የሥልጣኔው መንገድ ሳይጣሉ መነጋገር ነው

 

መስፍን ወልደ ማርያም

ሰኔ 2003

ሰኔ /2003 በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር ከተደረገው ስብሰባ በኋላ በጋዜጣ ያየሁት የመጀመሪያው ጽሑፍ፣ ከዚያም ቀጥለው የወጡት ጽሑፎች የሚያወሱት ስለስብሰባው ርእስ ሳይሆን ስለአቶ ስብሐት ነው (ጋዜጣው እንዳለው አቦይ እንዳልለው ካልካደ እኔ በዕድሜ ደኅና አድርጌ እበልጠዋለሁ)፤ ስብሐት ርእስ መሆኑ አግባብ ያለው ቢሆንም የስብሰባውን ርእስ ፍጹም እንዲሸፍነው መሆኑ ድንገተኛ ጎርፍ እየመጣ ከተኛንበት እያንቀረቀበ ሲወስደን የምናወራው ስለጎርፉ ሳይሆን አትግፋኝ፤ አትንካኝ እየተባባልን ነው፤ የአገር ጉዳይ ሆኖ ለውይይት ከቀረበው ጉዳይ ጋር ሲተያይ ስብሐት ነጋ ንጉሥም ቢሆን ኢምንት ነው፤ ከስብሰባው በኋላ ዋናው ጉዳይ ቀርቶ እሱ የጋዜጦች ርእስ መሆኑ ያለንበትን የድንብርብር ዘመን የሚያመለክት ነው፤ ይህንን ለመግቢያ ያህል ካልሁ በሚቀጥለው አጭር መተላለፊያ ወደጋዜጣው ርእስ ልግባ፡፡

አሁንም ዋናው ጉዳይ ጨርሶ እንዳይረሳ ፍሬ ነገሩን ባጭሩ ለማስታወስ በአሥራ አምስተኛው ምዕተ-ዓመት አባ እስጢፋኖስ የሚባሉ መነኩሴ ከእግዚአብሔር በቀር ለማንም ለምንም መስገድ ተገቢ አይደለም የሚል እምነት ይዘው ተነሡና ብዙ አባሎችን አፈሩ፤ ይህ የሆነው በአውሮፓም ገና ሉተር የሚባለው የፕሮቴስታንተት መሪ ከመነሣቱ ከሠላሳ ዓመት ግድም ቀድሞ ነው፤ ከተለመደው የተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ልማድ በመውጣቱ ደቂቀ እስጢፋኖስ በሚባሉት የአባ እስጢፋኖስና ተከታዮች የደረሰባቸውን መከራና ስቃይ የሚገልጸውን ገድላቸውን ዶር. ጌታቸው ኃይሌ ከግዕዝ ወደአማርኛ ተርጉሞ በአሜሪካ አሳትሞት ነበር፤ አሁን ደግሞ በአዲስ አበባ ኒቨርሲቲ አማካይነት አሳትሞታል፤ የስብሰባው ዋና ርዕስ በዚህ መጽሓፍ የተገለጸው የደቂቀ እስጢፋኖስ አበሳና መከራ፣ ሞት ነበር፤ በዕለቱ ከተናገርሁት ውስጥ የሚከተለውን ብያለሁ፤–

‹‹እነዚያ ሟቾችና ገዳዮች ለኛ ዛሬ ለምንኖረው ምን የሚያዛልቀን ትምህርት አስተምረውናል? የአቅመ-ቢሶቹ የደቂቀ እስጢፋኖስ ስቃይና ሞት ያስተማረን ነገር አለ? የጉልበተኞቹ ማሰር፣ ማሰር ሲሰለቻቸው ምላስና አፍንጫ መቁረጥ፣ ምላስና አፍንጫ መቁረጥ ሲሰለቻቸው እግርና እጅ መቁረጥ፣ እግርና እጅ መቁረጥ ሲሰለቻቸው መግረፍ፣ መግረፍ ሲሰለቻቸው መግደል አስተምሮናል? ይህ ትምህርት የዛሬ ስድስት መቶ ዓመት ግድም ከነበረው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ የተሻልን ሰዎች፣ የተሻልን ኢትዮጵያውያን አድርጎናል? ከታሪካችን ብንማር ነው በአሥራ ስድስተኛው ምዕተ ዓመት ደግሞ በክርስቲያንና በእስላም መሀከል አሥራ አምስት ዓመታት ያህል የፈጀ መተላለቅ የተደረገው? በአሥራ ሰባተኛው ምዕተ-ዓመትስ በካቶሊኮችና በኦርቶዶክሶች መሀከል የተፈጸመውስ ግፍና ስቃይ? ለዛሬውስ የኑሮ ሥርዓታችን ምርኩዝ የሚሆነን ከታሪካችን የተማርነው ነገር አለ?

ምንም ዓይነት አስተያየት ሳልሰጥበት ከታሪካችን መማራችንን ወይም አለመማራችንን የሚያሳይ አንድ እውነት ላሳያችሁ፤ በቅርቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታተመው የደቂቀ እስጢፋኖስ ገድል ትርጉም ውስጥ በገጽ 18 ላይ ተርጓሚው ዶር. ጌታቸው ኃይሌ የሚከተለውን ይላል፤

የረጅም ዘመን ወዳጄ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ረቂቁን አንብቦ እንደሱ ‹‹ሕግ ይዳኘን›› ከማለት በምንም ምክንያት ወደ ኋላ ላላሉ ኢትዮጵያውያን ታሪክ መግቢያውን የሚየዳብር ‹‹ቀዳሚ ቃል›› ስለጻፈልኝ አመሰግናለሁ፡፡

ሆኖም መጽሐፉን ብታገላብጡት መስፍን ወልደ ማርያም ጻፈው የተባለውን ‹‹ቀዳሚ ቃል›› አታገኙትም፤ ይህ የሚያሳዝን ስሕተት የመጽሐፉ ተርጓሚ የዶር. ጌታቸው ኃይሌና የአዲስ አበባው አሳታሚ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው፤ ዩኒቨርሲቲው እኔ የጻፍሁትን ‹‹ቀዳሚ ቃል›› ከአዲስ አበባው እትም እንዲወጣና ሺፈራው በቀለ በጻፈው እንዲተካ ሲያደርግ ከላይ የተጠቀሰውን ረስቶታል፤ ጌታቸውም ‹‹የረጅም ዘመን›› ወዳጁን እንዳያሳዝን ‹‹መስፍንን አስፈቅዱት›› ብሎ ከኃላፊነት ለመውጣት ሞከረ፤ መስፍን የጻፈው የወጣበት ምክንያት ገልጽ ነው፤ጌታቸው ኃይሌም ሆነ ሺፈራው በቀለ የጻፉት በኢትዮጵያ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ እንደተለመደው የተሸበበ የታሪክ አጻጻፍ ነው፤ዛሬ ከአለንበት ሁኔታ ጋር ለማያያዝ አይፈለግም፤ያለፈውን ከዛሬው ጋር ካያያዙትና ዝምድና ካገኙበት የደቂቀ እስጢፋኖስን ያህል ባይሆንም ዋጋ ያስከፍላል፤ ይሀንን ጉዳይ የማነሣው መስፍን የጻፈው በመውጣቱ ቆጭቶት ነው የሚል ከአለ ክፉኛ ይሳሳታል…፡፡››

ስለመጽሐፉ ይህን ካልሁ በኋላ ወደጋዜጣው ውይይት እገባለሁ፡፡

በመጀመሪያ በጣም የተደሰትሁባቸውን ጉዳዮች ልዘርዝር፤ አንደኛ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር ከብዙ ዘመናት በኋላ ለውይይት ተከፍቶ (ለእኔ ማለቴ ነው፤) ማየቴ በጣም ደስ ሲለኝ የስብሰባው መጨናገፍ ቢላዋ ሰጥቶ ሥጋ መንፈግ ዓይነት መሆኑ ቅር ያሰኛል፤ ሁለተኛ ከዚህ በፊት የጻፉት ሁሉ ደኅና አድርገው እንደገለጹት የስብሐት ነጋ በስብሰባው ላይ መገኘት የፓርቲውን ሳይሆን የግሉን የዴሞክራሲ ዝንባሌ የሚያሳይ በመሆኑና በተሳትፎውም ባሳየው መንፈሳዊ ወኔ በጣም ተደስቻለሁ፤ በአንጻሩ በቅርቡ በአጋጣሚ የኢትዮጵያን ቴሌቪዢን ሳይ ብዙ ታላላቅ ሰዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በየተራ እኛ (ኢትዮጵያውያን) ከማን እናንሳለን የሚል ዓይነት ንግግር ያደርጋሉ፤ ውይይት ነው ብለው ማቅረባቸው እንደሆነም አላውቅም፤ አንዱ ተናጋሪ በአየርላንድና በዴንማርክ የዛሬ ሠላሳና አርባ ዓመት ግድም ረሀብ ነበረ ሲል የሰማሁ መሰለኝ! ይህ ሰው ስንት ሚልዮን ኢትዮጵያውያንን አሳስቷል? ማንም አላረመውም! በኢትዮጵያ ያለው ትልቁ ችግር መሰላል ላይ ወጥቶ ቁልቁል ዲስኩር የሚግተው አንድ ሰው ብቻ መሆኑ ነው፤ ለንግግር፣ ለውይይት ቢያንስ ሁለት የተለያዩ ሀሳቦች ያላቸው ሰዎች ያስፈልጋሉ፤ የሚያቀረሸውን ዲስኩር መጋት ለምንም አይበጅም፤ የስብሐት ወኔ እዚህ ላይ ነው፤ ቁልቁል ለመናገር በማይችልበት መድረክ ላይ ተገኝቶ በእኩልነት የራሱን ሀሳብ ለመግለጽና አንዳንዴ ሸለብ ቢያደርገውም የሚቃወሙትንም ለመስማት መቻሉ ነው፤ ሸለብ ቢያደርገውም ያልኩበት ምክንያት በጻፈው ውስጥ ‹‹ቤተ ክህነትን የሚጎዳ አመለካከትና አካሄድ›› እንዳለኝ አስመስሎ የራሱን ምኞት መናገሩ በዕለቱ የተናገርሁትን አለመስማቱን ስለሚያረጋግጥ ነው፤ ‹‹ጳጳሶቹ አይረቡም›› ያለው እሱ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም፤ በሌላ በኩል ስመለከተው በቤተ ክህነትና በቤተ ክርስቲያን መሀከል ያለውን ልዩነት የተገነዘበ አልመሰለኝም፤ አሸልቦት ነበር ያልሁት የሚከተለውን ስናገር አልሰማኝም ለማለት ነው፤

‹‹ዛሬ በተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ተከፋፍለው ስንትና ስንት ሺህ ሰዎች ቀጥረውየሚያስሠሩት አብዛኛው ሥራ ያለምንም ክፍያ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የምትሠራው ነበር፤ ከፊደል ቆጠራ ጀምሮ ትምህርት በተለያየ ዘርፉ እስከከፍተኛ ደረጃ፣ ዛሬ ዩኒቨርሲቲ እስከሚባለው ድረስ የትምህርት ገበታ ዘርግታ በነጻ ታስተምር ነበር፤ ከተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ጋር የማትደፈር የደካሞች መጠጊያና የሙጢኝ የሚባልባት አድባር ነበረች፤ ነበረች ነው ማለት የምንችለው፡፡››

ሦስተኛ በአቶ ደሳለኝ የተጻፈው (ከአቦይ ስብሃት ምላሽ በስተጀርባ) ግሩም በሆነ የጨዋ አጻጻፍ ዋና ዋና ሀሳቦቹን በመግለጹ በአብዛኛው የምስማማበት ነውና አልደግመውም፡፡

ስብሐት በጽሑፉ ላይ የደረደራቸው ጥያቄዎች መረጃ ለመፈለግና ለማስፈራራት ይመስላል፤ በአደባባይ ከተራ ሕዝብ ጋር ተገናኝቶ በነጻና በእኩልነት ደረጃ መነጋገር ልማድ የሌለው ሰው ከእሱ ሀሳብ ጋር የማይለጠፉትን ሁሉ እንደስድብ ወይም እንደድፍረት ቢቆጥራቸው አያስደንቅም፤ ከላይ ሆኖ መናገርን ሲረሳና በእኩልነት መነጋገርን ሲለምድ የሌሎችን ሀሳብና አስተሳሰብ ባይቀበልም የሚያከብርበት ጊዜ ይመጣል፤ አንዳንድ ጓደኞቹ ለምደዋል፤ እሱም ይህ የሚያቅተው ሰው አይደለም፤ ለእኔ በኢትዮጵያ ውስጥ ዋናውና ትልቁ ችግር መነጋገር አለመኖሩ ነው፤ እንግሊዝኛው ይበልጥ ለሚገባቸው ሰዎች dialogue ወይም ዳያሎግ የለም፤ ሁሉም ልናገር አዳምጡኝ ባይ ነው፤ እዚህም ላይ ስብሐት በመናገርና በመነጋገር መሀከል ያለውን ልዩነት የተገነዘበ አይመስለኝም፤ ‹‹ሰው እየጻፈ፣ እየተናገረ፣ እየተደራጀ ነው፤›› ይለናል፤ ተመስገን የሚለው አልተነጋገርንም ነው፣ ስብሐት የሚለው ትናገራላችሁ፤ ነው፤ ተመስገን የሚለው አላዳመጣችሁንም ነው፤ እንዲህ ያለው አለመግባባት የሚመጣው ካለመነጋገር ነው፡፡

ትክክለኛ መረጃ የመስጠት ኃላፊነት የማን ነው?

ለአቶ ስብሐት ነጋ አንድ ቁም-ነገር ላስታውሰው፤ ወደደም ጠላም እሱ የሕዝብ ሰው ነው፤ ማለትም የአደባባይ ሰው ነው፤ ስለዚህ ስለሱ የሚባለው ነቀፌታ ሁሉ ሊያሰከፋው አይገባም፤ በተለይም በዚህ ሁሉም ነገር ምሥጢር በሆነበት ማኅበረሰብ ውስጥ ሐሜት ይትረፈረፋል፤ ለዚህ ኃላፊነታቸው ለሕዝብ መሆን ያለባቸው ዜና ማሰራጫዎች ናቸው፤ ዱሮ ሰዎች ሲሾሙም ሆነ ሲሻሩ በአደባባይ እየተነገረ ነበረ፤ ዛሬ በምሥጢርና በግል የሆነ ይመስላል፤ ታዲያ በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ሰዎች በመረጃ እጥረትና በወሬ ቢደናበሩ ምን ያስደንቃል? ስብሐት አልሰማ እንደሆነ እንጂ አንዳንዶቻችን በወሬ ፍዳችንን አይተናል፤ በእኩይ ክስ እሱና እኔ ጠላቶች ተደርገን ዕድሜ-ልክም ተፈርዶብን በምሕረት ወጥተናል፤ አሁንም አንዳንድ ሰዎች ፍዳቸውን እያዩ ነው፤ አንድ ምሳሌ ብቻ ለመስጠት ስብሐት ከወሬ ያገኘውን እንዲህ ገልጾታል፤ ‹‹አጼ ኃይለ ሥላሴ ቅዱስ ተብለው ታቦት ተቀርጾላቸው እንደነበረም (በካህናት) ይገለጻል፤›› ይህንን ጭፍን የሐሰት ወሬ ለመጀመሪያ ጊዜ መስማቴ ነው፤ በአንዳንድ ቤተ ክርስቲያኖች ስዕላቸው በመግቢያው ላይ በመደረጉ አንኳን ከባድ ተቃውሞ ነበር፤ ወያኔ ‹‹ስር የሰደደ ዴሞክራሲያዊ አንድነት›› አረጋገጠ ማለት ሌላው የሚናገረውን ካለመስማት የሚመጣ ቀረርቶ ነው፤ አጨብጫቢዎች መስሚያ ጆሮ፣ ማመዛዘኛ አእምሮ እንዳላቸው አድርገን ስንገምት ወደዚህ መደምደሚያ እንደርሳለን፤ የሰሙትን በጥያቄ ለማጣራት ያልደረሱ፤ እምነታቸውን በሰሙት የሚከልሱ፣ ለስደት ሲበቁ እውነትን ይተነፍሱ!

በመጨረሻ ስብሐት የችግሮቻችን ሁሉ መነሻ የሆነውን አውራ ችግር፣ለማናቸውም ዓይነት ሳይንሳዊና ፍረያማ ውይይት አስፈላጊ የሆነውን መመሪያ እንደሚከተለው ገልጾታል፤‹‹…የፖሊቲካ ልዩነት ካለው አካል ጋር መወያየት ጠቀሜታ አለው፤ እኔ በዚህ ዓይነት ሂደት በጽኑ አምናለሁ፡፡›› እስከዛሬ ሳይገለጽለጽት በመቅረቱ ባዝንም ለወደፊቱ ያበርታህ፤ ያበርታን፡፡

Advertisements
This entry was posted in ቀደም ሲል የወጡ ጽሑፎች. Bookmark the permalink.

One Response to የሥልጣኔው መንገድ ሳይጣሉ መነጋገር ነው

  1. denekew bayabele says:

    thank you our father pro.Mesfin/W the thriple thinker.you are working.but wish to have a son.b/c we are coming to moraly die.

Comments are closed.