ትራንስፎርሜሽን ምን ማለት ነው? ማን ገብቶታል? (ከልማት አድማስ ባሻገር)


ሚያዝያ 2004

‹‹ትራንስፎርሜሽን›› የእንግሊዝኛ ቃል ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማርኛ ችሎታው የሚደነቅ ሲሆን ለምን ይህንን የእንግሊዝኛ ቃል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ደነቀረውና ሰውን ሁሉ አደናገረው? ሰፊና ጥልቅ ማኅበረሰባዊ ለውጥ በማኅበረሰቡ ውስጥ ነውጥ (ይቺ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል ነች!) በሚፈጠርበት ጊዜ አእምሮም መንፈስም ይነካል፤ ግንበ ሰናኦርን ወደሰማይ ሲክቡ የቋንቋ አለመግባባት እንደተፈጠረና ሰዎቹ ሥራቸውን ለማከናወን እንደተሳናቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፤ በተጨማሪ በአብዮት ጊዜ እንዲሁ የቋንቋ መዘበራረቅ እንደሚፈጠር ሌኒንም ማኦም በቁጣ ጽፈዋል፤ በኢትዮጵያ አብዮቱ በጦፈበት ጊዜ ቋንቋ ድራሹ ጠፍቶ ነበር፤ አፍ ላይ የመጡትን ቃላት እንደልብ እየደረደሩ ሀሳብ የሌለበት ንግግር ማድረግ የዘመኑ ፈሊጥ ነበር፤ በዚያን ዘመን አዲስ ዘመን ‹‹ስለእርባታ ኃይሎች›› ሲያወራ ስለከብት እርባታ የመሰላቸው ሰዎች ነበሩ፤ አንዴ ደግሞ ርእሰ አንቀጹ ‹‹ሳይንሳዊ ቅጥፈት›› የሚል ነበር፤ የጋዜጣው አዘጋጅ ሳይንስና ቅጥፈት ሊዛመዱ የማይችሉ መሆናቸው አልገባውም ነበር፤ ወይም እንዳይገባው ተደርጎ ነበር! እውቀት በሥልጣን በኩል ተገኘ ሲባል ይህን ያመጣል።ወደ ትራንስፎርሜሽን እንመለስና፣ በ‹‹ትራንስ›› የሚጀምሩ የእንግሊዝኛ ቃላት ብዙ ናቸው፤ ትራንስፓርቴሽን፣ ትራንስሌሽን ሁለት ምሳሌዎች ናቸው፤ ትራንስፓርቴሽን ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ ማዛወር ወይም ማንቀሳቀስ ነው፤ ያንኑ ነገር ቦታውን መለወጥ ብቻ ነው፤ ትራንስሌሽን ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላ ቋንቋ መተርጎም ነው፤ ይህ ደግሞ አንዱን ነገር ከተቻለ ነፍሱን ብቻ በውስጡ አስቀርቶ አካሉን በሙሉ መለወጥ ነው፤ ትራንስፎርሜሽን ማለት መልኩን መለወጥ ነው፤ በዚህ ትርጉሙ ከተረዳነው የሕዝቡን መልክ መለወጥ አይቻልምና ገና በጥንስሱ ሰዎችን የመለወጥ ዓላማ አልነበረበትም ማለት ነው፤ ሕዝቡን አይመለከትም ማለት ነው፤ ለከተማዎች መልክ ሳይሆን አይቀርም፤ ትራንስፎርሜሽንን በአዲስ አበባ ላይ ስለጥፈው ትክክል ይመጣል፤ ተወልጄ ያደግሁበትን ከተማ፣ ከእንጦጦ እስከብሾፍቱ፣ ከኮተቤ እስከአምቦ፣ ከጊዮርጊስ እስከዝቋላ በእግሬ እየሮጥሁ ያደግሁበትን ከተማ ዛሬ አላውቀውም፤ በየሄድሁበት ይደናገረኛል፤ እኔ የማውቀው ሰፈር ድራሹ ጠፍቶ፣ ወይ የእንጦጦን፣ ወይ የኤረርን፣ ወይ የዝቋላን፣ ወይ የወጨጫንና የመናገሻን ተራራዎች እየሸፈነ ወደሰማይ ያንጋጠጠ ግንበ ሰናኦር፣ የቤት አነባበሮ ተሠርቶአል፤ ትራንስፎርሜሽን ማለት ይሄ ነው፤ ዱሮ ዱሮ መደማመጥ በነበረበት ዘመን በአራት ኪሎ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ውስጥ በነበረው ርዕደ-ምድር መካነ ጥናት በአዲስ አበባ ውስጥ ከአምስት ፎቅ በላይ እንዳይሠራ መባሉን አስታውሳለሁ፤ ትራንስፎርሜሽኑ የከርሰ-ምድርን ሁኔታ በጣም የናቀው ይመስላል፤ በዚያ ላይ የመብራት ኃይል ምን ያህል አስተማማኝ ቢሆን ነው አሥርና ሃያ ፎቅ የመውጣትና የመውረዱ ችግር ያልታሰበው! የአዲስ አበባ መልክ ተለውጦአል፤ አያጠራጥርም፤ እዚህ ላይ አንድ ታሪክ ትዝ አለኝ፤ አዲሱ የማዘጋጃ ቤት ሕንጻ ከጊዮርጊስ በታች ተሰርቶ ለአዲስ አበባ አዲስ ጌጥ ሊሆን በተቃረበበት ጊዜ በጊዜው የነበሩት ከንቲባ ከአንድ ጓደኛቸው ጋር ይጨዋወታሉ፤ ከንቲባውን በነገር ለመውጋት የከንቲባው ጓደኛ ‹‹አሁን ይሄ ሕንጻ ሲያልቅ እናንተው ናችሁ የምትገቡበት?›› ብለው በማሾፍ ጠየቁ፤ ከንቲባውም የዋዛ ሰው አልነበሩምና ‹‹ደምበኞቻችንም እኮ እናንተው ናችሁ!›› ብለው በማሾፍ መለሱላቸው፤ ከንቲባውና ጓደኛቸው ቢቀልዱም ንግግራቸው ትልቅ ቁም-ነገርን የያዘ ነበር፤ ሕንጻው አዲስ ነው፤ አላሉትም እንጂ ትራንስፎርሜሽን ሊሉት ይችሉ ነበር፤ በጊዮርጊስ ፊት ለፊት ከሚታየውና የአዲስ አበባን ሕዝብ ከሚመስለው የትራንስፎርሜሽን ቢሉት ዘመናዊ ያደርገዋል፤ አዲስና ዘመናዊ ሕንፃ ገንብተው በዚያ ውስጥ ገብተው የሚሰሩትና በዚያው ሕንጻ ውስጥ ለአገልግሎት የሚመጡት የሕንጻው አዲስነትና ዘመናዊነት በጭራሽ ያልነካቸው ከሆኑ የሕንጻው መገንባት ፋይዳው ምኑ ላይ ነው?በትራንስፎሜሽን የአዲስ አበባ ሕንጻዎችና መንገዶች በጣም ተለውጠዋል፤ አምረዋል ለማለትም ያስደፍራል፤ ከሕንፃዎቹና ከመንገዱ ሳንወጣ ስንት ዓመት እንዳማረባቸው ይቆያሉ? መንገዶቹስ ስንት ክረምት ያሳልፉናል?

ትልቁና ዋናው ቁም-ነገር ሕንጻዎቹና መንገዶቹ የተሰሩት ለማን ነው? የሚለው ጥያቄ ነው፤ ሰፊ አስፋልት መንገድ ተሠርቶ ለአህዮች መንጃ የሚውል ከሆነ፣ ወይም በቀለበት መንገድ ግራና ቀኝ የሚኖሩ ሰዎች መንገዱን ለማቋረጥ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች፣ ልጆችም ሆኑ ሕጻናት ከመኪና ጋር ሲሽቀዳደሙ የሚደርስባቸው ፈተናና አደጋ የሚያሳዝን ከሆነ፣ ትራንስፎርሜሽን የተባለው ከሰዎች ጋር ግንኙነት እንደሌለው ከዚህ በላይ ማስረጃ አያስፈልግም፤ መንገዱ ሲሠራ ሰዎቹ ተረስተው የነበረ ይመስላል፤ ጎጆዎቻቸው ፈርሰውባቸው መድረሻ ያጡትን ሰዎች እናስታውሳቸው፤ በሕንጻና በመንገድ ግንባታ የብዙ ሰዎች ኑሮ ፈራርሶአል፤ ብዙ ሰዎች ፈራርሰዋል።

ትራንስፎርሜሽን ለውጥ ማለት ሲሆን፣ ለውጥ ማለት ልማትን ብቻ ሳይሆን መሻገትንም ይጨምራል፤ ስለዚህም ለልማት የሚደረገው ለውጥ መሻገትን ካላቆመ ለሕዝብ የኑሮ እድገት አይመጣም፤ ግሩም ሕንጻ ተሠርቶ የተፈለገው ስም ቢሰጠው በሚሰጠው አገልግሎት ላይ በጎ  ለውጥ፣ ለተገልጋዩ ሕዝብ የሚበጅ ለውጥ  ካላመጣ ለግምቡና ለሰራተኞቹ የሚወጣው ኪሳራ ሊሆን ይችላል፤ በቅንነት ለመሥራት በጎ ፈቃድ ሲኖር የችሎታ ማነስንም ሊያሸንፍ ይችላል፤ ቅን መንፈስ በጎደለበት ሥልጣንና ተንኮል ሲገናኙ ሕግን መጫወቻ ያደርጉታል፤ በቅርቡ አንድ ከምርጫ ቦርድ ለአንድ እጩ የፖለቲካ ቡድን የተጻፈ ደብዳቤ አይቼ በጣም አዘንሁ፤ የትራንስፎርሜሽኑ የልማት መንፈስ መሥሪያ ቤቱን እንዳልጎበኘውና በአንጻሩ የማሻገት ኃይሉ የማያራምድ እንደሆነ በግልጽ ይታያል፤ ሌላም ምሳሌ በትግራይ የውሃ ጉድጓድን በሚመለከት የዛሬ ሳምንት በኢንጂነር (ዓብድልዋሃብ ቡሽራ ፍትሕ ጋዜጣ የሚያዝያ 26 ዕትም) አሳዛኝ መረጃ ተሰጥቶ ነበር፤ ደርግ የለውጥ ሐዋርያ የሚባሉ በየመሥሪያ ቤቱ ሾሞ ነበር፤ ዞሮ ዞሮ የለውጥ ሐዋርያቱን ከየት እናመጣቸዋለን? የዚሁ ማኅበረሰብ አካል ናቸው፤ ባህሉ፣ ችግሩ፣ ሕመሙ፣… ምኑም ምኑም ያለባቸው ናቸው፤ ስማቸውን በመለወጥ ባሕርያቸውን መለወጥ አይቻልም።ዱሮ. ዱሮ የአዋሽ ሸለቆ ባለሥልጣን  የሚባል መሥሪያ ቤት ተቋቁሞ ነበር፤ ለወንጂ ሸንኮራ አገዳ እርሻ መሬት ሲባል በዚያ አካባቢ ከብቶቻቸውን እያረቡ በዘላንነት የሚኖሩ ሰዎችን ወደዳር ገፍተው የበይ ተመልካች አደረጓቸው፤ ይህንን ለውጥ በመኮነን በኢትዮጵያ የጂኦግራፊ መጽሔት ላይ ጽፌ ነበር፤ የሰማኝ አልነበረም፤ ነገር ግን ልማት ብለው ከገቡት ውስጥ ዛሬ አንድም የለም፤ ትምህርት ሳይሆነን ቀርቶ ዛሬም በከረረ መልኩ እየተደገመ ነው፤ መሬትን መቆፈር፣ መጠፍጠፍ፣ መዳመጥ ቀላል ነው፤ በመሬት ላይ ለውጥ ለማምጣት ቀላል ነው፤ ነገር ግን ይህንን ቀላል ለውጥ ከማምጣት በፊት ሁለት ቀላል ጥያቄዎችን ማንሣት ያቅተናል፤ አንድ፣ በመሬቱ ላይ የሚደረገው ለውጥ (እርሻም ሆነ ግንባታ) ማንን ይጠቅማል? ማንንስ ይጎዳል? ቁጥራቸውስ ምን ያህል ነው? ሁለት፣ የለውጡ ኃይል ማን ነው? አዲሱ ለውጥ የአካባቢውን ነዋሪ፣ ባለቤቱን ያለማዋል? ወይስ ያሻግተዋል? ነዋሪዎቹ፣ ባለቤቶቹ ለውጡ የሚጠቅማቸውና የሚያለማቸው ከሆነ ፈቃዳቸውን ማግኘት ለምን ያቅታል?በአዲስ አበባና በአካባቢዋ የሚፈጸሙ ነገሮች ሁሉ ከዚያ አልፈው ወደገጠር አካባቢ ሲደርሱ ሁኔታዎች ኮረኮንች ይሆናሉ፤ የአዲስ አበባ ሕዝብ ውጥንቅጥ ነው፤ ብቻውን አዝኖ ብቻውን ይችለዋል፤ በገጠር የሕዝቡ ኑሮ በብዙ መንገድ የተሳሰረ ነው፤ አዲስ አበባ የቻለውን ለውጥ ሁሉ በሌላም ቦታ ለማድረግ መሞከሩ አደጋ አለበት።የለውጡ ዓላማ ምንድን ነው? ለውጡ ሰዎችን ይጨምራል ወይ? ሰዎችም እንደመሬት ተለዋጭ ናቸው? ወይስ ለዋጭም ናቸው?

Advertisements
This entry was posted in አዲስ ጽሑፎች. Bookmark the permalink.