የእውነት ዋጋ

የእውነት ዋጋ 

ሰኔ 2004

ለአገርና ለወገን እቆረቆራለሁ፤ ለአገርና ለወገን እቆማለሁ፤ በቃልም ሆነ በተግባር ገለልተኛ ተመልካች አልሆንም ብሎ በቁርጥ የተነሣ ሰው ጨርቄን ማቄን፣ ስሜን አጠፋችሁብኝ፤ ክብሬን አጎደፋችሁብኝ ብሎ ሲበሳጭና ከዚያም አልፎ ወደፍርድ ቤት ሲሄድ ያሳዝናል፤ ዱሮውኑ በአገርና ሕዝብ ጉዳይ ውስጥ ሲገባ ዘጠና ሚልዮን ሕዝብ ተሰብስቦ ያጨበጭብልኛል ብሎ ከሆነ ቂል ነው፤ ጥሩ ኑሮ በጥሩ ደመወዝ እየኖረ ደመወዙን ከሚከፍለው ሕዝብ መሀከል በእሱ ሥራ የማይደሰት ሊኖር እንደሚችልና ወቀሳም ሆነ ነቀፌታ ሊሰነዘርበት እንደሚችል ያልተገነዘበ ሰው በንግድ ቢሰማራ ይሻለዋል፤ (እዚያም ቢሆን በሱ ዋጋ ካልገዛችሁኝ ብሎ ሱቁን ዘግቶ ቢቀመጥ ትርፉ ችጋር ነው፤) ወፍራም እንጀራ ብቻ አይቶ በሕዝብ ጉዳይ ውስጥ በመንግሥት ሠራተኛነትም ሆኖ በፖለቲካ ጥልቅ ብሎ ገብቶ አትንኩኝ አርፌ ልብላ የሚል ጮሌ ወይም ጮሌ-መሳይ ቂል እዬዬ ቢል ሰሚ ሊያገኝ አይገባም፤ የአገርና የሕዝብ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሰው ለቤተዘመዶቹ፣ ለቤተሰቡና ለልጆቹ ማሰብ ያለበት ገና ሳይነከርበት ነው፤ ሊያስመሰግናቸውና ሊያስከብራቸው የተሰማራ መሆን እንዳለበት የሚወስነው እሱ ራሱ ብቻ ነው፤ ሥራዬን በአደባባይ አትናገሩብኝ ሚስቴንና ልጆቼን ታስቀይሙብኛላችሁ ማለት ሞኝነት ነው።

የመንግሥት ጉልበተኛም ሆነ ተስፈኛ ጉልበተኛ ሥልጣኑን ዱላ አድርጎ ሲጠቀምበት ከኖረ በኋላ ሥልጣን የሕዝብ አደራ እንጂ ዱላ አይደለም ሲሉት ረስቶት ወደቆየው ሕግ ልሸጎጥና የሙጢኝ ልበል ቢል ሕጉም ሊጠየፈው ይገባል፤ የሰዎች መብቶች ሲረገጡ ሳይሰቀጥጠው የኖረ ሰው ወቀሳንና ነቀፌታን መቀበል ተስኖት ስሜን አጎደፋችሁት ቢል አንዱን የመብት ጎን አላየውም፤ መብት በግልባጩ ግዴታ ወይም ኃላፊነት አለው፤ በአገርና በሕዝብ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሁሉ መብት አለው፤ ነገር ግን ከዚህ መብት ኃላፊነት የሚመነጭ መሆኑንም መረዳት ያሻል፤ ሕግ ንጽሕናን እንጂ ጉድፍን ጠባቂ ሊሆን አይችልም፤ ሊሆንም አይገባም።

አገሩና ወገኑ በትክክለኛ መንገድ እንዲጓዙለት፣ እንዲለሙና እንዲበለፅጉለት፣ እንዲበረቱና እንዲጠነክሩለት የሚጥር እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ነው፤ የሚያውቀውን ለማሳወቅና እስከዛሬ ለአገሩና ለወገኑ የታገለበትን ትክክለኛ ዓላማ ለማስረዳት እየጣረ ነው፤ ይህንን በሚያደርግበት ጊዜ ስሞችን ይጠራል፤ የሚወደሰውን ያወድሳል፤ የሚነቀፉትንም ይነቅፋል፤ በአንድ ወቅት የሚመሰገኑትም ሆኑ የሚወቀሱት በአንድ ላይ ለአገራቸውና ለወገናቸው የተሰለፉ ነበሩ፤ ዛሬ የተለያየ አስተሳሰብና የተለያየ እምነት ቢኖራቸውም ያንን አንድ አድርጎ የጠመዳቸውን ዓላማና በኋላ የተለያዩበትን ምክንያት ዘርዝሮ ለሚቀጥለው ትውልድ ማስቀረት ትልቅ ኃላፊነትን መሸከም ነው፤ አቶ አስገደ ይህንን ኃላፊነት በፈቃደኛነት ወስዶአል፤ በሀሳብ የሚለዩትም ሆኑ የሚስማሙት ሊረዱት ይገባቸዋል፤ በሀሳብ የሚስማሙት መረጃና ማስረጃ በማሰባሰብ ሊረዱትና ሥራውን በጣም ፍሬያማ ሊያደርጉት ይገባል፤ በሀሳብ የማይስማሙት ደግሞ የራሳቸውን እይታና አመለካከት ከማስረጃ ጋር የያዘ ጽሑፍ ቢያቀርቡ እውነቱን ይክቡት ነበር፤ አንድ ሰው ብቻውን ቤት ዘግቶ ከመላእክት ጋር እየተነጋገረ ዜና መዋዕል የሚጽፍበት ዘመን አለፈ፤ አይመለስም።

አቶ አስገደ የሚጽፈው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ለትግል ስለመሰለፋቸው፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የመጨረሻውን መስዋእት ከፍለው በዱር በገደሉ የቀሩ ስለመኖራቸው፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አንድ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆን የአካል ክፍላቸውን ገብረው በችግር የሚኖሩ ስለመሆናቸው፣ እነዚህ ሁሉ ያሳለፉትን የትግል ታሪክ ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍ ነው፤ ከዚህ የበለጠ ክቡር ሥራ ምን አለ? የሞቱትን በክብር ለማስታወስ፣ የተጎዱትን ለማመስገን፣ ያጠፉትን ለመውቀስና ለማስተካከል ሲሆን፣ የአሁኑና የወደፊቱ ትውልድ ሰዎች የተሰዉበት ዓላማ ጠርቶ እንዲታየው ለማድረግ ነው፤ ይህንን አንድ ሰው በራሱ ላይ የጫነውን ማኅበራዊ ግዴታ እንዳይወጣው እንቅፋት መሆን አገርንና ወገንን መበደል ይሆናል።

በእኔ አስተሳሰብ አቶ አስገደ የሁላችንም ድጋፍ ሊኖረው ይገባል፤ ምስክሮችን ከያሉበት ለማቅረብ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ተረዳድተን ብንከፍልለት የኃላፊነታችንን ድርሻ የምንወጣ ይመስለኛል፤ የምሰብከው በተግባር የፈጸምሁትን ነው፤ ለእውነት መቆማችንን ለማስመከር ዋጋ መክፈል ከአለብን ወደኋላ ልንል አንችልም፤ አቶ አስገደ በትግራይ የተካሄደውን ትግል የኢትዮጵያዊነት መሠረትና መልክ የኢትዮጵያ ሕዝብ በትክክል እንዲገነዘበው ይጥራል፤ ማን ይናገር የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ፤ በትግራይ የተጀመረውን የትግል ዓላማ በትክክል ስለሚያውቀው እንዴት እንደተለወጠና አጓጉል እየሆነ እንደሄደ ሲናገር የማይወዱለት አሉ፤ በበኩሌ የእነሱንም መብት አከብራለሁ፤ የእነሱ መብት የሚሆነው የራሳቸውን በኩል በሙሉ ነፃነት መናገር እንጂ አቶ አስገደን ማፈን ወይም ማሳፈን አይደለም።

በእኔ አመለካከት በአለፉት ሃያ አንድ ዓመታት የወያኔ/ኢህአዴግ አገዛዝ ውስጥ አንዳንዴ ቢሰናከልም ትልቁና ዋናው ጥቅም የጽሕፈት እገዳው መነሣት ነው፤ ይህ ነፃነት ሲጠፋ ጥፋቱ ሁሉ ሙሉ ይሆናል።

Advertisements
This entry was posted in አዲስ ጽሑፎች. Bookmark the permalink.