አምስት:- ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም! የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዢንና ራድዮ፤ ነገረኛነትን እንዴት እንገራዋለን?

 መስፍን ወልደ ማርያም

ሚያዝያ 2005

ሳይንሳዊ ውይይትም ወይም ክርክር የሚመራው በሕገ-ኀልዮት ወይም በእንግሊዝኛ ‹‹ሎጂክ›› በሚባለው የአስተሳሰብ መመሪያ ነው፤ ይህንን አዚህ ለመዘርዘር ከባድ ነው፤ ግን ሁለት መሠረታዊ ቁም-ነገሮችን ማንሣት እንችላለን፤ አንደኛው የሕገ-ኀልዮት መንገድ ከዝርዝር ተነሥቶ ወደማጠቃለል የሚሄድ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከአጠቃላይ ወደዝርዝር የሚወርድ ነው፤ (የትና መቼ እንደሆነ አላስታውስም እንጂ ከዚህ በፊት በጻፍሁት ከታች-ወደላይና ከላይ-ወደታች በማለት እነዚሁኑ መንገዶች ለማስረዳት ሞክሬ ነበር፤ከታች ወደላይ ከዝርዝር መነሣቱን ሲሆን፣ ከላይ ወደታች ያልሁት ከአጠቃላይ የሚነሣውን ነው፤) በቀላል ምሳሌ ላስረዳ፤ ከበደ ሁለት ዓይኖች አሉት፤ ወርዶፋ ሁለት ዓይኖች አሉት፤ ዘነበች ሁለት ዓይኖች አሏት፤ …. እንዲህ እያልን በአካባቢያችን ያሉትን ሰዎች ሁሉ አንድ በአንድ (በዝርዝር) ከገለጽን በኋላ ሰዎች ሁሉ ሁለት ዓይኖች አሏቸው ወደሚል ትክክለኛ መደምደሚያ (ማጠቃለያ) እንደርሳለን፤ በዓለም ውስጥ ያሉ ሰዎችን ሁሉ ማዳረስ አንችልም፤ ከምናገኛቸው ሰዎች ዘጠና አምስት ከመቶው ሁለት ዓይኖች ያሏቸው ከሆኑ አልፎ አልፎ ያጋጠሙንን ዓይን የሌላቸውን ሰዎች በመጥቀስ ማጠቃለያው አይፈርስም ወይም አይሻርም፤ ከተጠኑት ሰዎች ውስጥ ቢያንስ ዘጠና አምስት ከመቶ የሚሆኑት ሁለት ዓይኖች እንዳሏቸው ከተረጋገጠ ሰዎች ሁሉ ሁለት ዓይኖች አሏቸው የሚለውን ማጠቃለያ እንደእውነት ተቀብለነው እያንዳንዱን ሰው በተናጠል ሁለት ዓይኖች አሉት ለማለት እንችላለን፤ ይህ ሳይንስ እውቀትን ለማስፋፋት የሚጠቀምበት መንገድ ነው።

ማጠቃለያው ተረጋግጦ ከተቀመጠ በኋላ ከአጠቃላይ ወደዝርዝር በሚወርደው መንገድም መጠቀም አንችላለን፤ ስለዚህም ሰዎች ሁሉ ሁለት ዓይኖች አሏቸው ከሚል ከደረስንበት ማጠቃለያ እንነሣና ከበደም፣ ዘነበችም፣ ወርዶፋም ሰዎች በመሆናቸው ሁለት ሁለት ዓይኖች አሏቸው፤ እያልን ከማጠቃለያው ወደዝርዝሩ እንደርሳለን፤ ልብ በሉ ማጠቃለያው የቆመው እያንዳንዱን እውነት በማስተዋል ላይ ነው፤ ከማጠቃለያው የምንነሣው ግን ከሀሳብ ነው፤ ሰዎች ሁሉ ሁለት ዓይኖች አሏቸው ከሚል ሀሳብ ተነሥተን ከበደ ሰው ነውና ሁለት ዓይኖች አሉት … እያልን ስለእያንዳንዱ ሰው እንናገራለን።

በሁለቱም የአስተሳሰብ መንገዶች ብዙ ጊዜ አስከፊ ስሐተቶች ይፈጸማሉ፤ አንድ ወይም ሁለት ምሳሌዎችን በመያዝ ቶሎ ወደማጠቃለያ አንዘላለን፤ ሁለት ወንዶች ያታለሏት ሴት ወንዶች ሁሉ አታላዮች ናቸው ወደሚል ማጠቃለያ ትደርሳለች፤ ወይም ሁለት ሴቶች ያታለሉት ወንድ ሴቶች ሁሉ አታላዮች ናቸው ወደሚል ማጠቃለያ ይደርሳል፤ በዓለም በሙሉ ያሉ ስንትና ስንት ሚልዮን ሴቶችን በሁለት በሚያውቃቸው ሴቶች ወክሎ መናገር የማሰብ ውጤት ሊሆን አይችልም፤ ማጠቃለያው ከስሜት የመነጨ እንጂ ትክክለኛ አስተሳሰብን ተከትሎ የተገኘ አይደለም፤ በዚህም ምክንያት እያንዳንዱ ሰው የራሱን ስሜት ብቻ እየተናገረ ወደስምምነት ለመድረስ በፍጹም አይቻልም፤ እንዲሁም እውነተኛነቱ ከአልተረጋገጠ ማጠቃለያ ተነሥቶ እያንዳንዱን እዚያ ውስጥ መክተት ወደፍጹም ስሕተት የሚያገባ ነው፤ በለጠና ዘለቀ ያታለሏት ሴት ወንዶች ሁሉ አታላዮች ናቸው ወደሚል የተሳሳተ ማጠቃለያ ደረሰች፤ ያንን የተሳሳተ ማጠቃለያ ይዞ ሌሎችም ወንዶች ሁሉ አታላዮች ናቸው ማለት አለማሰብ ነው፤ ቀደም ሲል እንደተባለው ወደትክክለኛ ማጠቃለያ ለመድረስ ሰፊ ጥናት ተደርጎ ቢያንስ ዘጠና አምስት ከመቶው የሚሆኑት ወንዶች አታላዮች መሆናቸው ሲረጋገጥ ነው፤ በለጠና ዘለቀ ብቻ ወንዶችን ሁሉ አይወክሉም።

ብዙ ጊዜ በችኮላና በጅምላ የሚነገሩ ነገሮች ስሕተት አለባቸው፤ በቶሎ ካልታረሙ ክርክር ሲገጥማቸው እየጠነከሩ ይሄዳሉ፤ ለምሳሌ ቀሚስ የሚለብስ ሁሉ ሴት ነው፤ ወይም ሴቶች ሱሪ አይታጠቁም፤ እነዚህ ዓረፍተ ነገሮች በእውነት ላይ የተፈናጠጠ ሐሰትን የያዙ ናቸው፤ ይህንን ለማፍታታት አልሞክርም፤ ለአንባቢው እተወዋለሁ፤ አብዛኛውን ጊዜም ንግግራችን የጅምላ ነው፤ ከጅምላ አነጋገር ፈጽሞ ለመውጣት አንችልም፤ ግን አእምሮአችን ማበጠርና ማጣራት እንዲችል፣ ቀጥሎም ተቃውሞ ሲመጣ ለመታረም እንዲዘጋጅ ማስለመድ ይጠቅመናል።

አእምሮው በአንድ ዓይነት ጥላቻ የተመረዘ ሰው ከሱ ዘር፣ ወይም ከሱ ጎሣ፣ ወይም ከሱ ቋንቋ፣ ወይም ከሱ ሃይማኖት … የተለየውን ሰው ሁሉ በስሜት ብቻ እያጠቃለለ በጅምላ ይጠላል፤ ይንቃል፤ ይሰድባል፤ ያዋርዳል፤ እያንዳንዱንም ሲያገኝ በአእምሮው ውስጥ ያስቀመጠውን ምስል እያየ ሰውዬውን ይገምተዋል፤ ሰውዬውን የሚገምተው እሱ ራሱ አእምሮው ውስጥ ባስቀመጠው ምስል ነው እንጂ ሰውዬው በሚናገረው ወይም በሚሠራው አይደለም፤ አንዳንድ ወንዶችም አንዲት ሴት ክፉኛ ስላቃጠለቻቸው ሴትን በሙሉ ይጠላሉ፤ ከአንድ ተነሥቶ ወደጅምላ መዝለል በጣም ከባድ ስሕተት ነው።

ሳይንስ በአብዛኛው የሚጠቀምበት በመጀመሪያው፣ ከዝርዝር ወደማጠቃለያው በሚወስደው የአስተሳሰብ መንገድ ነው፤ የሳይንስ ሕጎች ሁሉ የተገነቡት በዚህ ከዝርዝር ወደአጠቃላይ በሚወስደው አስተሳሰብ ነው፤ እያንዳንዱ ካልታወቀ ሁሉም በአጠቃላይ ሊታወቅ አይችልም፤ የተረጋገጠ እውቀት የሚጀምረው ከእያንዳንዱ ነገር ነው አንጂ ከጅምላ አይደለም።

በኢትዮጵያ የፖሊቲካ ንግግር ዋናው ጅምላው ነው፤ ለሰነፍ አእምሮ በጅምላ ማሰቡ በጣም ይቀላል፤ አንዳንዱን እያገላበጡ ከማጣራት ጅምላውን በሩቁና በግርድፉ መፈረጅ ቀላል ቢመስልም ስሕተት ነው፤ ከለመደም አእምሮን ያባልጋል፤ በፖሊቲካ በተለይ የተሳሳተ የጅምላ አስተሳሰብና አነጋገር አገርንና ሕዝብን ወደከፋ አደጋ ውስጥ የሚጨምር ይሆናል፤ ለዚህ ነው የተሳሳተ የጅምላ አስተሳሰብን በጥንቃቄ ማገላበጥ የሚያስፈልገን፤ ኢሳት በዚህ በኩል ትክክልና በጎ አስተሳሰብን ለማበረታታት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።

Advertisements
This entry was posted in አፈናና ከአፈና መውጣት. Bookmark the permalink.

7 Responses to አምስት:- ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም! የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዢንና ራድዮ፤ ነገረኛነትን እንዴት እንገራዋለን?

  1. Yared says:

    እስካሁን በተከታታይ ፕሮፌሰር መስፍን ያቀረቧቸው ጽሁፎች ብዙዎቻችንን አወያይቶአል፡አከራክሮአል አንዳንዴም ስሜታዊ በሆነ መልኩ ዘለፋና ስድብ እስከመለዋወጥ አድርሶአል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት የፕሮፌሰር መስፍን ጽሁፎች ውስጣችንን የመኮርኮር ሃይል ስላላቸው በራሳችን መንገድ ምላሽ እንድንሰጥ ስለሚያስገድዱን ነው፡፡
    የፕሮፌሰር መስፍን ማንኛውም ቃላት ከማይጥመው ጀምሮ እስከ ‘ፕሮፌሰር መስፍን ለምን ተነኩብኝ’ አስከሚለው ድረስ የተለያዩ ሰዎችን ታዝበናል፡፡
    ይሁንና በመሀከል ፕሮፌሰር መስፍን በሚያነሱት ነጥቦች በከፊል የሚስማሙ እና በከፊል የማይስማሙ ሰዎች አሉ፡፡በተለይ እነዚህ ሰዎች በትክክል ምክንያታቸውን በማስቀመጥ ሃሳብ ሲሰጡ ታዝቤያለሁ፡፡እኔ ከሁለቱ ጽንፈኛ አመለካከቶች ይልቅ የእነዚህ ሰዎች ሃሳብ እጅጉን ይማርከኛል፡፡ጽንፈኞቹ ሙግታቸውን ባብዛኛው የሰው ማንነት ላይ ሲያደርጉ እነዚህ ሰዎች ግን በተቃራኒው ሃሳቡን ሲሞግቱ ይታያሉ፡፡
    እንግዲህ እውነቱ የት ጋር እንዳለ ልብ ያለው ልብ ይበል!

  2. ከዚህ በተያያዘ ጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ አስተያየቶች እየመጡ ነው። ሆኖም ቁም ነገሩን በማስታከክ ስድብና ዘለፋ ይዘው ሲመጡ ለማስተናገድ የማይመቹ ይሆናሉ። ነፃ ውይይትን እንጂ ሰው ላይ ያነጣጠረ ስድብን ይህ ገፅ ለማስተናገድ አልተዘጋጀም።

  3. Kacha says:

    የተከበሩ ፕሮፌሰር፣
    ለዚህ ጹሑፎ ዋቢ ምስክር ሩቅ መሄድ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፤ ምክንያቱም በባህርዳር አንድ ወታደር የፈጸመውን ዜና ተከትሎ ኢሳት ዜናውን እንዴት አድርጎ፣ አንድን ብሔር ካንዱ ሊያቆራቁስ በሚችል መልኩ ዘግቦት አንብቤያለሁና፡፡
    ኧረ ለመሆኑ እስከመቼ ነው የልማታዊ ጋዜጠኞችና የ “አክቲቭስቶች” መጫወቺያ የምንሆነው? . . . ፣ መቼስ ነው የጋዜጠኝነትን ሀሁ ጠንቅቆ በተረዳ መረጃ እፎይ የምንለው? .

  4. Andinet says:

    “የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዢንና ራድዮ፤ ነገረኛነትን እንዴት እንገራዋለን?” የሚለው የጽሁፉ ርእስ ክፍል አንዲሁም የእርስዎ ተከታታይ ጽሁፎች ኢሳትን ነገረኛ እንደሆነ የደመደሙ ይመስላል፡፡ ነገረኝነት በባህላችን እንዲሁም በፖለቲካችን ስር መስደዱ ኢሳትን ነገረኛ አያደርገውም፡፡ ኢሳትን በጅምላ ነገረኛ ብሎ ከመፈረጅ በፊት ኢሳትን ነገረኛ የሚያስብሉ ነጥቦች መዘርዘር ነበረባቸው፡፡ ለነገሩ እርሶ እንዳሉት በኢትዮጵያ የፖሊቲካ ንግግር ዋናው ጅምላው ነው፡፡

    • Teddy says:

      አይተ አንድነት፤ ያልተጻፈ ነገር፣ ከውስጥህ አውጥተህ ለምን ታቀረሻለህ? ፕሮፍ እንደዚያ አላሉም። የአማርኛ መረዳት ችግር ከአለብህ ወይም ሆን ብለህ ነገር ለመጠምዘዝ ካልሆነ፤ እርሳቸው ያሉት በጣም ግልጽና ግልጽ ነው። በተለይ ለእንዳንተ ላሉ፤ አእምሯቸው ለባለገ ሰዎች፤ ሁነኛ ክኒን ናት። በቀን ሶስቴ ጧት፣ቀንና ማታ) ብታነባት፤ ወደ እውነተኛ ሰውነተህ የመመለስ ሃይል አላት። እስኪ ሞክራት!

      • Andinet says:

        ወንድሜ ለስድብ ከመቸኮልህ በፊት የገባህን ለማስረዳት ብትሞክር የተሻለ ነው፡፡ ለማንኛውም በክፍል ሶስት ፕሮፌሰሩ የተናገሩትን ካላነበብከው ልጥቀስልህ፡-
        “……ከላይ ስጀምር ኢሳት የባህል ይዘት አለበት ያልሁት ነገረኛነትን ነው፤ ኢሳት የጠምንጃ-ያዥነትንና የጉልበተኛነትን ትምክህት ‹‹አከርካሪውን ሰብሮ›› የነገረኛነትን ባህል ስር ለማጠናከር የሚጥር ይመስላል፤ ይመስላል ከምል ነው ብል ደስ ይለኝ ነበር….”

  5. Yihonal Ayikerm says:

    It is true. This is the worst way of approaching an issue in an attempt to explain or convince others. I have experienced this way of addressing issues by considerable number of highly educated people who have done researches. For example, following the death of Meles Zenawi, a professor (medical doctor) said that if there is anyone who is happy on the death of Meles, he must be mentally ill. I was shocked and angry at him. I discussed a lot on the issue. Finally, he admitted his mistake infront of some TPLF disciples.
    May God liberate our people from such way of thinking, and of course from TPLF.

Comments are closed.