ ያለምንም ጥርጥር በቂ ጉልበት አላቸው፤ ነገር ግን ይህ ጉልበት የተባረከና የተቀደሰ አይደለም፤ ዝናብ እንደሚወርድበት ክምር ጨው ነው፤ ዝናቡ ከጉልበት ቁጥጥር ውጭ ነው፤ በዚያ ላይ አንድ የሁሉም አገር ታሪክ ያረጋገጠው እውነት አለ፤ አሸናፊ ይጠናከራል፤ ተሸናፊ ይዳከማል፤ ሕዝብ ተሸናፊ ሆኖም አያውቅ፡፡
በዚያ ላይ ወደእምነት ደረጃ ከፍ ስንል ኃያል እምኃያላን የሆነ አምላክ አለ፤ በጉልበታቸው የሚታበዩትን ይታገሳቸዋል እንጂ ለመጨረሻ ድል አያበቃቸውም፤ የደካሞቹንም ስቃይና መከራ የሚያበዛው የድል አክሊል አዘጋጅቶላቸው ይሆናል፤ ጉልበተኞች ከዕብሪታቸው ሲጸዱና የእግዚአብሔርን ኃያልነት ሲቀበሉ በነሱ ላይ ድልን ለተጎናጸፉት ያስተምራሉ፤ የጉልበተኛ ሥርዓት ወድቆ የሕግ ሥርዓት ይተከላል፤ አሸናፊም ተሸናፊም በሕግ ጥላ ስር ይተዳደራሉ፡፡
አሸናፊም ተሸናፊም አንድ ዋና ነገር ቦግ ብሎ እንዲታያቸው እመኛለሁ፤ ትግላቸውም ሆነ ውጤቱ የግል አይደለም፤ ከመሀከላቸው የአምባ-ገነንነት ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ቀስ በቀስ ትግሉን የግል እያደረጉ ሄደው በመጨረሻ ድሉንም የግል ያደርጉታል፤ ሌላ ቀርቶ ቤተ-ሰቦቻቸውንም ይረሳሉ፤ አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ የብዙ ሰዎችን ትብብርና ከባድ መስዋእትነትን የከፈሉ ሰዎችን የያዘ ነው፤ እነዚህ በብዙ መንገድ ብዙ ዓይነት መስዋእት የከፈሉ ሰዎች ለሚቀጥሉት ትውልዶች የሚያወርሱት ብዙ ነገር አለ፤ ራሳቸውን ሀብታም ማድረጋቸውንና ሰዎችን እንደፈለጉ ሲቆርጡና ሲፈልጡ መኖራቸውን ማንም እንደውርስ አይቀበላቸውም፤ ዘመን አልፎበታል፤ ታሪክም አይሆንም፤ የተጋድሎ ታሪካቸው፣ ለነጻነት፣ ለእኩልነትና ለአገር ባለቤትነት የሚያበቃና ለተከታይ ትውልዶች ሁሉ አርአያ የሚሆን ታሪክ በኩራት የሚተላለፍ ይሆናል፡፡
በቀል፣ ጭካኔና በስሜት መገዛት ውሎ አድሮ ያጋልጣል፤ የሀብታሙና የተመስገን ተገቢውን ህክምና ማጣትና መሰቃየት በምድርም በሰማይም ያስቀጣል፤ ይህንን ባህል አድርገን እንዳንቀጥል እሰጋለሁ፤ አእምሮአችንን ጡንቻ ብቻ ስናደርገው የማሰብ ሥራውን ያቆማል፤ ጠላት ለሚባለው ሰው የተመኙለት ገደል ላይ ዓይኖችን ተክሎ መራመድ ራስን ወደዚያ ገደል ማስገባት ነው፡፡

Posted in አዲስ ጽሑፎች | Leave a comment

ከትናንት ወዲያ፣ ትናንትና ዛሬ

መስፍን ወልደ ማርያም
ነሐሴ 2008

ዛሬ ላይ ቆሜ ወደኋላ ሳይ የትናንት ወዲያው ይናፍቀኛል፤ ትናንት ወዲያን አይቼዋለሁ፤ አውቀዋለሁ፤ ትናንትንም አይቼዋለሁ፤አውቀዋለሁ፤ ዛሬንም እያየሁትና እያወቅሁት ነው፤ ከትናንት ወዲያ በጃንሆይ ዘመን የአገዛዙ ነቃፊ ነበርሁ፤ የወደፊቱን የማየት ችሎታ ስለሌለኝ የጃንሆይን አገዛዝ ነቃፊ ነበርሁ፤ በትናንት ወዲያ ላይ በጃንሆይ ዘመን ላይ ቆሜ ዛሬን የማየት ችሎታ ቢኖረኝ የጃንሆይን አገዛዝ ነቃፊ አልሆንም ነበር፤ ትናንትን፣ የደርግን ዘመን ከዛሬው ከወያኔ ዘመን በመሠረቱ እምብዛም የማያለይ በመሆኑ አይናፍቀኝም፤ የዛሬው የወያኔ ዘመን አስመረረኝ፤ ምርር ብሎኛል፤ እንዳልሰደድ ቀዳማዊ ምኒልክ ያለውን ተከታይ ነኝ፤ እንዲህ ብሏል፡–

‹‹እናቴንና አገሬን እተው ዘንድ አይቻለኝም፤›› እናቴ ‹‹በጡቶቿ አምላኛለችና››፡፡

እናትና አባቴ የኢትዮጵያን ምድር ሆነዋል፤ አባቴ በማይጨው ዘምተው በጥይት ቆስለዋል፤ የመርዙንም ጋዝ በትንሹ ሳንባቸውን ሳይጠብሰው አልቀረም፤ ይቺን እናትና አባቴ አፈር የሆኑላትን አገር ትቼ መሰደዱ ስለማይሆንልኝ እየመረረኝ የመድኃኔ ዓለምን ምሕረት እጠብቃለሁ፡፡
ለምን የጃንሆይ ዘመን ይናፍቅሃል? ለሚለኝ የምሰጠው መልስ የሚከተለው ነው፤ በጃንሆይ ዘመን ኢትዮጵያ የታሪክ ክብርዋ ርዝራዥ ነበረ፤ ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሱን ችሎ በነጻነት የኖረ፣ በተደጋጋሚ የመጡበትን የተለያዩ ወራሪዎች እያሳፈረ የመለሰ ቆራጥ፣ ጀግናና ኩሩ ሕዝብ መሆኑን ዓለም በሙሉ አምኖ የተቀበለው ጉዳይ ነበር፤ በዘመኑም ከተባበሩት መንግሥታት ጦር ጋር ኮሪያ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ከአሥራ ሰባት አገሮች አንዱ ቢሆንም አንድም ምርኮኛ፣ አንድም ሬሳ በጠላት እጅ ሳያስገባ የተመለሰ ብቸኛ ጦር ነበር፤ ያኮራል፡፡
ከኢትዮጵያ ለመውጣት ቪዛ ማገኘት ቀላል ነበር፤ በዚያን ጊዜ ምን ዓይነት ኢትዮጵያዊ ነው ለመሰደድ የሚያስብ? አሜሪካ በየዓመቱ የሚመድበውን የኢትዮጵያን የስደት ድርሻ የሚጠቀሙበት ጥቂቶች ግሪኮችና አርመኖች ነበሩ፤ አርባ ሺህ ግድም ጦር ይዛ የምትፈራ፣ ደሀ ሕዝብ አቅፋ የምትኮራና የምትከበር፣ ጮሃ ሳትናገር የምትሰማ አገር ነበረች፤ እምነት የሚጣልበት የጨዋ ሕዝብ አገር ነበረች፤ ይህ ነው የናፈቀኝ!
ዛሬ በየጋዜጣው ላይ የማነበውና የማየው ፎቶግራፍ አሳፈረኝ! ውርደቱ አንገፈገፈኝ! ከሁሉም ይበልጥ ደግሞ ምንም ማድረግ አለመቻሌ፣ ኢምንትነቴ ያንገበግበኛል፤ አንድ ወጣት በባቡር መንገድ ላይ ወድቆ አምስትና ስድስት ፖሊሶች እየተሻሙ በዱላ ሲደበድቡት፣ በጫማቸው ቦታ ሳይመርጡ ሲረግጡት እነዚህ ከኛው የተወለዱ፣ በእኛው ባህልና እምነት ያደጉ፣ ለሕዝብ ደኅንነት የተሰማሩ ናቸው ወይ? የሚፈጽሙት ግፍ ጀግንነት ይመስላቸው ይሆን ወይ? ልጆች ያላቸው ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው እነዚህን የግፍ ምስሎች በጋዜጣም ሆነ በቲቪ ሲያዩ እንደሚያማቸው ይገነዘባሉ ወይ?
በሚያዝያ 30/1997 በሚልዮን የሚቆጠር ሕዝብ በጨዋነት ወጥቶ በጨዋነት ተበተነ፤ ለምን አይቀጥልም? እስከመቼ ተፈራርተን እንኖራለን? በሠለጠነ መንገድ መነጋገር አልቻልንም፤ በሰላማዊ ትግል መነጋገር አልቻልንም፤ በግድ ወደሕገ አራዊት መግባት አለብን?

Posted in አዲስ ጽሑፎች | 1 Comment

ወልቃይት የማን ነው? የማይረባ ጥያቄ

 

 

መስፍን ወልደ ማርያም

ነሐሴ 2008

 

አንድ

በነገረ አስተሳሰብ ወይም በአስተሳሰብ ሕግ (ሎጂክ) ትምህርት ላይ አንድ የማስታውሰው ምሳሌ አለ፤ ‹‹ሚስትህን መደብደብ ትተሃል ወይ?›› የሚል ጥያቄ ነው፤ ጥያቄው የሚነሣው ጠያቂው አውቃለሁ ብሎ ከያዘው እውቀት ወይም እምነት ነው፤ ስለዚህም ጠያቂው የሚፈልገው ጥያቄ ለማስተላለፍና መልስ ለማግኘት አይደለም፤ ጠያቂው የሚፈልገው በጥያቄ መልክ የራሱን ‹‹እውቀት›› ወይም እምነት ለተጠያቂው ለማስተላለፍና ተጠያቂውን የጠያቂው ደቀ መዝሙር ለማድረግ ነው፡፡

ሚስትህን መደብደብ ትተሃል ወይ? መልስ የሌለው ጥያቄ ነው፤ ‹‹አዎ›› የሚል መልስ ሰውዬው ሚስቱን ሲደበድብ እንደነበረ አመነ ማለት ነው፤ ‹‹አልተውሁም›› ከአለ በራሱ ላይ መሰከረ፤ ሁለቱም መልሶች ተጠያቂውን የሚያስወነጅሉ ስለሆኑ መልስ አይደሉም፤ ከዚያም በላይ ጥያቄው ትክክል አይደለም፤ የማይረባ መጥፎ ጥያቄ ነው፡፡

‹‹ወልቃይት የማን ነው?›› የሚለው ጥያቄ ትክክል አይደለም፤ የማይረባና መጥፎ ጥያቄ ነው፤ ጠያቂው የሚፈልገው መልስ የአማራ ነው፤ የጎንደር ነው፤ የትግሬ አይደለም፤ የሚል ነው፤ ነገር የሚገባው ተጠያቂ ጥያቄውን ጠያቂው በፈልገው መልክ አይመልስለትም፤ ሊመልስለትም አይገባም፤ ወልቃይት የኢትዮጵያ ነው የሚል መልስ አይፈለግም፤ የማይፈለግበትም ምክንያት ‹‹ወልቃይት የኢትዮጵያ ነው፤›› ማለት ወልቃይትን ከጎሠኛነት አጥር ስለሚያወጣ ነው፤ የትግራይ አይደለም፤ የአማራ አይደለም፤ የኢትዮጵያ ነው፤ አሁን ትግራይና አማራ የኢትዮጵያ ናቸው፤ ይህ ከተባለ በኋላ ወልቃይት የትግራይ ነው? ወይስ የአማራ? የሚለውን ጥያቄ ማንሣት የጎሠኛነት ጥያቄ ነው፤ የኢትዮጵያዊነት ጥያቄ አይደለም፤ ጥያቄው የማይረባ የሚሆንበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው፤ ሁለተኛው ምክንያት የጎሠኛ ጥያቄ በመሆኑ የወያኔን የጎሠኛ መመሪያ የሚያከብር መሆኑ ነው፡፡

ትልቁና መሠረታዊው ጥያቄ በአማራ ክልል ስር የነበረው ወልቃይት በወያኔ አገዛዝ ወደትግራይ ክልል መግባቱ ነው፤ እዚህ ላይ ጥያቄው የወልቃይት ወረዳ ወይም አውራጃ ነው፤ በውስጡ የሚኖሩት ሰዎች የጎሣ ዓይነት ወይም የጎሣ ስብጥር አይደለም፤ የፈለገውን ዓይነት አንድ ጎሣ ወይም የብዙ የጎሣ ስብጥር ሊኖርበት ይችላል፤ ክርክሩ መሆን ያለበት የወልቃይት አውራጃ ከጎንደር ክልል ወጥቶ ወደትግራይ የገባበት መንገድ ትክክል አይደለም፤ የአስተዳደር ለውጡ የተፈጸመው የፌዴራል መዋቅሩን ሥርዓት በጣሰ መንገድ አንዱ ክልል (ትግራይ) በሌላው ክልል ላይ የጉልበተኛነት ወረራ አካሂዷል ነው፤ ይህ ወረራ ሕጋዊ አይደለም፤ ይህ ወረራ ሊቀለበስ ይገባል፤ ዋናው መቋጠሪያ ይኸው ነው፡፡

ግን ጉዳዩን የጀመርነው ከመሀሉ ነው፤ ሲጀመር ወያኔ ከኦሮሞ ቡድኖች ውስጥ ኦነግን መረጠና አማርኛ ተናጋሪውን አለ እያለ እንደሌለ ቆጠረው፤ በዚያን ጊዜ ኦሮሚኛ ተናጋሪዎቹም ኢፈትሐዊነቱን አልተናገሩም፤ ዋና የፖሊቲካ ጉዳይ አድርገው አላነሱትም፤ ለምን? እነሱ በሎሌነት በመመረጣቸው በደስታ ተውጠው ስለነበረ ጌቶቻቸውን ለማስቀየም ፍላጎት አልነበራቸውም፤ ግን ወያኔ በእጁ ያሉትን ምርኮኞች ከአደራጀ በኋላ ኦነግ ተባረረና በኦሕዴድ ተተካ፤ የኦነግ መሪዎች አገር ውስጥ ሆነው ለመታገል የሚያስከፍለውን ዋጋ ላለመክፈል በአሜሪካና በአውሮፓ ተቀምጠው በስልክ ‹‹ትግሉን›› መምራት መረጡ፤ ወያኔ አነግን በብዙ መንገድ ተጠቅሞበታል፤ አንደኛና ዋናው አማርኛ ተናጋሪውንና ኦሮምኛ ተናጋሪውን ለመለያየትና በቅራኔ ለማጋጠም፤ ሁለተኛ የኦሮሞ መሪዎች ነን የሚሉ ሁሉ ለወያኔ ትሑት አገልጋይ ከመሆን ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው አረጋገጠላቸው፤ ኦነግንና እስላማዊ ኦነግን አፋጅቶ በኦሕዴድ አጋዥነት ሁለቱንም ከትግል መድረኩ አስወጣቸው፡፡

አለ ተብሎ እንደሌለ የተቆጠረው አማርኛ ተናጋሪው በነታምራት ላይኔ፣ በነበረከት ስምዖን፣ በነህላዌ ዮሴፍ፣ በነተፈራ ዋልዋ፣ (ሁሉም ያለጥርጥር አማርኛ ተናጋሪዎች ናቸው፤ ነገር ግን ከየት ከየት እንደበቀሉ አጠራጣሪ ነው፤) ተወከለ፤ ከጎንደርም ይሁን ከጎጃም፣ ከወሎም ይሁን ከሸዋ የእነዚህን ሰዎች ውክልና የተቃወመ የለም፤ እንዲያውም ለአሽከርነቱ ውድድር ነበር፤ በሁለቱ ድርጅቶች — በብአዴንና በኦሕዴድ — አማካይነት ወያኔ ወደሰባ በመቶ የሚጠጋውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በቁጥጥሩ ስር አደረገ፤ ይሄ ሁሉ ሲሆን በአገር ውስጥ ያሉት የአማርኛ ተናጋሪውና የኦሮምኛ ተናጋሪው ወኪሎች ነን ባዮቹ ለፍርፋሪ ሲፎካከሩና ሲነታረኩ ወያኔ የራሱን ክልል በትምህርትና በልማት ለማሳደግ እየሞከረ ነበር፡፡

ለእኔ ፍሬ ነገሩ አማርኛ ተናጋሪውም ሆነ ኦሮምኛ ተናጋሪው ሃያ አምስት ዓመታት ሙሉ እየተፎካከሩ ወያኔን ከማገልገል ሌላ መብትና ሥልጣን ፈልገው አያውቁም፤ ስለዚህም ከማይናገር ከብቱን፣ ከማይራገጥ ወተቱን እንደተባለው ወያኔም በከብቱም በወተቱም ተጠቀመበት፡፡

 

ሁለት

በ1996 ዓ.ም. የክህደት ቁልቁለት በሚል ርእስ ትንሽ መጽሐፍ አሳትሜ ነበር፤ በዚያ መጽሐፍ ውስጥ በገጽ 96ና 97 መሀከል ካርታዎች አሉ፤ ከነዚህ ካርታዎች አንዱ የኢጣልያ ምሥራቅ አፍሪካ (AFRICA ORIENTALE ITALIANA) 1928-1933 ዓ.ም. የሚል ነው፤ በዚያ ካርታ ላይ ፋሺስት ኢጣልያ ትግራይን በሙሉና አፋርን በሙሉ በኤርትራ ክልል ውስጥ አድርጎት ነበር፤ በደቡብም የኢጣልያን ሶማልያ ወደሰሜን ገፍቶ ኦጋዴንን በሙሉና ግማሽ ባሌን ጨምሮበት ነበር፤ ምዕራቡን ክፍል — ወለጋን፣ ኢሉባቦርን፣ ጋሞ ጎፋን፣ ሲዳሞን በአንድ ላይ አስሮ ጋላና ሲዳማ የሚል ስያሜ ሰጥቶት ነበር፤ ሀረር ሰሜን ባሌንና አርሲን ጠቅልሎ ነበር፤ ወያኔም ከፋሺስት ኢጣልያ የወረሰውን አስተሳሰብ ይዞ የጎሣ ክልሎችን ፈጠረ፤ በዚያን ጊዜ ግማሹ እልል እያለ ግማሹ እያጉረመረመ ተቀበለ፤ በዚህም ሥርዓት አንድ ትውልድ በቀለና በጫትና በጋያ አደገ፡፡

ወያኔ የበቀለበትን ትግራይን ሲያይ አነሰችው፤ በዚያ ላይ በሰሜን በቂልነት ደም ከተቃባቸው ከኤርትራውያን ጋር በደቡብ ደግሞ የሥልጣን ችጋሩ ጠላት በአደረጋቸው ኢጣልያ ‹‹አማራ›› ብሎ በከለላቸው ሰዎች በጎንደርና በወሎ በኩል ታፍኗል፤ በዚያ ላይ በትግራይ ውስጥ ካለው የእርሻ መሬት የተሻለ በጎንደርና በወሎ አለ፤ ጉልበተኛ ሆኖ መቸገር አይበጅምና በጊዜ፣ በጠዋቱ ከጎንደርም ቀንጨብ፣ ከወሎም ቀንጨብ አደረገና አበጠ፤ ሲያብጡ ቦታ ይጠብባል፤ ስለዚህ ወደቤኒ ሻንጉልና ወደጋምቤላ በመዝለቅ ሁለት ዓላማዎችን ማሳካት ይቻላል፤ አንደኛ ትግራይ ሰፊ ይሆንና በእርሻ ልማት የሚከብርበት ተጨማሪ መሬት ያገኛል፤ ሁለተኛ ጠላት ብሎ የፈረጀውን አማርኛ ተናጋሪ ሕዝብ የውጭ ንክኪ እንዳይኖረው ያፍነዋል፤ ከሱዳንም ጋር ጊዜያዊ ወዳጅነትን በመሬት ይገዛል፤ የወያኔ የእውቀትና የብስለት እጥረት ከብዙ ትንሽም ትልቅም ኃይሎች ጋር ያላትማቸዋል፤ ሱዳንን በመሬት በማታለል ሱዳንን ከደቡብ ሱዳን፣ ከኤርትራ፣ ከግብጽ፣ ከሳኡዲ አረብያ፣ ከየመን፣ ከሶማልያ … መለየት የሚችሉ ይመስላቸዋል (ልክ አማርኛ ተናጋሪውንና ኦሮምኛ ተናጋሪውን እንደለዩት)፤ የተዘረዘሩት አገሮች ሁሉ በሱዳን ላይ ከወያኔ የበለጠ ጫና ማድረግ የሚችሉ ናቸው፤ አሜሪካን ለብቻው ብቻ ሳይሆን ከነዚህ አገሮች ጋር አብረን ስንገምተው የወያኔን ደካማ ሁኔታ ለመገንዘብ ቀላል ነው፤ በአካባቢያችን ከአሉት አገሮች ሁሉ ወረተኛ የውጭ አመራር ያለው ሱዳን ነው፤ ሱዳን የኤርትራን መገንጠል የደገፈው በአሜሪካ ጫና መሆኑን አንርሳ፤ ለማንኛውም አሁን በወልቃይት የተጀመረው ውጊያ ከቀጠለ የወያኔና የሱዳን የጓዳ ጨዋታ ያበቃለታል፡፡

ጉዳዩ ሰፊ ጥናት የሚያስፈልገው ነው፡፡

 

ሦስት

ወደየጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄ ስንመለስ፡– ጥያቄው በቁሙ የወልቃይት-ጸገዴ ተወላጆች እንዳቀረቡት ሲታይ የወያኔ አገዛዝ ሃያ አምስት ዓመታት የደከመበት የጎሠኛ ሥርዓት ቢያንስ በአስተሳብ ደረጃ የተሳካ መሆኑን ያረጋግጣል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም ከጎሠኛ አስተሳሰብ ገና እንዳልወጣ የሚያረጋግጥ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ወያኔ በጎሣ ሥርዓት እየገዛ በጎሣ ሥርዓት የሚሸነፍ መሆኑ በግልጽ እየታየ ነው፤ ወያኔ ይህንን አዲስ ክስተት ገና አልተገነዘበውም፡፡

ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት ከመለስ ዜናዊ ጋር ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ ተገናኝተን ስንከራከር አማራ የሚባል ጎሣ አሁን የለም፤ ግን አንተ ትፈጥረዋለህ ብዬው ነበር፤ ገና በሕጻንነት ነው እንጂ አሁን ተፈጥሮአል!

በደቡብ አፍሪካ ኔልሰን ማንዴላ በእስር ላይ በሚንገላታበት ጊዜ ደ ክለርክ የሚባለው የደቡብ አፍሪካ መሪ ማንዴላን ከእስር አስወጥቶ እንደአኩያው በጠረጴዛ ዙሪያ ተነጋግረው የሁለቱ ተቃራኒ መሪዎች መተማመን የደቡብ አፍሪካን ችግር ለጊዜው ፈታው፤ ማንዴላ በክብር ሞተ፤ ደ ክለርክ በክብር ይኖራል፤ የሚያሳዝነው በወያኔ አመራር ውስጥ እንደደቡብ አፍሪካዊው ደ ክለርክ ያለ ሰው እንኳን ሊኖር ሊታለምም አይቻልም፤ እንኳን በወያኔ ውስጥ በአገሩም እንዲህ ዓይነት ሰው እንዳይኖር አረጋግጠዋል፡፡

የተጀመረውን ግብግብ ኢትዮጵያ ካላሸነፈች ማንም አያሸንፍም!

ኢትዮጵያ የድንክዬዎች አገር ሆናለችና የገጠማትን ችግር እግዚአብሔር በጥበቡ ይፍታላት!

Posted in አዲስ ጽሑፎች | 5 Comments

የነፍጠኞች ፖሊቲካ

መስፍን ወልደ ማርያም
ሐምሌ 2008

ነፍጠኛነት ባህላችን ነው፤ ፖሊቲከኛነት አዲስና ባዕድ የትግል ዘዴ ነው፤ ፖሊቲከኛነትና ነፍጠኛነት ተቃራኒ ተግባሮችን ያመለክታሉ፤ ተቃራኒ ተግባሮች አብዛኛውን ጊዜ ተቃራኒ ዘዴዎች ያስፈልጋቸዋል፤ ለምሳሌ መፍጨትና መቡካት ተቃራኒ ተግባሮች ናቸው፤ መፍጨት ሲበታትን፣ ማቡካት ሰብስቦ ያያይዛል፤ የሚፈጭ ሰው ማቡካት ይችላል፤ እንዲሁም ማቡካት የሚችል ሰው መፍጨት ይችላል፤ ፈጪ አቡኪ መሆን የሚችለውን ይህል ወይም አቡኪ ፈጪ መሆን የሚችለውን ያህል ነፍጠኛ ፖሊቲከኛ ወይም ፖሊቲከኛ ነፍጠኛ መሆን ይችላል ወይ? መልሱ ግልጽ ነው፤ አይችልም፤የነፍጠኛ ትግል በጠመንጃ ነው፤ የፖሊቲከኛው ትግል በቃላት፣ በንግግር ነው፤ በሌላ አነጋገር የነፍጠኛ በዱላ፣ የፖሊቲከኛ ትግሉ በመላ ነው፡፡
የፖሊቲካ ሥልጣንን ነክሶ ይዞ ሕዝብን በሕዝብ በዱላ እያደባደቡ በማሸነፍም ሆነ በመሸነፍ የሥልጣንን ክብር ማግኘት በጭራሽ አይቻልም፤ በዱላ ትግል በሁለቱም ወገን ያሉ ወጣቶች ይጎዳሉ፤ በተሸናፊው በኩል የተሰለፉ ወጣቶች የመረረ ኑሮአቸውን የሚጀምሩት ወዲያው ነው፤ መቃብራቸውም ሆነ ቁስላቸው ክብር የለውም፤ የየግሉ አበሳና ለቅሶ ሆኖ ይቀራል፡፡
በድል አድራጊው በኩል የተሰለፉ ወጣቶችም ቢሆኑ ማርና ወተት የሚያገኙት በጣም ጥቂቶች ናቸው፤አብዛኛዎቹ ያለ ማጋነን ዘጠና በመቶ የሚሆኑት ጠመንጃ ተሸክመው በወገናቸው ደረት ላይ ሳንጃ ደቅነው እየወጉና እያሰቃዩ በየዕለቱ ከርሳቸውን ለመሙላት ያለፈ ኑሮ የላቸውም፤ ወይም እውነቱን ፍርጥ አድርጎ ለመግለጽ ዘጠና ከመቶ የሚሆነው ከአሸናፊው ወገን ያለ ወጣት አሥር ከመቶ ለሚሆነው አሽከር ወይም ሎሌ ሆኖ ወገኑን በስቃይ እየጠበሰ ለሆዱ የሚያድር ይሆናል ማለት ነው፡፡
አብዛኛውን አሸናፊንም ሆነ ተሸናፊውን የሚያዋርደው ወይም ክብርን የሚነሣው የአሸናፊና የተሸናፊ ትግልም ሆነ የትግሉ ውጤት ከአብዛኛው የአገሩ ሕዝብ ፈቃድ ውጭ የተደረገ የጉልበተኞች ግብግብ ነው፤ እንዲህ ያለ ግብግብ የሚደረገው ከሕዝቡ ጋር ሳይሆን በሕዝቡ ላይ ነው፤ሁለቱም ተደባደቢ ወገኖች የሕዝብ ወገን መስለው ለመታየት ይሞክራሉ፤ ሆኖም ተፎካካሪዎቹ እርስበርሳቸው የሚታገሉት በዱላ እንደሆነ ሁሉ ከሕዝብም ጋር ያላቸው ግንኙነት በዱላ ነው፤ የሁለቱም መሠረታዊ እምነትም ሆነ ዓላማ፣ መሣሪያም ሆነ ዘዴ ዱላ ብቻ ነው፤ እንዲያውም አንዳንዴ ዱለኛነታቸው ድንበር እየጣሰ የሌሎች አገሮችን ሉዓላዊነት ይነካል፤ በዛሬው ጊዜ በዓለም ውስጥ ዋና ዱለኛ አገር አሜሪካ ነው፤ በሱ ጥገኝነትና በሱ ጥላ ስር ያሉ አምባ-ገነን አገዛዞች በበኩላቸው ዱለኛነትን ይለምዳሉ፡፡
የሕዝብን የገነፈለ ዓመጽ ከዱለኛነት ጋር እንዳናዛምደው ጥንቃቄ ያስፈልጋል፤ አንድ ሕዝብ በማይሰማ ደነዝ አገዛዝ ውስጥ ለብዙ ዓመታት ሲቆይ ተደብቆ የነበረው ሁሉ ገሀድ ይወጣል፤ በእንግሊዝኛ አንድ የአነጋገር ፈሊጥ አለ፤ የግመሉን ወገብ የሰበረው ሰንበሌጥ ይባላል (the straw that broke the camel’s back)፤ ሰንበሌጥ በእውነት የግመልን ወገብ የመስበር አቅም ኖሮት አይደለም፤ ነገር ግን ጭነቱ ተከምሮ፣ ተከምሮ በመጨረሻ የግመሉ ወገብ ሊሸከመው የማይችለው ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ የሚጨመር ሰንበሌጥ የተከመረውን ሸክም ከመጠን በላይ ያደርገውና የግመሉን ወገብ ይሰብረዋል፡፡
አበሳና ግፍም ከዓመት ዓመት እየተከመረ፣ ኑሮ እየከረረ፣ ከሞት ይልቅ ስቃይ እየመረረ፣ የግመሉን ወገብ እንደሰበረው ሰንበሌጥ ለዘመናት በሕዝብ ላይ በተከመረ ግፍ ላይ አንድ ግፍ ጣል ማድረግ የግፍ ግንፋሎትን ይፈጥራል፤ ትእግስት ይደርቃል፤ ጨዋነት ዋጋ ያጣል፤ እንኳን ሰው ድንጋይም ይገነፍላል፤ እሳተ ገሞራ የሚባለው በመሬት ውስጥ ያለው ድንጋይ ሙቀት ሲበዛበት እየቀለጠ መሬትን ሰንጥቆ ሲገነፍል ነው፤ ሕዝብም እንዲሁ ነው፤ ግፍ ሲበዛበት፣ ዙሪያው ገደል ሲሆንበት ይገነፍላል!
መገንፈል በሞት ውስጥና በሞት መሀከል መተራመስ ነው፤ ልዩ ኢላማ የለውም፤ በመንገዱ ላይ የሚያገኘውን ሁሉ ይጠብሳል፤ ሀሳብም፣ ስሜትም የለበትም፤ንዴት ብቻ ነው፤ አደጋውም ያለው እዚያ ላይ ነው፡፡

Posted in አዲስ ጽሑፎች

ኤርትራ በኢጣልያ አገዛዝ

መስፍን ወልደ ማርያም
ሰኔ/2008

በኢጣልያን የአገዛዝ ዘመን፣ ወይም ከዚያ በኋላ ከፌዴሬሽን በፊት አስመራን ያየ እንደሚያስታውሰው የነጮችና አበሾች ኑሮ የተለያየ ነበር፤ አበሾች የሚኖሩት ገዛ አባ ሻውል በሚባለው ችምችም ያለ መንደር ነበር፤ በነጮቹ ከተማ የሚሠሩ አበሾች ሁሉ፣ ወንድም ሴትም የፈረንጅ ልብስ እንዳይለብሱ ክልክል ነበር፤ ጠዋት ሊነጋጋ ሲል ቢስክሌት ያለው በበስክሌቱ፣ የቻለ በጋሪ፣ አለዚያ በእግር ወደነጮቹ ከተማ (በአስመራ) ይጎርፋል፤ በዚያ ሲሠራ ውሎ ማታ ጠዋት በመጣበት ሁኔታ ወደጭንቅንቅ መንደሩ ይጎርፋል፤ በገዛ አባ ሻውል ጠላውን በምኒልክ ብርጭቆ እየጠጣ አዝማሪ ሲሰማ ያመሻል፤ በኢጣልያ አገዛዝ ስር በነበረችው ኤርትራ የአበሻ ኑሮ ይኸው ነው፡፡
ቤቶችን ማፍረስ የአገዛዙ ዋና ሥራ ሆኖ ከቀጠለ ዛሬ በአዲስ አበባ አካባቢ ለአበሾች መኖሪያ በርከት ያሉ የተጨናነቁ ገዛ አባ ሻውሎች የሚያስፈልጉ ይመስለኛል፡፡
አለዚያ — …
አለዚያ ….
ቤቱ የፈረሰበት ቤተሰብ ቁጥር እየበዛ ሲሄድ ወይ በቀይ ባሕር ውስጥ መስመጥ፣ ወይ በሜዲቴራንያን ባሕር ውስጥ መስመጥ፣ ወይ በኮንቴይነር ውስጥ ታፍኖ መሞት፣ ወይ ዕድለኛ ከሆኑ በየሰው አገር አስር ቤት መማቀቅ የአበሻ ዕድል እየሆነ ነው፡፡
ቤቶች ሁሉ ፈርሰው ሲያልቁ ዛሬ የራሳቸውን ቤት ለማፍረስ የሚገዙት ወጣቶች ሁሉ ምን ሥራ ይፈጠርላቸዋል?
አገዛዙ አለሕዝቡ እንዴት ሊኖር ነው? በኢትዮጵያ ዙሪያ የሚሰማው ሁሉ ጥሩ አይደለም፤ መማረር ሳይመጣ አገሩን የሁላችንም ማድረጉ ሳይሻል አይቀርም!

Posted in አዲስ ጽሑፎች

ደብዳቤ

ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለጓደኞቻቸው በሙሉ
ሰላምታዬን አቀርብላችኋለሁ፡፡
ኢትዮጵያ የእግዚአብሔር አገር ነች፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የእግዚአብሔር ሕዝብ ነው፤ ክርስጢያኑም፣ እስላሙም፣ አረመኔውም የእግዚአብሔር ነው፤ እንደየእምነቱ በእግዚአብሔር ፈቃድ የሚኖር ነው፡፡
የእግዚአብሔር ጊዜ የተለየ ነው፤ ትእግስቱ ስለሚያረዝመው የተረሳ ያስመስለዋል፤ እግዚአብሔር ግፍን አይረሳም፤ እግዚአብሔር ሁሌም ለአቅመ-ቢሶች ጉልበት የሚሆንበት መንገድ አላው፤ ግፍ በእግዚአብሔር በር ላይ እንደተጣለ ግም ቆሻሻ ነው፤ እግዚአብሔር ሲፈቅድ ይጠርገዋል፤ ወይም ያስጠርገዋል፡፡
እግዚአብሔር መንገዱ ብዙ ነው፤ ግፍን የሚያስከፍለው በተለያየ መንገድ ነው፤ በግፈኛው ቤተሰብ ላይ ሁሉ የግፈኛነት ጠባሳን ያሳርፍበታል፤ ሰዎች ለሥልጣናቸው ባላቸው ቅናት የእግዚአብሔርን ሥልጣን ይጋፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ሥልጣን መጋፋት የግፍ ግፍ ነው፤ታሞ በእግዚአብሔር እጅ ባለ ሰው ላይ ጉልበተኛ መሆን በእግዚአብሔር ሥልጣን መግባት ነው፤ የግፍ ግፍ ይሆናል፤ ለእናንተም፣ ለቤተሰቦቻችሁም፣ ለአገሪቱም፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብም የሚበጅ አይደለም፡፡
ሀብታሙ አያሌው በእግዚአብሔር እጅ ነው፤ እግዚአብሔርን አትፈታተኑ፡፡
ደጉን ያስመልከታችሁ!
የግዛታችሁ ነዋሪ
መስፍን ወልደ ማርያም

Posted in አዲስ ጽሑፎች

ጳጳሶችና ስደት

መስፍን ወልደ ማርያም

ሰኔ/2008

እንዲያውም ርእሱን ካህናትና ስደት ብለው ይሻላል፤ ካህናት የሁሉንም ሃይማኖቶች መሪዎችን ይመለከታል፤ ዓላማዬም ሁሉም የሃይማኖት መሪዎችን የሚነካ ነው፤ ነገር ግን የእኔ እውቀት በክርስትናው ላይ ጎላ ያለ በመሆኑ የክርስቲያኖቹ መሪዎች ላይ ያተኮርኩ ቢመስልም ሁሉንም ይመለከታል፤ በተለይ መነኩሴዎች ላይ የማነጣጥርበትም የተለየ ምክንያት አለኝ፡፡

በመጀመሪያ አንድ መሠረታዊ ነገር ላብራራ፤ እንደማንኛውም ሰው ስለፍርሃትና ስለጥቃት አውቃለሁ፤ በተለያዩ መንገዶች በመርማሪዎች የተሰቃዩ ሰዎች ሲናገሩ ሰምቻለሁ፤ የጻፉትንም አንብቤአለሁ፤ ከሁሉም በላይ ፍርሃት የግል መሆኑን አውቃለሁ፤ በዚህም ምክንያት ሰውን ለምን ፈራህ ብሎ መውቀስም አስቸጋሪ መሆኑ ይገባኛል፤ ስለዚህም ይህንን የምጽፍበት ምክንያት የተሰደዱትን ለመውቀስና እነሱን ዝቅ አድርጌ ራሴን ከፍ ለማድረግ አይደለም፤ ከቃሌ በቀር ይህንን የማረጋግጥበት መንገድ የለም፤ እንዲህ ያለው ዓላማ ምንም ትርፍ የለውም፡፡

የኔ ዓላማ ሁለት ነው፤ አንደኛ የሚቀጥለው ትውልድ ሽሽትንና ስደትን እንደባህል እየወሰደው እንዳይቀጥልና የኢትዮጵያ መራቆት እንዳይባባስ እሪ! ለማለት ነው፤ እሪ! በማለት በተለይ የወጣቶቹን ትኩረት ለመሳብና ከሽሽትና ከስደት ሌላ አማራጭ እንዲፈልጉ ለማሳሰብ ነው፤ ይህንን ለማድረግ ስሞክር የማኅበረሰባዊ ግዴታዬ እስከዛሬ የተሰደዱትን ሰዎች የዜግነትም ሆነ የማኅበረሰባዊ፣ የሃይማኖትም ሆነ የታሪክ፣ የፖሊቲካም ሆነ የኑሮ ኃላፊነትን፣ ተጠያቂነትንና የወላጆችን ክብር አነሣለሁ፤ በዚህ ጽሑፍ ላይ የማተኩረው ከላይ እንደገለጽሁት በካህናት ላይ ነው፡፡

በክብረ ነገሥት ልጀምር፡–

 

‹‹ለካህናትሰ ሰመዮሙ ጼወ፤ ወዓዲ ለካህናት ሰመዮሙ መኅቶተ፤ ካዕበ ሰመዮሙ ብርሃኖ ለዓለም፣ ወካዕበ ሰመዮሙ ጸሐየ ዘያበርህ ጽልመተ እንዘ ክርስቶስ ጸሐየ ጽድቅ ውስተ አልባቢሆሙ፤

ወካህንሰ ዘቦቱ ልቡና ይገሥጾ ለንጉሥ በእንተ ምግባራት ዘርዕየ ወዘኢርእየሰ እግዚአብሔር ይፈትን ወአልቦ ዘይወቅሶ፤

ወዓዲ ኢይሕምይዎሙ አሕዛብ ለጳጳሳት ወለካህናት እስመ ደቂቀ እግዚአብሔር ወሰብአ ቤቱ እሙንቱ በእንተ ዘገሠጾሙ በእንተ ኃጢአቶሙ ወጌጋዮሙ፤

ወአንተኒ ኦ ካህን ለእመ ርኢከ ዕውቀ ኃጢአቶ ለብእሲ ኢትኅፈር ገሥጾቶ ኢያፍራህከ ሰይፍ ወኢስደት፡፡

 

እስቲ ዳዊት ያልደገሙት ይኮላተፉበት! ፍሬ ነገሩ ክብረ መንግሥት በመጀመሪያ ካህናትን በጣም ይክባቸዋል፤ ጨው አላቸው፤ መብራት አላቸው፤ የዓለም ብርሃን አላቸው እውነተኛው ጸሐይ ክርስቶስ በልባቸው ውስጥ ስላለ ጨለማን የሚያበራ የዓለም ብርሃን ይላቸዋል፡፡

ክብረ ነገሥት ክቦ፣ ክቦ አያቆምም፤ ይቀጥልና የካህናትን ግዴታ ይናገራል፤ ልቡና ያለው ካህን በሚያያቸው ጉዳዮች ንጉሡን ይገሥጻል፤ የማያየውን ጉዳይ ግን እግዚአብሔር ይመረምራል፤

ሕዝብ ጳጳሳትንና ካህናትን ማማት ተገቢ አይደለም፣ ስለምን የእግዚአብሔር ልጆችና ቤተሰቦች ናቸው፤

ካህን ሆይ አንተ ግን የሰውን ኃጢአት ስታይ መገሠጽን አትፍራ፤ ሰይፍም ሆነ ስዴት አያስፈራህ፡፡

ዳዊትን የደገመ ሁሉ እንደሚያውቀው ፡- ኢይፈርሆ ለእኩይ እስመ አንተ ምስሌየ፤ ይላል፤ አንተ ከኔ ጋር ነህና አልፈራም ማለት ነው፤

እንግዲህ ይህ የክብረ መንግሥት ትእዛዝ በጣም ግልጽ ነው፤ የክርስቶስም ትእዛዝ በጣም ግልጽ ነው፤ ተራራውንም ማዘዝ ትችላላችሁ ይላል፤ ለደቀ መዛሙርቱ ስለእምነታቸው ጎዶሎነት ደጋግሞ ተናግሯል፤ እንግዲህ ስደት የቅንጣት ታህል እምነት መጉደል ያመጣው ፍርሃት አይደለም? ሽሽት የራስን አካላዊና መንፈሳዊ ኃይል መካድ አይደለም? ‹‹እስመ አንተ ምስሌየ››ን መካድ አይደለም? መትረየስ ፊት የቆሙትን ጴጥሮስን መካድ አይሆንም?

ወይስ የኛዎቹ ጳጳሳትና ካህናት ሌላ መመሪያ አላቸው? ወይስ አንድ አጭበርባሪ ሰባኪ ልጆቼ እንዲህ አታድርጉ፤ እንዲህም አታድርጉ እያለ ሲሰብክ አንድ በጣም የሚያውቀው ሰው ትኩር ብሎ ሲመለከተው ዓይን ለዓይን ሲጋጠሙ ማርሽ ለወጠና ልጆቼ እኔ እንደምላችሁ አድርጉ እንጂ እኔ እንደማደርገው አታድርጉ አለ ይባላል፡፡

ወደሐዲስ ኪዳንም ገብቶ ብዙ ነገር ማለት ይቻላል፤ ግን በጣም ያሳፍራል፤ በመጀመሪያ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ያፈርሁት አንድ ባሕታዊ በእስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተገደለና በቤተ ክርስቲያን እንዳይቀበር የተደረገው ሙከራ ነው፤ ሁለተኛው በቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የሙጢኝ ያሉትን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች  መስቀል የለበሱ ሰዎች አሳልፈው ሲሰጧቸው ነው፡፡

የተሰደዱና ያልተሰደዱ ካህናት ብሎ መለየቱ ዋጋ የለውም፤ ዋጋ የለውም የሚባለው በምእመናኑ፣ በበጎቹ፣ ዓይን ሲታይ ነው፤ በጎቹን ጥለው የሸሹትም ‹‹ስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘሀበነ ዘንተ ፀጋ በመዋዕለ ስደትነ።›› እያሉ ለራሳቸው ይኖራሉ፤ ያልሸሹትም በሥጋ ነው እንጂ በመንፈስ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋር መሆናቸው ያጠራጥራል፤ በአንድ በኩል ሲታይ ሁለት ሲኖዶሶች የሚባሉት በአካል የሚገኙት በኢትዮጵያና በአሜሪካ መሆናቸው ነው እንጂ በመንፈስ አንድ ናቸው፤ የዝንጀሮ ቆንጆ!

ይህች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ልጆችን በትምህርት ስታሳድግ የኖረች፣ ደሀዎችን፣ ስትረዳ አሮጊቶችና ሽማግሌዎችን ስትትጦር፣ እናትና አባት የሌላቸውን ልጆችን እያስተማረች የምታሳድግ፣ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቅርሶች ስትጠብቅ የኖረች ዛሬ በብዙ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የሚደረገውን ስትፈጽም የኖረች ነች፤ መንፈሳውያን ሰዎች በነበሩባት ጊዜ፤ ዘመናዊነት በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ እንዳልሆናት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያኒቱም አልሆናትም፤ የዛሬ ሃምሳና ስድሳ ዓመት ግድም በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት የሠለጠኑትና በኋላም ነገረ መለኮት እንዲማሩ ወደወጭ የተላኩት ሁሉ እያደናቀፋቸው ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመርዳት አልቻሉም፤ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ግን ባልተጠበቀበት መስክ ሙያተኞችን አፍርቷል፤ በሕዝብ ‹‹ደኅንነት››ና በጦር ሠራዊት ታላላቅ መኮንኖችን አበርክቷል፡፡

በአገር ውስጥ ያሉት ካህናት-ጳጳሳት ‹‹በዶልቼ ቪታ›› (መለስ ታምራትን ሲያባርረው ስኳር ያለው) ተንደላቅቀው በመኖር ከአገር ውጭ ካሉት አያንሱም፤ አንዳንዶቹም ቀሚስ ለባሾች እዚያም እዚህም እየረገጡ አማርጠዋል፡፡

ወጣቱ ትውልድ ይቺን ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን ለትንሣኤ ማብቃት ያሻዋል፤ እግዚአብሔር ይርዳን!

ስደትን በሚከተሉት ቀልዶች አሳምረውታል!!!

‹‹በሥጋ እንጅ ከቅድስት አገራችን የተሰደድነው፣ ከቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችን አልተሰደድንም።››

‹‹የክርስትና ሃይማኖት እንደ ዓለማዊ መንግሥት የግዛት ወሰን የለውምና።››

 

 

Posted in አዲስ ጽሑፎች | 1 Comment