የብርሃኑ ደቦጭ የምኞት ትችት

(ልዕልና  ጋዜጣ)

 መስፍን ወልደ ማርያም

መጋቢት 2005

       ብርሃኑ ደቦጭ (የታሪክ ተመራማሪ) ስለመክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ ለመተቸት ተነሣና እሱን ሲያጉላላው የቆየውን ነገር ሁሉ ጻፈ፤ እንዲያውም ገና ሲጀምር ስለመክሸፍ ያለበትን ሁሉ አልነካውም በማለት ይናገራል፤ መጽሐፉ ስለመክሸፍ ነው፤ ብርሃኑ ደቦጭ የመክሸፍን ነገር አይወደውም ይመስለኛል፤ ስለዚህ ለምን አልተወውም? መጽሐፉን ትቶ ወደኔ! እኔን ሲደቁሰኝ ቢውል እንደመክሸፍ አልጠጥርበትም! እንግሊዝኛን በአማርኛ ፊደል መጻፍ የሚችል መሆኑን አወቅሁለት።

መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክን ብርሃኑ ደቦጭ የተጠቀመበት በአእምሮው ውስጥ መውጫ አጥተው ሲጉላሉ የነበሩ ሌሎች በጭራሽ ያልተያያዙ ቅንጭብጫቢዎችን ለመዘርገፊያ አጋጣሚ ማግኘቱ ይመስላል፤ የጠቃቀሳቸውንም ነገሮች ፍሬ-ነገራቸውን አልነገረንም፤ በዚህ ዓይነት ጽሑፍም ሊነግረን አይችልም፤ ፍሬ-ነገሩን ሊነግረን ያልቻለውን ነገር እያነሣ ማለፍ ብቻ እውቀትን አይጨምርም፤ እንዲያውም የአስመሳይነት ስሐተት ውስጥ ይከታል፤ ለምሳሌ እኔን ‹‹በማርክሲስት የሚያስፈርጀውን ገጽታ ይላበሱና …›› ይላል፤ አሁን ይህ ለምን ያገለግላል? ከየት አምጥቶ ነው የሚለጥፍብኝ? ተልእኮው ያነጣጠረው በመጽሐፉ ላይ እንዳልሆነ የሚያሳዩ ብዙ እንደዚህ ዓይነት ምልክቶች አሉ፤ ይኸው ይበቃኛል።

 1. የደርግ የጽሑፍ ተቆጣጣሪ (በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅና በለንደን ታሪክ የተማረ የታሪክ ተመራማሪ ካድሬ ነበር) አሁን ለትችት በቀረበውና ባልተተቸው መጽሐፍ ረቂቅ ላይ ‹‹የቷ ኢትዮጵያ? የማን ኢትዮጵያ?…) እያለ ጽፎ እንዳይታተም ከለከለ፤ ዛሬ ደግሞ ብርሃኑ ደቦጭ መጽሐፉ ከታተመ በኋላ ‹‹የመስፍን ኢትዮጵያ›› ብሎ ለጠፈባት! ‹‹በመጽሐፉ ከተነሡት ጉዳዮች  የክሽፈት ታሪክ ስለተባሉት ጉዳዮች፣ የአርበኞችና የባንዳ ሚና ታሪክ አዘጋገብ እና የአድዋ-ማይጨው-ጅጅጋ ትርክት በዚህ አስተያት ያልተካተቱ መሆናቸውን ከወዲሁ መግለጽ እወዳለሁ፤..›› ያልተመቸውን እየተወና የፈለገውን እየለወጠና እያጎበጠ ስለመጽሐፉ መተቸት ምን የሚሉት አዲስ ፈሊጥ ነው?
 2. እንደተማረው የተለያዩ የርእዮተ-ዓለማዊ አመለካከቶችን ስሞች ጠቅሶ የእኔ መጽሐፍ አንዱም ውስጥ አልገባልህም ስላለው አልተመቸውም።
 3. ከክብረ ነገሥት የተጠቀሰው ብርሃኑ ደቦጭን አላስደሰተውም፤ ምናልባትም ጊዜው ያለፈበት ብሎ ይሆናል፤ ጊዜ ስላለፈባቸው መጻሕፍት በሌላም ቦታ ተናግሮአል፤  የመስፍን አዲሱ መንገድ  ‹‹በብዙ መልኩ ጊዜ ያለፈባቸው መጻሕፍት›› መጥቀስ ነው ይላል፤ መጻሕፍት፣ በተለይም የታሪክ ፍልስፍና መጻሕፍት ጊዜ የሚያልፍባቸው እንዴት ነው? የብርሃኑ ቸግር ስለሁነት ያነበበውን ስለአስተሳሰብ፣ ስለአመለካከት ያደርገዋል፤ ምናልባት በፊዚክስ ጊዜው ያለፈ መጽሐፍ ሊኖር ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን የቶይንቢ ‹‹የታሪክ ጥናት›› የተሰኙትና ሌሎችም ጊዜያቸው መቼም አያልፍም፤ የመጻሕፍትን ባሕርይና ዋጋ ለፈተና ከመጥቀማቸው ውጭ ማየት ካልተቻለ የብርሃኑ አመለካከት በዓለም ያሉ ቤተ መጻሕፍትን ያራቁታል፤  በኋላ የተነገረው የተሻለ የሚባልበት ሁኔታ ስላለ በኋላ የተነገረው ሁሉ የተሻለ ነው ማለት አጉል አስተሳሰብ፣ ወይም በብርሃኑ ቋንቋ ‹‹ፋውል›› ነው።
 4. ‹‹የአንድ አገር ታሪክን ለማጥናት የአገር ተወላጅነትን ግድ የሚያደርግ››  ይህ አስተሳሰብ የኔ አይደለም፤ እሱ ለራሱ ዓላማ የደነቀረው ነው፤ እኔ ያልሁት       ‹‹…ባዕድ የሆነው የሌላ ሕዝብ ታሪክን ሲጽፍ ሁለት ምክንያቶች አሉት፤ አንዱ ለእንጀራ ነው፤ ሁለተኛው የእውቀት ፍላጎት ነው፡›› የቱ ላይ ነው ብርሃኑ ‹‹ግድ›› የሚለውን ያነበበው? ብርሃኑ ታሪክን የሚያጠናው ለእንጀራ  ብቻ መሆኑን ሳይናገር አስረዳን! እኔ ያልሁት ‹‹የውጭ ሊቃውንቱ ጥናት ልዩ ጥቅም ቢኖረውም ባይኖረውም ለራሳቸው ሲሉ የሚያደርጉትን ጥናት በጭራሽ ልንቃወም አንችልም፤ የምንቃወመው እነሱ እኛን እነሱ እንደፈለጉ አድርገው ሊቀርጹን  የሚያደርጉትን ሙከራ ነው፤ እኛም እንደጥቁር ሰሌዳ የእነሱን ነጭ ጠመኔ የባሕርይ አድርገን መቀበላችንን ነው፡፡››  ብርሃኑ ደቦጭ ይህንን የመቃወም መብት አለው፤  የራሳችን ሰዎች ብቻ መጻፍ ግዴታ ነው አላልኩም፤ ብርሃኑም እንኳን ይህንን አይልም፡፡ እንደገናም ‹‹ታሪክን ማጥናት የሚገባው የአገር ተወላጅ ብቻ ነው የሚለው አስተሳሰባቸው …›› ይላል፤ ይህንን ሐረግ በእኔ መጽሐፍ ውስጥ ላገኘ ሰው አምስት መቶ ብር እሰጣለሁ፤ የምሬን ነው! ብርሃኑ የራሱን እምነት ለማራመድ እኔን ምክንያት ያደርጋል፤  በብርሃኑ አመለካከት አንድ ስዊድናዊ ስለኢትዮጵያ ሲጽፍና ሌላው ከአንደኛው የኢትዮጵያ ጎሣ ሲጽፍ ያው ነው፤ ይህ የእሱ አመለካከት ይሆናል፤ እኔ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ጎሣዎችን ሁሉ አንድ አድርጎ የሚያመሳስላቸውና ከስዊድናዊው ወይም ከሌላው የውጭ አገር ሰው የሚለያቸው ነገር አለ ብዬ አምናለሁ፤ ይህ ለእኔ ይታየኛል፤ ለብርሃኑ አይታየውም፤ ልዩነታችን ነው።
 5. በጽሑፉ መጨረሻ ላይ ብርሃኑ ንዴቱ እየባሰበት ሄዶ ከመጽሐፉ ወጣ፤ ከመጽሐፉ ትችት ተሰናበተና ወደዘለፋ ገባ፤ ምክንያቱ አልገባኝም፤ ተለውጦአል ይለኛል፤ ለውጡን አይናገርም፤ የማያስፈልግ ሙግት፣ ከዚያም ከዚህም እየቀነጫጨበ የሚማታበት ልምጭ ይሰበስባል፤ አንዱ ስለታደሰ ታምራት የጥናት ዘመን (1270-1527) የሳትሁ አስመስሎ ወደዘለፋ የገባበት ነው፤ በትክክልና በቀና መንፈስ ላነበበ የሚከተለውን ብያለሁ፤– ‹‹ምንም እንኳን የታደሰ መጽሐፍ የጊዜ ገደቡ ቢያበቃም በመጨረሻው ምዕራፍ አጼ ምኒልክን ከአጼ ዓምደ ጽዮን ጋር በማመሳሰል በአሥራ አራተኛው ምዕተ-ዓመት ዓምደ ጽዮን ‹ክርስቲያን ኢትዮጵያን‹ እንዳስፋፋ ሁሉ ሁሉ  አጼ ምኒልክም ይህንን የመስፋፋት ተግባር ፈጸሙ ፤ … ፕሮፌሰር ታደሰ ከግራኝ ወረራ ቀደም ብሎ ዝርዝር የታሪክ ጥናቱን ከአቆመ በኋላ፣ አራት መቶ ሃምሳ ዓመት ያህል ጭው ባለ ዝምታ ዘሎ ወደአጼ ምኒልክ ዘመን ተስፈንጥሮ ይገባል፤ ይህንን ጭው ያለ የአራት መቶ ሃምሳ ዐመት የጊዜ ገደል አልተሻገረውም፤ ለዚህ ዋናው ምክንያት ታደሰ መስፋፋት በሚል ርእስ የጻፈውን ሁሉ የሚያስተባብልበት ታሪክ የሚገኘው በዝምታ ሊዘልለው በሞከረው አራት መቶ ሃምሳ ዓመት ውስጥና …›› ብርሃኑ ደቦጭም እዚያ ገደል ውስጥ ሆኖ ነው ዘለፋውን የሚያሰማው! አንድ ዓረፍተ ነገር ይዞ ለነቀፋ ከመቸኮል ሁሉም አንብቦ መገንዘብ የተሻለ ክብርን ያመጣል።
 6. ሌሎች ከባድ ከባድ የሆኑ የአገር ጉዳዮች በብርሃኑ ጽሑፎች ውስጥ አሉ፤  እነዚህ ውስጥ አልገባም፤ ዋናው ምክንያቴም ብርሃኑ እንዳለው ‹‹የመስፍን ኢትዮጵያ›› የሌሎቹ በተለይ የወጣቶቹም ካልሆነች እኔን ከሌላው ይበልጥ አይነካኝም፤ ብርሃኑ ደቦጭ ከማን ጋር ተማክሮ እንደሆነ የመጨረሻ ጥይት የሚል ውሳኔ ላይ የደረሰው አላውቅም፤ መገመት ቢችል ዝናሬ ገና ሙሉ ነው! ያለጥርጥር የብርሃኑ ደቦጭ ጽሑፍ ያነጣጠረው መጽሐፌ ላይ ሳይሆን እኔ ላይ ነው፤  ምክንያቱን አላውቅም፤ ስለዮሐንስና ስለምኒልክ ባለው ውዝግብ እኔን ወደምኒልክ ገፍቶ ከዮሐንስ ሊያርቀኝ ይሞክራል።
 7. የታሪክ ተመራማሪው ብርሃኑ ደቦጭ ርእሱን ብቻ ያመለከተውን የመጽሐፉን እምቡጥ አልነካውም፤ ወይ ደስ አላለውም፤ ወይ ግራ ገብቶታል፤  እንዲህ ያለ የመጽሐፍ ትችት አይቼም አላውቅም፤ በግድ መጻፍ አለብህ ካልተባለ በቀር ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ የሚባልለት ጽሑፍ ነው፤ ባይጽፈው ይሻለው ነበር፤ ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር ክፉኛ ይወርዳል።
Advertisements
This entry was posted in አዲስ ጽሑፎች. Bookmark the permalink.

24 Responses to የብርሃኑ ደቦጭ የምኞት ትችት

 1. የዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነውን የዶ/ር ብርሃኑ ደቦጭን ትችት ማግኘት ባለመቻላቸው ቅሬታ ያሰሙና ጥያቄ ያቀረቡ ጥቂት አይደሉም። እናመሰግናለን። ይህን ጥያቄ ለማስተናገድ ሲባል ጽሑፉን ፈልጎ በማዘጋጅት የረዱንን ግለሰብ እያመሰገንን ለሚገኝበት ግድፈት (ከተገኘ) በቅድሚያ ይቅርታ እንጠይቃለን። ጽሑፉ እነሆ፦

  የፕሮፌሰር መስፍን የመጨረሻ ጥይት/ቶች
  ቢትል ኤንቲሞሎጂ ብርሀኑ ደቦጭ (የታሪክ ተመራማሪ)
  ርዕስ፡-መክሸፍ እንድ ኢትዮጵያ ታሪክ
  ጸሐፊ፡- መስፍን ወልደ ማርያም (ፕ/ር)
  የታተመበት ዘመን፡- 2005 ዓ.ም
  ገጽ ብዛት፡-238
  ዋጋ፡- ብር 45
  የመስፍን ኢትዮጵያ ታሪክ ዕይታ ቡፌያዊ መልክና አዲስ አለመሆን
  በታወቀ ምክንያት የዛሬው መጽሐፍ ብዙ የተባለበት ሆኖ ስላገኘሁት የመጽሐፉን ይዘት በማስተዋወቅ የዓምዱን ቦታ አላጣብብም በመጽሐፍ ከተነሱት ጉዳዮች የክሽፈት ታሪክ ስለተባሉት ጉዳዮች፤የአርበኞችና የባንዳ ሚና ታሪክ አዘጋገብ እና የዓድዋ-ማይጨው- ጅጅጋ ትርክት በዚህ አስተያያት ያልተካተቱ መሆናቸውን ከወዲሁ መግለጽ እወዳለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ዕይታ የሚቃኙ የተለያዩ ኃይሉ ሃሳቦች አሉ። እነርሱም የሥልጣኔ መነሻ ትርክት (አፍሪካን ማዕከል ያደረገ “አክሱማዊ” ‘ኦሪዮንታል ሴሜቲስት’) የመቃኛ ርዕዮተ ዓለምና የትግል ዓይነት (ዘውግ ተኮር፤ መደብ ተኮር/ .ማርክሳዊ ናሺናሊስት፤ ሊበራል እና አዳዲሶች በተለያዩ ጉዳዩች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ («እርሻ ተኮር»፤ «ፆታ ተኮር» ወዘተ ዕይታ) ናቸው። ፕ/ር መስፍን የኢትዮጵያ ታሪክ ትርጉማቸውን በእነዚህ ዕይታዎች አማካኝነት ለመቃኘት አልመው ያደረጉት ባይሆንም፣ ከእነዚህ ዕይታዎች የብዙዎችን ባህርያት አሳይተዋል ኢትዮጵያ ከሮም ጋር ዓለምን ልክ እንደ እንግሊዞቹና ፈረንሳዊያኑ ተካፍላ ትገዛ እንድ ነበር (ገጽ 68) እና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከኢትዮጵያ መጣን ስለሚሉ ሰዎች የሚጠቁሙት (ገጽ 70) እና የጥናቱ ውጤት ገና አላለቀም እንጂ ከህንድ እስከ ሞሮኮ የኢትዮጵያውያኖች ማኀተም ስለመገኘቱ የሚያትቱበት ጽምጸት (ገጽ 37) ባልተብራራ መልኩም ቢሆን ስለኢትዮጵያ ሥልጣኔ ምንጭ ያላቸውን አረዳድ ፍንጭ የሚሰጡበት ነው። በዚህ ረገድ መስፍን የመጀመሪያው አይደሉም፡፡ ዕይታው እ.ኤ.አ ከ1970ዎች ጀምሮ በአፍሪካ ደረጃ እነሼክ አንታ ዲዮፕን፤ ቲዮፈል ኦቤንጋን ፤ ሄንረክ ክላርክን የመሳሰሉ አራማጆች ያሉት ነው። ከውስጥ እነ ዶ/ር ኃይሉ ሃብቱን ፕ/ር አየለ በከሪን፤ ፕ/ር ተሻለ ጥበቡን ዶ/ር ላጵሶ ጌዴሌቦን ጸጋዩ ገብረመድኀንን መሪ ራስ አማን በላይን፣ ዶ/ር ተወልደ ትኩዕንና አቶ አሥረስ የኔ ሰውን መጥቀስ እንችላላን። የአቶ አስረስ ሥራዎች የወጡት በ1951 ዓ.ም ስለሆነ ቅድምና አላቸው፤ ለእነአየለ በከሪም ሃሳብ ከውስጥ የቆየ መነሻዎች ናቸው። ይህ ዕይታ የኦሪዬንታል ሴሜቲስቱን ዕይታ በቂ መረጃ የሌለው ብሎ በማጣጣልና አፍሪካዊ መነሻዎችን ለመጠቋቋም፤ የኑብያን፤ የግብፅንና የሰሜን ኢትዮጵያን ግንኙነት ለማሳያት በመሞከር የሚታወቅ ሲሆን፤ የዚህ ዕይታ ጠንከር ያለው ሙግት የሴሜቲክ ቋንቋ በኦሪዬንታሊስቶቹ ወደሰሜን ኢትዮጵያ መጣ ከሚባልበት ጊዜ በፊት እንደነበር የሚጠቁመው ነው። የግርማቸው “ The Origins of Amharic” ሥራ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ጀምስ ከሪ እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም ያሳተመው የፕ/ር ዴቪድ ፊሊፕሰን “ Foundation of an African Civilization.Aksum the the Northern Horn 1000 BC-AD 1300” በአርኪዎሎጂ ጥናታ የተገኙ አዳዲስ ግኝቶች ተካቶበት የወጣ በመሆኑ የኦሪዬንታሊስት አስተሳሰቦችንና የቀደሙ የታሪክ ትርጉም ታሳቢዎችን ለመቃኘት የሚረዳ ነው፡፡
  ሌላኛው ዕይታ ፈራ ተባ እያሉ የንግሥት ሳባ ትረካን የሚደግፍን አሰተያየታቸውን ስርግው ሐብለሥላሴን በማመስገንና (ገጽ 70) እና የንግሥት ሳባን ጉዳይ እንደ ተረት ቆጥረው ብዙም ዋጋ አልሰጥ እሉ ብለው በሚወቅሷቸው በታደስ ታምራት ላይ በመፌዝ (ገጽ 95) የሚገልጹት “ አክሱማዊት” ዕይታ ነው፡፡
  ይህ ዕይታ በአብዛኛው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት የሚደገፍ ሲሆን፤ የቀድሞዎቹ እነአስረስ የኔሰው፣ መሪ ራስ አማን በላይ፣ ንቡረ ዕድ ኤርምያስ ከበደ በዚህ ዕይታ ብዙ በመጻፍ የሚታወቁ ናቸው፡፡አቶ አስረስና ዶ/ር ተወልደ ልክ እንደ ፕ/ር መስፍን የሁለቱም ዕይታ አራማጅ ሆነው በመገኘታቸው የበለጠ ከፕ/ር መስፍን ጋር ልናመሳስላቸው እንችላለን።
  ሁለቱም ሰዎች ከዚህ መጽሐፍ ጋር በተያየዘ የሚጠቀስ ሌላ ነገርም አላቸው፡፡ ዶ/ር ተወልደን ፕ/ር መስፍን በዚህኛው መጽሐፍም ሆነ ከዚህ ቀደም በጻፋት መጽሐፍ ደግመው የሚያነሷቸው ናቸው፡፡የአቶ አስረስ የኔሰውን ስም እዚህ የማነሳው በፕ/ር መስፍን መጽሐፍ ውስጥ ስለተጠቀሱ ሳይሆን በ1951 ዓ.ም በጻፋት «ትቤ አክሱም መኑ እንተ» በተባለ መጽሐፋቸው ምክንያት ነው፡፡ አስረስ ይህን መጽሐፍ የጻፋት አባ ጋስፓሪና በ 1948 ዓ.ም በጻፋት (የኢትዮጵያ ታሪክ) በተሰኘ መፅሐፍ ላይ ፈጽመዋል ያሉትን ስህተት ለመተቸት ነው። የአስረስ ትችት የሚያጠነጥነው ሴሜቲክ ቋንቋ ከደቡብ ዐረቢያ መጣ ስለመባሉና አቢሲኒያ እና ኢትዮጵያ በሚለው አከፋፈል ዙሪያ ነው፡፡ እነዚህ ጉዳዩች ፕ/ር መስፍን በኢዲሱ መጽሐፋቸው ከሚያነሷቸው ጉዳዮች መካከል መሆኑ የሃሳብ መጋራት እንዳለ የሚያሳይ ሲሆን ፤ አቶ አስረስ ከ54 ዓመታት በፊት በጻፋት በዚህ መፅሐፍ ካካተቱት በአምስቱ ዓመታት የጣሊያን ጦርነት በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሱ ሰቆቃዎችን የሚያሳዩ ፎቶዎችን የፕ/ር መስፍን አዲሱ መፅሐፍም (ፎቶዎቹ ከሲልቪያን መፅሐፍ የተወሰዱና በቁጥርም የበዙ ሆነው) ያካተተ መሆኑ የሃሳቡን ቆይታና ውርርሱን ስለሚያመለክት ነው፡፡
  የኢትዮጵያን ታሪክ በውጪ ከመጡባት ወራሪዎች አንጻር ለመቃኘት መሻታቸውንም (ናሺናሊስት ዕይታ) ዐፄ ዮሐንስና የሒወት ውል፤ ዐፄ ምንሊክና የውጫሌ ውል፤ የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነትን አስመልክቶ ስለባንዳና አርበኛ ትርክትና ለዓድዋና የማይጨው ጦርነት በሚስጡት ቅድምና ያመለክታሉ።
  እዚያው የኢትዮጵያ መሪዎችና የእንግሊዛውያኑና የጣሊያኖቹ ስምምነት ውሎችን የሚያነሱት የትኛው መሪ ለወራሪ የበለጠ አስተዋፅኦ አደረገ ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጫ በመሆኑ ዘውግ ተኮር ዕይታንም የሚያንፀባርቅ ሆኖ ይታያል፡፡ ታሪክን አማራጭ እንደሌለው ከዝቅተኛ ወደከፍተኛ የሚደረግ ዕድገት ሒደትና (ከዚህ በፊት ከፍተኛ ዕድገት ያሳየች ኢትዮጵያ አሁን ታሪኳ ከሸፈ ሲሉ)የወደፊቱን ሁነት ለመቆጣጠር የሚረዳ የዕውቀት ዘርፍ አድርገው በመመልክትም እይታቸውን በ “ማርክሲስት” የሚያስፈርጅውን ገጽታ ይላበሱና የቡፌያቸውን ዓይነት ያበዙታል፡፡
  የመስፍን አዲሱ መንገድ የታሪክ ፅንስ ሃሳብንና የኢትዮጵያ ታሪክ ባለሙያዎችን መሞገት
  በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ ክርክሮች ሲፈጠሩ ብዙ ጊዜ ማጠንጠኛው የትርጉም ልዩነት ነበር ፡፡ ስለዚህ ውድድሩ በተፎካካሪ የኢትዮጵያ ታሪክ ትርጉም አቀንቃኞች መካከል ነበር። አሁን መስፍን ያመጡት ሙግት ለየት ያለ መልክ እንዳለው መናገር ይችላል ፡፡ ይህ የፕ/ር መስፍን ሙግት ሁለት ጫፎች አሉት። አንደኛው የታሪክ ጥናት በተፈጥሮው አለበት የሚሉት ባህርይ ላይ ተንተርሰው ልክ ለበሽተኛው “መድሀኒት ማዘዝን” በሚተካከለው አቀራረባቸው ለኢትዮጵያ ታሪክ እጠናን የሚሰጡት አቅጣጫ ነው። ባለፋት ጥቂት ዓመታት ብዙዎች ስለታሪክ በሜታፈርም (ጎርፍ፤ ዳኛ፤ ወቃሽ፤ተወቃሽ መስካሪ አተላና ዕድፍ ያለው የሚበቃው፤ የሚቆም እንዘጭ (በቀደመ መጽሐፋቸው የተጠወሰው የራሳቸውን የመስፍን ሜታፈር) የሚል የሚከሸፍ (አዲሱ) ወዘተ ሆኖ እየቀረበ) በዝርዝርም አስተያየት ሲሰጡ ማየት የተለመደ ቢሆንም ፤ በዚህ ስፋትና ደፋር እርግጠኛነት መጠን ሲሰጥ የመጀመሪያ ሊሰኝ ይችላል። የታሪክ ሰዋዊ ባህርይን አንስቶ በሁነት መጠን፤ የክስተት ጊዜና የአጥኚው ማንነትና ሁነቱና በመተርጎም ደርጃ ያለውን ተፅዕኖ (ገፅ 35-50) ያብራሩበት ክፍል ይህንን የተመለከተ ነው። ይህንን አሰተያየተቸውን አለን ኔቪስ፤ ኢ ኤች ካርና ኦርቴጋ ጋሴት እ.ኤ.አ በ1962፤ በ1960 እና በ1961 ዓ.ም ካሳተሟቸው መጻሕፍት በወሰዷቸው መረጃዎች ላይ ተመስርተው ያዳበሩት ነው። በነዚህ በብዙ መልኩ ጊዜ ያለፈባቸው መጻሐፍት ባለንበት ዘመን ለሚቀርብ ትችት ዋና መደገፊያ መደረጋቸው ብዙ ክፍተት እንደፈጥር ይተወቃል። በአንድ በኢ ኤች ካር ላይ ብቻ ደርዘን የሚደርሱ መጻህፍትና በብዙ አሥሮች የሚቆጠሩ መጣጥፎች (በአርተር ማርዊክ “ the practice of history”(1968) በዴቪድ ካንዳይን «what is history now(2002)» ሲጠቀሱ የራሱ የካር እኤአ የ1987 ዕትም (የልብ አድርጉ ድግግሞሾቹን አይደለም ) የታዋቂው የ In Defense of History ጻሐፊን ሪቻርድ ኢቫንስ ከካር እስከ ኢቫንስ ያሉ ለውጦችን የሚያመለክት ነው፡፡ ለጊዜው ግን ካለው የዓምዱ ቦታ አንጽር መስፍን በታሪክ ስነዘዴ ዙሪያ ብዙ ያነሷቸውን ፍሬ ነገሮች ካነሱት ዓላማ አንጻር በመፈተሽ ብቻ እወሰናለሁ። የጉዳዬ ማዕከልም ታሪክ መጻፍ የዛሬውን ሁኔታ ለማነጽና ለመቅረጽ መሆን ያለበት (ገጽ 52)፤ የአንድ አገር ታሪክን ለማጥናት የአገር ተወላጅነትን ግድ የሚያደርግ እንደሆነ (ገጽ 53 እና 65) በማስረገጥ ጸሐፊው ራሱን ገለልተኛ ለማድረግ እየጣረ የሚጽፈው ዓይነት አጻጻፍ ግን ሐቅን ያልተከተለ አድርገው መመልከታቸው ይሆናል።

  ዕሳቤና ድርጊት -ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ
  ፕ/ር መስፍን ዓላማዬ የሚሉት ኢትዮጵያን በጊዜና በቆዳ ሽፍን የረዥምና የስፈ አገር ታሪክ ባለቤት ማድረግ (ዓብይ ትረካ/ ግራንድ ናሬቲቭ ) እንደሆነ ከመጽሐፉ እንረዳለን። ታሪክን ማጥናት የሚገባው የአገር ተወላጅ ብቻ ነው የሚለው አስተሳሰባቸው ግን አጥኚው የተጠኚውን ክፍል አካል መሆን አለበት የሚል ትርጉም (ቢትል ኢንቲሞሎጂ) ይስጣል (ገጽ 53-54) በነገራችን ላይ አፍሪካውያኖችን ከቀኝ ግዛት ከመውጣታቸው በፊት በነበሩበት ዋዜማና ከነፃነት በኋላ ባሉት ጥቂት ዓመታት ከዚህ አስተሳሰብ ጋር የሚሔድ የአፍሪካውያን ታሪክ ስለአፍሪካ በአፍሪካውያን እንዲሆን የሚወተውቱ ልሒቃን፣ በታወቁት እንድ ኢባዳንና ዳሬሰላምን በመሳሰሉ ዩኒቨርሲቲዎችና ሎንዶን ጨምሮ ራሳቸው ምዕራባውያኑ እያሰለጠኗቸው (የእነ ሮላንድ ኦሊቨርን አስተዋፅኦ ማሰብ ያስፈልጋል)ተስፋፍተው ነበር ፡፡ እውነትም በአፍሪካ ከፖሊቲካ ነፃ ከመውጣት ጋር የታሪክ ነጻ የመውጣቱ እንቅስቃሴ ተደርጎ ተወስዶ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የነበረው የታሪክ ጥናት እንደሙያ የተጸነሰበትና ያደገበት ሁኔታ ከዚህ ጋር የሚነጻጸር ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ማንሳት ያስፈልጋል። ነገሩን በዜኖፎቢክ ዕይት መመዘን ዕውቀትን ከመሻት፣ ከመሞገት፣ ከማጥራትና ማስፋት መቻል ጋር ለማስማማት አለመቻል ተቀጣጣይ ችግር አይፈጥር ይሆን? ታሪክ አጥኚው የሚጠናው አካል አባል መሆን አለበት ስንል ስዊድናዊውን ስቨን ሩቤንስንን የኢትዮጵያዊውን ታሪክ ማጥናት የምንከለክለው ብቻ ሳይሆን የኦሮሞን ትግሬውን ወይም የትግሬውን ኦሮሞው ሊያጠናው አይችልም የሚልስ መግፍኤ ሃስብ አይኖረውምን ? መቼም በስዊድናዊውና በኢትዮጵያዊው መካከል ያለውን ልዩነት በአማራው /ትግሬውን/ ኦሮሞውና ሌላው ኢትዮጵያዊ መካካል ካለው ልዩነት ጋር ማስተካከሌ እንዳልሆነ እንደምትረዱልኝ ተስፋ አደርጋለሁ ልዩነቱ በየራሱ አውድ የሚፈጥረው ክፍተት እንዳለ ለማመልከት እንጂ፡፡
  በምርምር ላይ ተመስርተው ለሚሠሩ ስራዎች ሳይቀር ማንነትን (የዘውግ/ ብሔር ?) በየመጽሐፎቻቸው መግቢያ እያስቀደሙ የመጻፍ ልምድ የመጣው ከዚህ መንፈስ (መሐመድ ሐስን “History of the oromo of Ethiopia” እና ተሻለ ጥበቡ the making of modern Ethiopia) ይመስላል። ጉዳዩ በዚህ ብቻ የሚቆም አይሆንም፡፡ ፕ/ሩ እንደሚፈልጉት ዓይነቱን አጠቃላይ የኢትዮጵያ ታሪክንስ ማንው ይጻፍ ከሚል ጥያቄ ጋር የሚያጋፍጠን ይሆናል። የ “ዘረነኛው ማነው?” ጽሐፈ ይትባረክ ግደይ የኢትያጵያን ታሪክ አጻጻፍ አስመልክቶ ሁሉም በያለበት የየራሱን እያጻፈ መስማማት እንድቃተን ያማርሩና የሚሰጡን መፍትሔ ጸሐፊዎችን ከያካባቢው ተውጣጥቶ ተጽፎ በፓርላማ እንዲጸድቅልን ነው። ስለዚህ የመስፍን የታሪክ አጠናን /አጻጻፍ አረዳድና ስለኢትዮጵያ ታሪክ ያላቸው ህልም አፌን በምላሴ(self defeating) ይሆናል ማለት ነው።
  ሁለተኛው ጫፍ ፕ/ር መስፍን ታሪክን ለዓላማ ብቻ ያሉት ጉዳይ ነው፡፡ የዚህ አስተሳሰብ አንድምታ ታሪክን ለዓላማ (ብሔራዊነት ግንባታ) ለማዋል ካልጠቀመ ምን ያደርጋል የሚል ነው። አቀራረቡ ምንጭ መር የሆነውን የታሪክ ሙያተኛውን መርህ በዓላማ መር ለመቀየር የሚዳዳው ዕሳቤ ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ታሪክን ለታሪክነቱ እና ታሪክን በጥናቱ ጊዜ፤ በሚጻፍበት ወቅትና ሲነበብ የሚያስገኘውን የመስተሐልይ ዕድገት ለማግኘት የሚደክመውን የታሪክ ባለሙያ ሆድ አደር አድርጎ የማየቱ አባዜ አንድምታ አገር አሳልፎ በመስጠት የሚወነጅል አስገራሚ አስተያየት ነው፡፡
  የፕ/ር መስፍንና ሌሎችንም ለታሪክ ነክ ጥያቄዎቻቸው የኢትዮጵያ ታሪክ ባለሙያዎች መልስ በመንፈጋቸውና በሌላው በሌላውም እየተበሳጩ ታሪክ ምን ያደርጋል ወደሚል መደምደሚያ የሚደርሱ ሰዎች ታሪክን ለተወሰነ ዓላማ ታኮ እያደረጉ መምጣታቸውና የሚፈልጉትን አለማግኘታቸው ይመስላል፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ሁሉም ወገን ፓለቲካን ተንተርሶ ለሚሰጠው ትርጉም የሚመችና እንደተፈለገ የሚተጣጠፍ ዛላ አልሆነም። ለዚህም ይመስላል እንገነጠላለን የሚሉት ብቻ ሳይሆን ሌሎቹም አልመች ሲላቸው በባለሙያዎቹ አለመርካታቸውን በስድብ ጭምር የሚገልጹት። አሁን አሁን ደግም በቡድን በቡድን ራሱ የሚፈልገውን ታሪክ ለመጻፍ እየተደራጀ ነው፡፡ ምናልባት የወደፊቱ ሕዝባዊ ታሪክ ገፅታ በዚህ መልኩ ሊጎለብት ይችላል፡፡ እስከዛው ግን ሁሉም ከያለበት የራሱን ያለቀለት የታሪክ ትርጉም ይዞ መጥቶ (ሂስቶሪካል ዲፊደንስ ስላለበት) የግድ የታሪክ ባለሙያዎች ማኅተም እንዲመቱለት መሻቱና መጋጨቱም አይቀርም፡፡ ግጭቱ ሉላዊ ከሆነው በታሪክ ሙያ ስነዘዴ ዙሪያ ከሚፈጠሩ ክርክሮች ጋር ሲደባለቅ የባለሙያውን ፈተና እንደሚያከብደው እገምታለሁ፡፡
  ልክ በዚህ ዓይነት ነው እንግዲህ ፕ/ር ካሰቡት ዓለማ በተቃራኒው እንዲውል (የቅኝ ግዛትነትን ዕይታ አራማጆችን ጨምሮ አሁን በምትታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች አብሮነትን አጭር አስመስሎ ለማቅረብ ምክንያት ሆነዋል ያሏቸውን የታሪክ ባለሙያዎች ሥራዎች እየቀነሱ ጸሐፊዎቹን የተቹት (77-103) የፕ/ሩ ትችት በታሪክ ባለሙያዎቹ ላይ ከአንደኛው ቡድን የሚነሳው የመጨረሻው ጠርዝ ማሳያ አድርገን ልንወስደው እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ፕ/ር መስፍን በዛሬዋ የኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ካሉት ሕዝቦች ውስጥ ጽሐፈዎቹ ባጠኗቸው ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ ተዘለዋል ብለው የሚወቅሱትን ያህል በዛሬዋ ኢትዮጵያ ወሰን ክልል ውስጥ ስላሉ ሕዝቦች የ19ኛው መቶ ከፍለ ዘመን ታሪክ ሲነገር የኢትዮጵያ አካል አድርጎ ማውራት ትክክል አይደለም የሚሉም አሉ(ሰሚር የሱፍ “ the politics of historying፦ a post modern contemporary on Bahru Zewde’s history of modern Ethiopia”):: ጸሐፈዎቹ ፕ/ር ታደሰ ታምራት፣ ፕ/ር መርዕድ ወልደ አረጋይ፣ ዶ/ር ስርግውና በተደጋፊ ፕ/ር ትሪሚንግሃም ናቸው፡፡ በእነዚህ የታሪክ ባለሙያዎች ላይ የቀረቡት ትችቶች ‘ስቴት’ ፤ «ኤምፓየር»፤ “ቦርደር”/ ወሰን እና «ፍሮንቲር» ጠረፍ የሚሉ የውጭ ቃላቶች ትርጉም በቅጡ ታስቦበት የአገባብ ትርጉማቸው በግልፅ ባለመቀመጡ፤ ስለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከማጥናት ይልቅ (ታደሰ ክርስቲያኖች ላይ ትሪሚንሃም መስሊሞች ላይ ብቻ ማተኮራቸው ወይም ራሳቸውን የቻሉ የተለያዩ ሃገረ-መንግሥት አስመስለው ማቅረባቸው) አቢሲኒያና ኢትዮጵያ የሚሉ ክፍፍሎችን መቀበላቸው በኢትዮጵያ ውስጥ ሊካተቱ የሚገባቸውን ሕዝቦችና አካባቢዎች ከኢትዮጵያ ቁጥጥር ውጪ ማስቀረታቸው እና በመሳሰሉት ጉዳዩች ላይ ነው።
  የፕሮፌሰር መስፍን ፋውል
  ይህ ክፍል ስለ ፕ/ር መስፍን ሁለት ነገሮችን እንደሚነግረን መገንዝብ እንችላለን፡፡ አንደኛ ፕ/ር ታሪክን ላለሙት ዓላማ ለማዋል የሚያስከፍላቸውን ሁሉ ለመክፈል የሔዱበትን ርቀት የሚያሳይ ሲሆን ሁለተኛው የሚታገሉበትን አቀጣጫ ለመቀየር መገደዳቸውን ነው። የመጀመሪያውን አስመልክቶ “ ሥልጣን ባህልና አገዛዝ …..”በተሰኘ መጽሐፋቸው የታሪክ መዛባትን አስመልክቶ የሚኮንኑት እምባገነኖችን ነበር (ገጽ 96)። ከዚያ ቀደም በ1996 ዓ.ም በጻፋት «የክህደት ቁልቁለት» ላይም የኢትዮጵያን ታሪክ ባለሙያዎች ከገዢው ቡድን የሚሰነዘርባቸውን ወቀሳና ትችት ሲከላከሉ ነበር የተስተዋለው (ገጽ 36)። ከዚህ አንጻር ምንም መፅሐፉ ቀድሞ እንደተጻፈ ቢታሰብም ያልተጠበቀውን ለውጥ አስደናቂ ያደርገዋል። ሁለተኛው ጉዳይ ብዙዎቻችን እንደምንስማማው ፕ/ር መስፍን የማይታክታቸው የሥርዓቱ ተጋፊ ናቸው፡፡ ይህንንም በሲቪክ ማህበረሰቡ ሞክረውት ተገቢውን ለውጥ አላመጣም ሲል በፓለቲካው ማዕቀፍ የተቻላቸውን አድርገዋል፡፡ እሱን ተወት እድርገውት ሃሳብ ማንሻራሽሩ ላይ አተኩረዋል። ይሔ መጽሐፍም በዚህ መንፈስ የተዘጋጀ/ እንዲቀርብ የተደረገ እንደሆነ መገመት ይቻላል።
  መስፍን በዚህ ክፍል ከሚየነሷቸው ሙግቶች በመነሳት ሰፊዋንና ባለረዥም ታሪክ ባለቤቷን ኢትዮጵያ (የእሳቸው ኢትዮጵያ-በነገራችን ላይ እኔም ኢትዮጵያዬ እንደሳቸው ብትሆንልኝ ምኞቴ ነው፡፡ የራንኬያንን ትውፊት በሚከተል ታሪክ ግን የነገሩ መጨረሻም መዝጊያም ምንጭ መሆኑ እንጂ፡፡ ምናልባት የቤኔዲክት አንደርሰንን “ Imagining Communities፦ Reflections on the Origin and Spread of Nationalism’’ የሶሬንሰንን “ Imagining Ethiopia’’ እና የዶ/ር ዮናስ አድማሱን የፒኤች ዲ ጽሑፍ “Narrating Ethiopia A panorama of the National Imaginary’ መመልከት ሌላውን አማራጭ ይጠቁም ይሆን ?) ……… ተፃራሪ የሆኑት ትርጉሞች አራማጆች የአቋማቸውን መሰረት ያገኙትም ያስደገፉትም በእነዚህኛዎቹ መጽሐፍት ነው ብለው ሳያምኑ አልቀረም። ይህ አስተሳሰብ ደግሞ አንድም ስህተት ነው አሊያም እጅግ የተጋነነ ነው። ለምሣሌ ቃላትን እየለጠጡ መተርጎም ከፈለገ መከልከል አይቻልም። ወሳኙ ጉዳይ የመነሻው መንፈስ ነው። ለምሣሌ በመጽሐፎቹ የኤርትራ አካባቢዎች የጥንቷ ኢትዮጵያ ታሪክ አካልነቷ እንደተጠበቀ ቢጻፍም ታሪኩ ከመገንጠል አላዳናትም። ስለዚህ በዚህ ተበሳጭተው ጉልበታቸውን የሚጨርሱበት ምክንያት ተገቢ አይሆንም። ትርፉ እሳቸውን ከአጉል መነሻ አስጅምሯቸው ጉዟቸውን ሚዛኑን የሳተ አድርጎባቸው አለፈ እንጂ። እርግጥ ነው በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ ማይግሬሽን/ፍልሰት፣ ኤክስፓንሽን/መስፋፋት፣ ኮሎናይዜሽን/ቅኝግዛት፣ ናሽናል ኦፕሬሽን/ ብሔራዊ ጭቆናና የመሳሰሉት ቃላት ለረዥም ግዜ ክርክር ሲፈጥሩ የቆዩ ናቸው። በዚህ መጽሐፍም መስፍን በታሪክ ጽሑፍ ውስጥ የቃላት እንድምታ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ መሆኑን ከማመልከታቸውና እስካሁን በነበሩe «አጨቃጫቂ» ቃላት ላይ ሌሎች ጥቂት ተጨማir አከራካሪ ሊሆኑ የሚችሉ ቃላቶች እንዳሉ ሕዝቡ እንዲያውቁ አድርገዋል። ችግሩ ግን ከአላስፈላጊው ድካማቸው በተጨማሪ ትችት ውስጥ የሚከታቸው ግድፈቶችን በቀላሉ እንዲፈጽሙ አድርጓቸዋል።
  በነገራችን ላይ የፕ/ር ታደሰ ታምራት መጽሐፍ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌና ፕ/ር ዶናልድ ክራሜ የጻፏቸው መግቢያዎች ታክለውበት እ.ኤ.አ. 2012 ዓ.ም. በፀሐይ አሳታሚ ድርጅት ታትሟል። የፕ/ር ጌታቸው መግቢያ በተለይ የመጽሐፉ ላለው ዕውቀት እስካሁን ያበረከተውን አስተዋፅኦ በማፅናት መጽሐፉ ከተጻፈ በኋላ በነበሩት ዓመታት የተደረጉትን ለውጦች በመጠቆም ዋጋው ከፍተኛ መሆኑን ይመሰክራል። የስርግው ሐብለሥላሴን መፅሐፍ እንዳለ ማሳተም ስለሚያስቸግር የተራዘመ መግቢያ በማዚጋጀት ግልጋሎት ላይ እንዲውል እየተመከረ ሳለ በጥንታዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ የገፉት ዴቪድ ፊሊፕሰን እስከ አሁን ያለውን ለውጥ አካተውበት የሳፉትና ከላይ የጠቀስኩት መፅሐፍ በመውጣቱ በዚህ በኩል ያለውን ክፍተት ለመሙላት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል ተብሎ ታስቧል። መቼም በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያለው ዕውቀትን የማነፅ ትውፊት ይህ ነውና።
  የሀገረ መንግሥት ምሥረታን አስመልክቶ ሰለሚኖር ደረጃ ግምት ውስጥ ባላስገባ ሙግት የአሁኗ ኢትዮጵያን ባትበልጥ የማታንስ ኢትዮጵያ እንደነበረች አድርገው የታሪክ ባለሙያዎቹ ማቅረብ እንደነበረባቸው ለማሳየት የለፉት ልፋት በሚታወቀው የመስፍን ልቀት ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። በሙግቶቻቸው የታሪክ ጥናት ምጣኔ ጊዜ ጽንሰ ሃሳብን ለመረዳት ሲያቅታቸው የስኮላርሺፕ ችግር አድርጎ እንዲወሰድ ያስገድዳል። ለምሣሌ ታደስ, ታምራት እ.ኤ.አ. በ 1299 የክርስቲያኑ ኢትዮጵያ ዋና ዋና ክፍሎች ብለው ያስቀመጧቸው ቦታዎች የሚፈልጓት ኢትዮጵያን አልሰጥ ብትላቸው ፕ/ር መስፍን እንዲጨመር የፈለጓቸው ቦታዎችና ሕዝቦች አህመድ ግራኝን የተዋጉ ብሎ የሺሃብ አዲን የዘረዘራቸው ስሞችን ነበር(ገጽ 93)። የፕ/ር መስፍን ሙግት ለምን የ ሺሃብ አል ዲን የዘረዘራቸው ሕዝቦች ፕ/ር ታደሰ በ1299ኙ «የክርስትያን ኢትዮጵያ» ግዛት ውስጥ አልከተቷቸውም ነው። እንግዲህ ጦርነቱ የተካሔደው በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከመጀመሪያው ሩብ ዓመት በኋላ መሆኑን ልብ ይሏል። ከ1299 በኋላ ዓምደ ጽዮንን ጨምሮ ግዛቱን ያስፋፉት ተከታታይ ነገሥታት ያመጡት ለውጥ እነዚያን ሕዝቦች በልብነ ድንግል ወገን ሆነው በ1520 ዎቹ መጨረሻና በ1530ዎቹ መጀመሪያ ከአህመድ ግራኝ ጋር ለመዋጋት መብቃታቸውን ልብ ሊሉ አልቻሉም። ከዚህ ውጪ ሦስቱም ባለሙያዎች ያጠኗቸውና በየመፅሀፍቱ ስለኢትዮጵያ ግዛት የጠቃቀሷቸው ጉዳዮች ዘመን መለያየታቸው እየታወቀ (97፣ 98 እና 102) በአንድ ዘመን እንደነበረች ኢትዮጵያ ላይ እንደተሰጠ የተፋለሰ አስተያየት አድርጎ መመልከት ጸሐፊዎቹ የሚያብራሩት ጉዳይ ስለማዕከላዊ ወይም አጠቃላይ ግዛት መሆኑን ባለመለየት (98) የተሰጠ አስተያየት፣ የ16ኛው መክዘ አልቫሬዝ ስለ አክሱም ዘመን የሚሰጠውን የግዛት ስፋት መረጃ ፕ/ር መርዕድ ባለመቀበላቸው (101) የሚተቹበት መንገድ እና ሌሎች ማሳያዎች ሁሉ ወዳልተፈለገ ስህተት (ፋውል) ውስጥ እንደገቡ እንድናስብ የሚያደርጉ ናቸው።
  የመስፍን እንዲህ ዓይነቱ ተቃርኖ ግን በኢትዮጵያ ታሪክ አረዳድ ላይ የተፈጠረ የእሳቤ ችግር ብቻ ሳይሆን የመዋቅር መጣመም እንዳለባቸው ያመለከቱ ሌሎች ሁለት ምዕራፎች (አጼ ምኒልክና የውጫሌ ውል፣ አጼ ምኒልክና የሒወት ውል)ን እንድንመለከት ያስፈልጋል። ካሉት የኢትዮጵያ ታሪክ ሁነቶች ሁሉ ይህ ርዕሰ ጉዳይ የተመረጠበትን ሁኔታ ከ«ብሔራዊ» ታሪክ ዕይታ ምርጫ ጋር ልናያይዘው እንችላለን። በምዕራፎቹ ፕ/ር መስፍን ዐፄ ምንሊክን ለመረዳት (118፤ 119 እና 127) ዐፄ ዮሐንስን ለመተቸት (109፤ 111፣ 114 እና 117) የሚደክሙበት መንገድ ርቱዕነት የሚጎለው የቢትል ኤንቲሞሎጂ መዳረሻ ልክ ማሳያ ሆኖ ይታያል። በሁለቱ ምዕራፎች ውስጥ የቀረቡት ጉዳዮች በአግባቡ ለማስተንተን ከሚያስፈልገው ታሪኩ ሁነት የተፈቀመጸበትን መንፈስ ለመረዳት የሚያስችል አብርኆት ይልቅ የምንሊክ ለኤርትራ መለየት ተጠያቂ እየእየተባሉ መነቀፍ ያናደደው ስሜት ያመዘነበት ነው። በነዚህ ምዕራፎች የርዕሱ ጉዳይ አቀራረብ እንድምታና ጸሐፊውን በእነመምህር ገብረ ኪዳን (« የትግራይ ሕዝብና የትምክህተኞች ሤራ»ን እና በቅርብ የዮሐንስ ሕልፈት 124ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ስለዐፄው የጻፉ ) ምድ የሚያስመዘግብ እንዳይሆን ያሰጋል።
  በመጨረሻም የታሪክ ፍሬ ነገር በፖለቲካ ሙግት ውስጥ ያለውን ሚና፣ የገዥው ቡድን ዕመቃና መሰል ጉዳዮች ሕዝቡንም ፖለቲከኞቹን ውጥር ማድረጉ ታሪካዊ፣ ብሔራዊ በዓላትንና መሰል ጉዳዮችን ለማክበር ወይም ለመወያየት ከሚደረጉ መሯሯጦች ጋር ስላለው ግንኙነት እንዳስብ ያደረገ ይህ መጽሐፍ፣ አገሪቱ ስላለባት የታሪክ ሽሚያ ብዙ የሚያስብል፣ ሕዝባዊ ታሪክ ጸሐፊያን መስፍን ያላቸውን ዕምቅ ጉልበት የሚጠቁም፣ የታሪክ ባለሙያዎች በሕዝባውያን ፍላጎት እንዲመሩ ሳይሆን ፖለቲካም ሆነ ሌሎች ጉዳዮች መራሹ የሆነውን የሕዝባውያን ታሪክ ጸሐፊዎች ስነልቦና ለሕዝብ የመድረስ አቅማቸው የሚያመጣውን ጫና ልብ እንዲሉት የሚገፉ መሆኑን እመሰክራለሁ። ጸሐፊውን ፕ/ር መስፍንንም እንደሁልግዜው እያደነቅሁ የዕለቱን አስተያየቴን እቋጫለሁ።

 2. Madeinchina says:

  ጤና ይስጥልኝ ሁላችሁንም፡
  በአጋጣሚ የብርሃኑ ደቦጭን “መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ” የሚለውን የፕሮፌሰር መስፍንን ድንቅ መጽሐፍ ትችት ተመርኮዞ የተደረገውን እሰጥ አገባ አነበብሁ፣
  እናም እንደሁልግዜውም ምክንያቱን በማላውቀው ጉዳይ ብዙዎቻችን እኛ ከምንስማማበት እውነት በስተቀር ሌላ ያወቀውን እውነት ከመቀበል ማጥላላት፣ መፈረጅ፣ ማንኳሰስ፣ ማድበስበስ—– ይመቸናል ከምን የወረስነው ይሆን? በተቃራኒ ከደረቅ ሀቅ ይልቅ ድለላ፣ ሽንገላ፣ሽሙጥ፣ ውስጠወይራ——ይሰማሙናል ለምን? የፖለቲካ ጉዳዮቻችንስ ከዚህ የመነጩ ሳይሆኑ ይቀራሉ ፖሊሲያችን፣ አንደበታችን፣ ምህላችን፣ ቃልኪዳናችን—— ሌላ ድርጊታችንና እውነታ በምድር ላይ ሌላ (ቲቪና ራዲዮ መቼም አይታሙም ብዬ ነው) በመጽሐፍ የወጣው ሌላ ትችቱ ሌላ፡፡
  ሰውየው በመጽሐፋቸው እንዳሉት ከመጻፍ በፊት፣ከመናገር በፊት፣ ከመዝለፍ በፊት( ተገቢ እንኳ ባይሆን) በታወቀ እውነትና በተረጋገጠ እውነት መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ ከዚያም እንደእርሳቸው በማስረጃ አስደግፎ አጥንቶ አረጋግጦ ለታዳሚ ማቅረብ መልካም ገበያ ያስውላል እወቀትንም ያስተላልፋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ሁሌም እንደድሮው እንደአሁኑም እኛ እናውቃለን ብቻ ሆኖ ነገራችን ሁሉ የእምቧይ ካብ፣የእምቧይ ካብ፣ ስለዚህ “መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ” ሐሰት ነው የሚል የተረጋገጠ እውነት ያቅርብና ያስኮምኩመን፡፡ ያለበዚያ እገሌን ገደለ አስገደለ ፡ የእገሌ ደጋፊ አማካሪ ነበረ ፣ ዘረኛ ነው፣ በተማረው ዜጋ ላይ ያነጣጠረ ነው ገሌ መሌ ርባና የለውም፡፡ስንሰማው ስንሰበክበት የኖረ ነው፡፡ ከደሙ ንጹህ ነኝ የሚል “ምሁር”፣ ለህሊናዬ ነው የማድር የሚል ዜጋ አደባባይ ይውጣ እውነት ያውጣ ጊዜውን አይጨርሰው እንማርበት ፡፡ ለአልባልታውማ ኤርታና በየዘመኑ የሚለዋወጠው የዘመን ርዕሰ አንቀስ መቼ አነሰን? አድማጭ አንባቢም እውነት መራር ብትሆንም ለመቀበል መንፈሳን ይበርታ፣ ሞትንስ እንቀበል የለ እንኳን እውነትን ለምን? ሞትም እውነት ነው ጥሬ ሐቅ!
  አላድለን ብሎ እንጅ የምሁሮቻችን ብዛትማ የትየለሌ ባይባልም መች ያንሰን ነበር! ግና ከጥቂቶች በስተቀር ጀማው ምሁር እወነትን የምታያት እንዴት ነው? የሚባል ዓይነት ሆነ፡፡
  ለማንኛውም ፕሮፌሰር መስፍንን የዕድሜ ጸጋ ያድልልኝ

 3. abichumyicho says:

  ፕሮፍ እባክዎን ከዝናርዎ ቶሎቶሎ ይልቀቁልን እድሜና ጤናዎን ፍጣሪ አብዘቶ ይስጥልኝ ዘንድ የዘውትር ዱዓየ ነው:: አክባሪዎ

 4. Senait T says:

  To Prof: My question is, where can we get what Berhanu Deboch wrote? otherwise, only reading this doesn’t give sense.

  • የብርሃኑ ጽሁፍ የዛሬ ሁለት ሳምንት በታተመው ልእልና ጋዜጣ ስለወጣ እዚያ ማንበብ ይቻላል፤ ያው ሁሌም እንደሚታወቀው ብርሀኑ የአአዩ. ታሪክ ትምህርት ክፍል የብእር ስም ሆኖ ቀርቧል። በፕ/ር መስፍን መጽሀፍ ለእንጀራ ያደረ ጸሃፊ የተባለውን የፕ/ር ባህሩ ዘውዴ “ስምና ክብር” ለመጠበቅ ብርሃኑ ደቦጭ በጻፈው “የመጽሀፍ ግምገማ” የቅልውጥ ልምጭ ይዞ ፕ/ርን ለመዝለፍ ጥሯል። የብርሃኑ ትችት እንደ እድር ወጥ ከዚህም ከዚያም ተውጣጥተው የተደበላለቁ ሃሳቦች ያካተተና በቋንቋውም ሚስቶ ሊባል የሚችል አይነት ግራ አጋቢ ሲሆን “ የፕ/ር መስፍን የመጨረሻ ጥይት/ቶች” በሚል ርእስ ነው የቀረበው።
   ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም “ዝናሬ ገና ሙሉ ነው!” አሉ የዋዛ አይደሉምና። በአአዩ. ታሪክ ትምህርት ክፍል መሽገው ብርሃኑ ደቦጭን እንደ ብእር ስም የሚጠቀሙበት (ስሙን ፎቶውንና ጭንቅላቱን ተከራይተው) የታሪክ ምሁራን ስለሙያቸው እንኳ ባደባባይ የመናገርና የመጻፍ ድፍረት የላቸውም። በስውር ግን ደብተራዊ አካሄድ ይችሉበታል፤ ምናልባት ባደባባይ ማድረግ የሚችሉት ነገር ካለ ፈረንጅ ስር እየተከተሉ ቱሪስት ጋይድ መስለውም ጭምር ዶላር ማሳደድ ነውና በፕ/ር መስፍን “ለእንጀራ ያደሩ” ተብለው መወቀሳቸው በጣም አምሟቸዋል፤ ለዚህም ነው ልምጭ አዋጥተው በ “ብርሃኑ ደቦጭ” በኩል ፕ/ርን ሊዘልፉ ጥረዋል። ፕ/ር መስፍንም ቀላል ሰው አይደሉምና ብርሃኑ የራሱ ያልሆኑ መሟገቻዎች ስሙን፣ ፎቶውንና ጭንቅላቱን ከተከራዩ ጌቶቹ ቀራርሞ እንዳመጣ ስለተረዱ ስህተቶቹን በሚገባ ነቅሰው ሎሌነቱን ነግረውታል። “በግድ ጻፍ ካልተባለ በቀር ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ የሚባልልለተ ጽሁፍ ነው፤ ባይጽፈው ይሻለው ነበር፤ ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር ክፉኛ ይወርዳል።” ብለውለታል።
   በፕ/ር መጽሀፍ ያሉ ችግሮች እንዳሉ ሁነው ለብርሃኑ በሰጡት ምላሽ ግን የደብተራዎቹን መንገድ በደንብ እንደተረዱ ያሳያል። ይህንን ከምንታዘብበት አንዱ ምላሻቸውም “የመጻህፍትን ባህርይና ዋጋ ለፈተና ከመጥቀማቸው ውጭ ማየት ካልተቻለ የብርሃኑ አመለካከት በአለም ያሉ ቤተመጻህፍትን ያራቁታል” ማለታቸው ነው። እዚህ ላይ በብርሃኑና በተከራዮቹ(ስሙን ፎቶውንና ጭንቅላቱን በተከራዩ ሰዎች) መካከል ያለውን እኩይ የድብትርና ትስስር በሚገባ ነቅሰው ማሳየት መቻላቸው እንረዳለን። በኔ አስተያየት ይህ ትችታቸው ብርሃኑ ደቦጭ ራሱን ይሆን ዘንድ ይረዳዋልና ጠቃሚ ነው እላለሁ። የፈሪ ደብተራዎች ሃሳብ ወይም ጽሁፍ በስሙና በፎቶው ሊያቀርብና ደረቱን ገልብጦም “ታሪክ አዋቂዎች እነ እከሌ ብቻ ናቸው” ብሎ መፈክር ለማሰማት በቋሚ አምደኝነት የተሰማራ ሰው የድንቁርና ሎሌ እንጂ የታሪክ ምሁር ሊባል አይችልም። ለማንኛውም ዝናሬ ሙሉ ነው ያሉን ፕ/ር መስፍን ይህንን የታሪክ ምሁራኑን ግብዝነት ለማጋለጥ ብዙ ተኩስ ያሰሙናል ብለን እንጠብቃለን። ሩም ታታ…ታታታ …ሩም…ታታ…ታታታ….ግብዝነት ይመታ!

   • Senait says:

    Dear Woldebirhan Sihul ,
    Thank you for the response and the excellent analysis you provide.However, for those people who are abroad and couldn’t read the newspaper, It’ll be reasonable to understand the issue by hearing from the two parties than simply reading what the Prof said. It would be my pleasure if this blog helped us to access what Berhanu wrote on Lielina. Thank you again

   • Dan says:

    ከላይ የሚከተለውን ያልኩት ያለምክንያት አልነበረም:: “ጣት የመቀሳሰሩ ኋላቀር የፖለቲካ ባህል (እሳቸው እንደሚሉት የከሸፈው የፖለቲካ ባህላችን) ከፖለቲካው መድረክ አልፎ “የተማረው ወገናችን” ላይም ለማዛመት ሲሞከር ከማየት የበለጠ ዘግናኝ ነገር አይኖርም::” ግ/ች ችሎማደር ይህ አስተያየት ባይጥማቸው ንፍጥ ማለቅለቅ ቢሉትም በጋህዱ አለም የታዘብኩት እውነታ እዚህም ላይ እየተደገመ ነው:: ውድ ወልደብርሃን ስሑል፥ አዩ ሰናይት የጠየቀችው በጣም አጭርና ግልጽ ጥያቄ ሆኖ ሳለ (በነገራችን ላይ እኔም የምጋራው ጥያቄ የአንዱን ወገን ሽርደዳ አዘል የመልስ ምት ብቻ ነው እያነበብኩ ያለሁት) ነገሩን ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ እየጎተቱት ይገኛሉ:: መጥፎው የፖለቲካ ባህላችን ወደዚህም ዘልቆ እየገባ ነው:: ቢቻሎት ሊንኩን ቢያቀብሉንና አንብበን የራሳችንን ሚዛን እንድንይዝ ቢያደርጉ ተመራጭ ነበር:: ካልሆነ ደግሞ ሚዛናዊ የሆነ ግንዛቤዎን ቢያካፍሉን ነበር አስተዋይነት እንጂ የአሁኑ ድርጊቶ “የቅልውጥ ልምጪቱን” እርሶ የያዟት አስመስሎቦታል 🙂 ለማንኛውም ከእርሶ መልስ አሁን እየታዘብኩ ያለሁት የቅንጅቱ ጊዜ የነበረውን ጎራ ይዞ እርስበእርስ የመሸካሸክ ዓይነት አባዜን ነው:: የከሸፈው የፖለቲካ ባህል ወደዚህ የምሁራን እሰጣገባ ሲዛመት ከአንደበቶ እንስማው: “ሩም ታታ…ታታታ …ሩም…ታታ…ታታታ….ግብዝነት ይመታ!” 😦

   • Thank you. Please be patient with us as we work to obtain the referenced article.

 5. Long live for professor mesfin Woldemariam!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!

 6. Dan says:

  I used to enjoy reading ideas that came out of Pr. Mesfin’s intellect. But lately, Pr. Mesfin is becoming extermly emotional and biased. Sometimes he indulged himself into unnecessary tit-for-tats. Admit that Mekshef is far below my expectation. I would expect much scholarly claims in such critical “topic” rather than mere emotions and bias toward his own ‘jebdu’. (Excerpts from my up coming review of Mekshef)

 7. Mekonnen says:

  Prof. which means all what you say is subject for no criticism. In which case you are GOD.kkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkk. I know you are guilty of murdering true Ethiopians, like Aklilu Habtewold, when you were presiding the killing of 60 officials of the monarch regime.

  • netsanet says:

   ወንድሜ መኮንን አንድን ግለሰብ በነፍስ ማጥፋት መክሰስ ከባድ ወንጀል ነው፡፡ ማስረጃህ የታለ… ነው ወይስ መረጃ እንጂ ማስረጃ የለህም!!! ጋሼ መስፍን አትተቹ አላሉም ያላልኩትን አትጨምሩ ነው ያሉት፡፡ እርሳቸውን የማከብረውን ያህል ፍፁም እንዳልሆኑ ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ አንተም ድክመታቸውን በጨዋ ደንብ በስነ-ስርዐት መንገር መፃፍ ነው እንጂ ተራ ክስ መደርደር አይገባም፡፡ በስም ማጥፋት ልትከሰስ እንደምትችል ታውቃለህ…….. ነው ወይስ ማን ያውቀኛል ብለህ ነው…… ሀገርህን የምትወድ ከሆንክ ከግለሰብ ማንነት በላይ ከፍ ብለህ ትምህርቱን ፈልግ፡፡ አንብብ ተማር ጠይቅ ተለወጥ አንተም ለሌውን ለውጥ፡፡ ሀገርህ ከአንተ ብዙ ትጠብቃለችና! የማይረባውን ትተህ የሚረባውን እንድትፈልግ እንድትይዝ እግዚአብሄር አምላክ ይርዳህ ይርዳን፡፡ አሜን

  • israbcdeisr says:

   Gashe Mekonen ere befetereh…ho wodew ayiseku alu

  • Gerazmach Chilomader says:

   willing mental slave mekonnen መኮንን ከዚህ ጭንቀት እና የማስተዋል ጨለማ እንድትወጣ ላንባዲና ያስፈልግሃል እምልህ ጮማ የሚያቀልጥ ሁሌ አግድም ማሰብ ደግ አይደለም ደግሞ ከ እውቀት ማነስ ደም ማነስ ይሻላል ደም ማነስ ቢያንስ ሳያንዘላዝል ይገድላል እውቀት ማነስ ግን እንዲህ ስድ ልቅ ያደርጋል

 8. Gerazmach Chilomader says:

  የብርሃኑንም አነበብኩ በሳምንቱ ለብርሃኑ የተጻፈውንም አነበብኩ መልሱ በድንብ ለብርሃኑ ተሰጦታል አሁን ደግሞ ያለ ባለቤቱ አይነድም እሳቱ እንዲሉ የኔታ በግሩም ማስረጃ ምላሽ ለብርሃኑ ተሰጧል
  ግን ግን ብርሃኑ ሲፈራ ሲቸር የጻፈው ጽሁፍ አንድ ቢሉ እንድ ቦታ እንኳ ዳር ሲደርስ አላየሁትም ነጥብ ሳያስጨብጠኝ በአራት ነጥብ እፎይ ሳይል የተደረተ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ለእኔ እንዲያውም የብርሃኑ ጽሁፍ ገና ረቂቁ ይመስለኛል የታተመው
  ሌላው ብርሃ በመጽሃፉ ላይ ያሉትን እውነቶች እና አመክንዮዎች ሳያነጥር የፈረንጅ ስም ማዕት ይደረድራል እንዚሁ ሁሉ የፈረንጅ ስሞች በተማረው መጽሃፍ ላይ በተሰጡት ክፍለ ትምህርቶች ሊኖሩ ይችላሉ ግን ከየኔታ መጽሃፍ ጋር በፍጹም አላሰናሰላቸውም ለእኔ ለአንባቢውም ቀለል ባለ መልኩ አልተጻፈም ለክርክርም አልተመቸም መቸም ስለ ገዛ ሀገራችን የፈረንጅ ምስክር እየጠራን አንከራከር ከዚህ አንጻር በዚያች ውድ ጋዜጣ በዚያ ቀን ብብርሃ ጽሁፍ አንድ ጋሻ የሚያክል ቦታ መወሰዱ ብርሃኑን ፊውዳል ወይም በዝባዥ የሚያሰኘው ይመስለኛል
  ዝናሬ ሙሉ ነው ላሉት የኔታ የኔም የሁል ጊዜ ጸሎቴ ምን ሆነ እና ሁሌም ዝናርዎት ሙሉ ይሁንልኝ
  አምላክ በቸርነት እድሜውን ከጤና ይቸርዎት ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን የኔታ
  ክፉውን ከደጉ እስክንለይ መብራት ይሁኑን
  ሁሉም የጋን መብራት በሆነበት ዘመን ባውዛነትዎ ለእኔ ምትክ የለውም

  • netsanet says:

   በዚያች ውድ ጋዜጣ በዚያ ቀን ብብርሃ ጽሁፍ አንድ ጋሻ የሚያክል ቦታ መወሰዱ ብርሃኑን ፊውዳል ወይም በዝባዥ የሚያሰኘው ይመስለኛል loooooool very funnnnny! loved it!

   • Gerazmach Chilomader says:

    ነጻነት ግራ ቢገባኝ እኮ ነው የራስ መስፍን ስለሺን ርዕስት የሚያክል ቦታ ላይ እኮ ነው የተንጎራደደው ብርሃኑ

 9. Tsinat says:

  ……………..ከማን ጋር ተማክሮ እንደሆነ የመጨረሻ ጥይት የሚል ውሳኔ ላይ የደረሰው አላውቅም፤ መገመት ቢችል ዝናሬ ገና ሙሉ ነው! ………………………. አገላለፁን ወድጄዋለሁ

 10. Senait T says:

  Prof. If you post what Berhanu Deboch wrote, it will help us to understand the issue more and to give our judgment .
  Thank you!!!

 11. ነፃነት አሸናፊ says:

  መገመት ቢችል ዝናሬ ገና ሙሉ ነው!
  ወይ መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ; ጉደኛ መፅሀፍ ሆነ እኮ!!!!! ወቸው ጉድ! እኔ የምለው ውይይት ተደርጎበትም ሰው አልገባውም፡፡ ለምን ይሆን….! እኔ የገባኝ መክሸፍ እራሱ በመደጋገሙ ባህልም ሆነ ታሪክም ሆነ/ነው የሚለው ነው፡፡ ታሪካችን ከሸፈ ሳይሆን ክሽፈት እራሱ የታሪካችን አካል ነው፡፡ ታሪክ ፀሀፍትም ይህንን ልብ አላሉም ቢሉም አልዘገቡም የሚለው ነው፡፡ አለመሳሳቴን ለማረጋገጥ ከተሳሳትኩም ለመታረም መፅሀፉን መድገም ይኖርብኛል፡፡ በተረፈ ጋሼ መስፍን እኔም እንደእርስዎ የመጨረሻ ጥይት የምትለዋ አልተመቸችኝም፡፡ እውነትም ከማን ተማክሮ ነው ያስብላል፡፡ መቼ ተማርንና ነው የመጨረሻ የሚባለው!!!!!!!!! ኧረ ገና ብዙ ይቀረናል በጣም ብዙ…. ከእርስዎ ብዙ እንጠብቃለን፡፡ እሰይ!!! እንኩዋንም ዝናርዎ ሙሉ የሆነ፡፡ ከተማሪ ቤት ያጣነውን ከእርስዎ እያገኘን ነው፡፡ ለምሳሌ አደጋ ያንዣበበት የአፍሪካ ቀንድ የሚለው መፅሀፍዎ ስለ ሀገሬ ስለ አለንበት አካባቢ ብዙ አሳስቦኛል አስተምሮኛልም፡፡ ሀገሬ ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ቢያሳዝንም ቢያስቆጭም አምላክ መቼም ሰው አሳጥቱዋት አያውቅም፡፡ ይኑሩልኝ ይኑሩልን፡፡ ቸሩ አምላኬ እድሜና ጤና ይስጥልኝ፡፡
  አክባሪዎ
  ነፃነት አሸናፊ

  • Dan says:

   ነጻነት አደጋ ያንዣበበት የአፍሪካ ቀንድ የሚለው መፅሀፍ ከአንድ የተማረና ሰፊ ግንዛቤ ካለው ሰው የሚጠበቅ ነው:: መክሸፍ ግን በጭራሽ ከፕ\ሩ የማይጠበቅ የሓሜት መጽሃፍ ነው:: ሲጀመር በጣም ከባድ ርዕስ መርጦ የተነሳ ሰው አካሔዱን መገምገም የነበረበት የተነሳበትን አላማ ዳር ከማድረስ አኳያ እንጂ እንደ እሳት በሚንቀለቀል የቁጭት ስሜት መግቢያው ላይ የተጻፈውን ስቶ ይዘቱን በሓሜትና ሚዛን በሌለው ሁለገብ ወቀሳ እስኪሞላው ድረስ በስሜት መነዳት አልነበረበትም:: ፕ|ሩ መጽሃፉን የሞሉት ራሳቸውን በሚያወዳድሱ: ሌሎችን በጅምላ በሚያሳንሱ ስሜታዊ አረፍተ ነገሮች ነው:: ከመጽሃፉ ሙሉ ይዘት ራሳቸውን የወቀሱባት ወይም ተጠያቂ ያደረጉባት አንዲትም ሓረግ አታገኝም:: ጣት የመቀሳሰሩ ኋላቀር የፖለቲካ ባህል (እሳቸው እንደሚሉት የከሸፈው የፖለቲካ ባህላችን) ከፖለቲካው መድረክ አልፎ “የተማረው ወገናችን” ላይም ለማዛመት ሲሞከር ከማየት የበለጠ ዘግናኝ ነገር አይኖርም:: “አካዳሚክ ሆነስቲ” የጎደለበት ስሜታዊና ዘረኛ መጽህፍ ከአንድ የተማረ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ያነበብሁት የፕ|ሩን “መክሸፍ”ን ነው:: ገና ብዙ ከሳቸው ስለምንጠብቅ ሊወደሱ በሚገባቸው ማወደስ ያለብንን ያህል: መተቸት ባለባቸው መተቸት ይኖርባቸዋል:: ለሁሉም መጽሃፉን ድጋሚ ረጋ ብለህ|ሽ ብቻነበው|ቢው አይከፋም:: ወደ አምልኮ ከሚጠጋ ከንቱ ውዳሴ ይታደግሃል|ሻል እንጂ ለክፉ አይሰጥም::

   • Gerazmach Chilomader says:

    ዳን ከተቹ በደንብ መተቸት ነው አለበለዚያ አላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል ነው ነገሩ ነጻነት የኔታን አነበባቸው ገቡት አከበራቸው አመሰገናቸው ከዚህ ባለፈ ምንም ከንቱ ውዳሴ የሚለው ሀተታ እዚህ ውስጥ እንዴት እንደደነጎርከው አልገባኝም እናም ውድ ዳን የራስህን ሀሳብ ራስህን ችለህ ለእሳቸው ግለጽ እንጅ ለነጻነትም እኔ ላስብለት የሚከብድ ይመስለኛል

   • Dan says:

    ውድ ግ\ች ችሎማደር
    ነጻነት “አለመሳሳቴን ለማረጋገጥ ከተሳሳትኩም ለመታረም መፅሀፉን መድገም ይኖርብኛል፡፡” ሲል ስላነበብኩት ነበር ድጋሚ ብታነበው አይከፋም ያልኩት እንጂ እኔ ላስብልህ ከሚል ግብዝነት ተነስቼ አልነበረም 🙂 ማወደስ እርሶም ቢሆኑ መብቶት ነው:: እንደሚመስለኝ “የኔታም” ቢሆኑ ሚዛናዊ ትችትን እንጂ (ከንቱ) ውዳሴን አይመርጡም:: ምንም እንኳን እስካሁን የተሰነዘረባቸውን ትችት በሙሉ ለመቀበል ቢቸግራቸውም ቢያንስ ስለራሳቸው ከሚጽፏቸው አንዳንድ ነጥቦች በመነሳት ትችትን እንጂ ውዳሴን የሚመርጡ አልመሰለኝም:: ሰላም!

Comments are closed.