የኖርዌዩ ወጣት የጥላቻ ማኅደር


ሚያዝያ 2004

የኖርዌይ ሕዝብ በጣም ሃይማኖተኛና  በጣም ሰላማዊ የሚባል ነው፤ በዓለም-አቀፍ  ደረጃም ግጭትና ጦርነት ባለበት ሁሉ እርቅንና  ሰላምን ለማምጣት የሚጥር ህዝብ ነው፤ ነገር  ግን የዛሬ ዓመት ግድም አንድ የኖርዌይ ወጣት  ከኖርዌያውያን የማይጠበቅ በጣም የሚያሰቅቅ  ክፉ ወንጀል ፈጸመ፤ ሰሞኑን በፍርድ ቤት  ቀርቦ ጉዳዩ እየታየ ነው።

ይህ መልካም የሰው ቅርጽ የያዘ  ወጣት ተግባሩ የአውሬ ነበር፤ በኦስሎ  በኖርዌይ ዋና ከተማ በመኪና ውስጥ ቦምብ  ጠምዶ በፍንዳታው ስምንት መንገደኞችን  ገደለ፤ አልበቃ ብሎት በጣም ዘመናዊ መሳሪያ  ይዞ ወጣቶች ወደተሰበሰቡበት ደሴት ሄዶ  እያነጣጠረ ስድሳ ዘጠኝ ያህል ወጣቶችን ገደለ፤  አልሸሸም፤ ሆን ብሎ በእሱ ግምት በአገሩ  ላይ የአንዣበበውን አደጋ ለማየት ህዝቡ ጥሩ  እንዲነቃ ለማድረግ ነበር፤ አውሮፓ በእስላሞች  እየተወረረ በመሆኑ የአውሮፓ ህዝብ ይህንን  አደጋ እንዲገነዘብ ለማድረግ የፈጸመው  አስፈላጊ ተግባር ነው ብሎ በአደባባይ ተናገረ፤  እስልምናንና እስላሞችን ይጥላ እንጂ ቆም ብሎ  ማሰብ ቢችል እንደሱ በጥላቻ የታጨቀ እስላም ብቻውን ሆኖ ኖርዌያዊው ራሱ ከአደረሰው  ጥፋት የበለጠ ምን መስራት ይችል ነበር?

ስለዚህም በጥላቻ በታጨቀ እስላምና በጥላቻ  በታጨቀ ክርስቲያን መሀከል ልዩነት የለም  ማለት ነው፤ ሁለቱም የጥፋት መልእክተኞች  ናቸው፤ ሁለቱም የሰው ልጆች ጠላቶች ናቸው፤  ሁለቱም ሃይማኖታቸውን የክፋትና የወንጀል  መሸፈኛ እያደረጉ ናቸው፤ የራስን እምነትም  ሆነ አመለካከት በግድ በሌሎች ላይ ለመጫን  መሞከር፣ የማይሆንለት ሲሆን ደግሞ በጭካኔ  በመደዳው መግደል በአንድ በኩል የማመዛዘን  ችሎታ ያለው፣ በሌላ በኩል የሉዓላዊ ኃይል  መንፈስን የታደለ የሰው ልጅ የሰይጣን ማኅደር  ሲሆን የሚያደርገው እኩይ ተግባር ነው።  የኖርዌዩ ወጣት ጥላቻው ለእስልምናና  ለእስላሞች ብቻ አይደለም፤ ጥላቻው ለሰው  ልጆች ሁሉ ነው፤ በአፍጋኒስታንና በኢራቅ፣  በፓኪስታንም እንደኖርዌዩ ወጣት ሰዎችን በጅምላ የሚያቃጥሉ ሰዎች አሉ፤ የእነዚህን  ከኖርዌዩ የሚለየው በአገራቸው ውስጥ  ‹‹ወራሪ›› የሚሉት የውጭ ኃይል መኖሩና  ለትግላቸው የሉዓላዊነት ሽፋን ማግኘታቸው  ነው፤

ልብ በሉ፤ ይህ የኖርዌይ ወጣት  ጥላቻው በእስልምና እና በእስላሞች ላይ  ይመስላል፤ ነገር ግን የጨረሳቸው ሰባ ሰባት  ሰዎች የአገሩ ልጆች ናቸው፤ ግራ የሚያጋባ  ይመስላል፤ ፍቅርና ጥላቻ ኃይላቸው ሙሉ  የሚሆንበት ጊዜ አለ፤ ፍቅርም ሆነ ጥላቻ ልብን መቶ በመቶ አፍኖ ሲይዝ መስፈሪያ ነገር  ሁሉ፣ ሚዛን ሁሉ ይሰባበራል።

የኖርዌዩ ወጣት ልቡ በጥላቻ ሞልቶ፣  ዙሪያውን በሙሉ በጥላቻ ቀለም ሲቀባ ኖሮ  የመጨረሻውን የጥላቻ ቅብ ሲቀባ አድሮ፣ ጠዋት ሲነሣ ዙሪያው ጠላት ሆኖ አገኘው፤  ያኔ መግደያ መሣሪያውን አነሣና ያገኘውን  ሁሉ፣ ሰባ ሰባት ሰዎች ጨረሰ፤ በፍጹም  አልተጸጸተም፤ ጥላቻው የጣለበትን ግዴታ  ፈጸመ እንጂ ጥፋት ወይም ወንጀል መሥራቱን  አላመነም፤ መግደሉን አልካደም፤ የገደላቸው  የገዛ ወገኖቹ መሆናቸውን አልካደም፤  የሚጠላው እስልምናን መሆኑን ተናግሮአል፤  ከእስልምና ጋር አያይዞ የሚጠላው እስላሞችን  መሆኑን ገልጾአል፤ ታዲያ እስላሞች እስልምና  ሊከላከልላቸውና ሊጠብቃቸው የሚፈልገውን  የሚወዳቸውን ሰዎች የገደላቸው እስላሞች  እንዳይሆኑበት ነበረ?

የጥላቻን ጭካኔና ክፋት፣ የጥላቻን  ጭፍንነትና ድፍንነት የምናየው የኖርዌዩ  ወጣት የገደላቸው የገዛ ወገኖቹ በመሆናቸው  ነው፤ ጥላቻ የመጥፎ ስሜቶች ሁሉ ቅይጥ ነው፤ ቁጣና ንዴት፣ ክፋትና ተንኮል፣  ዕብሪትና ጭካኔ፣ ፍርሃትና ጥርጣሬ በአንድ  ላይ ተፈትለው የተሰሩበት መጥፎ ስሜት  ነው፤ በእንዲህ ያለ የጥላቻ ስሜት ተቀስፎ  የተያዘ ሰው እንቅልፍ አያገኝም፤ አካሉ በሙሉ  ከአለው ሁሉ ችሎታ ጋር የጥፋት ፋብሪካ  ይሆናል፤ አጋጣሚ አግኝቶ ሂትለርን ወይም  ሙሶሊኒን፣ ስታሊንን ወይም ኢዲ አሚንን  ከሆነ የጥፋት ፋብሪካው በብዙ ሠራዊትና  በብዙ የተለያዩ መሣሪያዎች የታገዘ ስለሚሆን  የጥፋቱ መጠን ሰፊና የከፋ ይሆናል፤ እንደ  ኖርዌያዊው ወጣት ብቸኛ ከሆነና እንደኖርዌይ  ባለ የሠለጠነ አገር ግን ጥፋቱ የተወሰነ ይሆንና  ሕግ ያቆመዋል።

 

ሰባ ሰባት ሰዎችን ገድሎ የጥላቻው  ደንዳናነት ምንም ጸጸት እንዳይሰማው  ኅሊናውን የጋረደው፣ ምንም የሞቱት ሰዎች  ዘመዶች መሪር ሐዘን በጨረፍታ ያላረፈበት፣ ምንም የሟቾቹ የተቋረጠ ተስፋና የተቀጨ  ሕይወት ያልከነከነው ሰው እጁን ጨብጦ ‹‹ደግ አደረግሁ!›› በሚል የፉከራ ምልክት በፍርድ ቤቱ ውስጥ እጁን ጨብጦ ‹‹ደግ አደረግሁ!››  በሚል የፉከራ ምልክት በፍርድ ቤቱ ውስጥ እጁን አነሣ፤ ዕድሉን ካገኘ የሠራውን አስከፊ  ተግባር እንደገና እንደሚያደርገው ሳያፍር ተናግሮአል።

እንዲህ ያለው የጥላቻ ማኅደርና  የጥላቻ መልእክተኛ ሕጋዊ ሥርዓት  በሰፈነበት ማኅበረሰብ ውስጥ በቶሎ ይቀጫል፤  ማኅበረሰቡም ትምህርት ያገኝበታል፤ ሕጋዊ  ሥርዓት ባልሠለጠነበት ማኅበረሰብ ውስጥ ግን  እንዲህ ያለ እኩይ አመለካከት እንደቆላ ቁስል  ውስጥ ውስጡን እየተሰራጨ ማኅበረሰቡን  መርዞ እስከመግደል ይደርሳል።

Advertisements
This entry was posted in አዲስ ጽሑፎች. Bookmark the permalink.