መርዝ ከውጭ ይረጫል ወይም ከውስጥ ይመነጫል

መስፍን ወልደ ማርያም

Publication1-150x150የካቲት 2005

በአለፉት ሠላሳ አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ ችግሮችን መፈልፈያ መሣሪያ ሆናለች፤ ለብዙ ምዕተ-ዓመታት ይዘናቸው (ምናልባትም አቅፈናቸው ማለት ይሻል ይሆናል) ስንንከባለል የቆዩ ችግሮች ሞልተውናል፤ እያሰብን እነዚያን የቆዩ ችግሮቻችንን በመፍታት ፋንታ ሌሎች አዳዲስ ችግሮችን እየፈለፈልን የተቆላለፉና የተወሳሰቡ፣ ውላቸው የጠፋ ችግሮችን ፈጥረናል፤ እየፈጠርንም ነው፤ አሁን በመፈጠር ላይ ያለው አዲስ ችግር እስላማዊ መንግሥት በኢትዮጵያ የሚል ነው፤ እስቲ እንመልከተው፡፡

በሩቁ እንጀምር፤ እስላማዊ መንግሥታት ያቋቋሙ አገሮች አሉ፤ አንዳቸውም ሰላም የላቸውም፤ እስላማዊ ቡድኖች በምርጫ አሸንፈው ሥልጣን የያዙ አሉ፤ ለምሳሌ በቅርቡ በአረብ አገሮች በተጀመረው የፖሊቲካ እድገት ለውጥ በቱኒስያና በግብጽ እስላማዊ ቡድኖች አሸንፈው ሥልጣን ይዘዋል፤ በዚህም ምክንያት በቱኒስያና በግብጽ የለውጥ ጥያቄ አገርሽቶ አንደገና ሰዎች እየሞቱ ነው፤ በነዚህና በሌሎችም አገሮች የሚገኙት ወጣቶች የሚፈልጉት የሰው ልጆች ሁሉ መብቶች የሚከበሩባቸውና በሙሉ የግለሰብ ነጻነት የተረጋገጡባቸው አገሮች እንዲኖራቸውና በእኩልነት ኩሩ ዜጎች ሆነው እንዲኖሩ ነው፤ የአንድ አገር ዜጎች የተለያየ ዘር፣ የተለያየ የቆዳ ቀለም፣ የተለያየ ቁመትና ውፍረት፣ የተለያየ ጾታና ዕድሜ፣ የተለያየ ቋንቋ፣ የተለያየ ሃይማኖት፣ የተለያየ የፖሊቲካ አመለካከት፣ የተለያየ ትምህርት፣ የተለያየ ሙያና የተለያየ ገቢ ሊኖራቸው ይችላል፤ የጋራ ማንነታቸው ዜግነት ነው፤ እኩልነታቸው በዜግነታቸው ነው፤ አንድነታቸው በዜግነታቸው ነው፤ እኩልነታቸውንና አንድነታቸውን የሚያረጋግጥላቸውና ሚዛኑን የሚጠብቅላቸው ከበላይ ሆኖ ሁሉንም የሚገዛው ሕግ ነው፡፡

በቡድን ወይም በጅምላ የሚያስቡ ሰዎች የሕግን ባሕርይ አያውቁትም፤ ‹‹ክርስቲያኖች እስላሞችን እንጨርሳለን›› አሉ፤ ወይም እስላሞች ክርስቲያኖችን እንጨርሳለን›› አሉ፤ በሚል አሉባልታ ላይ ክስ ተመሥርቶ ሕጋዊ ፍርድ መጠበቅ አይቻልም፤ በየትም ሆነ በማንኛውም ጊዜ ጽንፈኛ እምነትና አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ይገኛሉ፤ እነዚህ ግለሰቦች ሕልማቸውንም ሆነ ቅዠታቸውን በስውርም ሆነ በአደባባይ ይገልጻሉ፤ ለምሳሌ በአሜሪካ ጥቁሮችንና ይሁዲዎችን ከአገሩ ጠራርገን እናወጣና ንጹሕ የነጮች አገር እንፈጥራለን የሚሉ ግለሰቦች አሉ፤ ይህ እምነት ለአሜሪካ ማኅበረሰብ መርዝ ነው፤ አሜሪካ የነጻነት አገር ነው፤ የነጭ ዘረኞቹ መርዛቸውን ለመንዛት መብት አላቸው፤ የዘረኞቹን መብት ለማፈን የሚወሰድ የጡንቻ እርምጃ ሁሉ አሜሪካ የነጻነት አገር መሆኑን ይሽራል፤ ከዚያም በላይ የአሜሪካ መንግሥት በሚከተለው ዘዴ ከነጭ ዘረኞቹ የተሻለ አይሆንም ነበር፤ ስለዚህም ነጭ ዘረኞችን ለመቋቋም የሚወሰደው አርምጃ አሜሪካ የነጻነት አገር መሆኑን ሳይሽርና ነጭ ዘረኞቹም እምነታቸውን የመግለጽ መብታቸው ሳይደፈጠጥ መሆን አለበት፤ የነጻነት ትርጉሙ ይህ ብቻ ነው፡፡

በሥልጣን ወንበር ላይ ስለተቀመጡ ብቻ አንድ ዓይነት የፖሊቲካ እምነት ብቻ ይዞ ሌላውን መደፍጠጥ፣ መንግሥት የባረከውን አንድ ዓይነት የኦርቶዶከስ ሃይማኖት ብቻ ማደርጀትና ሌላውን ማፈን፣ መንግሥት የባረከውን አንድ ዓይነት የእስልምና ሃይማኖት ብቻ ማደርጀትና ሌላውን ማፈን ልማድና የአሠራር ባህል እየሆነ ሲሄድ ሁሉንም ነገር አንድ ዓይነት ብቻ ለማድረግ የሚታየው ጥረት የኢትዮጵያን ጉራማይሌ ባሕርይ የሚቃረን በመሆኑ ስር አይኖረውም፤ ይህ ሁሉም ሰው ሊያስብበት የሚገባው አንዱ ነገር ነው፤ ሁለተኛው አንድ ወይም ጥቂት ሰዎች በኢትዮጵያ ውስጥ እስላማዊ መንግሥት እናቋቁማለን ቢሉ አገር የሚሸበርበት ምንም ምክንያት የለም፤ ኢትዮጵያን የኦርቶዶክስ ክርስቲያን አገር ለማድረግ የሚመኙም አሉ፤ ኢትዮጵያን ሃይማኖት-አልባ የጉግማንጉግ አገር ለማድረግ የሚፈልጉ አሉ፤ ኢትዮጵያ በአንድ አጋጣሚ ወንበሩ ላይ የወጣ ጉልበተኛ የሚያትምባትን እምነትም ሆነ ሃይማኖት የማትቀበል አገር መሆንዋ ተደጋግሞ የታየ ነው፤ ኢትዮጵያን የይሁዲ አገር ለማድረግ ተሞክሮአል፤ ኢትዮጵያን የክርስቲያን አገር ለማድረግም ተሞክሮአል፤ ኢትዮጵያን የእስላም አገር ለማድረግም ተሞክሮአል፤ ሁሉም አልሆነም፤ ኢትዮጵያ የሁሉም አገር ሆና ዘልቃለች፤ ይህንን በማክሸፍ ለማንም ምንም ጥቅም አይገኝም፤ በአንጻሩ ደግሞ የሥልጣን ወንበሩ ላይ የወጡ ጉልበተኞች ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጉጉት የሚጠብቀውን የነጻነት ጮራ እያዳፈኑ የነጻነትን፣ የእኩልነትንና የሕግ የበላይነትን ዓላማ ለማክሸፍ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እየቀጠለ ነው፡፡

የነጻነትና የሕጋዊነት መክሸፍ የሰላም ጠንቅ ነው፤ የሰላም መክሸፍ የልማት ጠንቅ ነው፤ የልማት መክሸፍ ደሀነት ነው፤ ደሀነት የሞት አፋፍ ነው፤ ይህንን ለመገንዘብ የሚያዳግተው ሃያ አንድ ዓመት የሞላው ሰው አለ? ኢትዮጵያን ለመምራት የሚደናበሩት ሰዎች ሁሉ ሃያ አንድ ዓመት አልፎአቸዋል፤ ነገር ግን ከላይ የተገለጸው የመክሸፍ ጉዞ ጭራሽ አይታያቸውም፤የሚታየውም ሲነግራቸው የተበለጡ ስለሚመስላቸው አይሰሙትም፤ ስለዚህም የሚታየውን ሳያዩ፣ የሚሰማውን ሳይሰሙ ጊዜ የሚበላውን ጉልበታቸውን ብቻ ተማምነው በጭፍን እንምራችሁ የሚሉትን ተከትለን ለእኛ በሚታየንና ለእነሱ በተሰወረባቸው ገደል ውስጥ ለምን አብረን እንግባ? አብረን ገደል በመግባት አንድነታችንን የምንጠብቅ የሚመስላቸው ሰዎች በሁለት በኩል ይሳሳታሉ፤ አንደኛ ከአገዛዙ መሪዎች ዘንድ የሎሌ ተከታይነትን እንጂ የአኩልነት አንድነትን አያገኙም፤ እኩልነት በሌለበት አንድነት አይፈጠርም፤ ሁለተኛ ወደገደል የሚጨምር አንድነትን መምረጥ ሕይወትን ትቶ ሞትን መምረጥ ነው፡፡

በሃያ አንድ ዓመት ውስጥ መክተፍ-መከታተፍ ሙያ ሆነ፤ ብዙ ሰዎችና ድርጅቶች ሠለጠኑበት፤ መክተፍ-መከታተፍ አብሮ የመኖር ጸር ነው፤ አብሮ የመኖር ጸር የሚሆነው በፍቅር ፋንታ ጥላቻን፣ በሰላም ፋንታ ጠብን፣ በመረዳዳት ፋንታ መጋጨትን፣ በልማት ፋንታ ጦርነትን በመንዛት ነው፤ አንዳንድ ቋንቋ ተናጋሪዎችን በግልጽም ሆነ በስውር እንደጠላት መቁጠርና በእነሱ ላይ ቂምን እንዲቋጥሩ ማድረጉ የማንንም የፖሊቲካ ቡድን፣ የኢትዮጵያን ሕዝብም ይጎዳል እንጂ አይረዳም፡፡

አሁን ደግሞ በአንድ በኩል በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ላይ በየገዳማቱና ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃትና በሊቀ ጳጳሳት ምርጫው ላይ አገዛዙ እያሳየ ያለው ጣልቃ-ገብነት የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮችን እያስቀየመና እያስኮረፈ ነው፤ በሌላ በኩል በእስልምና ሃይማኖት ላይም የሚታየውን ጣልቃ-ገብነት ተከታዮቹ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ በርትተው በመቋቋማቸው እየደረሰባቸው ያለው ግፍ ለጆሮ እየቀፈፈና በጣም አሳፋሪ እየሆነ ነው፡፡

ይህ በሃይማኖቶች ላይ የተጀመረው ዘመቻ ውጤት ይኖረዋል፤ ውጤቱ በአገዛዙ የውስጥም ሆነ የውጭ አመራሩ ላይ ከባድ ተጽእኖ ይኖረዋል፤ የሃይማኖቶቹ ጉዳይ እንደጎሣዎች መከታተፍ በኑሮ ላይ ብቻ ጫናውን የሚያሳርፍና በምድር የሚንከላወስ አይደለም፤ ወደሰማይ ያርጋል፤ የሰማይ ሠራዊትን ይጠራል፤ ያንን ኃይል እንኳን የኢትዮጵያ የጦር ኃይልና የአሜሪካውም አይችለውም፤ ዓይን ያለው ያያል፤ ጆሮ ያለው ይሰማል፤ ልብ ያለው ያስተውላል፤ ዶላር ነፍስን አይገዛም፤ ክብርን አይገዛም፤ ወዳጅንም አይገዛም፡፡

Advertisements
This entry was posted in አዲስ ጽሑፎች. Bookmark the permalink.

21 Responses to መርዝ ከውጭ ይረጫል ወይም ከውስጥ ይመነጫል

 1. Kolotemari says:

  Dear Professor Mesfin,

  Is the government oppressing Muslim or doing its job of safeguarding the nation from Arab revolution tide fringing? I know the government is largely working for itself and we have to wait and struggle for utterly Freedom and justice. At this point i was expecting your fair comment however you seem always distancing yourself from approving the government actions and this is not heroic.

  Thank you

 2. zelalemawi says:

  ፕሮፌሰር መስፍን ለዳንኤል ክብረት በሰጡት ምላሽ በአብላጫው እስማማለሁ:: በአንድ ወቅት አንብቦ, አሰላስሎና አስተውሎ የሚጽፍ መስሎኝ የሚጽፋቸውን ሁሉ እከታተለው ነበር:: አሁን ግን እውነቱን ለመናገር ስሙን እንኳን ለማንበብ የማልፈልግበት ደረጃ “አድርሶኛል”:: ጽሁፎቹ ሞጋች ስለሆኑ አይደለም… በጣም ሲበዛ ግልብና ብስለት የጎደላቸው በመሆናቸው ነው:: የፕሮፌሰር መስፍንን መጽሐፍ ለመተቸት ቀርቶ ለማንበብና ለመረዳት እንኳን አቅም የሌለው ድኩም ሰው ያላቅሙ ሲንጠራራ ማየት ያሳፍራል::

  ሳያነብብ አንባቢ, ሳያውቅ ለቅላቂ የሆነን ደብተራ ማስተንፈስ የግድ ይላል:: አለበለዚያ አቅሙን ሳያውቅ ያለእውቀቱ ገብቶ ሲያቸፈችፍ ብዙ ነገር ያበላሻል:: በዚህ ዘመን ከሚጽፉ ብዕረኞች በጣም ጮርቃ የሆነ ስራ እያቀርቡ, እያደናገሩ ታላቅ ነን እያሉ ከሚኮፈሱ እቡያን ሰፈር የምመድበው ዲያቆን አቅሙ የማይመጥንለትን ነገር መንካቱን ነው ፕሮፌሰር ያሳዩት:: ቋንቋቸው እንደተለመደው ተንኳሽ ነው… ፕሮፌሰርን ከሌሎቹ ልዩ የሚያደርጋቸው ይኽው አቀራረባቸው ነው::

  አሁንም ከተንኳሽ ብዕራቸው የሚወጣውን ለማንበብ እድሜና ጤና ተመኝቼላቸዋለሁ!

 3. zelalemawi says:

  ፕሮፍ:- ቀጥላ ያለቸውን አንቀጽ ከጽሁፍዎት ውስጥ በተለይ ወደድኳት::

  “በቡድን ወይም በጅምላ የሚያስቡ ሰዎች የሕግን ባሕርይ አያውቁትም፤ ‹‹ክርስቲያኖች እስላሞችን እንጨርሳለን›› አሉ፤ ወይም እስላሞች ክርስቲያኖችን እንጨርሳለን›› አሉ፤ በሚል አሉባልታ ላይ ክስ ተመሥርቶ ሕጋዊ ፍርድ መጠበቅ አይቻልም፤ በየትም ሆነ በማንኛውም ጊዜ ጽንፈኛ እምነትና አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ይገኛሉ፤ እነዚህ ግለሰቦች ሕልማቸውንም ሆነ ቅዠታቸውን በስውርም ሆነ በአደባባይ ይገልጻሉ፤ ለምሳሌ በአሜሪካ ጥቁሮችንና ይሁዲዎችን ከአገሩ ጠራርገን እናወጣና ንጹሕ የነጮች አገር እንፈጥራለን የሚሉ ግለሰቦች አሉ፤ ይህ እምነት ለአሜሪካ ማኅበረሰብ መርዝ ነው፤ አሜሪካ የነጻነት አገር ነው፤ የነጭ ዘረኞቹ መርዛቸውን ለመንዛት መብት አላቸው፤ የዘረኞቹን መብት ለማፈን የሚወሰድ የጡንቻ እርምጃ ሁሉ አሜሪካ የነጻነት አገር መሆኑን ይሽራል፤ ከዚያም በላይ የአሜሪካ መንግሥት በሚከተለው ዘዴ ከነጭ ዘረኞቹ የተሻለ አይሆንም ነበር፤ ስለዚህም ነጭ ዘረኞችን ለመቋቋም የሚወሰደው አርምጃ አሜሪካ የነጻነት አገር መሆኑን ሳይሽርና ነጭ ዘረኞቹም እምነታቸውን የመግለጽ መብታቸው ሳይደፈጠጥ መሆን አለበት፤ የነጻነት ትርጉሙ ይህ ብቻ ነው”

  ስለዚህች አንቀጽ እጅግ በጣም አድርጌ አመሰግንዎታለሁ:: በአንድ አገር ውስጥ ተቻችሎ መኖር የሚቻለው ጽንፈኛ እምነትና አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎችንም ቢሆን በመጨፍለቅ ሳይሆን “አሳባቸውን የመግለጽ መብታቸው ሳይደፈጠጥ” መሆን አለበት በጣም ክቡር የሆነ አመለካከት ነው:: ቢሆንልን ይህቺ አሳብ በኢትዮጵያችን ብትለማ, ብስትፋፋ, ብትንሰራፋ እንዴት ውብ ነበረ! እድሜና ጤና የሰጠዎት አምላክ ይክበር ይመስገን!

 4. Pingback: መርዝ ከውጭ ይረጫል ወይም ከውስጥ ይመነጫል | netsanetforethiopia

 5. Pingback: መርዝ ከውጭ ይረጫል ወይም ከውስጥ ይመነጫል | EthioSun

 6. Pingback: መርዝ ከውጭ ይረጫል ወይም ከውስጥ ይመነጫል | National Affair

 7. Pingback: መርዝ ከውጭ ይረጫል ወይም ከውስጥ ይመነጫል | National Affair

 8. Pingback: መርዝ ከውጭ ይረጫል ወይም ከውስጥ ይመነጫል

 9. Lila says:

  በእውነት እንደታላቅ ወንድም ጋሽዬ፤ እንደአባትም አባብዬ፤ እንደምሁርም ፕሮፌሰር ብልህ የማላፍርብህ የእድሜ ጸጋውን ሰጥቶህ እኔ ላለሁበት ዘመን ላደረሰህ ጋሽ መሥፍን፤ አጠር አጠር ባሉ ቃላት ነገር ግን የረጅሙን የ100 ዓመታትን ታሪክ ቅልብጭ አድርገህ እንደፊልም ትእይንት አሳየኸኝ። ዛሬ ላይ አብረኸን ስላለህ የድካምህን ዋጋ ሳናውቀው የተረት ልጆች ሆነን ተረት ብቻ ከኅሊናችን ተከትቦ ድካምህ ባይታየንም ምሁር ካለፈ በኋላ እንደለመድነው ሁሉ ኖረንበት ያልተቀበለውን ሙያና ክብር ለማንገስ እንደሩጫችን ለወሬ የሚቀድመን እንደሌለ ያለፈው ኋላችን ይመሰክርብናል። ጋሼ መሥፍን የምሁርነት ጥግ ግድግዳ ላይ በሚሰቀል የድግሪ ባጅ እንዳማይለካ በአንተ አይተናል። ብዙ ወዳጅ እንዳፈራህ ሁሉ፤ ጠላቶችንም ያፈላብህ ያንን በዘመናት ጥረት ያካበትከውን ማእረግ ከግድግዳ ላይ ሰቅለህ እዚህ አስኳላ ገብቼ እንዲህ ተሸልሜ እያልክ እንደሱቅ በደረቴ ለዝና ሽያጭ ሳታቀርብ ብእርህን መዝዘህ በወረቀት ሰሌዳ ላይ ሻጥ እያደረግህ ስለምትወጋቸው እንጂ አንተ ከእነሱ የከፋ ሰው ሆነህ አይደለም። ፈጣሩ ,ደጉ የማይሰጡህን እድሜ ቸሮህ የኑሮ መጽሐፋችን ሆነህ እነሆ እናነብሃለን። እድሜና ጤና እግዚአብሔር ይስጥህ። የማታውቀኝ የማውቅህ የዚህ ዘመን ልጅ ነኝ!!!!!

 10. bati says:

  ይህ በሃይማኖቶች ላይ የተጀመረው ዘመቻ ውጤት ይኖረዋል፤ ውጤቱ በአገዛዙ የውስጥም ሆነ የውጭ አመራሩ ላይ ከባድ ተጽእኖ ይኖረዋል፤ የሃይማኖቶቹ ጉዳይ እንደጎሣዎች መከታተፍ በኑሮ ላይ ብቻ ጫናውን የሚያሳርፍና በምድር የሚንከላወስ አይደለም፤ ወደሰማይ ያርጋል፤ የሰማይ ሠራዊትን ይጠራል፤ ያንን ኃይል እንኳን የኢትዮጵያ የጦር ኃይልና የአሜሪካውም አይችለውም፤ ዓይን ያለው ያያል፤ ጆሮ ያለው ይሰማል፤ ልብ ያለው ያስተውላል፤ ዶላር ነፍስን አይገዛም፤ ክብርን አይገዛም፤ ወዳጅንም አይገዛም፡፡

 11. ዳንኤል says:

  “የነጻነትና የሕጋዊነት መክሸፍ የሰላም ጠንቅ ነው፤ የሰላም መክሸፍ የልማት ጠንቅ ነው፤ የልማት መክሸፍ ደሀነት ነው፤ ደሀነት የሞት አፋፍ ነው፤ ይህንን ለመገንዘብ የሚያዳግተው ሃያ አንድ ዓመት የሞላው ሰው አለ? ” እድሜዎትን ያርዝምልን ፕሮ…..ምነ እናት ኢትዮጵያ እንደርስዎ ያሉ ሰዎችን አብዝታ ብትሰጠን፡አልሆነም!!ሙህር ተብየውም በየቤቱ ተወሽቆ ያላመነበት ሰራ ይሰራል፣አይቶ እንዳላየ ያልፋን ወይም ተመሳስሎ ይኖራል…ምን ያደርጋል ከላይ ስሙ ያልተጠቀሰውስሙንም ለመግለጽ ድፍረት የሌለው)…አንብቦ እንኳን መረዳት የማይችል ቅል እራስ…በልቶ አደር እና አስመሳይ የሆነውን ዳንኤል ክብረት የሚባል ጭራቅ ለአገራችን ትልቅ ፋይዳ ካለው ሰው ጋር ያወዳድራል…እስቲ ይቅር ይበለን እሱ አንድየ!!!!!!!!

  • Amare says:

   @Daneal kum negeregna meslehegn neber sitijemir.bemecheresha gin antem kil ras honeh tegegneh. D/N Daneal Kibret Chirak , belto ader sayhon be ethiopia andinet yemiyamin ,sile ethiopia andinet yemitsif lik new. Tsihufochune silalanebebikachew batitechew melkam new.

 12. elias says:

  አመሰግናለሁ ጋሼ መስፍን የሃገሮች እመቤት የነበረችዉ የኢትዮጵያ አምላክ ይጠብቅዎ!

 13. hyder zeediogenes says:

  እስማማለሁ፣በኢትዮጵያ ረጅም የመኖር የጊዜ ሂደት ውስጥ ጎል ቶ የሚታየውና ለመንግስቱ ማዕከላዊ ግዛት መጠናከርና ማህበረሰባዊ አደረጃጀቱን ፈር ለማስያዝ ሃይማኖት ከሌሎች ተቃማት ግንባር ቀደም ሚና እንደተጫወተች እይካድም፣ ለዚያም ነዉ ጥንት ነጮቹ ከሩቅ ማዶ ካለው አድማስ ጫፍ ላይ ሃይማኖታዊት ሃገርና ጥቅማዊ ዳሰሳ ሲያካሄዱ የኖሩት።አረቦቹም ቢሆኑ እስከ ቅርቡ ሙሃመድ ሲያድባሬ ና ኢሳያስ አወቄ የራስ አስተዳደር፣ከኤርትራ ጀርባ ተፈናጠው የጦር መሳሪያ እገዛ ለማድረጋቸው ከባድሜ የህዝብ ድል ማግስት የመከኑ ፈንጆች ስሬት ምስክር ነው።ይህን እንደ መነሻ ካልሁ፣አሁን ወዳለው ወቅታዊ ና ምን አልባትም አስፈሪ ሁኔታ ስመጣ፣ለኔ የታዩኝ ድንጋጤዎችን ከሃገሬ ብዥታና ካለማቀፋዊ ከስተቶች አንጻር የሚከተሉት ጠያቄዎች ውስጤ ላይ አሉ።
  ፩. መንግስት ለምን ገለልተኛ መሆን አቃተው?
  ፪. መንግስት ገለልተኛ ለመሆኑና አለመሆኑ በመንግስት ባለስልጣናት ና ተሻሚዎች የሚነገሩ አመላካቾች ምንን ያመለክታሉ?
  ፫. የመንግስት አሽባሪነት ትርጉም ከራስ ወይስ ከህዝብ ጥቅም አንጻር?
  ፬. የተዳከመው የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ማጉረምረም እንዳለ ሆኖ አሁን በመካህይድ ላይ ያለው የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄ ቢመለስ ቀጣዩ ጉዞ ምን ሊሆን ይችላል?
  ፭ .ማንም ሊነግርን ካልፈለገዉና ታሪካዊ ስተት ከተባለለትና ከመንግስቱ ሃ ማሪያሙ ደርግ ሰነድ ከሚያትተዉ የሁለቱም አደሃሪያን ሃይማኖቶች ማጋጨት ቅያሴ አንጻር ሲታይ መጠርጠሩ ጥሩ ሆኖ አሁን በማሊ፣ግብጽና ቱኒስያ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ እኛን ስላለመንካቱ ምን ማረጋገጫ አለ ብየ እጠይቃለሁ።በመሆኑም፣ በሃይማኖትና የመንግስት መለያየት ስም ድንኻን ዉስጥ አድፍጦ ያለ መንግስት ሁለቱንም ሃይማኖቶች ለማላተም ጉልበት የለውም ብየ አላስብም ከዚህ በተጨማሪ፣እነዚህን ሃይማኖቶች በማቻቻልና መማቀራረብ ጽኑ በሆነው እሴታቸው ላይ ማቅ የሚነሰንሱ ሽረኞችን ተው የሚልና ሃገራዊ ብዥታ ባለው ይህ ትውልድ በሃይማኖት ስም ከሚሰራ ደባ ግንዛቤ ሊሰጠው የሚችል፣ መንግስታዊ ያልሆነም ይሁን የሆነ ፣በጎ አድራጊ ያለመኖሩ ሲታይ እኔም እንደርስውዎ እፈራለሁ።
  ለርስዎ ጤና ና እድሜ እመኛለሁ። በተረፈ መክሽፍ በሚለው መጽሃፍዎ የሰጡትን የርስዎ መልስ እንደሚጽፉ ተስፋ አደርጋለሁ። ቻው።

 14. TebejeMM says:

  Ageritu teqamochua bemulu shiba tedergewu ye ande budn agelgay behonuber bezih kifu zemen ersewon yemesele le ewunet yemikom bayinor yene tiwul min yiwutewu neber? Egizabher edmewon yarzimiln.

 15. Mesfin Hailemariam says:

  ከእርስዎ ‘’ምሁራዊ” ስድብ ይልቅ የዳንኤል ክብረት ጨዋዊ “ማህይምነት” በእጅጉ ይሻላል፡፡ ብዙ ሰው ሳይመርዙ አምላክ ተሎ በጠራዎት- ግና እንዲህ በጥላቻ የተሞላ ምን ያደርግልኝ ብሎ!

  • binyam says:

   ይህ የሰጠኃዉ አስተያየት ምን አየነት ሰዉ እንደሆንክ የሚያሳይ ነዉ፡፡አንተ እራስህ ከጥላቻ ያልወጣህ ግለሰብ መሆንህን ነዉ የሚያሳየዉ፡፡ ፕሮፌሰሩን ልናከብራቸዉ ይገባል፡፡ ምክኒያቱም ለዚች ሀገር የቻሉትን ያህል ያበረከቱ ያገር ፍቅር መቸዉንም ተለይቷቸዉ ያላየናቸዉ ናቸዉ፡፡ አሁን በ85 አመታቸዉ እንኳን ሳይቀር ከህይወታቸዉ የተማሩትን ለቀጣዩ ትዉልድ በጽኁፍ ትተዉ ለማለፈፍ የማይደክሙ ናቸዉ፡፡ ስለዚህ ከበስተጀርባህ ያለዉን ተወዉና እንደ አንድ አገሩን እንደሚወድ እትዮጵያወዊ አሰስተያየት መስጠት ነዉ የሚሻለዉ፡፡ በርግጥ ፕሮፌሰሩ ስሜታዊ ሆነዉ ምላሽ መስጠታቸዉን ታዝቤያለሁ ነገር ግን እንደዚያ ስሜታዊ ያደረጋቸዉ የዳንኤልም ጽሁፍ ነቆራ የታከለበት ስለሆነ ይመስለኛል፡፡

  • Haile says:

   ጌታው አትሳሳት፤ ብዙ ሰውን ይመርዛሉ ያላቸውን አምላክ ጠርቶአል ፤ ጭፍን ጥላቻህን ትተህ ከህሊናህ ጋር ተመካከር እውነትን እውነት ነው ብለህ ተቀበል ። ያኔ ሰው ወደመሆን የሚወስደውን መንገድ እንዳገኘኸው አስብ፤ ቀጥሎ ደግሞ ለህሊናህና ለእውነት ራስክን አሳልፈህ መስጠት ስትጀምር (ልክ የተከበሩ ፕሮፌሰር መስፍን እንደሚያደርጉት ማለቴ ነው ) ፊደል ብትቆጥርም ባትቆጥርም ችግር የለውም ቢያንስ ለህሊናህ ተገዥ በመሆንህ ሰው የሚለውን መስፈርት ማሙኣላት ትችላለህ ። ካልሆነ ግን ራስክን ባታስገምት ጥሩ ነው ኢንተርኔትና አግዳሚ ወንበር ሁሉንም እኩል ያደርጋል ብለህ የመጣልህን አትናገር።

  • zelalemawi says:

   “ጨዋዊ መሃይመነት በእጅጉ ይሻላል” ነው ያልከው? ከጨዋ መሃይም ምን ትጠብቃለህ… ደፋር ምሁር ግን ያሰበውን ቢናገር ይበጀናል! በየትኛውም የሰው ልጅ ሥልጣኔ ውስጥ “ጨዋ መሃይማን” አይደሉም የለውጥ እሳት የሚለኩሱት:: አፈንጋጭ የሆኑ ሰዎች ናቸው ለለውጥ መነሻ አሳብ የሚሆኑት:: በባህልና በህብረተሰብ ልማድ የተቀመጠላቸውን ድንበር አንቀበልም ያሉ ሰዎች ናቸው ለውጥን የሚያመጡ! እኔስ ከመሃይም ደብተራ ብዕር የሚመነጭን ፍሬቢሰ ተረት ከምሰማ ይልቅ; ከፕሮፌሰር መስፍን ብዕር የሚፈልቀውን የተንኳሽ ብዕር ጠብታ ማንበብ ይሻለኛል… በአሳባቸው ባልስማማ እንኳ… “ከለዛዛ መሃይም ደብተራ” ይልቅ ተንኳሹ ፕሮፌሰር ይመቹኛል!

   ምድረ ደንባራ አዋቂ ነኝ ባይ ደብተራ መስሎኝ ኢትዮጵያን ከሥልጣኔ ራስነት የሥልጣኔ ጭራ እንድትሆን ያደረሳት! ሳይማር, ሳያነብብ እና ሳይመራመር ራሱን ምሁር ነኝ ብሎ የሾመ ደብተራ መስሎኝ ህዝባችንን የችጋር ምሳሌ እንዲሆን ያደረገው! በ21ኛው ክፍለዘመን እነዚህን በሆዳቸው የሚያስቡ ደብተራዎች ስፍራቸውን ማስያዝ ይገባል! እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ሃይ ባይ ሲጠፋ ደብተራ ምድሪቱን የመሃይምነት ጨለማ ውስጥ ይከትታታል!

 16. ነፃነት አሸናፊ says:

  “ይህ በሃይማኖቶች ላይ የተጀመረው ዘመቻ ውጤት ይኖረዋል:: በምድር የሚንከላወስ አይደለም፤ ወደሰማይ ያርጋል!!! የሰማይ ሠራዊትን ይጠራል::!!!!”
  ይህቺን አባባል ስንፈታት……… ወያኔዎች ሆይ ጥጋባችሁ ከሰው አልፎ አልፎ እጅግ አልፎ አንገታችሁ ደርሶ ቀና አድጉዋችሃል፡፡ አንጋጣችሁ መዳፈር ጀምራችሁዋል፡፡ እግዚአብሔር በክብሩ አይደራደርም፡፡ ማንንም አይፈራምም፡፡ ልጆቹን ሊታደግ ይመጣል፡፡…… ማለት ነው፡፡ ኧረ አሜን!!!
  ጆሮ ያለው ይስማ……..
  ወገኖቼ- እኛ ደግሞ በቀናነት ትዕግስት ፍቅር እና መረዳዳት ነብስ ትውልድ ሀገር ለመታደግ በአንድነት እንነሳ!!!! የክብር አምላክ እግዚአብሔር ከላይ ሀይል ያስታጥቀናል፡፡
  ጋሼ መስፍን እግዚአብሔር እድሜና ጤና ይስጥልኝ፡፡

 17. Madeinchina says:

  የፕሮፌሰር መጽሐፍ ብታንስም እውነት ናት

  ፕርፌሰር መስፍን ወ/ማርያም “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” የሚል ከደረቅ እውነቶች ፊት የቆመ# በይልኝታ ያልተሸረበ#በጥቅም ያልተኮማተረ# በፍርሃት ያልተሸበበ#……… መጽሐፍ ጽፈው አስነበቡን ፡፡ ዕውነት ለመናገር በትንሹ ከማንበብ በስተቀር መጣጥፍ ጽፌ ወይም አስተያየት ሰጥቼ አላውቅም ይህ የመጀመሪያዬ ነው፡፡እኒህ ያገር አጉማስ የሊቃውንት አድባር እንኳንስ የሚጽፉትን አንብቤ የሚናገሩትን አድምጬ ይቅርና ከነሙሉ ኢትዮጵያዊ ክብራቸው\ ከነሙሉ መንፈሳዊና አካላዊ ጥንካረያቸው በመጽሔቶች ላይ ፎቶግራፋቸውን ስመለከት የመልካም ኩሩ ዜጋ ብሐራዊ ስሜት እየተሰማኝ ክፉን ከዕርሳቸው አርቅ ስል እመኛለሁ፡፡
  ይህ መጽሐፍ ድብቅ እውነቶችን ያወጋኝ#የአገሬን ታሪክ ከነጉድፉ የጀመረልኝ#ጥያቄዎቼን የጠየቀልኝ ስለመሰለኝ እነሆ ስሜቴን ልገልጽ ነው፡፡ እርሳቸው ……… ደልቶት የሞቀው የረጋ መንፈሱን እንዳይረብሽ መጽሐፌን አያንብበው እንዳሉት እኔም በቅን ልቦና የሚወደኝ ጥላቻን እንዳይገዛብኝ የእርሳቸውን መጽሐፍ ማንበብ የጠላ የእኔን አስተያየት ባያነበው ወዳጄ ነው፡፡ በጥንታዊት ኢትዮጵያ ህዝቦቿ እውቀት አፍላቂ የስልጣኔ ምንጭ ስመ ገናና እንደበሩ አሳይተውን በቅርቡ ዘመን ታሪካችን ግን ልጆቿ እውቀት ተቀባይ እውነትን ሳይሆን የተቀበልነውን ተራኪ ለውስጣችን ሳይሆን ለውጭ ያደርን አርጋጅ አጎንባሽ መሆናችንን ስም እየጠሩ ጊዜ እየቆጠሩ የምሁሮቻችንን ክሽፈት የነጋሲዎቻችንን ለሥልጣኔ’ ያልሆነች ኢትዮጵያ ባይነት የሃይማኖት አባቶቻችንን ሀብተ ሥጋ ወዳድነት የሚያቅለሸልሹ እውነቶች እያሉ በማስረጃ አረዱን፡፡ ግን ደግሞ ፈራ ተባ እያሉ ይሁን ሆነ ብለው ጠይቀህ መርምረህ ተረዳ ለማለት የሚያቅለሸልሹ ብቻ ሳይሆን የሚያስመልሱ እውነቶች እንዳሉ አይተው እንዳላዩ ስምተው እንዳልሰሙ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ለምሳሌ በአምስቱ ዓመት የተጋድሎ ዘመን ለጣሊያን ባንዳ የነበሩ ከነጻነት መልስ ግን የኃ/ሥላሴ ሹማምንት ለመሆን ከበቁትም ከተወነጀሉትም መካከል የቄሳር ጋዜጣ አዘጋጅ የነበሩት አፈወርቅ ገ/እየሱስ ብንጠቅስ የእኝህ ሰው ባንዳነት ትልቁን የጽናትና የመስዋዕትነት ተምሳሌት# ትልቁን የሞራል አርአያ አቡነ ጴጥሮስን “ህዝቡን አታስጨርስ ህዝብ ሊያሰለጥን አገር ሊያቀና የመጣ ገናና የስልጣኔ መንግሥት ነውና ለጣሊያን መንግሥት እደር ገዝቸሃለሁው” ያሉትን የሃይማኖት አባት ጉድፍ በምንም መልኩ አይወዳደርም፡፡ በዳኝነት ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ ለከንቱ ውዳሴና ለእንጀራ መቁረሻማ ስንቱ ባንዳ ነው የፍርድ (የችሎት) ውሳኔ እየተባለ የጀግና ወንድሞቹን አንገት በገመድ ያንጠለጠለ አናታቸውን በጥይት ያስተረተረ፡ ይሄ ተግባር እኮ በንጉሱም በደርግም የነበረ ዛሬም የዳበረ የብዙ ኢትየዮጵያውያን ወራዳ ሥራ ነው፡፡ በላይፍ መጽሔት ላይ የእገሌ አባት የመሐል ዳኛ ሆነው አቡነ ጴጥሮስ ላይ ፈርደዋል ይባላል ግን ማስረጃ አጥሯል ስላሉ ነው፡፡ አይደረግም ብለው ነው? ከየት ይለመዳል ከአያት ቅድመ አያት ነው እንጂ፣ እንዲህ ያለው ጽዩፍ ሥራ በዛሬው ዘመን ነውርነቱ ቀርቶ ተቀባይነት ያገኘና የሚያኮራ ሥራ የሆነ ይመስላል፡፡
  በማስረጃ የተረጋገጠ#ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የተደራጀ የታሪክ እውነት ለትውልድ ባለመተላለፉ ሳይሆን አይቀርም በየዘመኑ ብቅ በሚሉ ምሁራን መካከል በዘር ላይ ያጠነጠነ የታሪክና የእውነትነት እሰጥ አገባ ትርምስ የሚከሰተው፣፣ ለምሳሌም ያህል ከቀደምቶቹ ነጋድራስ ገ/ህይወት ባይከዳኝና ነጋድራስ አፈወርቅ ገ/እየሱስ
  ፕሮፌሰር መጽሐፉን በታተመበት ዘመን ወይም ወቅት እንዳልጻፉት ከውስጡ ባሉት መቼቶችና የግርጌ ማስታወሻዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡ምንአልባት ቀደም ብለው ቢጽፉትም የሚያስመልሱ የአሁኑን ዘመን እውነቶች እየጨመሩ ቢከልሱት ኖሮ መጠኑም እየጨመረ እንዳሉትም የተረጋገጡ እውነቶች ለትውልድ የሚተላለፉበት የታሪክ መማሪያ ዋጋነቱ የበለጠ ይሆን ነበረ የሚል ምኞት አለኝ፡፡ ለምን የአንተን ሳትወጣ ይህን ትመኛለህ እንደማይሉኝ ተስፋ አለኝ አቅመ ውሱንነቴና እጥረቴ አያወጣኝምና፡፡ የምኞቴ መሰረት የሚሆነው በእኛ ዘንድ በተገለጠ እውነት ተደፋፍኖ የተረጋገጠ እውነት እጥረት በመብዛቱ ታሪካችን ሁልግዜም በነበረው ላይ ከመጨመር ይልቅ የነበረውን አፍርሶ አዲስ መጀመርና ያለፈውን መውቀስ አዳብረናል፡ የአሁኑ ለራሱ ጥፋት እንኳን ያለፉትን መውቀስ ትልቁ ጥበቡ አድርጎታል፡፡ ታሪካችን በተጠኑ የታሪክ እውነቶች ላይ መመርኮዝ አለበት፡፡
  ለምሳሌ፡- በአምስት ዓመቱ የአርበኝነት ዘመን በኋላ ባንዳ የነበሩ ሹማምንት ልጆችና ቤተሰቦች ምንያህል ለአገራቸው በጎ አስተዋጽኦ አበረከቱ? የባንዳነቱ ተጽዕኖ አድሮባቸውስ ምንያህል አሉታዊ ሆኑ? የሚለው ቢጠና መጭውን ትውልድ አያስተምርም? በነገራችን ላይ ይህን ሃሳብ በተመለከተ አንድ ነገር ላንሳ! ነፍሳቸውን ይማረውና ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ባንዳው አያታቸው ኢትዮጵያን# ኢትዮጵያዊነትንና ሰንደቅ ዓላማዋን የመጥላት ተጽዕኖ ሳያሳደሩባቸው ቀሩ ብላችሁ ነው? ለዚህም ይመስለኛል የቺሩሊን (የጣሊያንን) ውጥን በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ሀገረ -መንግሥት ሽንሸና ከፍጻሜ ያደረሱት ያለበለዚያማ ከየት አመጡት ሌኒንም#ስታሊንም#ማኦም የሚጠሉት ሊብራሊዝምም ቋንቋ የህዝቦች ድንበር ይሁን አላሉም ከቺሩሊ በስተቀር፡፡ የጣሊያንን ምስራቅ አፍሪካ (Africa Orientale Italiana, or AOI) ካርታ ከአሁኑ የወያኔ የቋንቋ አሸናሸን (ክልል)ጋር አንባቢ ማነጻጸር ይችል ዘንድ በመጽሐፉ ከተካተቱት ካርታዎች ጋር ቢያካትቱት ኖሮ አስተማሪነቱ የጎላ ነበር፡፡በተገለጠ እውነት ተሸፋፍነው ሲያስፈልግ ለመቀስቀሸሻ ሲያስፈልግ ለመውቀሻ ሲያስፈልግ ለማደንዘዣ ከሚውሉት ያልተጣሩ ጉዳየዮች መካከል ፣-
  • አጼ ዮሐንስ ወደመተማ ከመዝመታቸው በፊት በሸዋው ሚኒሊክ# በጎጃሙ ተ/ሃይማኖትና በእርሳቸው መካከል የነበረው የመልካም ወይም የቁርሾ ግንኙነትና ለመተማ ውድቀት የነበረው ድርሻ፡
  • ሰሎሞናዊው ስርወ-ንግሥና ለአማራው ወይም ለሌላው አይገባውም የተቀባ አይደለም ስለሚለው አክሱማዊ ተምቤናዊ ትግሬያዊ የተገለጠ እውነት\ በትረ ሥልጣኑ በመዛነፉ ኢትዮጵያ ያልረጋች ሆነች ኢሰሜናዊ በሆኑ ህዝቦቿ እጅ የሥልጣኑ አልጋ በመውደቁ አገሪቱ ባሕር በር አልባና ለዛሬው ምስቅልቅል አስተዳደር ዳረጓት አሁን ወደ ጥንት ባለ እጆታዎቿ በመመለሷ ስልጣኔዋ አበበ ህዝቦቿ በለጸጉ ስለሚለው አደናጋሪ የውስጥ ለውስጥ የተገለጠ እውነት
  • በሶማሊያና በሌሎች የዘመናት ጠላቶቿ ፓስፖርት በመጠቀም ከበረከት ኃ/ስላሴ ባለፈ ሌሎች ከስልጣን በላይ ምንም የለም በሚል አገራቸውን የከዱ ዳር ድንበሯን የሸጡ የሸቀጡ\ ለስልጣን ካበቃችሁን ኢትዮጵያን አረባዊ እናደርጋታለን ሲሉ ከነጋዳፊ ዙፋን ሥር የተንበረከኩ\ ለተራበው ህዝባቸው የተለገሳቸውን የጠኔ ማስታገሻ እህል እያዟዟሩ የሸጡ # ባገኙት ገንዘብ ለሥልጣን በሚደረግ ጦርነት የጦር መሣሪያ የገዙ\ በአደባባይ በይፋ ለባለጋራ ለተሰጠ የአገራችን ክፋይ መሬት ህዝባቸውን እልል በሉ አደባባይ ውጡ በማለት የቀለዱ…….. ለስልጣን ለሃብት ሲሉ የሸፈጡ በቂም በእልህ በጥላቻ የነሳስተው ገናናውን የሃገራቸውን ታሪክ የረገሙ ያኮሰሱ ኢትዮጵያውን እውነት ከማቅለሽለሽ አልፎ አያስመልስም? ነው ወይስ የዚህ ዘመን ሸፍጦች ሁሉ በታሪክ ይመርመሩ በሚል የተተወ፡፡በእኔ እምነት የመጽሐፉ ዓላማ የተረጋገጠ እውነት ለትውልድ ለማጋራትና ሌላው እንዲጨመርበት በመሆኑ እንዲህ ዓይነት እውነቶች ተመርምረው ተጨምረውበት ቢሆን በታሪክ ውድነቱን አይጨረውም ነበር?
  • በኃ/ስላሴ#በዘውዲቱ #በእያሱ መከካከል ተዳፍነው የቀሩ እውነቶች……..
  • ለመጽሐፋቸው ንዑስ ርዕስ ያደረጉት፡-
  ኢትዮጵያ ሃገሬ ሞኝነሽ ተላላ
  የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ
  የሚለው ግጥም በእርግጥ የዮፍታሔ ንጉሴ አይደለም?
  ከላይ በግርድፍ ያነሰኋቸው ሃሳቦች ፕሮፌሰር በመጽሐፋቸው ገጽ 199 ላይ አንስተው በእንጥልጥል ከተዋቸው የብዙውን ሰው አእምሮ ከሚቆጠቁጡ ያልጣሩ እውነቶችና ሌሎች ያልተነካኩ የተገለጡ እውነቶችን አካትተውና ጨማምረው በሌላ መጽሃፍ እናነባቸው ይሆን ከሚል ቀና ምኞት የመነጨ እንጂ ለመንቀፍና ለመተቸት ቅንጣት ታክል እንኳን እንዳልሆነ አንባቢ ሁሉ ይረዳልኝ፡፡
  ፕሮፌሰር በብዙ ጽሑፎቻቸው ላይ እንደሚገልጹት በዚህ መጽሐፍም ታሪካችን “ማሰብ ክልክል ነው” በሚል ዓይነት በታሰረ የሰዎች ህሊና ከማሰብ ከማሰላሰል ርቆ የተሰጠውን ብቻ የሚቀበል አእምሮ ስንገነባ መኖራችንን ልብ ላለው ልብ ይላል፡፡ በአሁነኑ ዘመን ከዚህ አላለፈም ብለው ነው? ጥንትስ ባደበባባይ “ማሰብ ክልክል ነው” ቢባልም ሰው በቤቱ በጓዳው በነጻ ህሊናው ከፈጣሪ በታች ነገሥታቱን ያማ ነበር፡፡አሁን አሁንማ የተሰጠን አዋጅ መቼ “ማሰብ ክልክል ነው” በሚል አበቃ ህሊናችን # ማሰቢያችን ታሽጓል የሚል ማኅተም ታተመበት እንጂ\ የአእምሮሯችን ጓዳ በቁልፍ ተከረቸመ እንጂ\ ማሰላሰያችን ተለጎመብን እንጂ እንዲያው በጥቅሉ አዋጁ ጠበቀብን እንጂ መች ላላልን፡፡ማኅማችን ጥርነፋ ነው\ ቁልፋችን አንድ ለአምስት ነው \ ልጓማችን ግምገማ ነው፡፡
  ታሽገን እንዳንቀር ተቆልፎብን እንዳንዝግ ተለጉመን እንዳንዝል እናንተን ማስተንፈሻ እናንተን ማስታገሻ አገኘን ሳይደግሥ አይጣላም ይባል ይሆን! እናንተ ለእኛ ጭንቅ ሲበዛ መፈናፈኛዎቻችን እውነት ሲጠፋ መባዘኛዎቻችን በድቅድቅ ጨለማ ማጮለቂያዎቻችን ናችሁ፡፡ አሁን አሁን የቃሊቲው ወሳጅ መፈናፈኛችንን እያጠበበ መባዘኛችንን እየለቀመ ማጮለቂያችንን እየደፈነ በዝምታ እንደወጠረን አካለችንን እንዳገረረው ህሊናችንን እንደሰበረው በእኩይ ምግባሩ እንደተጋ ነው፡፡ እኛስ መፈናፈኛው ሲጠፋ መሰናዘሪያው ሲያከትም እንደበርሜሉ እንፈነዳ እንደ ፊኛው እንተረተር ይሆን? ማን ያውቃል? ለማንኛውም አሁን እናንተ ለእኛ እስካሪኮ ናችሁ ማስተንፈሻ፡፡

Comments are closed.