ሰሞኑን———-

ሰሞኑን ኢትዮጵያን በአሜሪካ እርዳታ አንመራለን የሚሉት ሰዎች ገበናቸው ክፉኛ ተጋለጠ!
!. ‹‹የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የግራዚያኒን መታሰቢያ ዓለም-አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያወግዘው በይፋ ጥሪ አቀረበ፤›› (ሰንደቅ ጋዜጣ፣ ሚያዝያ 2/2005) ስለአገር ውስጥ ጉዳይ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አያውቅም ካልተባለ በቀር በሚያዝያ 8/2005 የግራዚያኒ ባለሐውልት መሆን ያንገበገባቸው ጥቂት ኢትዮጵያውያን ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ሲሞክሩ በፖሊስ እየተደበደቡ ተያዘው በወረዳ ዘጠኝ ፖሊስ ጣቢያ አድረው በበነጋታው ዋስ እየጠሩ ተለቀዋል፤ ለተራ ፖሊሶቹ አለቆቻቸው የነገሩአቸው ሰላማዊ ሰልፉ የየካቲት አሥራ ሁለትን ሐውልት ለማፍረስ የታቀደ ነበረ፤ ይህ ሐሰትና እኩይ ዘዴ ፖሊሶቹ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ እንዲጨክኑ ለማድረግ የታቀደ ስለነበረ እውነቱ እስቲታወቅ ሠርቶላቸዋል፡፡
የግራዚያኒ ተቃዋሚ ኢትዮጵያውያን ተደብድበውና ታስረው ካደሩ ከሠላሳ ቀኖች በኋላ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያንኑ ሰላማዊ ሰልፉ ሊደረግ የነበረበትን ጉዳይ ደግፎ በይፋ ሲናገር ምን አንበል? ፖሊሶቹ ያደረጉትን እሱ አልሰማም እንበል? ወይስ አሱ የተናገረውን ፖሊሶቹ አልሰሙም እንበል? ወይስ አንድ መንግሥት የለም እንበል? ወይስ ማናቸውም ባለሥልጣን ቢሆን የሚያደርገውን አያውቅም እንበል? እንደፈለጋቸው እንደበግ የሚነዱን ሰዎች ወዴት እንደሚነዱንም አያውቁትም እንበል? እኛስ ራሳችን ከፋሲካ በጎች የተሻልን አይደለንም እንበል?
ለመሆኑ እነዚያ በዱላና በእስር የተንገላቱ ኢትዮጵያውያንን ፖሊስ ይቅርታ ይጠይቃል ወይ? የጠሩት ዋስትና ሁሉ ይወርድላቸዋል? ካሣ ይከፈላቸዋል ወይ?
መቼም ይቅርታ መጠየቅ፣ ዋስትናን ማውረድ፣ ካሣ መክፈል ትምህርትና የኃላፊነት ስሜት ያስፈልጋሉ፤ በዚህ ላይ ለመፍረድ ውጤቱን እንጠብቅ፡፡

2. መጀመሪያ በጉራ ፈርዳ፣ በኋላ ደግሞ በቤኒ ሻንጉል በሺዎች የሚቆጠሩ አማርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ለብዙ ዓመታት ከነበሩበት ቦታ በግድ እየተፈናቀሉ መሰደዳቸውን ዓለም ሰምቶታል፤ የክልል ባለሥልጣኖች አልሰሙም ቢሰሙም የመይመለከታቸው አድርገው በማሰባቸው፣ የፌዴራል ባላሥልጣኖችም የማያገባቸው መሰሎ ስለታያቸው ሁሉም ገለልተኛ ተመልካች ባለሥልጣኖች ሆነው ቆዩ፤ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ስቃያቸውን ካዩ በኋላ፣ ብዙ ሰዎች ከሞቱ በኋላ፣ ብዙ ንብረት ከተበላሸ በኋላ፣ ጉዳዩ ብዙ መድረኮችን አልፎ፣ የአሜሪካንና የአውሮፓን መንግሥታት አልፎ በተባበሩት መንግሥታት ከደረሰ በኋላ ‹‹የቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ ርዕሰ መስተዳድር›› አቶ አህመድ ናስር ስሕተት ተፈጽሟል ማለታቸው ተገለጸ፤ (ሰንደቅ ሚያዝያ 2/2005)፣ ስሕተቱን የፈጸመው ‹‹ከታች ያለው አስተዳደር›› መሆኑ ተነገረ፤ አመራር ከታች ወደላይ ነው ወይስ ከላይ ወደታች? ለዚህ ሁሉ ሕዘብ መንገላታት፣ መታመምና መሞት ኃላፊነቱ ማን ላይ ይወድቃል? የጠፋውን ንብረትና ካሣ አንኳን አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት ትንሽ ዘግነው ቢወረውሩ ይበቃል፡፡

https://www.facebook.com/mesfin.woldemariam.5?fref=ts

 

Advertisements
This entry was posted in አዲስ ጽሑፎች. Bookmark the permalink.