ሕዝብና የፖለቲካ ፓርቲዎች

ፍትሕ ጋዜጣ

ግንቦት  17 2004

የፖሊቲካ ፓርቲ ሦስት የአካል ክፍሎች አሉት ለማለት የሚቻል ይመስለኛል፤ አብዛኛውን ጊዜ ፓርቲ የሚባለው ድርጅቱ ነው፤ ይህም አንጎሉ ነው ለማለት ይቻል ይሆናል፤ ጡንቻውና ጉልበቱ ሕዝብ ይመስለኛል፤ አንደበቱ ነፃና ያልተለጎመ የዜና ማሰራጫ ነው፤ እንዲህ ያለው የፖለቲካ ፓርቲ በተንኮልና በሸር እሾህና ጋሬጣ መንገድ ላይ እያርከፈከፈ የሚያደናቅፈው የምርጫ አስፈፃሚ ድርጅት የሌለበት፣ እንዲያውም ጎዳናውን ሁሉ እየጠረገ የሚያለሰልስ የፓርቲው አንጎል በሙሉ በኃይሉ በሰላም እንዲያስብ፣ አንደበቱ በሙሉ ነፃነት ሀሳቦችን መግለጽ እንዲችል፣ የፓርቲዎቹ ጡንቻና ጉልበት በሕጋዊ ሥርዓትና በሰላም እንዲፈረጥም የሚያደርግ ድርጅት መሆን አለበት።

በኢትዮጵያ የሚታየው ሁኔታ ሁላችንም እንደምናውቀው፣ ዓለም በሙሉ እንደሚያውቀው በስልጣኑ መንበር ላይ ያለው ፓርቲ በአለፈው ምርጫ ዘጠና ዘጠኝ ነጥብ ሰባት የሕዝብ ድምጽ አገኘ ተብሎ ተቀናቃኝ ቡድኖችን ድባቅ መትቶ ያሸነፈ ጉልበተኛ ፓርቲ ነው፤ ጉልበተኛ ያደረገው ምንድን ነው? አንጎሉን ዘልዬ ወደጉልበቱ የሄድሁት ወድጄ አይደለም፤ አንጎሉ አይታይም፤ ጎልቶ የሚታየው ጉልበቱ ነው፤ አንጎሉ በጉልበቱ ተሸፍኖአል፤ ለምሳሌ ምርጫውን ያሸነፈው በስድሳ ከመቶ ቢሆን አንጎል ይታይ ነበር፤ በዘጠና ዘጠኝ ከመቶ ሲያሸንፍ ግን አንጎሉ በጉልበቱ ተደፍጥጦአል፤ ጉልበት ሕዝብ ነው ብለናልና ጉልበት ሆኖ አንጎሉን የደፈጠጠው ሕዝብ ሊሆን ነው።

ገዢው ቡድን የመንግስት ስልጣን የሚባለውን ሁሉ በሁለት እጆቹ ጨብጦ ይዞአል፤ የጦር ኃይሉና የፖሊስ ኃይሉ፣ ዓቃቤ ሕጉና የዳኝነት ወንበሩ፣ የሕዝብ የዜና ማሰራጫዎች በሙሉ ረጅሙን ምላስ ሲከነዱለት እየዋሉ ያድራሉ፤ ባለብረት ቁልፍ የቃሊቲ የቆርቆሮ በቆርቆሮ ማጎሪያዎች አሉ፤ በዚያ ላይ የገንዘብ ጉዳይ ሲነሳ ሁሉ በጁ ሁሉ በደጁ፣ የማመላለሻ ጉዳይ ቢነሳም ሁሉ በጁ ሁሉ በደጁ ነው፤ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በሽበሽ ነው፤ በምንስ ቢሆን ምን ይጎድለዋል!

ወደተቀናቃኝ ቡድኖች ሰፈር ስንመጣ ስለአንጎሉ ባለፈው ሳምንት ተነጋግረናል፤ አንደበቱ የተለጎመ ነውና ምንም ማለት አይቻልም፤ እንዲሁ ከአንገት በላይ ዜሮ ብለን እንለፈው፤ የገዢውን ፓርቲ አንጎል የደፈጠጠው ሕዝብ የተቀናቃኝ ቡድኖቹን አንጎል አጫጭቶታል።
የተቀናቃኝ ቡድኖችን ሕዝብ አልተጠጋቸውም፤ ወዶ ይሁን ተገዶ ገና ብዙ ምርምርን የሚጠይቅ ነው፤ ተቀናቃኞቹ ሕዝቡን እንዳይጠሩ አንደበት የላቸውም፤ ሕዝቡን የሚሰበስብበት አዳራሽ የላቸውም፤ ሀሳባቸውንና እምነታቸውን የሚያሰራጩበት ሬዲዮና ቴሌቪዥን የላቸውም፤ ስለዚህ ሕዝቡ ተቀናቃኝ ቡድኑን አልተጠጋውም፤ አሁን አዙሪት አስተሳሰብ ውስጥ ገባን፤ ተቀናቃኝ ቡድኖች ሕዝብ ስላልተጠጋቸው ጉልበት አላገኙም ብለን ነበር፤ አሁን ደግሞ ተቀናቃኝ ቡድኖቹ ደካሞች ስለሆኑ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ መሰብሰቢያ አዳራሽ… ወዘተ ስለሌላቸው ደካሞች ናቸውና ሕዝቡ አልተጠጋቸውም፤ ስለዚህም ጉልበት የላቸውም፤ ስለዚህም ተቀናቃኝ ቡድኖች ገዢውን ፓርቲ ሊጋፈጡት አይችሉም፤ ከአዙሪቱ ለመውጣት ወይ ሕዝቡ ደካማ በመሆኑ ተቀናቃኝ ፓርቲዎችን ከ1997 ወዲህ እንኳን ማቀፍ አላስጠጋም፤ ወይ ተቀናቃኝ ቡድኖች ሕዝቡን አላገኙትም።
ሕዝቡ ከሀብታሙና ከሚያስፈራው ገዢው ፓርቲ ጋር ነው፤ የፓርቲ ጡንቻውና ጉልበቱ ሕዝብ ነው ብለናል፤ የጫጨ አንጎል ይዞ፣ በገዢው ፓርቲ ተጠርንፎና ታፍኖ ጡንቻ ከየት ይመጣል? የፓርቲ ጉልበት ሕዝብ ነው ስንል ምን ማለታችን ነው? ዴሞክራሲያዊና ሕጋዊ ስርዓት ባለበት የገዢውም ሆነ የተቀናቃኝ ፓርቲዎች ዓላማ ሕዝቡ ነው፤ ዓላማው የሕዝቡ ጥቅም ነው፤ የሕዝቡ ጥቅም ማለት የአገር ጥቅም ነው፤ የአገር ጥቅም ማለት የመንግስት ጥቅም ነው፤ የመንግስት ሌቦች የተሰገሰጉበት ከሆነ የሕዝብ፣ የአገርና የመንግስት ጥቅም አንድ ሊሆን አይችልም፤ የመንግስት ሌቦች የሕዝብንና የአገርን፣ የመንግስትንም ጥቅም የሚሰርቁ ናቸው፤ እንግዲህ ፓርቲዎች ለምርጫ የሚወዳደሩበት ጉዳይ የመንግስት ሌቦችን ለመቀነስና የሕዝብን፣ የአገርንና የመንግስትን ጥቅም ለማዳበር በሚያመለክቱት ዘዴና በሚሰጡት አስተማማኝ ቃል ኪዳን ነው፤ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ዓላማቸው ሕዝብ ነው፤ መሳሪያቸውና ጉልበታቸው ሕዝብ ነው፤ ዳኛቸውና ገላጋያቸው ሕዝብ ነው፤ የመንግስት ሌቦች ሰይፋቸውን መዝዘው ሕዝቡን እያደኸዩና እያደከሙ በሚገዙበት ሁኔታ ህዝብ አደግድጎ ፍርፋሪ ጠባቂ ነው፤ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ሕዝብ ዓላማ ነው የምንለውም ሕዝብን ካለበት ክፉ ሁኔታ ለማውጣትና ወደ ከፍተኛ የነጻነት፣ የክብርና የብልጽግና ደረጃ ለማድረስ ነው፤ ይህንን ሊያደርግለት የሚችለው የትኛው ፓርቲ እንደሆነ ህዝብ በቁርጥ አልወሰነም፤ ይህንን ለመወሰን እንኳን አልነቃም።

በፓርቲዎች መሀከል የሚደረገው ፉክክር የመንግስት ሌቦችን አስወግዶ የሕዝብን፣ የአገርንና የመንግስትን ብልጽግና የሚያረጋግጥ ስርዓት የሚዘረጋውን ለመምረጥ ነው፤ የጠገቡትን የመንግስት ሌቦች አስወጥቶ አዲስና ያልጠገቡ ሌቦችን ለማስገባት አይደለም፤ ሕዝብ ይህንን በደንብ ተገንዝቦታል፤ ስለዚህም ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጡ፣ በማለት በፍርፋሪ ሕይወቱን ጠግኖ ጉልበት እስቲያገኝ እያሾፈ ለጉልበተኛ ያደገድጋል፤ ቂል አይደለም፤ ፈረንጆች እንደሚሉት ዳቦው በየት በኩል ቅቤ እንደተቀባ ያውቃል፤ የጠገበው ይተርፈዋል፤ ገና ያልጠገበው ምንም አይወድቀው፤ በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ሕዝብ ለተቀናቃኝ ቡድኖች የሚሰጠው ምን ጉልበት አለው? ራሱ እየደማ፣ እየደኸየና እየተዳከመ የሚሄድ ሕዝብ ጉልበት ከየት ያመጣል? ጉልበት የሌለው ሕዝብ እውነተኛ እምነቱንና ፍላጐቱን ደብቆ ለእንጀራው ሲል ተረግጦ መጠምዘዙን እያወቀ የተመቸው ሁኔታ እስቲፈጠር ድረስ ነፍሱ እንደገፋው ጎምበስ ይላል፤ ማጎንበሱ ከትውልድ ወደትውልድ እየባሰ ሲሄድ ማጎንበስ መሆኑ ቀርቶ መደፋት ይሆናል።

ወደጀመርንበት ስንመለስ የተደፋ ሕዝብ ራሱን ቀጥ አድርጎ ማቆም የተሳነው ነው ማለት ነው፤ ራሱን ቀጥ አድርጎ ማቆም ያልቻለ ሕዝብ፣ ጆሮውን የተነሳ ሕዝብ፤ አንደበቱን የተነሳ ሕዝብ፣ በልቶ ያልጠገበ ሕዝብ ለመሆኑ ተቀናቃኝ ቡድኖችን ያውቃቸዋል?

ይህንን ሁኔታ ማን ፈጠረው? የሕዝብ ደካማነት? የተቀናቃኝ ቡድኖች ደካማነት? የገዢው ፓርቲ ጨቋኝነት?

ሕዝብ ቀና ብሎ ማየት ሲጀምርና ሲቆርጥ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲውን ራሱ ይፈጥረዋል፤ ሕዝቡ የሚፈጥረውና የሚገነባው የፖለቲካ ፓርቲ ሀሳቡ የጠራ፣ አንደበቱ የተፈታ፣ እርምጃው የማይገታ ጉልበት ይሆናል።

ባጭሩ ለጊዜው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕዝቡን ለማንቃት አልቻሉም፤ በጊዜው ሕዝቡም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለመደገፍ አልቻለም።

Advertisements
This entry was posted in አዲስ ጽሑፎች. Bookmark the permalink.