ዳገት ላይ ሰው ጠፋ

ዳገትላይሰውጠፋ

ኅዳር 2004

ፍትሕ ጋዜጣ

የአሜሪካ ብሔራዊ መዝሙር ውስጥ “ነፃ ሰዎች ምድር፣ የጀግኖች አገር” የሚል አለበት፤ በሰማሁት ወይም ባነበብሁት ቁጥር ልቤ ያብጣል፤ በአገሬ መኩራት ናፍቆኝ ነው እንጂ አሜሪካዊ የመሆን ምኞት አድሮብኝ አይደለም፤ ነገር ግን በአሜሪካኖች እቀናለሁ፤ በሰማይ ላይ በሚበሩ ወፎችም እቀናለሁ፤ ሁለቱንም ልሆን አልችልም፤ ግራ ገባኝ የሚለውን ግጣሜን የደመደምሁት በሚቀጥሉት መስመሮች ነበር፤

ዓላማው ጠፋብኝ፤ፍጹም ግራገባኝ፤

መልአክነት ስሻ ሰው መሆን ከብዶብኝ..

እንኳን በኢትዮጵያዊነትና በሰውነትም ለመኩራት ከባድ እየሆነ ነው፤የቁልቁለት ኃይል የሚለውን ግጥሜን ደግሞ የዘጋሁት

በሚከተሉት መስመሮች ነው፡-

ዳገት ላይ ሰው ጠፋ፤ አቀበት ከበደ፤

ሁሉም በሸርተቴ ቁለቁለት ወረደ፤

ሰው ተዋረደ፤

ገንዘብ ተወደደ፤

በምነቱ፣በፍቅር፣ በክብሩነገደ፤

በቁልቁለት ኃይል እየተገደደ፡፡

አባቶቻችንና እናቶቻችን ክብራቸውን ከምንም ነገር በላይ አድርገው ይመለከቱት ነበር፤ ይህንንም ዓለም ሁሉ አውቆላቸው ክብርንና አድናቆትን አትርፎላቸዋል፤በአንዳድ አገሮች ለኢትዮጵያውያን ቪዛ አያስፈልጋቸውም ነበር፤ዛሬ ኢትዮጵያዊነት ረክሶ ኢትዮጵያውያን ለስደት ሲጓዙ ጀልባ እየተገለበጠ በባሕር ይሰምጣሉ፤ መኪና እየተገለበጠ ይሞታሉ፤ወደ አረብ አገር እየተጓዙ ፍዳቸውን የሚበሉትን በሺህ የሚቆጠሩ ሴቶችን ሳናነሣ፤ በዚህ ሁሉ የኢትዮጵያውያን አበሳ የሚነግዱና የሚጠቀሙ ወገኖች አሉ፡፡

ደሀነት እየቆጠቆጣቸው፣ ወይም የልጆቻቸውና የወላጆቻቸው ረሃብና ሰቀቀን እየበላቸው የሚሰደዱ ሴቶች አሉ፤ ጉልበታቸውን፣ አእምሮአቸውን፣ የፈጠራ ችሎታቸውን በሙሉ ኃይላቸው ሊጠቀሙበት ባለመቻላቸው እድላቸውን ለማቃናት ወይም የውስጣቸውን ጩኸት ለማስተጋባት የሚሰደዱ አሉ፤ በጣም የተማሩና የተራቀቁ ሰዎች በነፃነት ለመተንፈስ የማያስችለውን ዓየር የሚሰደዱ አሉ፤ ነጋ ጠባ የአገዛዙ ሰላይ ሎሌዎች እየተከታተሉ መውጫ መግቢያ እያሳጡዋቸውና እያስፈራርዋቸው ተደናብረው የሚሰደዱ አሉ፤ ብዙ የመሰደጃ ምክንያቶች ይኖራሉ፤ ነገር ግን ደስታን በአገሩ ባያገኝም ደስታን በስደት ለማግኘት የሚሰደድ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም፡፡ ገና ወያኔ አዲስ አበባ እንደገባ በአገዛዙ ትእዛዝ አርባ ያህል የኃይለ ስላሴ ዩኒቨርስቲ መምህራን ችሎታ የላቸውም ተብለው ተባርረው ነበር፤ እንዴት ያሉ ሰዎች እንደተኳቸው ተማሪዎቹ ይናገሩ፤ ላነሳው የፈለግሁት ነጥብ ግን ከነዚያ አርባ መምህራን ውስጥ ብዙዎቹ በህይወት አሉ፤ ከቀሩት ውስጥ ከአንድ ሰው በቀር ሁሉም በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ከዱሮው በበለጠ ሁኔታ በተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ናቸው፤ ችሎታቸውን የሚያውቅላቸው እያገኙ ተጠቅመው ይጠቅማሉ፤ እኔን በጣም የሚደንቀኝ ሌላ እውነት አለ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ቢጨምቋቸው ምንም የማይወጣቸው የሚመስሉ ሰዎች አሜሪካ ገብተው በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚያበረክቱት ጽሑፍ አንቱ የሚያሰኛቸው ነው፤ የአፈና አየር ስንቱን አደንዝዞታል.. ዱሮ፣ ዱሮ በምን ላይ እንዳነበብሁት ትዝ የማይለኝ የፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ግጥም በከፊል ትዝ ይለኛል፤

አንድ ነገር ሲያምር ያየሁት እንደሆን፣

ያንን ካላጠፋሁ ከቶ ምንም ቢሆን፣

እንቅልፍ አይወስደኝም

እያለ የሚቀጥል ነበር፤ ይህ ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት በዘመናቸው ያስተዋሉት አጉል ጠባይ እያቆጠቆጠ ኖሮ እየተኮተኮተ አድጎ ኢትዮጵያውያንን እያቆረቆዘ ለምልሞአል፤

ህዳር 2/2004 አቤ ቶኪቻው አገር ጥሎ ሄደ የሚል ወሬ ሰማሁ፤ “አንድ ነገር ሲያምር ያየሁት እንደሆን”፤ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ጉዞ ወይ ወደማዕከላዊ እስር ቤት ወይ ወደ ስደት እየሆነ ነው፤ ሰው እንዳይበቅልባት የተረገመች ሀገር ይመስል አንድ ባለሙያ ሲያቆጠቁጥ ማየት ዓይናቸውን የሚፈጀው ሰዎች ያሉ ይመስላል፤ “አንድ ነገር ሲያምር ያየሁት እንደሆን”፤ ቀደም ሲል በማቆጥቆጥ ላይ የነበረችው ጎበዝ ፀሐፊ ርዕዮት ዓለሙም ቃሊቲ ከገባች ቆየች፤ አንድ ነገር ሲያምር ያየሁት እንደሆን..__ ህዳር 12 ደግሞ የአውራምባ ጋዜጣ ባለቤት፣ በቅርቡ በዓለም ጋዜጠኞች ማህበር ሽልማት የተሰጠውና በ1998 ታስሮ ሁለት ያህል በእስር ቃሊቲ ቆይቶ በምህረት የተለቀቀው ዳዊት ከበደም የጥቃቱ እሳት ለበለበውና በቃኝ ብሎ ሄደ፤ “አንድ ነገር ሲያምር ያየሁት እንደሆን”፣ እነዚህ ጋዜጠኞች የአገሪቱን ስም ሊያስጠሩ የሚችሉ በኢትዮጵያ ውስጥ የአእምሮም የመንፈስም ችሎታ መኖሩን ሊያስመሰክሩ የሚችሉ ነበሩ፤ በቃሊቲ የተዘጋባት ርዕዮት ዓለሙም ስምዋ የሚጠራ ፀሐፊ ለመሆን እያቆጠቆጠች ነበር፤ “አንድ ነገር ሲያምር ያየሁት እንደሆን” ሆነና ቃሊቲ ተዘጋባት፤ እግዚአብሔር አእምሮዋን እንደከፈተው ያቆይላት እንጂ ችሎታዋ የሚታይበት ጊዜ ይመጣ ይሆናል፡፡

በማናቸውም የእውቀትና የሙያ መስክ አእምሮአቸውና ህሊናቸው የተሳለ ሰዎች ለሎሌነት አይመቹም፤ እነሱም ሎሌነት አይመቻቸውም፤ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ በአንድ በኩል የሰው ደሀ እየሆነች ልጆችዋ የዓለምን አገሮች በር እያንኳኩ ስደተኞች ሆነው ደሀነትንና ስደትን የሚያጋቡ ይመስል ሁሉም ይጠላቸው ጀምሯል፡፡

አንድ አገር ዜጎቹ በደሀነትና በለማኝነት በችጋርና በስደት ሲታወቅ በነእዚህ ከችጋር በተረፉ ለማኞችና ስደተኞች ላይ የበላይነት እየተሰማው የሚኮራና አገሩን የሚያኮራ ሰው አለ? የአገር ውርደት ለማን የኩራት ምንጭ ይሆናል? የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደአሜሪካ ወይም ወደአውሮፓ (የተሙዋላ ነፃነት ባሉባቸው አገሮች) ሲሄድ የሚያጋጥመው ዜጎች ተሰብስበው እንኳን ደህና መጣህ የኛ መሪ የሚል ጭብጨባ አይደለም፤ ይህ አያሳፍርም? አያስቀናም? ሰዎችን አዋርዶ መከበር አይገኝም፤ ጠመንጃና ጉልበት የውስጡ እውነት እንዳይወጣ ያፍናል እንጂ እውነቱን አያጠፋውም፤ ዞሮ ዞሮ ሰዎችን ማዋረድ ራስን ማዋረድ ነው፤ የተዋረዱ ሰዎች በውስጣቸው የሌለውን ክብር ለሌላ ሊሰጡ አይችሉም፤ የተዋረደ ሰውስ አከበረ ወይ አላከበረ ምን ፋይዳ አለው? ፋይዳ ያለው የሚያከብሩት ሰው ሲያከብር ነው፡፡

የአገር ደህንነት ማለት ትርጉሙ ግራ እያጋባ ነው፤ እንደሚገባኝ የአገር ደህንነት ሁላችንንም የሚነካ በመሆኑ ፊታችንን የምናዞርበት ተግባር አይደለም፤ ለግዮን ሆቴል የቆየሁ ደንበኛ ነበርሁ፤ ቦምብ እስከፈነዳበት ድረስ፤ በዚያ ቦምብ ፍንዳታም ህይወታቸውን ያጡትን አውቃቸዋለሁ፤ የምንቀላለድ ነበርን፤ ዛሬም ግዮን ሆቴል ስሄድ የእነዚህ ሰዎች ፊት ይታየኛል፤ እንባዬ ይመጣብኛል፤ ቦምቡን አስቀምጦ የሄደውን ሰው ባወቀው ምን የማላደርገው አለ? ከግዮን ያስቀረኝ ኪሴ ብቻ ሳይሆን የአነዚያን ወዳጆች መልክ በሐዘን በማስታወስ ነው፤ በየሰው ቤትና በየቢሮ እየሄዱ ሰላማዊ ሰዎችን ማስፈራራት ሽብርተኛነት ነው ወይስ ደህንነት?

ከእንደዚህ ያለው በሆቴል ውስጥ ቦምብ የሚያፈነዳ አረመኔ ራሳችንን ለመጠበቅ በየሰው ቤት ወይም ቢሮ እየሄዱ ሰዎችን ማስፈራራት እንዴት ይበጃል? የሚያስፈራሩት ሰው ሽብርተኛ ከሆነ እንዳወቁበት መረጃ ሰጥተው ሊያስጠነቅቁት ነው? ካልሆነ በማስፈራራት ወደሽብርተኞች መንደር ሊገፋፉት ነው? በሃያ አንደኛው ምዕተ-ዓመት እነዚህ ሰዎችን እንዲህ የሚያደርጋቸው ሙስና ነው? አለማወቅ ነው? ግዴለሽነት ነው? መጽሐፍ ማንበብ ቢያቅታቸው ቪዲዮ እያዩ መማር ለምን ያቅታል? ያለማወቅ ምሽግ አንድ ብቻ ነው፤ አውቃለሁ እያሉ ባለማወቅ መታበይና ማበላሸት.. የአሜሪካ መንግስትና ኢትዮጵያ በሽብር ላይ ጦርነት አብረው የተሰለፉ ናቸው፤ ነገር ግን ስለሽብርተኛነት ያላቸው አመለካከት ግልጽ የሆነ ቅራኔ ውስጥ እየገባ ነው፤ ኢትዮጵያ ሽብርተኞች ከምትላቸው ውስጥ በአሜሪካ ተከብረውና ሙሉ ሰብዓዊ መብቶቻቸው ተጠብቀውላቸው የሚኖሩ ሰዎች አሉበት፡፡ የምዕራብ አውሮፓ መንግስታትም ቢሆኑ ኢትዮጵያ ሽብርተኞች የምትላቸውን ከእነ ሙሉ ሰብአዊ መብቶቻቸው ያኖሩአቸዋል፤ ይህ በአንድ በኩል ስናየው ነው፤ በሌላ በኩል ስናየው ደግሞ አሜሪካና አውሮፓ ሽብርተኞች የሚሉአቸው ሰዎች (የመብቱን ጉዳይ እንርሳውና) በኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ይችላሉ ወይ? ካልቻሉ ለምን? ኢትዮጵያስ ሽብርተኞችዋን ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ አስገደዳ የማታሰመጣበት ምክንያት ምንድን ነው? የኢትዮጵያ ሽብር ከዓለም- አቀፋዊው የሽብር ትርጉምና ከዓለም-አቀፋዊው የሽብር ሕግ የተለየ ነው ማለት ነው? ወይስ አሜሪካና አውሮፓ በአለም-አቀፋዊ የሽብር ህግ አይገዙም ማለት ነው? ወይስ ኢትዮጵያ በዓለም-አቀፋዊው ሕግ አትገዛም ማለት ነው? ስለሽብርተኛነት ዓለም-አቀፋዊ ሕግ የለም?

በአንድ የአውሮፓ መንግስት በሽብርተኛነት የተፈረጀ ሰው አሜሪካ ሄዶ የሙጢኝ አይልም፤ ታዲያ በኢትዮጵያ በሽብርተኛነት የተፈረጀ ሰው አሜሪካ ሄዶ የሙጢኝ ሲል በሁለቱ አገሮች መሀከል ያለው ቅራኔ የአስተሳሰብ ነው? ወይስ የተግባር? በአሜሪካ በሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ የጥናት ግብዣ በሄድሁ ጊዜ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሌላ ስራ ጠፍቶበት፣ የእኔን በዩኒቨርስቲው መጋበዝ ትልቅ የአገር ጉዳይ አድርጎ ለዩኒቨርስቲው የጻፈውን የተቃውሞ ደብዳቤ እየቀለዱበት አሳዩኝ፤ ምንም የኔ ጉዳይ ቢሆንም የአገሪቱ ባለስልጣኖች ሲሰደቡ ያሳፍረኛል፡፡

በስንት ነገር እየተዋረድን ገለባ እንሆናለን? በስንት ነገር እያፈርን አንገታችንን እንደፋለን? ፈርተን፣ አስፈራርተን፣ በወሬ እየተሸበርን ሽብርን እናስተምራለን? የአንዳንድ ባለስልጣኖች ንግግርም ሆነ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሽብርን የሚያስተምሩ ይመስለኛል፤ አስቡ፤ አንድ ኢትዮጵያዊ ራሱን በእሳት ሲያቃጥል ለመጀመሪያ ጊዜ ይመስለኛል፤ ባለስልጣኖችና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አስተማሪው ራሱን ማቃጠሉ የሽብር ጥንስስ ሊሆን እንደሚችል የተረዱት አይመስልም፤ እግዚአብሔር ልቡና ይስጣቸው!__

 

Advertisements
This entry was posted in ቀደም ሲል የወጡ ጽሑፎች and tagged . Bookmark the permalink.

One Response to ዳገት ላይ ሰው ጠፋ

  1. Pingback: ዳገት ላይ ሰው ጠፋ « yabedew / ያ – በደው

Comments are closed.