አለውክልና ግብር የለም

 ሚያዝያ 2004

ስለግብር ስናገር ወደ አርባ ዓመት  ሊሆነኝ ነው፤ ዛሬ ሁሉም ስለግብር ይናገራል፤  እንዲያውም ወሬው ሁሉ ስለግብር፤ ስለቫት  እየሆነ ነው፤ ዱሮ እኔ የምጮኸው በገበሬው  ላይ ስለተጫነው ግብር ነበር፤ የዛሬው ጩኸት  በነጋዴው ላይ ስለተጫነው ግብርና ወደበላተኛው ስለሚተላለፈው ግብር ነው።

በፈረንጆች አንድ የታወቀ አባባል  አለ፡- አለውክልና ግብር የለም –ተረት ሳይሆን  ከፖለቲካ ፈላስፋዎቻቸው የመነጨ ቁም- ነገር ነው፤ ለአንድ አገር መንግሥት ገንዘብ  እንደሚያስፈልገው ሳይታለም የተፈታ ነው፤  የአገርን ዳር-ድንበር ለማስከበር ወታደር  ያስፈልጋል፤ የሕዝቡን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ  የፖሊስ ኃይል ያስፈልጋል፤ የሕግ አስተዳደሩን  የሚያካሂዱ ዳኞችና የሕግ ሰዎች ያስፈልጋሉ፤  አስተዳደሩን በየደረጃው የሚያስኬዱት ብዙ ሰዎች  ያስፈልጋሉ፤ ለትምህርት ቤቶች መምህራንና  መጻሕፍት፣ ሌሎችም ነገሮች ያስፈልጋሉ፤  ለሀኪም ቤቶች ሀኪሞች፣ እቴዋዎች፣ ሌሎችም  ባለሙያዎችና መሣሪያዎች ያስፈልጋሉ፤ ከነዚህ  ሁሉ ጋር የውሃ፣ የመብራትና የመንገድ ነገሮች  ሁሉ ሰዎች ያስፈልጓቸዋል፤ እነዚህ ሁሉ ሰዎች  እንደሌላው ሰው ሁሉ መብላትና መጠጣት  ብቻ ሳይሆን የተደላደለ ኑሮ እንዲኖራቸው  ያስፈልጋል፤ ይህ ሁሉ ‹‹ያስፈልጋል›› ሳይታለም  የተፈታ ነው።አንድ ያስፈልጋል ያላልሁት በጣም  የሚያስፈልግ ነገር አለ፤ ግን የአገዛዞች ሹማምንት  ሁሉ ከጉዳይ የማይቆጥሩት የመኖሪያ ቤት  ጉዳይ ነው፤ የመኖሪያ ቤት ምን ያህል አስፈላጊ  መሆኑን ሹማምንቱ ዱሮም አሁንም ለራሳቸው  እያንዳንዳቸው ለአምስት ቤተሰብ የሚበቃ ቤት  በመስራታቸው ይረጋገጣል፤ ይሁን እንጂ  በዝቅተኛ ኑሮ ላይ ለሚገኘው ሕዝብ በአቅሙ  መኖሪያ ቤት ለመገንባት የሞከረ አገዛዝ የለም፤  ደርግ መሬቱን ነፃ በማድረግ ትንሽ ተቃርቦ  ነበር፤ እንደሚመስለኝ ዋናው ምክንያት ትንንሽ  ቤቶችን በመሥራት ብዙ የሚገሸለጥ አለመኖሩ  ነው፤ አንድ ምስክርነት ልስጥ፤ በ1967 ግድም  ቀበሌዎች እንደተመሰረቱ በየዋህነት ለሕዝቡ  ጥቅም የሚያገለግሉ መስሎኝ የልማት ኮሚቴ  የሚባለው ውስጥ ገባሁ፤ በባለሥልጣኖች  እንደተለመደው ኮሚቴው የቀበሌው ችግሮች  የሚላቸውን በመላ-ምት መዘርዘር ሲጀምር፣ ልክ  እንዳልሆነ ተገንዝበን በእኛ ስብሰባ የቀበሌውን  ሕዝብ ችግር በቅደም-ተከተል ልናውቀው  አንችልም፤ ስለዚህ ራሱ ችግሩን ይናገር በማለት  ተወሰነ፤ ሕዝቡን አንደኛ ችግር፣ ሁለተኛ  ችግር፣… እያለ እስከአምስተኛ ችግር ድረስ  እንዲገልጽ መጠይቅ ሠርተን ሰዎች በየቤቱ  እየተዘዋወሩ እንዲሞላ ተደረገ፤ ውጤቱ ማንም  ጠበቀው አልነበረም፤ አንደኛ ችግር ቤት፣  ሁለተኛ ችግር ሰገራ ቤት!   ከዚህ ተነስተን በጥሩ ሁኔታ በእንጨትና  በጭቃ የሚሰሩ ቤቶች እቅድ አወጣን፤ ወጪውን  ሁሉ አሰላን፤ ለነጠላ ሰዎች በአምስት ብር፣  ለባልና ሚስት በሃያ አምስት ብር የሚከራይና  በአስር ዓመታት ዋጋውን የሚመልስ አድርገን  ለቀበሌው ስናቀርበው የቀበሌው ሱቅ ለሚባለው  ገንዘቡን ሲሰጡ ለእኛ ከለከሉ፤ ቀረ! እኔም  ከቀበሌ ጋር በየዋህነት የጀመርሁትን ግንኙነት  አቋረጥሁ፤ ዛሬም ቢሆን ‹‹የመንግሥት ሌቦች››  ከፈቀዱ በዝቅተኛ ኑሮ ላለው ሕዝብ መጠነኛ  ቤት በመጠነኛ ኪራይ ለመሥራት ይቻላል፤  ኮንደሚኒየም የሚባለውን አለማንሣቴ ረስቼ  እንዳይመስላችሁ! ጥያቄዎች የሚነሡት ገንዘቡ እንዴት  ይሰብሰብ? እንዴት ይደልደል? የት የትና እንዴት  ይከፋፈል? በሚሉትና ሌሎችም ጥያቄዎች ላይ ነው፤ የፈረንጆቹ አለውክልና ግብር የለም  የሚለው ቁም-ነገር ሥራ ላይ የሚውለው እዚህ  ላይ ነው፤ ማህበረሰቡ ወይም ህዝቡ ችግሩን  ያውቃል፤ የችግሩን ቅደም-ተከተል ያውቃል፤  ስለዚህም እንኳ ገንዘብና ጉልበቱንም ቢሆን  ለመገበር ዝግጁ ነው፤ ማናቸውም የሹማምንት  ውሳኔ ላይ የችግሩ ባለቤት የሆነው ሕዝቡ  በእውነት ተወክሎአል ወይ? በስራውስ ላይ  እውነተኛ ተሳትፎ ነበረው ወይ? የመንግሥት  ሌቦች የፈለጉትን፣ በፈለጉበት ጊዜና በፈለጉበት  ቦታ እየሠሩ ደሀውን ከደሀነት እናድንሃለን ቢሉ  ደሀው ከቁልቁለቱ መንገድ አይወጣም፤ ደሀው  ግብሩን ይከፍላል፤ ከግብር በተገኘው ገንዘብ  የሚጠቀመው ግን ሌላው ነው።

የተመረጡ ‹‹ደሀዎች›› በቴሌቪዥን  ጨዋታ ቢያሳዩም ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ  መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነው፤ የቴሌቪዥን  ጨዋታው ወደአልጀዚራም መተላለፉ አስደናቂ  አይደለም፤ ደሀነትን ለማጥፋት ሊወጣ የሚገባው  ገንዘብ ለአንድ እበላ-ባይ ጋዜጠኛ ኑሮ ማዳበሪያ  መሆኑ ያሳዝናል።

ሕጋዊ ግብር ሲባል የከፋዩ የገቢ መጠንና የኑሮ ሁኔታ መታየት አለበት፤ ለምሳሌ  አንድ ሰው በዓመት አራት መቶ ብር ቢያገኝና  የቤተሰቡ ቁጥር አምስት ቢሆን ከዚህ ሰው ላይ ምንም ያህል ገንዘብ በግብር ስም መውሰድ  ወደወንጀል ይጠጋል፤ ልብስንና ሌላውን  እንርሳና ለምግብ ብቻ ብናስብ ቤተሰቡ በሙሉ

የሚያገኘው በቀን አንድ ብር ከአስር ሳንቲም  ነው፤ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል እኩል ከተካፈለ  በቀን የሃያ ሁለት ሣንቲም ምግብ ያገኛል፤  ይህም ቁርስን ትቶ ለምሳ አስር ሣንቲም፣ ለራት  አሥር ሣንቲም ይሆናል ማለት ነው፤ ይህንን  ቤተሰብ ግብር ማስከፈል ወንጀል አይሆንም? ደሀውን ገበሬ አስቡት፤ ምናልባት  በኩርማን ሄክታር መሬት ላይ ሶስት ኩንታል  ጤፍ ያመርት ይሆናል፤ ለምግብ ሳያስቀር  ሶስቱንም ኩንታል እያንዳንዱን በስምንት

መቶ ብር ሂሳብ ቢሸጠው ለእያንዳንዱ አባል  የሚደርሰው አንድ ብር ከሠላሳ ሣንቲም ነው፤  ማሽላና ዘንጋዳ፣ ወይም በቆሎ የዘራው ያንን  ያህል አያገኝም፤ ለጅምላ ሞት የሚያበቃ ችጋር አለመከሰቱ እርዳታ እያሉ ጥገኛነትን የሚያስፋፉ  አገሮች በሚሰጡት እርዳታ ነው።

በአለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ ትልቅ  እርምጃ (ወደፊት ይሁን ወደኋላ ባይታወቅም) የታየው ከህዝብ ገንዘብ የመሰብሰቢያው ዘዴ  ነው፤ አልፎ አልፎ ከሚደረግ የደርግ ‹‹የእናት  አገር ጥሪ›› በጣም የረቀቀና ፋታ የማይሰጥ ነው፤  ማንም አያመልጥም፤ በረሀብ እየተዝለፈለፉ  ተማሪ ቤት የሚሄዱ ተማሪዎችም መዋጮ እንዲከፍሉ ይገደዳሉ፤ ልዩ ልብስ ገዝተው  እንዲለብሱ ይገደዳሉ፤ ሕጋዊው ግብር ጭነቱ በዛ  ሲባል ከሕግ ውጭ ያለው መገበሪያ እየተስፋፋ  ነው።

     ችጋር ወደሞት አፋፍ ላይ የሚያደርስ  የደሀነት አዘቅት ነው፤ የሞት አፋፍ ላይ  የቆመውን ግብር ማስከፈል ወይም መዋጮ  መጠየቅ ደሀነትን ያስፋፋል እንጂ አይቀንሰውም፤  አለውክልና ግብር የለም የሚባለውንም ቁም-ነገር  ይጥሳል።

Advertisements
This entry was posted in አዲስ ጽሑፎች. Bookmark the permalink.