አገዛዝና ዓለም-አቀፍ ፖለቲካ የሶርያ ምሳሌ

ፍትሕ ጋዜጣ

   መጋቢት 2004

በአረብ አገሮች የተካሄደውና በመካሄድ ላይ ያለው ሕዝባዊ አብዮት ማስተዋልና መማር ለሚችሉ ሁሉ ጠቃሚ ትምህርት እያሳየ ነው፤ መጀመሪያ በአገዛዝና በሕዝብ መሀከል ያለውን ገደል ገልጦ ያሳያል፤ ከሕዝብ ቁጥር ጋር ሲነጻጸር በጣም ጥቂት በሆኑ የተቀለቡ የሰላማዊና መለዮ-ለባሽ ሎሌዎች በቃሬዛ ታዝሎ ልዩ ዓለም ውስጥ የሚኖር መሆኑ በቱኒዚያም፣ በሊብያም፣ በግብጽም፣ በየመንም ታየ፤ ገና አልለየም እንጂ በሶርያም እየታየ ነው፤ በተጠቀሱት የአረብ አገሮች ሁሉ የይስሙላ ምርጫ ሲደረግ ኖሮአል፤ ሕዝቦቹም የዓርባ ቀን ዕድላችን ብለው ወደእግዚአብሔር ሲያመለክቱ ቆይተዋል፤ እግዚአብሔር ልቦናቸውን አሳያቸውና የጋረዳቸውን ጥቁር መጋረጃ ቀድደው ጸሐይ ሲወጣ አዩ፤ የአእምሮአቸው ዓይን ተከፈተ፤ ብርሃንን ያየ ወደጨለማ መመለስ አይችልም።
በሕዝቦቹ በኩል አስደናቂው ነገር በመሸጦነት ከተያዙት በቀር ወንድ፣ ሴት፣ አሮጊት፣ ሽማግሌ ሕፃናት ሳይቀሩ አገዛዙን ለመጣል በቆራጥነትና በአንድነት ተነስተው ለብዙ ወራት ለአገዛዙና ለሎሌዎቹ ፋታ ሳይሰጡ ትግላቸውን ለድል ማብቃታቸው ነው፤ የሴቶቹ ተሳትፎ የሚያስደንቅ ነበር፤ ከአገዛዙ ሎሌዎችም ቢሆን ከህዝብ ጋር ቅራኔ ውስጥ ላለመግባት የፈለጉ ብዙዎች ሎሌነት በቃን እያሉ ከህዝባዊው ትግል ጋር ተቀላቅለዋል።
የአምባ-ገነኖቹ መልስም በጣም የተለያየ ነበረ፤ የቱኒዚያው አምባ-ገነን ገና በመጀመሪያው ላይ ሳይባባስ ሚስቱን ይዞ ሹልክ አለና ሳኡዲ ገብቶ የሙጢኝ አለ፤ የግብፁ ደግሞ ትንሽ ከተግደረደረ በኋላ ሥልጣኑን ለምክትሉ አስረክቦ ወጣና በሕዝባዊው ኃይል ቁጥጥር ስር ገባ፤ ታምሜአለሁ ቢልም በቃሬዛ እየተያዘ ፍርድ ቤት እየቀረበ ነው፤ የሊቢያው ጋዳፊ ከነልጆቹ ፎከረ፣ ሸለለና በመጨረሻ ስንት ሺህ ሰዎች አጫርሶ የጎርፍ መውረጃ ቦይ ውስጥ ተወሽቆ ተያዘና ጭካኔ ባስተማራቸው ሰዎች አጉል አሟሟት ሞተ፤ የሱ ቢጤው የየመኑ አምባ-ገነን ከወንበሩ ጋር ተጣብቆ እምቢኝ ብሎ በተጣለበት ቦምብ ቆስሎ ለህክምና ሳኡዲ ሄዶ ቆየ፤ ተሽሎት ከተመለሰም በኋላ ሥልጣን አልለቅም በማለት ቀጥሎ ብዙ ሰዎችን ከአስጨረሰ በኋላ በድርድር ለቀቀ፤ ለህክምና ብሎ ወደአሜሪካ ሄደ፤ ምናልባት እዚያ ለመኖር የማይፈቀድለት በመሆኑ በኢትዮጵያ በኩል ወደአገሩ ገባ፤ በኢትዮጵያ በጥገኝነት ለመኖር እየተዘጋጀ ነው ይባላል፤ እጅ እየነሡ ቼክ ሲቀበሉ የነበሩት ሁሉ ለጋዳፊ ለቅሶ አልተቀመጡም፤ ፈረንሳይ ለቱኒዚያኑ ቤን አሊ ለቅሶ አልተቀመጠም፤ አሜሪካ ሙባረክን በርታ አላለም። እነዚህ አምባ-ገነኖች በሥልጣን ላይ የቆዩባቸው ዓመታት ብዙ ናቸው፤ ጋዳፊ ዓርባ ሦስት ዓመት፣ ሙባረክ ሠላሳ፣ ቤን አሊ ሃያ ሦስት፣ ሳላህ ሃያ ሁለት፣ ገና በትግል ላይ ያለው ሀኪሙ አምባ-ገነን ዶር. አሳድ አሥራ ሁለት ዓመታት ገዝተዋል፤ አእምሮአቸው በትዕቢት ባይደፈን ለትምህርትና ለንስሐ በቂ ጊዜ ነበራቸው፤ መማርና ንስሐ መግባት ተስኖአቸው ራሳቸውንም አገሮቻቸውንም አጠፉ፤ በአንጻሩ ሥልጣን አልጠግብ ብሎ ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ለሦስተኛ ጊዜ ለምርጫ የገባው የሴኔጋሉ የሰማንያ አምስት ዓመት ሽማግሌ መሸነፉን ሲረዳ ለአሸናፊው ስልክ ደውሎ ‹‹እንኳን ቀናህ!›› ብሎ ሥልጣኑን ለማስረከብ ቆርጦአል፤ የአፍሪካ መሪዎች ሰማንያ እስኪሞላቸው አይበስሉም እንዳይባል የዚንባብዌው ሙጋቤ አለ።
ዛሬ የዓለምን ሁሉ ትኩረት የሳበው የአረብ አምባ-ገነን የሶርያው አሳድ ነው፤ የግብጹና የየመኑ አምባ-ገነኖች በአሜሪካ ስር የነበሩትን ያህል የሶርያው በሩስያ ስር ነው፤ ከዚያም በላይ ለእስራኤል፣ ለቱርክና ለኢራቅ ጎረቤት ነው፤ የሶርያ ደቡባዊ ጎረቤት ዮርዳኖስ ነው፤ ዮርዳኖስ የዙፋን አገዛዝ ሆኖ የምዕራባውያን ምሽግ ነው፤ ለሶርያ ፋርስም ሩቅ አይደለም፤ የሶሪያ ጦስ ጦሰኛውን አካባቢ ይበልጥ እንዳይመርዘው ሁሉም ይፈራል፤ የሶርያው አምባ-ገነን ይህንን እንደጥንካሬ ቆጥሮታል፤ ስለዚህም የሚቀጣጠለውን እሳት ፈርተው አይነኩኝም በማለት ከሕዝቡ ጋር ሙሉ ጦርነት እያካሄደ ነው፤በመድፍና በታንክ ሳይቀር ሕዝቡን እየደበደበ ነው፤ እስካሁን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ አሥራ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ሞተዋል፤ ቆም ብለን ራሳችንን አንድ ጥያቄ ጠይቀን ከየራሳችን ጋር እንነጋገር፤ የሶርያው አምባ-ገነን ከሕዝቡ ሲገነጠልና በሕዝቡ ላይ ሲነሣ በርከት ያሉ የጦር ኃይሉ አባላት ከሕዝቡ ጋር ተሰለፉ፤ ብዙዎች ግን ሎሌነት በልጦባቸው ሕዝቡን እየጨፈጨፉት ነው፤ አገርንና ሕዝብን አጥፍቶ የሚገኘው ጥቅም ምንድን ነው?
በሶርያ ጉዳይ ለተባበሩት መንግሥታት በምዕራባውያን ኃይሎችም በአረቦች ማኅበርም የቀረቡትን የውሳኔ ረቂቆች ሩስያና ቻይና እየተቃወሙ ለሶርያ ህዝብ ማንም ሳይደርስለት አሳድ በሩን ጥርቅም አድርጎ ዘግቶ ሕዝቡን በጭካኔ እየደበደበ ነው፤ ሩስያና ቻይና ከዓለም መንግሥታት ተገንጥለው አሳድን የሚደግፉበት ምክንያት ምንድን ነው? ጥቅም ነው፤ አሳድ የጦር መሣሪያውን የሚገዛው ከነዚህ አገሮች ነው፤ ከገንዘብ ጥቅምም ሌላ የሶሪያ አቀማመጥ ለሩስያ ወታደራዊ ፋይዳ አለው፤ ለዚህ ነው አሜሪካ የሶርያን መዳከም የሚፈልገውን ያህል ሩስያ የሶርያን ጥንካሬ የሚሻው፤ የምዕራባውያንን በጥቅም ላይ የተመሠረተ አመራር አሜሪካ አሁን ለማሊ ወታደሮች በሰጠው የእርዳታ መንፈግ ማስጠንቀቂያም ይረጋገጣል።

በሦስተኛው ዓለም የሚገኙ ደሀ ሕዝቦች ቢጨራረሱ ምዕራባውያንም ሆኑ ሩስያና ቻይና ከይስሙላ በላይ ግድ የላቸውም፤ ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም እንደሚባለው ነው፤ የሦስተኛው ዓለም አገዛዞች የሕዝቦቻቸውን ሕይወት እንዲጨነቁላቸው መመኘት ከንቱ ነው፤ አንድ ጊዜ ተማሪዎች ለሰላማዊ ሰልፍ ሲወጡ ተገድለው ስለሞቱት ሳዝን አንድ ጎረምሳ ዲፕሎማት (አገሩን መጥቀሱ አስፈላጊ አይመስለኝም) ‹‹እዚህ አገር ሰዎች በችጋር ያልቁ የለም እንዴ እነዚህ ተማሪዎች በጥይት መሞታቸው ምን ያስደንቃል!›› አለኝ፤ ሁነቱን መካድ አልቻልሁም፤ በወገን ጥይት መሞትና በችጋር መሞት ውጤቱ አንድ ነው፤ ግን ሁለቱንም አሟሟቶች ማኅበረሰባዊ ኃላፊነት የሚመለከታቸው ቢሆንም መንፈሳዊ ቁም-ነገር የጨበጠ ሰው በችጋር የሚሞተውን በጥይት ከሚገደለው ጋር አያመሳስለውም፤ ለጎረምሳው ዲፕሎማት የሰጠሁትም መልስ ይኸው ነበር።
የሦስተኛው ዓለም አገዛዝና የምዕራባውያን ዓለም-አቀፋዊ ፖለቲካ በጥብቅ የተቆራኘ ነው፤ አሁን ግን ለምዕራባውያን ኃይሎች የአምባ-ገነኖች ጠቀሜታና አገልግሎት በጥያቄ ውስጥ ገብቶአል፤ ከአሁን በኋላ ሕዝብን ችላ ብለው በአምባ-ገነኖች ላይ መተማመኑ የማያዛልቅ ለመሆኑ የአረብ አገሮች አብዮት ትምህርት እየሰጣቸው ነው፤ አምባ-ገነኖች ግን በዚያው ልክ ለመማር ይችላሉ ለማለት የሚቻል አይመስለኝም።

Advertisements
This entry was posted in አዲስ ጽሑፎች. Bookmark the permalink.