የማፍረስ አባዜ

 ታኅሣሥ 2005

 በአለፉት ሃያ አንድ ዓመታት፣ በተለይም ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ፣ የወያኔ/ኢሕአዴግ አገዛዝ ልዩ መታወቂያው ያደረገው  እያፈረሱ መገንባትን ነው፤ ማፍረስ ቀላል ሥራ ነው፤ ጭንቅላትም፣ ማሰብም አይጠይቅም፤ ልብም፣ ስሜትም አይጠይቅም፤ የሚጠይቀው የዝሆን አካልና ጉልበት ብቻ ነው፤ አንድ ቤተሰብ ስንት ዓመት በዚያ ቤት ውስጥ ኖረ? ጎረቤቶች ምን ዓይነት ትስስር አላቸው? በማኅበር፣ በእድር፣ በዝምድና በቤተ ክርስቲያን ወይም በቤተ መስጊድ፣ በመቃብር፣ በሥራ፣ በአጠቃላይ የእያንዳንዱ ሰው ኑሮ ከልደት ጀምሮ የተፈተለበትና የተደራበት ውስብስብ የኅብረተሰብ አካል መኖሪያ ነው፤ ይህንን አካል ለማፍረስ ትንሽ ጭንቅላትና ግዙፍ ጡንቻ ያለው አይቸግረውም፡፡

መኖሪያ ቤቶችን ማፍረስ፣ መቃብሮችን ማፍረስ፣ የንግድ ድርጅቶችን ማፍረስ፣ ትምህርት ቤቶችን ማፍረስ፣ … ማፍረስ… ማፍረስ… ማፍረስ! ሳያለቅሱ እያስለቀሱ ማፍረስ፤ መሬቱን ማራቆት፣ ሰዎቹን ማራቆት፤ እያፈረሱ ማራቆት፤ እያራቆቱ ማስለቀስ፤ እያስለቀሱ ማፈናቀል፤ እያፈናቀሉ መጣል፤ የሚፈርሰው ቤት ብቻ አይደለም፤ የሚራቆተው መሬት ብቻ አይደለም፤ የሚፈርሰው ሰው ነው፤ የሚፈርሰው ከልደት ጀምሮ የነበረ ጉርብትና ነው፤ የሚፈርሰው ለዘመናት የተገነባ ዝምድና ነው፤ የሚፈርሰው የኑሮ የመደጋገፍ ተስፋ ነው፤ የሚፈርሰው የ‹‹ቀባሪ አታሳጣኝ!›› ጸሎት ነው፤ የሚፈርሰው የአጥቢያና የእድር የቀብር ዋስትና ነው፤ የሚበጣጠሰው ለብዙ ዘመናት የቆየ፣ በደስታና በሐዘን፣ በሳቅና በለቅሶ ማኅበረሰቡን ያስተሳሰረው ገመድ ነው፤ ይህ ለዘለዓለም ጠፍቶ የሚቀር፣ ማንም በምንም የማይተካው ማኅበረሰባዊ ክስረት ነው፤ የትውልድ መቋረጥ ነው፤ የታሪክ መቋረጥ ነው፤ የማይሽር የዜግነት ቁስል ነው፤ ከዜግነት የአገር ባለቤትነት ወደባይተዋርነት፣ ከሰውነት ወደኢምንትነት፣ ወደገለባነት መውረድ ነው፤ መዋረድ ነው፤ የተወለዱበትና ያደጉበት በጉልበተኞች ሲፈርስ አቅመ-ቢስ ሆኖ መፈናቀል፣ አገሬ ነው ባሉት ቦታ ባይተዋር ሆኖ መሰደድ ነው፤ በሌላ አገር ተሰድዶ ሁለተኛ ዜጋ መሆንን የሚመርጡ ሞልተዋል፤ ያውም ከተገኘ!

ይህ ሁሉ ሀሳብ-የለሽ ማፍረስ የሚካሄደው በደሀዎች የኢትዮጵያ ዜጎች ላይ ነው፤ ይህ ሁሉ ሀሳብ-የለሽ ማፍረስ የሚካሄደው በሕገ መንግሥቱ በግልጽ የተዘረዘሩ መብቶች በአሏቸው ሰዎች ላይ ነው፤ በብዙ የዓለም-አቀፍ ሕጎችና ስምምነቶች የታወቁ መብቶች በአሏቸው ሰዎች ላይ ነው፡፡

የማፍረሱን አባዜ ክፋቱን ገልጦ የሚያሳየው አንደኛ አብዛኛውን ጊዜ በክረምት መሆኑ ነው፤ ሁለተኛ ቤታቸው ለሚፈርስባቸው ሰዎች ጊዜያዊ መጠለያ እንኳን ሳይመቻችላቸው ሴቶችና ወንዶች፣ ሕጻናትና ልጆች፣ አሮጊቶችና ሽማግሌዎች፣ ሕመምተኞችና ደካሞች ሜዳ ላይ መውደቃቸው ነው፤ በኢጣልያ ወረራ ጊዜ ያየሁትን እየመረረኝ ልናገር፤ ኢጣልያኖቹ ደህና ደህና ቤቶችን ለሹማምንት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን መጀመሪያ ለባለቤቶቹ በመርካቶ ኢንዲጂኖ (የአገሩ ሰው ገበያ) የጭቃ ቤቶች ሠርተው ያስገቧቸው ነበር፤ ባለቤቶቹን ከቤታቸው የሚያስወጡት ወደአዲሶቹ ቤቶቻቸው ካስገቡ በኋላ ነበር፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ነኝ የሚል ከወራሪ የፋሺስት ቄሳራዊ አገዛዝ እንዴት የባሰ መስሎ ይገኛል?

ለመሆኑ እነዚህ ቤቶቻቸው የሚፈርሱባቸው ሰዎች ኢሕአዴግን ከመረጡት 99.7 ከመቶ ውስጥ ያሉ ናቸው ወይስ ከዚያ ውጭ ያሉትና ያልመረጡት እየተፈለጉ ነው?

ቤት አፍራሾቹ ጊዜ የፈቀደላቸው ዘመናዮች ናቸው፤ በእነሱ ጭንቅላት ጊዜ ጸጥ ብሎ የቆመና በእነሱ ጡንቻ ብቻ የሚነጋና የሚመሽ ነው፤ ትዕቢት የሚባለው ይህ ነው፡፡

ቤቶቻቸው፣ የዘመዶቻቸው መቃብሮች፣ የንግድ ድርጅቶቻቸው የፈረሱባቸው ሰዎች ተራ የኢትዮጵያ ዜጎች ናቸው፤ ለእነሱ ዓለም ተደርምሶ ለእነሱም ጊዜ ጸጥ ብሎ ቆሞአል፤ ትናንት ያለፉበት ሁሉ በጨለማ ተውጦአል፤ ትውስታም አልተወላቸውም፤ ነገ በጥላቻና በመረረ ቂም ተጋርዶ ንጋትን አያስመኝም፤ ቢጮሁ ድምጻቸው የማይሰማ፣ አቤት ብለው የሚጮሁበት መድረክ የሌላቸው፣ የእገሌ ያለህ! ወይም በእገሌ አምላክ! የሚሉት የሌላቸው፣ ቀኑ የጨለመባቸው ሰዎች ናቸው፤ አምላካቸው ብቻ ያያቸዋል፤ እንባቸውንም ይሰፍራል፤ ቀኑ ሲደርስም ያስከፍላል፤ የብርዱን ግርፋት፣ የጸሐዩን ጥብሳት፣ ረሀቡንና ጥማቱን ጉልበተኞቹ፣ ትዕቢተኞቹ ባያዩም እግዚአብሔር ያያል፤ አይቶም ይመዘግባል፤ መዝግቦም ዋጋ ያስከፍላል፤ ታሪክም መዝግቦ ለነገው ትውልድ ያስተላልፋል፤ ያፈረሱ የሚፈርሱበትን፣ ያራቆቱ የሚራቆቱበትን፣ ያዋረዱ የሚዋረዱበትን ቀን እግዚአብሔር ያመጣዋል፤ ያኔ ሁሉም እኩል የአገሩ ባለቤት ይሆናል፤ አፍራሽ ጉልበተኛ በሕግ ይታሰራል፤ ደካማውም ደሀ በነጻነት ጉልበትን ያገኛል፡፡

+++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++

በቅርቡ ደግሞ ሌላ ዓይነት የማፍረስ ተግባር መጀመሩ ይሰማል፤ ዙሪያውን እየተቆፈረ ስለሆነ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ቢፈርስስ? የአጼ ምኒልክ ሐውልት ቢፈርስስ? ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢፈርስስ? ማን ይመክትላቸዋል? እንደእንግሊዝ፣ እንደቤልጂክና እንደሩስያ ኤምባሲዎች ያለ የሚመክት ኃይል በአካባቢው የለም፤ በአንዳንድ አገሮች ለምሳሌ በእንግሊዝ አገር እንኳን ብሔራዊ ታሪክንና ስሜትን ያዘለ ሐውልትና ጥሩ የእርሻ መሬትም ለመንገድ እንዲውል ሕዝቡ አይፈቅድም፤ የሕዝብ ድምጽ ዋጋ ባለው አገር፡፡

ደሞስ እንኳን ሐውልትና አርበኞችን፣ ለአገራቸው ለወገናቸው፣ ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው የቆሰሉትንና የደሙትን፣ ስቃያቸውን ያዩትን ገድለናቸው የለም እንዴ? ሰቅለናቸው የለም እንዴ? በጥይት ደብድበናቸው የለም እንዴ? ባንዳዎቹ አርበኞቹን እየገደሉ ጨርሰው የባንዳዎቹ ልጆች የሚገድሉት አርበኛ ሲያጡ ሐውልት ቢያፈርሱ፣ ወይም የአሉላን ሐውልት ለሌላ፣ የሙሉጌታ ቡሊን መታሰቢያ ለሌላ ቢያደላድሉ አዲሱ ነገር ምንድን ነው? መካብ ሲያቅት ማፍረስ ሥራ ይሆናል፤ ወይም የማፍረስ አባዜ ከያዘ ካላፈረሱ መካብ የማይቻል ይሆናል፡፡

እግዚአብሔርም ያፈርሳል፤ ‹‹ዝናብም ወረደ፤ ጎርፍም መጣ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያንም ቤት መታው፤ ወደቀም፤ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ፡፡›› ማቴ. 7/27

 

Advertisements
This entry was posted in አዲስ ጽሑፎች. Bookmark the permalink.

3 Responses to የማፍረስ አባዜ

 1. በለው ! says:

  የአቡነ ጴጥሮስ እና ዳማዊ ምን ልክ ሀውልት ሊፈርስ ነው
  ለመሆኑ ምን ያልፈረሰ አለ? ወደፊት እንዲፈረስ ያልታቀደው የወያኔ ‘ሞኖፖል’ ብቻ ነው። ለአንድ ሀገር ዕድገት መለኪያ የሚሆነው ቤት መሥራት እና መንገድ ማስፋት ነው ብለው የሚያምኑ አፍሪካ መሪዎች በአብዛኛዎቹ በነጭ አለቆቻቸው ሙገሳ አድናቆት ኒሻን እና የክብር ዶክትሬት ሲሸለሙ አይተናል! ዕንባም እየተናነቃቸው ዝናቸውን ሲለፉፉላቸው አይተናል ሰምተናል ተገርመናል ይህም ለእኛ ቤት ሰውዬ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ተንቆለጳጵሰዋል… መቼም ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው የአፍሪካ ሕዘብ የሚጠቅመውን ሳያውቅ ሌሎች ስለእሱ ሲመሰክሩ መስማት እራሱ ታላቅ ውርደት ነው። ነገሩ በሆነ ባልከፋ መንገድም ተሰራ ህንፃ በሀገራችን ነው ግን ብዙ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ መሠረታዊ ነገሮች አልተሰሩም አድናቂዎቻችንም ተደናቂዎችም የድንቁርና ‘ራዕይ’ አላቸው እንላለን።
  “ጫማ ተጫምቶ ሱሪ ለማጥለቅ የመተናነቅ ቅጥ አንባሩ የጠፋ አባዜ! ይህ ሁሉ አፍረሶ መሥራት ለምን አስፈለገ?
  &&&&&&&&&&&&&&&&&%%%%%%%%%%%%%%%%%
  አድናቆት የተቸረው የቀለበት ማሳላጫ መንገድ ለባቡር ሀዲድ ሲባል በመጠኑ ይፈርሳል…መቶ ዓመት ያስቆጠሩ በቅርስነት መጠበቅ የሚገባቸው ጥንታዊ ህንፃዎች ይፍረሱ!…ለምን? ቢባል ታሪክና ሕዝብ ከኢህአዴግ በፊት አልነበረም የሕገ መንግስቱን ፅሁፍ በጥሞና ያንቡ እያንዳንዳችሁ ከሚከተለው አንዱ ደርሶባችኋል አትደብቁ!!አደራ
  …ዕድር፤ ዕቁብ፣ፀበል ፀዲቅ፣ አድባር፣ አበልጅ፣ ያገር ልጅ፣ ማህበርተኛ፣አብሮ አደግ፣ጉርብትና፣ የትምህርት ቤት ጓደኛ፣ የመሥሪያ ቤት ጓደኛ፣ጋብቻሞች፣የቤተሰብ የቀብር ቦታ፣ተስካር መደገስ(ማስተዛዘን)፣ከጥንት ወዳጅ ጋር ልጅን መዳር፣ በዓመት በዓል(የሥጋ ቅርጫ) መገባበዝ፤ቡና መጠራራት፣ እና ሌሎችም(…)አሁን አሉን ? ? የሉም ! አይኖሩምም !ይህ ከቀጠለ አንድ ትሆናለህ!ትተባበራለህ !ትመክራለህ!ታልማለህ !ትሰባሰባለህ! ትፅፋለህ! ታነባለህ! መብትህን ትጠይቃለህ!ትጠነክራለህ!ግን እላችኋለሁ ወዳጆቼ ወገኖቼ ተሞኛችሁ! ተሸወዳችሁ!እራሳችሁን አጠፋችሁ!! ለሌባ በራችሁን ከፍታችሁ ተዘረፍን ትላላችሁ! ፍቃደኛ ሆናችሁም ስትራዱ ኖራችሁ አሁን የአዞ እንባም ታነባላችሁ? ነውር ነው!!

  ቀበሮ ያህያ ጆሮ ይወድቃል ብላ ስትከተል ውላ ደከማት ጠኔ ይዟት በአፍ ጢሟ ተደፋች አሉ…ያየ ሰው ነው የነገረኝ…የብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ከላይ የነበራቸውን (ሕብረሰባዊነት)መብት ሁሉ ጥለው ወያኔ እጥልላችኋለሁ ያላቸውን አማራ መጥፋት እና መውደቅ ሲከተሉ እለግሳችኋለሁ ያለውን መሬት፣ ሥልጣን፣ፍርፋሪ ጥቅም ሲያሳድዱ ህሊናቸውን ሸጡ ካዳሚም ሆኑ ወያኔ ዞሮ ከእላያቸው ላይ ቄጤማ ጎዝጉዞ ጨበሰባቸው!!።

  በሁለት የድሮ የመንግስት ት/ቤት የገጠመኝ…’ከጉዞዬ ማስታውሻ’ ትንሽ ላካፍላችሁ(…) ነባሮቹ በንጉሳን የተሰየሙ ት/ቤቶች ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ህንፃ ዘር ሃይማኖት ቋንቋ ዘር ሳይል የድሃ ልጅ ዕውቀት ቀስሞ ለሀገሩ የተሰማራበት እስከዛሬም በእነኝህ ት/ቤት ግብረገብነትን፣ ኢትዮጵያዊነትን አጎልብቶ ትውልዱን የተካ ዜጋ የፈለቀበት ቤት ተከተሉኝ >ኑ>ግቡ> ዛሬ ከመግቢያ በሩ ወደ ትምህርት ክፍሎች ለመሄድ በበጋ ከዘራ በክረምት ጀልባ ያሰፈልግዎታል… ወንበርና ጠረጴዛው ላይ ያለ ሚስማር ለልብስና ለሰውነት አደለም ለዓይን የሚያስፈራ ነው፣ ጣሪያቸው ያፈሳል፣መስኮቶቻቸው የሉም፣ግድግዳው ቀለም የነካው በዚያው በሰገሌ ዘመቻ ጊዜ ነው፣ጥቁር ሰሌዳው ገበጣ ያጫውታል፣የኮርኒሱ ግጥምጣም ተነቅሎ ጠፋ ይላሉ፣ በሮቻቸው አይገጠሙም በድንጋይ ተደግፈዋል፣ መምህር እና ተማሪዎች ይላፋሉ፣በት/ቤቱ አጥር ግቢ ጥጥና አልኮል የያዘች ተንቀሳቃሽ ትንሽ የመጀመሪያ ዕርዳታ መስጫ ሳጥን አለች(አይቻት አሳዘነችኝ!)በባዶ እግሩ የሚሄድ ተማሪ አላየሁም አብዛኛው ተማሪ ያደረገው የቻይና የፕላስቲክ ሲሊፐር ግማሹ አካሉ ተቆረጦ የለም፣ሁሉም ተማሮ(ሪ)ዎች ዩኒፎርም አላቸው ግን የተቀደደ እና የተተለተለ የለበሱት ይበዛሉ፣ሕፃናት ለእስፖርት ግድ ያላቸው አይመስልም የእስፖርት ሜዳው እዳሪ የእርሻ ቦታ መስሏል ልጆች ሲጫወቱ ሲዘሉ ሲቦርቁ አይታዩም ተሰባስበው ተደብተው ቆመውም ተቀምጠው ይታያሉ ሲጮሁ ይሰማል ተነጋግረው መደማመጣቸውን እንጃ…ተጠራጣሪ ፈሪ ድንጉጥ ናቸው።በመንግስት ይሁን በት/ቤቱ አስተዳደር ወጪ በመሠራትም ላይ ያለ የተሰራም አዲስ ሕንፃ አለ ግራ ያጋባው ከመግቢያ በሩ እስከ አዲሱ ህንፃ ያለው መንገድ ጭቃ በቻይና ሲሊፐር ተዝቆ ፎቁ ላይ ወጥቷል በረንዳው ሲታጠብም ሕንፃው ላይ እዥ ፈጠሮ ነባሩ ሕንፃ ከአዲሱ ከውጭ ያምራል ከተሰራ ሁለት ዓመት ያልሆነው ህንፃ መፈረካከስ ጀምሯል። አቤት እየሰሩ ማፍረስ? ?እያፈረሱ መሥራት መፀዳጃ ቤቶች ውሃ መጠጫው አካባቢንም አየሁ!!!
  አሁን ወጣሁ <<<ኑ<<<
  ከዋናው መግቢያ ሙሉ ለሙሉ አጥሩ ፈርሷል።የውስጥ መንገዱን ያልሰራ መሃዲስ? መማሪያ ክፍሎቹን ያላደሰ ምሁር!ቀደም ተከተል የማያውቅ አሰተዳደር? እንዴት? አጥሩ ታየው? ሲመልሱልኝም "ዕድሜው ከ፵ ዓመት በታች የሆነ ሁሉ የኢህአዴግ ልጅ እንጂ ያለፈው ዘመን ልጅ አደለም የድሮውን ታሪክ፣ባሕል፣ሃይማኖት፣ በጭራሽ ሊያውቅ አይገባውም ስለዚህ መፍረስ አለበት።ምክንያት የተደረገው ግን "የዲያስፖራውን ድልድይ" ለመሥራት ሲባል ነው። ድልድዩ እና ት/ቤቱ ምን አገናኘው? ይህ ሁሉ በአንድ መስመር የሚገኝ የ፭ ኤምባሲዎች አጥር ለምን አለፈረሰም? አልሰማኽኝም እንጂ ምክንያት!በቃ የማፍረስ ምክንያት!!(አሁንም የባቡሩ ሀዲድ በምክንያት ሆን ተብሎ በሀውልቶች ላይ የተሰመረ ይሆን??…አዎን ያጫወትኳችሁ ስለ የቀድሞው ት/ቤቴን የቀዳማዊ ኀይለስላሴ አንደኛና ሁለተኛ ት/ቤት(ኮከበ ጽብሐን) ነበር። የመጨረሻውንም ላውጋችሁ ለመሆኑ የግንቡ ጥርብ ድንጋይ እና ሥም ያለበት ብረቶች የት አሉ? አልኳቸው… አዎን, የትምህርት ቤቱ አስተዳደር መልሶ ለመገንባት ወላጆችን ሰብስቦ ገንዘብ እንዲያዋጡ ጠይቋል ሕዝቡም ፍራሹ ንብረት የት ሄደ?ሲል ጠይቋል?። ምላሹ ሌባ ወስዶታል ነው!።ይቺ ነች ጨዋታ!!ለምን መጀመሪያውኑ ፈረሰ ለሚለው ግን በኢንጂነሩ (መሐንዲሱ) በሥራ ተቋራጩ ስሕተት ለድልድዩ መሠራት የሚያደናቅፍ ስለመሰለው!።በለው! በለው!

  የኢትዮጰያ ልጆች ሆይ ! በመጀመሪያ ስሕተት እንቢኝ! ካላላችሁ ሁለተኛ ጥፋት ሆን ተብሎ ይፈፀማል።አራት ነጥብ። እየተለመደም ይሄዳል!። ባህልም ህግም ይሆናል… ቀሪውን በሌላ ጊዜ ታሪክን ቅርስን አብረን እንታደግ የጥፋት ጨርቆችን እናስቁም ከአደራ ጋር "ኢትዮጵያ እጆቿን ዘርግታ ቅን አሳቢ ልጆቿን ትሰበስባለች!"
  በቸር ይግጠመን ..በለው! ከሀገረ ከናዳ

 2. Pingback: የማፍረስ አባዜ

 3. netsanet says:

  ማፍረስ ቀላል ሥራ ነው፤ ጭንቅላትም፣ ማሰብም አይጠይቅም፤ ልብም፣ ስሜትም አይጠይቅም፡፡ ልክ!!! እግዚአብሄር ይስጥልኝ ጋሽ መስፍን፡፡

Comments are closed.