ሰውዬውን ከሀሳቡና ከአስተሳሰቡ እንለየው

መስፍን ወልደ ማርያም

መጋቢት 2004

አቶ ስብሐት ስለውይይትና ስለክርክር ጠቃሚነት ደጋግሞ ይጽፋል፤ በሰንደቅ ጋዜጣም በጻፈው ውስጥ (መጋቢት 12/2004) ‹‹ውይይት እየተደረገበት፣ ሕዘብ እየተሳተፈበት፣ ሓቁ እየተነጠረ፣ እውቀት እየተመረተ፣ ሕዝባዊ ጉልበት እየተጠናከረ እንዲሄድ የሚያደርግ ዓይነተኛ የዴሞክራሲ ሂደት ይመስለኛል፤ ሂደቱ መበረታታት አለበት፡፡›› ይላል፤ በመሠረቱ ይህ ግሩም ሀሳብ ነው፣ ግን ማንም የማይደግፈው የለም ለማለት አይቻልም፤ ይህንን ሀሳብ የማይደግፉት ለስብሐት ቅርብ ናቸው፤ መልእክቱ አንደሚደርሳቸው ተስፋ አለኝ፤ አፈና በኢትዮጵያ ታሪክ በተከታታይና በተለያዩ አገዛዞች የኢትዮጵያን ሕዘብ ጸጥ-ለጥ አድርጎ ለመግዛት መሣሪያ ሆኖ እስከዛሬ ቆይቶአል፤ ከላይም ሆነ ከታች፣ በግልም ሆነ በአደባባይ ይህንን ኋላ-አስቀሪ ባህል ብናጠፋው ትልቅ የአስተሳሰብ እመርታ ይሆን ነበር፤ አስተሳሰብ ሲቃና ብዙ ነገሮች ይቃናሉ፤ እኔ ስጽፍ ዓላማዬ የተዛባ አስተሳሰብ የመሰለኝን ለመጠቆም ነው፤ አስተሳሰባችን ትክክል ካልሆነ ተነጋግረን ለመግባባት አንችልም፤ ከአቶ ስብሐት ነጋ ጋርም ያለኝ ችግር ይኸው ነው፡፡

በተግባር ሲታይ አቶ ስብሐት የሚሰብከውን አያምንበትም፤ አንድ ጊዜ ተመስገን ለጻፈው ሲመልስ፣ በቅርቡ ደግሞ አቶ አስገደ ለጻፈው ሲመልስ የሦስተኛ ክፍል አስተማሪ ጠባይ አሳይቷል፤በአገራችን በመሠረቱ ሥልጣኑ ጎልቶ ለሚሰማው ሰው በእኩልነት ከተራ ሰው ጋር ያለቅሬታ ለመነጋገር በጣም ያስቸግረዋል፤ የተለመደው ለተራው ሰው ትእዛዝ መስጠት ነው፤ የተለመደው ተራው ሰው ባለሥልጣኑ ሲናገር ከሰማ በኋላ እጅ ነሥቶ መቀበል ነው፤ የደጃዝማቾቹ ሥርዓት እንዲህ ነበር፤ በተግባር እንደደጃዝማች በቃል አንደምሁር ለመሆን መሞከሩ እምብዛም አያራምድም፤ በሕዝብና በአገር ጉዳይ በአደባባይ ክርክር ለመግጠም የፈለገ ሰው ነጻነትና እኩልነት የተከራካሪዎቹ ሁሉ መብቶች መሆናቸውን አስቀድሞ ማወቅ ብቻ ሳይሆን በሙሉ ልብ መቀበልም አለበት፤ አለዚያ ይወርዳል፤ ሀሳብን በሀሳብ መመለስ ሲያቅት እንደስብሐት ወደሰውዬው ዞሮ እሱን ለማብጠልጠል መሞከር ማንንም አይጠቅምም፤ እንዲያውም ወደሌላ ስሕተት ያስገባል፡፡

ክርክሩ አቶ ስብሐት ስለአክሱምና ስለከተማ መንግሥት በተናገረው ላይ እኔ የሰጠሁት አስተያየት ነው፤ ለእኔ አስተያየት ስብሐት የሰጠው መልስ ስለመስፍን ወልደ ማርያም ምንነት ነው፤ እኔ ስለእኔ ለሚጻፉ አሉባልታዎች መልስ መስጠት አልለመድሁም፤ ጠቃሚም አይደለም፤ ስለቁምነገር መነጋገሩን ትተን ስለግለሰብ ያውም ተራ ግለሰብ መነጋገሩ ፋይዳ የለውም፤ የዛሬው የመጀመሪያዬና የመጨረሻዬም ይሆናል፤ በአጭሩ የሚከተሉትን አራት ነጥቦች ላንሣ፤ —

1.‹‹ከትልልቅ ሰዎች መገናኘትና ‹‹ማማከር›› እንደታላቅነትና ዝና (Glorification by Association) ስለምታየው ይመስለኛል አንጂ …›› ይለኛል፤ (ለእኔ በቀጥታ ነው የሚናገረው፤ የአጻጻፍ ሥርዓት አለማወቅ ሆኖ ነው እንጂ ለእኔ በቀጥታ መናገር አልነበረበትም፤) የእንግሊዝኛውን ሐረግ ከየት አምጥቶ እንደሻጠውና ከዝና ጋር እንዳያያዘው ቢጠየቅ መልሱ መስሎኝ ነበር ሳይሆን አይቀርም፤ አንድ ሰው በትክክል የማያውቀውንና ያልተገነዘበውን ሀሳብ ከግራም ከቀኝም እየነጠቀ ከወረወረ በኋላ ‹‹መስሎኝ ነው›› ቢል ምን ግምት ይሰጠዋል? በተለይ ደግሞ ልማድ ሲሆን ከሳይንሳዊ ጥርጣሬ ይወጣና ሌላ ነገር ይሆናል፤ በአጠቃላይ ግን ከመምሰል ለመሻገር አለመሞከር የአእምሮ ስንፍናን እንጂ አዋቂነትን አያመለክትም፤ በአለፈው ጽሁፌ ለወዳጄ ለአቶ ስብሐት ለማመልከት ከፈለግኋቸው ነጥቦች አንዱ አደባባይ ከመውጣቱ በፊት ሀሳቡን እንዲያጣራ የሚል ነበር፤ በአለፈው ንግግሩ ላይ ስለአክሱም፣ ስለተምቤንና ስለአጋሜ ያነሣውን የተዛባ ነጥብ በአጋጣሚ ‹‹አንድ የኦሮሞ ልጅ ፕሮፌሰር›› እንዳስለወጠው ነገረን፤ በጡንቻ እርግጠኛነት የተናገረውን በአንድ ‹‹ልጅ›› አስረጂነት መለወጡ የሚያስመሰግነው ነው።

2.‹‹ጃንሆይና ሥርዓታቸው ሲፈረድበት አንተ መርማሪ ነበርክ።›› እግዚአብሔር ያሳያችሁ! አሁን ይህንን ከአክሱም ጋር ምን አገናኘው? የማያውቀው ነገር ውስጥ እየዘለለ የሚገባው ለምንድን ነው? አዋጁን ቢያነብበውና በጊዜው የነበረውን ሁኔታ ቢያውቅ ጃንሆይ ዘንድ ቀርበን መሐላ እንደፈጸምን ይረዳ ነበር፤ ከዚህ አለማወቅ ለመውጣት አንድ ሌላ ‹‹ልጅ›› ፕሮፌሰር በአጋጣሚ እስቲያገኝ መጠበቅ የለበትም፤ ሰነዶቹ ሁሉ በእጁ እንዳሉ የሚቆጠሩ ናቸው፤ እነዚህን ሰነዶች አይቶ ቢናገር አሉባልታ ውስጥ አይወድቅም ነበር።

 

3. ‹‹ጠመንጃ በእጃቹህ እያለ የምን ምርመራ መጠበቅ ነው›› ብሎናል ነው የሚለው መንግሥቱ።›› ስብሐት ነጋ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ለምስክርነት ጠራ፤ ምስክርነቱንም ተቀበለ፤ መንግሥቱ ስለስብሐት የሚለውን እንድነግረው ፈልጎ ከሆነ እኔ መንግሥቱን ለምስክርነት አልጠራም።

4. ‹‹የብስጭትና የጥላቻ ፖሊቲካ ግን ያደባድባል። ከውጭ ጠላት ጋርም ስለሚያሰልፍ ምናልባት በየጊዜው ይቀያየር ይሆናል።›› አንደኛ አያደባድብም፤ ቢበዛ ያጨቃጭቃል ወደዱላ አያመራም፤ ወደዱላ ካመራ ፖሊቲካ መሆኑ ቀርቷል፤ ሁለተኛ በእነዚህ ዓረፍተ ነገሮች ውስጥ ስለተነገሩት ስሜቶችና ዝንባሌዎች ሁሉ ከውጭ ጠላት ጋር ስለመሰለፍም ጨምሮ አቶ ስብሐት ከእኔ ይበልጥ በጣም ያውቃል፤ በእኔ በኩል አገርን ለሆድ ወይም ለሥልጣን የለወጠ ዘመድም የለኝ፤ ታላቅ ወንድሜ (ነፍሱን ይማረውና) ባንዳ ሆነና እናቴ ‹‹ማንን ልትገል ነው የጣልያን ወታደር የሆንከው!›› ብለው ቤት አላስገባም አሉትና ወጣ፤ አባቴም ማይጨው ዘምተው የቆሰሉ ናቸው፤ አንድ ወንድሜም በማይጨው ሞቶአል፤ በአባቴም ሆነ በእናቴ በኩል ከጠላት ጋር የተሰለፈ የለም፤ ስብሐት የሚያውቀው ከአለ ይህ የአገር ጉዳይ ነውና በይፋ ሊያወጣው ይገባል።

አቶ ስብሐት ስለሀሳቤ ወይም ስለአስተሳሰቤ ሳይሆን ስለኔ የተናገረውን እዚህ ላይ እስከዘላለሙ እገታና ወደአቶ ስብሐት አስተሳሰብ እገባለሁ፤ በየካቲት 14 ለሰንደቅ ጋዜጣ በተናገረው ላይ ‹‹ታሪክ የፖሊቲካ አቋም ስላልሆነ ተነቦ ሊስተካከል ይችላል፤›› በማለቱ የሀሳብና የአስተሳሰብ ግድፈት አድርጌ ያነሣሁት ነጥብ ነበር፤ ታሪክ ተማሪው፤ ታሪክ ተመራማሪው ይለወጣል እንጂ ታሪክ አይለወጥም፤ በአጭሩ እኔ ያልሁት ታሪክ የሆነ፣ የተደረገ፣ ያለፈ ነገር ስለሆነ አይለወጥም የፖሊቲካ አቋም ግን እንደጊዜው ሁኔታ ሊለዋወጥ ይችላል፤ ስለዚህም ትክክለኛ አስተሳሰብ የሚሆነው ስብሐት ከተናገረው ተቃራኒው ነው፤ ነበር ያልሁት።

አሁን ደግሞ በወሩ ስብሐት ‹‹ፖሊቲካዊ አቋም የተነሣበት ሁኔታ እስኪቀየር ድረስ አይለወጥም››!!! ይለናል፤ የቃላት ችግር ነው? ወይስ የአስተሳሰብ? እንደሚመስለኝ የፖሊቲካው አቋም ግቡን እስቲመታ ድረስ የፖሊቲካው አቋም አይለወጥም ማለቱ ነው፤ ይሄ ሃይማኖት ነው ፖሊቲካ? በብሪታንያ የሠራተኞችም ሆነ የወግ አጥባቂዎቹ ቡድኖች በኛ ዕድሜ በጣም ተለዋውጠዋል፤ በሶቭየት ኅብረትማ ትልቅ ለውጥ አይተናል፤ በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ ውስጥ ሁለቱም የፖሊቲካ ቡድኖች በጣም እየተለወጡ ናቸው፤ ከዱሮው ይበልጥ እየተራራቁ የሚሄዱ ይመስላሉ።

ፖሊቲካ ማለት ጥቂቶች ሰዎች ተመራርጠው ሥልጣን ላይ ለመውጣት የሚዘረጉት መሰላል ከሆነ የእነዚያ ሰዎችና የሎሌዎቻቸው ዕድሜ ልክ መስሎ ሊታይ ይችላል፤ ግን ከአለፈው ዓመት ጀምሮ በአካባቢያችን እንደምናየው የገዢዎቹ የፖሊቲካ ዓላማና የሕዝቡ የፖሊቲካ ዓላማ የተራራቀ በመሆኑ ፖሊቲካው እየተለወጠ መሆኑን  ነው፤ ታሪክ ግን አይቀየርም።

‹‹የኢትዮጵያ ግዛቶችን ሳንገደድ በውዴታ ለምን አሳልፈን እየሰጠን ቆየን? … በምን ምክንያት ነው ነጋ ጠባ ለውጭ ወራሪ ተጋልጠን ተወራሪዎችና ተደብዳቢዎች››  የሆንነው? ጥሩ ጥያቄ ነው፤ ግን ጥያቄው በተለይ ከእንደአቶ ስብሐት ካለ ሰው ለእንደኔ ያለው መቅረቡ ያስደንቃል፤ የቱን ታሪክ ለማስታወስ ነው የተፈለገው፤ የቀድሞው ታሪክ ብዙ ተጽፎበታል፤ በአለፉት ሃያ ዓመታት ስለተቆራረሰው የኢትዮጵያ አካል የሕወሓት (ወያኔ) መሪ የነበረ ሰው ማንን ይጠይቃል? ከአረቦች አርዳታ ሲቀበል የነበረው ማን ነው? የሻቢያ ጥገኛና ረዳት ሆኖ ያደገ ማን ነው? ስለአክሱም ታሪክ ስንነጋገር ስለትናንትናው ልንካካድ አንችልም።

Advertisements
This entry was posted in አዲስ ጽሑፎች. Bookmark the permalink.