እየመረረ፣ እያመረረ፣ እያስመረረ…

እየመረረ፣ እያመረረ፣ እያስመረረ…

ፍትሕ ጋዜጣ

ሰኔ 2004

ከኢትዮጵያ ሕዝብ ስንት በመቶው በራሱ ጉዳይ፣ በእህል በውሀው ጉዳይ ከማንሾካሾክ አልፎ አፍ አውጥቶ ይናገራል?፤ ለማንስ ይናገራል?፤ ማንስ ይሰማል?፤ በቴሌቪዥኑ፣ በራዲዮውኑ በጋዜጣዎች የሚነጋገረው በአጠቃላይ አምስት ሚልዮን ይሞላል? ሌላው ሰማንያ አምስቱ ሚልዮን ተመችቶት ነው? የዕለት እንጀራውን ማሳደድ ፋታ አልሰጥ ብሎት ነው? መነጋገሩን ንቆት ነው? ብሶቱን ለመናገር ዕድሉን ባለማግኘቱ ነው? ፈርቶ፣ ጎመን በጤና እያለ ነው? ሌላም ምክንያት ሳይኖር አይቀርም፤ ሁሉም ከተናገሩ ሆድ ባዶ ይቀራል! ሆድ ባዶ ከሚቀር ቁርጠት ይሻላል፤ ቆሽቱ ድብን ቢል ይሻላል፤ አንጀቱ እርር ቢል ይሻላል፤ እንደወጣ ከሚቀር! አዲስ ነገርም መጥቶአል፤ አንዳንድ ጓደኞቻችን ዓለምን ስተዋል፤ ምን ሲደረግ እንደነበረም ሆነ ምን እየተደረገ እንዳለ ምንም የሚያውቁት ነገር የለም፤ እነዚህ ሰዎች እንኳ ስለምግብ ሊያስቡና መብላትም እንዳለባቸው ረስተዋል፤ ስለዚህ ምንም ችግር የለባቸውም።
እንግዲህ አፍ አውጥቶ ራበኝ፤ ጠማኝ፤ በረደኝ፤ አመመኝ፤ ታፈንሁ፤ ተበደልሁ፤ ተጠቃሁ፤ የሚለው ከአምስት ሚልዮን ግምታችን ውስጥ አራት ሚልዮን ይሆናል? ይህ ወደ እውነቱ የሚጠጋ ከሆነ የተመቸው አንድ ሚልዮን ነው ማለት ነው፤ እንግዲህ ንግግሩ ሁሉ በጠገቡና በተመቻቸው በአንድ ሚልዮንና በተጨቆኑትና በደሃዎቹ አራት ሚልዮን መሀከል ነው ማለት ነው፤ የቀረው ሰማንያ አምስት ሚልዮን የሚሆነው (ከሠላሳ በላይ የሚሆኑ ዩኒቨርስቲዎችንም ጨምሮ) በዝምታ ተውጦአል! (አንድ ሚልዮን፣ አራት ሚልዮንና ሰማንያ አምስት ሚልዮን ግምቶች እንጂ የተረጋገጡ ቁጥሮች አይደሉም፤ ካልተስማማችሁባቸው በራሳችሁ ግምት መለወጥ ትችላላችሁ)።
ደሀውና ጭቁኑ ዕለት በዕለት የብሶቱን ቁስል የሚጎረጉሩት ነገር ያያል፤ ይሰማል፤ የሚሰማው ነገር ሁሉ እውነት መሆኑ ወይም አለመሆኑ ለሱ ጉዳይ አይደለም፤ ለሱ ዋናው ነገር ያሳደረበት ስሜትና የሚፈጠርበት ጥላቻ ነው፣ የምሬቱ ሕመም መባባስ ነው፤ እውነቱን ለማጣራት ጊዜ የለውም፤ በዜና ማሰራጫዎቹ የሚሰማቸውና የሚያያቸው ሁሉ የተቀነባበሩና የተዋቡ ሐሰቶች መሆናቸው ከገባው ቆይቶአል፤
ሕመሙ ሲያምመው፣ ሲመርረው፣
ረሀቡ ሲያመው፣ ሲመርረው፣
ብርዱ ሲያመው፣ ሲመርረው፣
ጭቆናው ሲያምመው፣ ሲመርረው፣
ውርደቱ ሲያምመው፣ ሲመርረው፣
ሲመርረው፣ ሲያስመርረው
መኖር ሲያስጠላው
ሞትን ሲያስመኘው፤
በገዛ እጁ ተቃጥሎ ሲሞት፣ ተሰቅሎ ሲሞት፣ ተኝቶ ሲሞት፣ አንድ በአንድ እያለ አራት ሚልዮኑ ቢያልቅ፣ የደላው አንድ ሚልዮኑ ከዝምተኛው ሰማንያ አምስት ሚልዮን ጋር ቢቀር ምን ዓይነት ማኅበረሰብ ይፈጠራል? እንዲያውስ ማኅበረሰብ የሚባል ነገር ይኖራል?
አረቦቹም እንደኛ መረራቸው፤ አመረሩ፤ አስመረሩ፣ ለየላቸው፤ እነሱ ከአደረጉት ለእኛ ምን አስተማሩ? ለአንድ ሚልዮኑ? ለአራት ሚልዮን አረቦቹ የሄዱበትን መንገድ ጭራሽ አይመኘውም፤ አራት ሚልዮኑ ሁሌም ግራ የገባው በመሆኑ ከትግሉ ሜዳ ካልወጣ አይፎክርም፤ ከትግሉ ሜዳ የወጣ ፉከራ ደግሞ ከቲያትር ቤት ጨዋታ አያልፍም፤ ሰማንያ አምስት ሚልዮኑ የዕለት እንጀራውን ለራሱና ለቤተሰቡ ሲያስብ አምስት ሚልዮኑ ለሚሠሩት ቲያትር ለተመልካችነትም ጊዜ ያለው አይመስልም።
ሊብያውያን የጋዳፊን ጭቆና አስወግደው አሁን እየተደባደቡ ነው፤ ግብጻውያንም ለድብድብ እየተዘጋጁ ይመስላል፤ የመናውያን ደንበኛ ጦርነት ላይ ናቸው፤ በቅርቡ የየመኑ ጄኔራል ተገደለ፤… ሶርያውያን ምናልባት ማንም የማያሸንፍበት በጣም ከባድ የሆነ የጦርነት ሁኔታ ውስጥ ናቸው፤ በእነዚህ የአረብ አገሮች የተፈለገው ምን ነበረ? ምን ተገኘ? ለብዙኃኑ ሕዝብ ሥልጣንን የሚያስረክብ ሁኔታ በአንዱም አገር አልተፈጠረም፤ የዓለም ልዕለ-ኃያላኑም የብዙኃኑን ሥልጣን መረከብ አይፈልጉም፤ ወይም አንዱ ቢፈልግ ሌላው አይፈልግም፤ በሥልጣን ወንበር ላይ ለብዙ ዓመታት ተጣብቀው የነበሩት በግድ ወረዱ፤ ተደራጅተው ለሥልጣን አሰፈስፈው ሲጠብቁ የነበሩት ደግሞ አንዱን ዓይነት ጭቆና በሌላ ዓይነት ጭቆና ለመተካት ተጣደፉ፤ በ1966/67 እድሜያቸው ሃያ ዓመት ግድም የደረሰ በዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ የሆነውን ያስተዋሉና የሚያስታውሱ ሁሉ የዚያን ጊዜ ተዋናዮች እነማን ነበሩ? አሰላለፋቸውና ትግላቸው እንዴት ነበረ? ውጤታቸውስ ምን ሆነ? ዛሬ በግብጽ ያለውን ሁኔታ ልብ ላለ፣ ልዩነቱ የኢትዮጵያ ጄኔራሎች ፈቃዱም ወኔውም ስላልነበራቸው የጦር ኃይሉ በሻለቆችና በበታች ሹማምንት መመራቱ ብቻ ይመስለኛል፤ ወይም ከላይ በአቀረብሁት ምሳሌ ለመቀጠል የ1966/67 የኢትዮጵያ የጦር ኃይል በጠቅላላ ከተመቸው አንድ ሚልዮን ጋር ሳይሆን ከአራት ሚልዮኑ ጋር ሲቆም ጄኔራሎቹ ከአንዱ ሚልዮን ጋር ቀሩ።
ስለዚህ በራሳችን ታሪክ በተከታታይ ሀሳብ በጥይት እየተጨናገፈ፣ ሰላም በጉልበት እየታመሰ፣ እውነተኛ እድገት በማታለል እየጫጨ፣ ስምምነትና ትብብር በግል ምኞትና በፍቅረ ንዋይ እየመነመነ፣ አፈና ጥላቻን እየወለደ፣ ጥላቻም አፈናን እየወለደ፣ አንዱ ሌላውን እያስመረረው፣ የመረረው እያመረረ ሠላሳ ስምንት ዓመቶች ቆጥረናል፤ ከዛሬዎቹ አንድ ሚልዮን ጋርም ሃያ አንድ ዓመቶችን ቆጥረናል፤ እየመረረንም፣ እያስመረረንም ምንም አልተማርንም? አናሳዝንም?

Advertisements
Aside | This entry was posted in አዲስ ጽሑፎች. Bookmark the permalink.