የሃይማኖት ነጻነትና መቻቻል

የሃይማኖት ነጻነትና መቻቻል

ሐምሌ 2004

የሃይማኖት ነጻነት በሕገ መንግሥቱ የተከበረ ነው፤ አንቀጽ 27/1

‹‹ማንኛውም ሰው የማሰብ፤ የሕሊናና የሃይማኖት ነጻነት አለው፤ ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል፣ ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ፣ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር፣ ወይም የመግለጽ መብትን ያካትታል፡፡››

 

ብዙ ሰዎች ይህ አንቀጽ አንደገባቸው አድርገው ይናገራሉ፤ አንቀጹ ከሃይማኖት ነጻነት በተጨማሪ ብዙ ሌሎች መብቶችንም የያዘ ነው፤ የሕሊና ነጻነትና የሃይማኖት ነጻነት አንድ አይደለም፤ የሃይማኖት ነጻነትና እምነት አንድ አይደለም፤ እነዚህ የተጠቀሱት ሀሳቦች አንድ እይደሉም ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ ይጋጫሉ ወይም ይቃረናሉ፤ ኅሊናና እምነት፣ ወይም ኅሊናና ሃይማኖት፣ ወይም እምነትና ሃይማኖት አንዳንድ ጊዜ አይስማሙም፡፡

እነዚህን በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተጠቀሱትን፤ ቃላት በትክክክል ከተረዳን ሕጋዊ ሥርዓት ባለበት ሁሉ ችግሮች አይኖሩም ወይም በጣም ይቀነሳሉ፤ ለምሳሌ ሴቶች በሃይማኖት የተደገፈ ጥቃት ወይም በደል ይደርስባቸዋል፤ በዚህ ምክንያት ኅሊና ከሃይማኖት ጋር ያቃረናል፤ ሃይማኖትም ኅሊናም ያለው ሰው ይጨነቃል፤ የሃይማኖትን ትእዛዝ ማክበር ወይም የኅሊናን ድምጽ መቀበል ለብዙ ሰዎች አስቸጋሪ ምርጫ ነው፤ በዚህ ላይ የማኅበረሰቡም ድምጽ አለ፤ መሠልጠን ማለት፣ መብሰል ማለት፣ ማደግ ማለት እነዚህን ውስጣዊና አፍአዊ ግጭቶች ከራስ ጋር ሳይጣሉ በሰላም ማስተናገድ ነው፤ አማራጩ ምንድን ነው? አማራጩ ልጅ ሆኖ መኖር ነው፤ አማራጩ የፈለጉት ካልሆነ ሲያለቅሱ መኖር ነው፤ አማራጩ የፈለጉት ካልሆነ እየተበሳጩና እየተጣሉ ሲደባደቡ መኖር ነው፡፡

ለብዙ ሰዎች መቻቻል ማለት አትንካኝ-አልነካህም ብቻ ይመስላቸዋል፤ አይደለም፤ ከአትንካኝ-አልነካህም በጣም ያልፋል፤ ለምሳሌ የሀሳብ ነጻነት ማለት የሚቃወሙትን እምነትም ሆነ ሃይማኖት፣ ሀሳብም ሆነ ድርጊት መተቸትና መንቀፍን ይጨምራል፤ በቅርቡ አንድ ቀደም ብሎ የተጻፈ መጽሐፍ አየሁ፤ ጥቂት ገጾች ካነበብሁ በኋላ በቃኝ፤አንድ ካቶሊክ ስለኦርቶዶክስ ሃይማኖት ጽፎ ኖሮአል፤ አንድ ኦርቶዶክስ ይህንን የካቶሊኩን ጽሑፍ አልወደደውም፤ አለመውደድ መብቱ ነው፤ ነገር ግን ኦርቶዶክሱ ሲመልስ አትኩሮቱ በፍሬ ነገሩ ላይ ሳይሆን በካቶሊኩ ሰውዬ ላይ ነው፤ ይህን ሲያደርግ መብቱን አለፈ፤ የሰው መብት ነካ፤ በአጭሩ ኦርቶዶክሱ ካቶሊኩ ሰውዬ ላይ ማትኮሩ ለእኔ ምንም ጥሩ ምክንያት አይታየኝም፡፡

አንድ ሰው ከፈለገ የሃይማኖቱን ተከታዮች ሳይነካ የትኛውንም ሃይማኖት ሊተችና ሊነቅፍ ይችላል፤ መብቱ ነው፤ የመቻቻል ሙሉ ትርጉሙ ካልገባቸው የተነቀፈው ሃይማኖት ተከታዮች ሊቀየሙ ወይም ሊከፉ ይችላሉ፤ ግን ሰውዬው የራሱን ሀሳብ ወይም እምነት በመግለጽ የማንንም መብት አልጣሰም፤ በሌላ አነጋገር መቻቻል መታፈንን አይጨምርም፤ ሀሳብን ወይም እምነትን የመግለጽ መብትም ጨዋነትን አይደመስስም፤ መቻቻል ማለት የአንድን ሰው የመናገር መብት መገደብ ማለት አይደለም፤ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 27/1 ደጋግሞ ማንበብ ያስፈልጋል፡፡

አንዳንድ ሃይማኖት-ነክ ነገሮች ማኅበረሰብ-ነክም ሊሆኑ ይችላሉ፤ ስለዚህም በሃይማኖትና በማኅበረሰቡ ድንበር ላይ የሚገኙትን ነገሮች ካልሆነ በቀር በእምነትም ሆነ በጣዕም ላይ ክርክር መክፈት የዋህነት ነው፤ ማንም ሊያሸንፍ የሚችልበት ሚዛን የለም፤ ለምሳሌ በመጀመሪያ የተጠቀሰው በሴቶች ላይ የሚፈጸም አድልዎ፣ ወይም በልጆች አስተዳደግ ላይ የሚታይ ጉድለት፣ ወይም ማኅበረሰቡን ለአደጋ የሚያጋልጥ ጉዳይ ሆኖ ሲታይ በሃይማኖት ወይም በእምነት ላይ ትችት ማቅረብ አስፈላጊ የሚመስልበት ጊዜ ይኖራል፤ ማኅበረሰቡ ከነሃይማኖቶቹና ከነእምነቶቹ የተሳሰረበት የመንፈሳዊና የሕግ ቃል ኪዳን ተጠብቆ እንዲቆይ የሚነቀፈውን ሁሉ እያወጣ ማበጠር ያስፈልገዋል፤ ማናቸውም የተሸፈነና የተሸሸገ ነገር ጊዜውን ጠብቆ ባሕርዩን ይለውጣል፤ በዚያን ጊዜ የእርምት እርምጃን ለመውሰድ አይቻልም፤ ቢቻልም በጣም አስቸጋሪ ይሆናል፤ ላይ ላዩን መቻቻል ውስጥ ውስጡን መቆሳሰል ውሎ አድሮ ለማኅበረሰቡ በአጠቃላይ ጉዳትን እንጂ ጥቅምን አያመጣም፡፡

በተጠቀሰው የሕገ መንግሥት አንቀጽ ውስጥ ቁልፉ ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት መብት ነው፤ አንድ ግለሰብ፣ ወይም አንድ ቡድን፣ ወይም አንድ አገዛዝ ለእኔ የማይበጅ ወይም የማልወደውን ሀሳብ መግለጽ አትችልም ወደማለት ደረጃ ላይ ከደረሰ የእኔን ሀሳብና እምነት አትንቀፍ ለማለት ምን ያግደዋል? የእኔን ሃይማኖት አትንቀፍ የሚል ትክክለኛው ሃይማኖት የእኔ ብቻ ነው ለማለት ምን ያቅተዋል? አንዱ መሠረታዊ ችግራችን የነጻነት ግንዛቤያችን እኛ በምንፈልገውና በምንወደው ላይ ብቻ የቆመ ነው፤ ማንንም ሰው ሳልነካ እኔ የምወደውን ለማድረግ ነጻነት አለኝ ብሎ የሚያምን ሰው ሌላውም ሰው እንዲሁ ማንንም ሰው ሳይነካ የወደደውን ለማድረግ ነጻነት እንዳለው ማመን አለበት፤ አለዚያ የራሱም ነጻነት አደጋ ላይ ነው፤ ከአሥር ዓመታት በፊት ከገንዘብ በላይ ምንም ነገር አለ ብለው በማያምኑ ሰዎች አንዳንድ የብልግና ጋዜጦችና መጽሔቶች መውጣት ጀምረው ነበረ፤ እነዚህን መጽሔቶችና ጋዜጦች ለማገድ ሙከራ ሲደረግ በኢሰመጉ ውስጥ ጉዳዩ ሲታይ አንዳንድ ሰዎች መታገድ አለባቸው የሚል እምነት ነበራቸውና ኃይለኛ ክርክር ነበር፤ እነዚህን የብልግና ማሰራጫ ጽሑፎች መከላከልና ማጥፋት የሚቻለው ነጻነትን በመገደብ ሳይሆን ጽሑፎቹን ባለመግዛት ባለው ነጻነት በመጠቀም ነው፤ አለዚያ የአንዱን ነጻነት በሌላው ነጻነት እየመነዘረና እያጋጨ የሁሉንም ነጻነት የሚገፍ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

ሀሳብን የሚፈራ ማኅበረሰብ እንደረጋ ውሀ ባለበት ይቀራል፤ የሚያድሰውን መንገድ ሁሉ ስለዘጋ አይታደስም፤ ከራሱ የሚተርፈውም አይኖረውምና ለማንም አይበጅም፡፡

አብሮ መኖር አብሮ ማደግንም መጨመር አለበት፤ ይህንን ከአመንን መቻቻልን ከእምነትና ከሃይማኖት፣ ከሙሉ ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት ጋር መቀበል አለብን፤ ሀሳብን የመግለጽ ነጻነትን ችላ ብሎ የሃይማኖትን መብት ለማስከበር በጣም ያስቸግራል፡፡

 

Advertisements
This entry was posted in አዲስ ጽሑፎች and tagged . Bookmark the permalink.

One Response to የሃይማኖት ነጻነትና መቻቻል

  1. Pingback: የሃይማኖት ነጻነትና መቻቻል « Amsalutamirat's Blog

Comments are closed.