በሕግ አምላክ!

በሕግ አምላክ!

ጥቅምት 2001 ዓ.ም.

በቢሾፍቱ መንገድ አራተኛ ክፍለ ጦርን አልፌ እየነዳሁ ወደመሀል ከተማ እመጣለሁ፤ ትራፊክ መብራቱ ዘንድ በግራ በኩል ዳር ይዤ ቆምሁና አረንጓዴ ሲበራ መንገዴን ቀጠልሁ። በድንገት ከኋላዬ የነበረ ሚኒባስ በቀኝ በኩል በጣም ተጠግቶ ወደግራ ለመታጠፍ ተጠመዘዘ፣ ፍጥነቴን ቀንሼ ላሳልፈው ስል ድንገት ቆመ። አንድ የካድሬ አንደበት ያለው ጎረምሳ ወረደና ወደኔ መጥቶ “መታጠፍ መብቴ ነውኮ!” አለኝ እየተቆጣ፤ በቀኝ በኩል ተጠምዝዞ መቅደም እንዴት መብቱ ሊሆን እንደሚችል በጥሞና ጠየቅሁት። ወደግራ መዞር መብቱ እንደሆነ ደጋግሞ ይነግረኛል። እኔም እንግዲህ የትራፊክ ፖሊስ መጥቶ ይገላግለናል ብዬ አርፌ መኪናዬ ውስጥ ተቀምጬ ቲያትር የማይ መሰለኝ።

አንድ ከሚኒባሱ ጋር ይሁን ከሌላ ግንኙነቱ ያልገባኝ ሰው፣ ከሚኒባሱ ወጥቶ ሞባይሉን ጆሮው ላይ ደቅኖታል፤ ግን ምንም ንግግር አይሰማኝም። ከእኔም ጋር ይሁን ከሹፌሩ ጋር ምንም አልተነጋገረም፤ ሞባይሉን ይዞ ይንጎራደዳል፤ እኔ ተመልካች ነኝ። አንዲት ወጣት ሴት ነገሩ አላማራትም መሰለኝ ከሚኒባሱ ወጥታ ወደ ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት አጥር አቅጣጫ ኼደች። ሹፌሩ እንደተሰበረ ሸክላ ያንኑ በቀኝ በኩል የመታጠፍ መብቱን እጆቹን እያወራጨ ይነግረኛል፤ ወጣቱን ካድሬ ሹፌሩ ትኩር ብዬ ሳየው ተወው! ቀልድ ነው! የሚለኝ ይመስላል። ባለሞባይሉም መኳንንት የማስመሰል ትርዕይቱን ቀጥሏል። ከእኔም ጋር ሆነ ከሹፌሩ ጋር ንግግር የለውም። አለኝ የሚለውን ክብሩን በዝምታ ሸፍኖታል፤ የወጣቱን ሹፌር አንደበት የሚያንቀሳቅስበት የራሱ ዘዴ ያለው ይመስላል። ወጣቱ ሹፌርም መሣሪያነቱ ገብቶት የሚቀልድ ይመስላል፤ እኔም ከተቀመጥኩሁበት አልተንቀሳቀስሁም፤ መናገርም ትቻለሁ። የትራፊክ ፖሊስ መጥቶ ይገላግለናል እያልሁ አስባለሁ። በድንገት ባለሞባይሉን መኳንንት ሹፌሩን በዓይኑ ጠቅሶት ወደ መኪናው ውስጥ ገባ። መኼድ ሲጀምሩ እኔ አሁንም እንደተደናገርሁ ነኝ፤ ምናልባት ትራፊክ ፖሊስ ሊያመጡ እንደሆነ በማለት ሳልንቀሳቀስ ትንሽ ቆየሁ፤ ሲርቁ ጊዜ እኔም መንገዴን እየተገረምሁ ቀጠልሁ።

የተፈለገው ምን እንደሆነ አሁንም አልገባኝም። በሆነው ባልሆነው ምክንያት እየተፈጠረ ሰውን ማጉላላት የሚቻል መሆኑን ለማሳየት ነው? ጉራ መንፋት የሚባለው ነው? ለማስደንገጥ ነው? ለማስፈራራት ነው? አደጋ ፈጥሮ በዚያ ሳቢያ ትንሽ ጥቅም ለማግኘት ነው?

ነገሩ ሁሉ ፍፁም ፉርሽ ሲሆንብኝ ያደረብኝ ጥርጣሬ ጥሩ አይደለም። በወንበዴነትና በሕጋዊ ሥራ መሀከል ያለውን የሠፋ ልዩነት በጣም ያጠብበዋል። ስለዚህም ወንበዴውን ከሕጋዊው ሠራተኛ ለመለየት አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ ሕጋዊ ሥራውን ያረክሰዋል። በአሁኑ ጊዜ በፈረንሣይ ውስጥ አንድ ፖለቲከኛን ሲከታተሉ የነበሩ አሥር ሰዎች ታስረው በምርመራ ላይ መሆናቸውን ከዚያው የተሠራጨው ዜና ይናገራል። እኛ ዘንድ እንዲህ ያለውን አቤቱታ ማን ይሰማው ይሆን?

በአፄ ምኒልክ ዘመን አንድ ዘፈን ነበር ይባላል። ንጉሥ ምኒልክ ከወይዘሮ ባፈና የወለዱአቸው ልጃቸው ወይዘሮ ማናለብሽ ይባላሉ። ታዲያ ወይዘሮ ማናለብሽ አንዱን ሰው በድለዋል መሰለኝ፤ መነሻውን ረሳሁት፤ ማስታወሻዬም ጠፋብኝ፤ አንድ የሚያስታውስ ሽማግሌ ባገኝ ደስ ይለኛል፤ ለማናቸውም ዘፈኑ የሚቀጥለው ነው፦

“እናትሽ ባፈና፣ ምኒልክ አባትሽ፣

ባልሽ ማመድ አሊ አንቺ ማናለብሽ፣

ከየትኛው ዳኛ አቤት ልበልብሽ?

      ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ በያለበት በመንገድ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በሬስቶራንት ውስጥም እየገቡ የቅንጅት ሰዎችን ማዋከብ፣ ማስፈራራትና አንዳንድ ጸያፍ ነገሮችን ማደረግ የተለመደ ሆኖ ነበር፤ በእውነት ያሳፍር ነበር። ጨዋነት የት ገባ? ጥልቁ ሀብታችን እሱ ነበር፤ ዛሬ የተናካሽ ውሻ ባሕሪ ከየት አመጣን? ያውም በባቡር መንገድ ላይ!

Advertisements
This entry was posted in ቀደም ሲል የወጡ ጽሑፎች. Bookmark the permalink.