ለአንዳንድ አስተያየቶች መልስ

መስፍን ወልደ ማርያም

ግንቦት 2005

በጽሑፎቹ ላይ የቀረቡት አስተያየቶች በመሠረቱ ሁለት ዓይነት ናቸው፤ አንዳንዶቹ እንደምክር ያለ ነገር፣ አንዳንዶቹ ጽሑፎቹን መውደዳቸውን ወይም አለመውደዳቸውን በመግለጽ ጽፈዋል፤ በነዚህ ላይ ምንም አስተያየት የለኝም፤ መውደድም ሆነ መጥላት፣ መንቀፍም ሆነ ለወደፊት የምሻሻልበትን ምክር መስጠት መብታቸው ነው፤ በግድ እኛ የምንልህን ተቀበል ሲሉኝ ከመብታቸው ያልፋሉ፤ ቢሆንም መልስ አያስፈልጋቸውም።

ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ወደፍሬ-ነገሩ ውስጥ ገብተው ለመሞገት ይሞክራሉ፤ ግልጽ የሆነ የሁነት ግድፈት ሲያገኙ ቢያመለክቱኝ በደስታና በምስጋና እቀበላቸዋለሁ፤ ሁነቱ ለእነሱ በሚጥም መንገድ ባለመገለጹ ወይም ሁነቱን እነሱ የሚወዱት ባለመሆኑ ሙግት ውስጥ የሚገቡ ሲሆን የማይጠቅም መሆኑን ስለተረዳሁ አንድ ዘዴ አቀረብሁ፤ ሁነቱ እኔ ከገለጽሁት ውጭ ሆኖ ከተገኘ አምስት መቶ ብር እከፍላለሁ ብዬ ጻፍሁ፤ እስከዛሬ ብሩን የጠየቀኝ የለም፤ ሊሞግተኝ የሞከረውም አዋቂ ነኝ-ባይ ከዝምታ አልወጣም፤ ፍሬ-ነገሩ ሙግት የሚያቀርቡ ሰዎች ሁለት ዓይነት ይመስሉኛል፤ በቅን መንፈስ በውይይቱ ላይ አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚፈልጉ አሉ፤ ሌሎች ደግሞ ሌላ ሰው ሲጽፍ እየጠበቁ ‹‹እኛ የተሻለ አለን›› እያሉ የሚጮሁ አሉ፤ ዓላማቸው ውይይቱን ለማዳበር ሳይሆን ራሳቸውን አብጧል ከሚሉት ሰው እኩል ማሳበጥ ቢቻልም መብለጥ ነው፤ በራሳቸውም ሆነ በሀሳባቸው እምነት ስለሌላቸው የሚናገሩት ራሳቸውን በመቃብር ውስጥ ከትተው ነው፤ በመቃብር ቤት ውስጥ ማበጥ ለምስጦች እንደሆን እንጂ ለሌሎች ‹‹የጭቃ እሾህ›› የሚል ስያሜን ከማትረፍ አያልፍም።

በተከታታይ በቀረቡት ጽሑፎች ላይ ሁለት አንባቢዎች በተቸገሩባቸው ሀሳቦች ላይ አስተያየቴን ልስጥ፤ በመጀመሪያ አርበኛና ባንዳ የሚባሉትን ቃላት የማይወዳቸው አንባቢ ችግሩ አልገባኝም፤ ስገምተው ከቅን መንፈስና ከኢትዮጵያዊ ይሉኝታ ጋር የተያያዘ ይመስለኛል፤ አርበኞችና ባንዶች መኖራቸውን የካደ አይመስለኝም፤ አርበኞች ነበሩ፤ አሁንም አሉ፤ ባንዶችም ነበሩ፤ አሁንም አሉ፤ አርበኛም የለም፤ ባንዳም የለም ለማለት አልችልም፤ ባንዳነት ሲነሣ ኅሊናቸውን የሚቆረቁራቸውና የሚያፍሩ ባንዳዎችና የባንዳ ልጆች ከአሉ፣ ይቆርቁራቸው፤ ይፈሩ፤ የሚያሳፍር ሥራ ውጤት ነው፤ አርበኝነት ሲነሣ ልባቸው የሚያብጥና የሚኮሩ ካሉ፣ ይበጡ፤ ይኩሩ፤ የሚያኮራ ሥራ ውጤት ነው፤  ምንድን ነው ስሕተቱ? የታሪካችን መክሸፍ አንዱ ምክንያት በይሉኝታ ዓይኖችን ሸፍኖ ፍሬውንና አንክርዳዱን ለመለየት አለመፈለግ ነው፤ (በአሥራ ዘጠኝ መቶ አርባዎቹ አጋማሽ ላይ በጾም ጊዜ በምግብ ቤቶች የሚቀርብ የፍስክ ወጥ ነበረ፤ ሽፍንፍን ይባል ነበር፤ ሳይጾሙ የሚጾሙ መስሎ ለመታየት፤) እንክርዳዱንና ፍሬውን እኩል አድርጎ ለማየትና ለማሳየት መፈለግ ነው፤ የኢትዮጵያ አርበኞች ታሪክ ተዳፍኖ የቀረው በአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ውስጥ ባንዶች ተሰግስገውበት ስለነበረ ነው፤ በዚህም ምክንያት ፍሬና እንክርዳዱ ሳይለይ አንዱ ትውልድ ለሚቀጥለው ትውልድ እያስተላለፈ መማርና መሻሻል ያቅተናል፤ አንባቢው ይህንን ይመኛል ብዬ አልገምትም፤ እውነትን የሚገፋ፣ እውነትን የሚያደበዝዝ፣ እውነትን የሚያጨልም ነገር ሁሉ በአገርም ሆነ በግለሰብ ደረጃ መጨረሻው ገደል ነው።

ሁለተኛው ምንም አንኳን በጎ ፈቃድ ከሌለው ሰው የተሰነዘረ ቢሆንም ሌሎችን ሰዎች ሆን ተብሎ ከሚረጨው መርዝ ለመጠበቅ ባጭሩ በአንድ ሀሳብ ላይ ብቻ የሰውዬውን ጤናማ ያልሆነ ዓላማ ላሳይለት፤— እኔ የሚከተለውን ጻፍሁ፤–

የኢሳት መክሸፍ የኢትዮጵያውያንን ተስፋ ያጨልማል፤ አንፈራጥጠው ከላይ ቤት እታች ቤት እየቀላወጡ አካላቸውን፣ አእምሮአቸውንና መንፈሳቸውን የሚያባልጉ ሰዎችን ያበራክታል፤ የድብቅብቆሽ ዓለምን እየፈጠሩ የጠራውን ከደፈረሰው፣ የጸዳውን ከአደፈው፣ ሳይለዩ ለሚያወሩት ደካሞች ሜዳውን ያሰፋላቸዋል፤ የወያኔ/ኢሕአዴግን ፍርሃት ወደመርበድበድ ይለውጠዋል፤ የጦርነት ጥሩምባ ለሚነፉትም ሜዳውን እያሳየ  የቀረርቶ በር ይከፍትላቸዋል፤ ይህ ሁሉ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምንና ስምምነትን፣ እድገትንና ብልጽግናን፣ ኩራትንና ክብርን አያስገኝም።

በነዚህ አምስት መስመሮች ላይ የሰፈረው ሀሳብ አስቸጋሪ አይደለም፤ ማንበብና መጻፍ እችላለሁ ለሚል ሰው ቀላል ነው፤ ዋናውና መሪው ሀሳብ የኢሳት መክሸፍ የኢትዮጵያውያንን ተስፋ ያጨልማል፤ የሚለው ነው፤ አራት የሚሆኑ አጫፋሪ ሀሳቦች ተከታትለው ቀርበዋል፤ የኔን ጽሑፍ ሲያነብ አንጎሉ እያጠናገረ የሚመዘግብለት ሰው ሲጽፍም አንጎሉ አጠናግሮ የመዘገበለትን ስለሚያቀርብለት የተወላገደ መደምደሚያ ላይ ይደርስና ያንኑ ለሌሎች አዋቂ መስሎ ያስተላልፋል፤ ላንዳንዶች ሰዎች ይህ አገላለጼ የከረረ ይመስላቸው ይሆናል፤ በአውነት ይህ አገላለጽ ከበጎ መንፈስ የመነጨ ነው፤ በጎ መንፈስ የሌለበት አገላለጽ ብመርጥ የበለጠ የሚያስከፋ ይሆን ነበር፤ የእውነት ውበት የሚታየው ጨለማውን ሲገልጠው ነው፤ አንዱ አስተያየት ሰጪ እንዳለው ‹‹የጭቃ እሾሁን›› ማየት መቻል ነው፤ እንግዲህ ከላይ የተጻፈውን ሰውዬው እንዴት አወላግዶ እንደተገነዘበውና እንዴት አወላግዶ እንዳወጣው እዩት፤ —

“የኢሳት መክሸፍ የኢትዮጵያውያንን ተስፋ ያጨልማል፤ ………………………………የጦርነት ጥሩምባ ለሚነፉትም ሜዳውን እያሳየ የቀረርቶ በር ይከፍትላቸዋል፤ ይህ ሁሉ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምንና ስምምነትን፣ እድገትንና ብልጽግናን፣ ኩራትንና ክብርን አያስገኝም። ”እኔም ‹ለሃገራችን ችግር መፍትሄው አንድ መንገድ (የእርሶ መንገድ) ብቻ አይደለም› ያልኩት ኢሳት ነጻ ሚዲያ እንዲሆን የምንሻ ከሆነ ከመርህ አኳያ ሁሉንም በእኩል መድረክ መስጠት እንዳለበት ለመግለጽ ፈልጌ ነው፡፡ ከተሳሳትኩ ለመታረም ዝግጁ ነኝ።››

እግዚአብሔር ያሳያችሁ! ከላይ በትክክል የጠቀስሁትና ይህ ተቆራርጦና ተወላግዶ የቀረበው አንድ ናቸው? እኔ ከጻፍሁትስ እንዴት ብሎ ከውልግድግዱ የተሰጠው መደምደሚያ ሊወጣ ይችላል? ‹‹የጭቃ እሾህ›› ለምን ይጠቅማል? ለማን ይጠቅማል? በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሔው አንድ መንገድ ብቻ ነው (የኔ ብቻ) ያልሁት የት ነው? ተከታታይ ጽሑፎቹን ሁሉ ያነበበ ሁሉ የተለያዩ አመለካከቶች በእኩልነት ይስተናገዱ የሚል እንደሆነ ከዚህ ሰው በቀር የተረዳው ይመስለኛል።

‹‹ከተሳሳትሁ ለመታረም ዝግጁ ነኝ›› የምትለዋ አስቂኝ ነች!  የተሞከረው ማታለል አልሠራ ሲል ወደሌላ ማታለል! አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት መች ይሰማል!

Advertisements
This entry was posted in አፈናና ከአፈና መውጣት. Bookmark the permalink.

9 Responses to ለአንዳንድ አስተያየቶች መልስ

 1. Teddy says:

  አቶ አንድነት በእርግጥ የዘለፋ ቃላት ሊያም ይችላል፤ ባስ ሲልም ያሳብዳል። የሰውልጆች እንዲህ አይነት ቃላትን እንደ አስፈላጊነታቸው ሲጠቀሙ ኑረዋል፤ እየተጠቀሙ ነው። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፤ ክርስቶስም እንደተጠቀመባቸው መዘንጋት የለብዎትም! ትልቁ ነገር፤ እንዲህ አይነት ቃላት ወደ እርስዎ ከተሰነዘረ፤ ቆም ብሎ ለማሰብ ይረዳል! ለምን እንዲህ ተባልሁ? ምን ሰራሁ? ምን አስቀይምሁ? እያሉ እራስዎን ለማረም የሚረዳ፣ ጠቋሚ በትር ነው። የሰው ልጅ ሲብስበት እንኳን የዘለፋ ቃላት፤ ወደ ጦርነትም ይገባል-አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ። ፕሮፌሰሩ የተጠቀሙባቸውን ቃላት ብቻ መርጦ አውጥቶ፤ እርስዎ ዘላፊ ነዎት፤ ብሎ ለመኮነን መንደርደር ግን ትርፉ ድካም ነው። ከወንጌል ክርስቶስ የተጠቀመባቸውን የዘለፋ ቃላትን መርጠን ማውጣት፤ ክርስቶስን ዘላፊ ወይም ተሳዳቢ እንደማያደርገው!!
  እናም አቶ አንድነት፤ ፕሮፌሰሩ ተከታታይ ጽሑፎቹን ሲያወጡ፤ ከመጀመሪያው ጀምረው፤ በእርስዎ ግንዛቤ መሰረት፤ ስህተት ያሏቸውን እየመዘዙ፤ ፕሮፌሰሩን ከመስመር ለማስወጣት፤ ሲታትሩ ተመልክቻለሁ። ለማረጋገጥ ከፈለጉ-አስተያየትዎን ደግመው ያንብቡ!! አስታውሳለሁ፤ አቅጣጫዎ ስላላማረኝ፤ ፕሮፌሰሩ ከተጠቀሙባቸው የዘለፋ ቃላት በከረረ መልኩ፤ የራሴን በእርስዎ ላይ ያለኝን ግንዛቤ አስቀምጫለሁ።
  አቶ አንድነት፤ ይቅርታ ያድርጉልኝና፤ የወያኔ እስኪብርቶ ይመስሉኛል! በፕሮፌሰሩ ጽሑፍ ብቻ ሳይሆን፤ ሌሎቹም በሚያወጡአቸው፤ ቅን የሆኑ ኢትዮጵያዊ ጹሑፎች ላይ፤ ተናዳፊ የሆኑ የእርስዎን አስተያየቶች አንብቤያለሁ! እባክዎትን ቆም ብለው ያስቡበት። አገራችን ነጻ ብትወጣ፤ እርስዎም ነጻ ይወጣሉ። የሌላ መጠቀሚያ ከመሆን ነጻ ይወጣሉ። የነጻነት አየር እኩል ይተነፍሳሉ!!! ስለዚህ፤ የወያኔን ካባ ውልቅ አርገው፤ ማንነትዎን ይዘው፤ ውሃ በሚቋጥር ክርክር ውስጥ እንግባ!

  • Andinet says:

   ውድ ቴዲ
   ብዙ ጊዜ ሰዎችን በሃሳባቸው መሞገት ሲያቅተን ሰዎችን ወደ መፈረጅ እንገባለን፡፡ ስለዚህ እኔን ከመፈረጅ ይልቅ በአስተያየቴ ላይ ቢያተኮሩ ለውውይትም ገንቢ ይሆናል፡፡
   በመጀመሪያ የኔ ሃሳብ እርስዎ እንዳሉት ተናዳፊ ሃሳብ ወይም ፕሮፌሰር እንዳሉት መርዘኛ ሃሳብ አይደለም፡፡ ሃሳቡ እናንተን ካልመረዘ ሌላውን እንዴት ሊመርዝ ይችላል ? ወይስ እኛ አዋቂ ስለሆንን አንመረዝም ሌላው ግን አላዋቂ ስለሆነ ይመረዛል ለማለት ነው ?
   ፕሮፌሰር የሚጠሏቸው ወይም የማይደግፏቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይህንንም በተመለከተ በግልጽ የሰዎቹን አመለካከት መነሻ በማድረግ በጨዋነት ገንቢ በሆነ ሁኔታ መተቸት አንድ ነገር ነው፡፡ ነገር ግነ ለኢሳት ምክር በሚል ሽፋን ዳን እንዳለው በጎራ እየከፋፈሉ ጨዋነት በጎደለው ሁኔታ መዝለፍ ሌላው ቢቀር ቢያንስ ሚዛናዊ ትችት አደርገውም ፡፡
   በተለይ ደግሞ ትልቅ ተጽዕኖ ሊፈጥሩ በሚችሉ በተከበሩ ፖለቲከኞች ወይም ምሁራን በተለይ በፕሮፌሰር መስፍን ሲቀርብ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ነው የኔ ሙግት፡፡ በጣም የሚቆጨኝ እና የሚያመኝ ደግሞ የፕሮፌሰሩ አመለካከቶች ገንቢ በሆነ መልኩ ቀርቦ ቢሆን ኖሮ በተለያየ መንገድ ለዚህች ሀገር ችግር የራሳቸው ጥረት የሚያደርጉ ውድ ኢትዮጵያንን ጎራ ሳይከፋፍል አንድ አድርጎ በአንድነት ያሰልፍ እንደነበር ሳስብ ነው፡፡ የእሳቸው የትችት አካሄድ በ1997 ምርጫ ወቅት ያመጣው ውጤት መከፋፈል፤ መለያየት ነው ያተረፈልን፡፡ አሁንም ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ያልኩት ለዚህ ነው፡፡
   በአጠቃላይ የእኔ አስተያቶች በሙሉ የሚያጠነጥነው በአንድ ጭብጥ ላይ ብቻ ነው፡፡ ይሀውም ለአንድ ዓላማ የተሰለፍን አትዮጵያዊያን መንገዳችን የተለያየ ሆኖ በጋራ መስራት ቢያቅተን እንኳን አንዳችን የሌላውን አካሄድ የማናከብረው ወይም የምናጣጥለው ለምንድን ነው? ይህን ባህል ለማዳበር የግድ “ያ ትውልድ” የተባለው እስኪያልፍ እንጠብቅ ?

 2. Dan! says:

  ውድ ፕ/ር መስፍን: አስተያየቴን በቅንነት ስላዩትና መልስ ስለሰጡበት በቅድምያ ላመሰግኖት እወዳለሁ:: ሆኖም የሰጡት መልስ አመክንዮ የጎደለውና በስሜታዊነት የታጀበ ይመስለኛል:: እርሶ እንዳሉት ችግሬ ከቃላቱ ጋር አይደለም:: ቃላቱን ስሰማ ደስ ስለማይለኝ ወይም ስለማልወዳቸውም አይደለም:: ቅሬታዬ ከቃላቱ ጀርባ ያለው የተሳሳተ የሰዎች ግንዛቤ ነው:: በዚህ ረገድ እርሶም በጣም የተሳሳተ ግንዛቤን ይዘዋል እላለሁ:: ይህን የምለው በተደጋጋሚ ሲገልጹት ከምሰማውና ከማነበው ተነስቼ ነው::

  በቅድሚያ ስለ አርበኛና ባንዳ መኖርና አለመኖር ትንሽ ልበልና ስለ ይሉኝታ ደግሞ ላስከትል::

  የኔ ጥያቄ ባንዳ አለ ወይስ የለም የሚል አይደለም:: እንደየ አመለካከታችን ሰዎችን የባንዳነት ቅጥያ ስለምንሰጣቸው ሊኖርም ላይኖርም ይችላልና:: ጥያቄዬ የሚጀምርው ከትርጉም ነው:: በተለይ ባንዳ ስንል ምን ማለታችን ነው? ማንን ምን ስላደረገ ነው ባንዳ ብለን የምንፈርጀው? ማን በማን አይንና ሚዛን አርበኛ ይባላል ነው? በማን ሚዛንስ ባንዳ ይባላል? በአብዛኛው የእርሶ ጽሁፍ ላይ እንደሚንጸባረቀው ባንዳ ማለት “አገሩንና ያገሩን ጥቅም ለባዕድ አሳልፎ የሚሰጥ ዜጋ” ማለት ከሆነም፤ የማን ጥቅም የአገርን ጥቅም ይወክላል? ነው ጥያቄዬ::

  “የአገርን ጥቅም ለባዕድ አሳልፎ ይሰጣል: የአገሪቱን ጥቅም በተደጋጋሚ አላስጠበቀም” ተብሎ ያለውን አፋኝና “ልማታዊ” ስርዓት በባንዳነት የሚፈርጁ በርካታ ዜጎች አሉ:: በተቃራኒው ደግሞ ከግብጽና ከኤርትራ ጋር በመተባበር የአገራቸውን የልማት እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ ተግተዋል: ለምሳሌ የአባይ ግድብ እውን እንዳይሆን ጠንክረው ይሰራሉ: በሚል ፍርጃ የባንዳነት ቅጥያ ከገዢው መደብ የተሰጣቸው በርካታ የተቃዋሚ ጎራ አሉ:: በዚህ ረገድ እርሶም ከዚሁ ሳይመደቡ አይቀሩም:: ጠበብ ሲል ደግሞ እነ አብርሃ ደስታን የመሳሰሉ ኢትዮጵያውያን ከእርሶና እርሶን ከመሳሰሉ ሌሎች ኢትዮጵያውያን አጋሮቻቸው ጋር በመተባበር ጸረ ህውሓት እንቅስቃሴ አድርገዋል ተብሎ በአካባቢያቸው በባንዳነት ሲፈረጁ እናያለን:: ይህ ሁሉ የሚያሳየን ሰዎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ልዩነት ምክንያት እርስ በእርስ የሚሰጣጡት ስያሜ እንጂ ይህ ነው የሚባል ወጥ ትርጉም እንደሌለው ነው:: ሌላው ቢቀር: አንዳንዶች ላገራቸው መስራት ባይችሉና አገራቸው ብትገፋቸው፤ “ለባዕዳን ጥቅም” ስለሚሰሩ ተብሎም ባንዳ ሲባሉ እንሰማለን:: ካልተሳሳትኩ እርሶም በዚህ መልኩ የሚፈርጇቸው ሰዎች እንዳሉ ከስራዎቾ ያነበብኩ ይመስለኛል::

  ውድ ፕሮፌሰር: ከላይ ያቀረብኩት በኛ ዕድሜ በአይናችን እያየን በጆሮዎቻችን እየሰማን የባንዳነት ስያሜን ስለሚሰጣጡት ዜጎቻችን ጥቂት አብነቶችን ነው:: ከጊዜ ጋር ወደ ኋላ ብንመለስም ተመሳሳይ ስያሜን ነው የምናገኘው:: ለምሳሌ ስለችጋር በሚያትት ቆየት ያለ አንድ ጥናታዊ ጽሁፎት ያቀረቡትን ማየት ይቻላል:: በንጉሱ ዘመን ርሃብ የሰሜኑን የአገራችን ክፍል ባጠቃበት ጊዜ፡ ለጥናት ሄደው አይተው የተመለከቱትን ለቤተ መንግስቱ ሰዎች ባቀረቡ ጊዜ የተሰጠዎት ምላሽ እንኳንና የተራቡትን ዜጎች ቀርቶ: እርሶንና እርሶን መሰል ቅን ኢትዮጵያውያን ምን ያክል እንዳስቆጣ ከስራዎት መገንዘብ ይቻላል:: በዛ አይነት ግፍ የተንገፈገፈ ዜጋ: ለቤተ መንግስት ቀለብተኞች በግብር ጉልበቱን አላሽቆ አቅሙን የሟጠጠ ዜጋ: ከማንኛውም ሃይል ጋር ይሁን (ከባዕዳንም ጭምር) ተባብሮ ያንን ግፈኛ ስርዓት ቢወጋ በማን እይታና ሚዛን ባንዳ ይባላል? እርሶ ከአቦይ ስብሓት ጋር በሚከራከሩበት ጊዜ የጠቀሱትና ደጋግመው አንባቢዎቾ እንዲያነቡት በሚመክሩት በአዶልፍ ፓርላስክ (ትርጉም በተጫኔ ጆብሬ) ስራ የሚታዩት የሰሜን “ባንዳዎች” የዚህ አይነት ስርዓት ውጤት ናቸው:: አንድን ዜጋ አገሩ እንደ አንድ ዜጋ ልትቀበለው ካልቻለች: ራሱን ከአገሪቱ ነጥሎ ቢያይና ለራሱ ጥቅም መቆም ቢጀምር: ባንዳ የሚያስብለው ምክንያት ምንድን ነው??? ይህንን ባለመገንዘብ የቆየወን የባንዳነትና የአርበኛነት ስያሜ ይዘው በመዝለቆና በመደጋገሞ ነው ስሜታዊና አመክንዮ የጎደለው ነው የምሎት::

  እዚህ ላይ አንድ ነገር ግልጽ ማድረግ እወዳለሁ:: መስሏቸውም ይሁን በትክክል: ለአገራቸው አንድነት የተዋደቁ: ነገር ግን ታሪካቸው ቀርቶ ሞታቸው በቅጡ ያልተነገረላቸው አርበኞች እንደነበሩን አንድና ሁለት የለውም:: እነዚህ ሊዘከሩም ሊወደሱም ተገቢ ነው:: የአርበኛነትና የጀግና ትርጉማችንና ስያሜያችን ጠበብ ብሎ አንዱን ጎራ ከሌላኛው ጎራ የተለየ ጀብደኛ ለማስመሰል ስንጠቀምበት ግን አሁንም ኢምክንያታዊ ይሆናልና አይመቸኝም:: ልክ እርሶ በፌስቡክ ገጾ ላይ ሚያዝያ 27ንና የካቲት 23ን ጠቅሰው የግንቦት 20ን ትርጉም እንደጠየቁት ማለት ነው:: ወደ ኋላ መለስ ብለን ብንመለከት እንዲሁ ሰዎች በዚህ መልኩ የአርበኛነትና የጀግናነት ማዕርግ ተሰጥቷቸው እናያለን:: የአንዱ ጀግና የሌላኛው ወገናችን ጨቋኝና በዝባዥ መኖሩን ማስታወስ እንኳን አንፈልግም:: ለዚህም ነው አርበኛና ባንዳ ብለው የሚከፋፍሉት ጎራ የማይመቸኝና ገና በጽሁፎ ሳየው የሚቀፈኝ:: ከአንድነትና መቻቻል ይልቅ መራራቅንና መለያየትን እንደሚያስከትልም የተገነዘቡት አይመስለኝም::

  ጥቂት ደግሞ ስለ ይሉኝታ ልበል::

  ውድ ፕ/ር: ይሉኝታ ሲበዛ ነው ክፋቱ እንጂ አንዱ በጎ ባህላችን ይመስለኛል:: እውነታ ኮ ሁሌም በጎ ላይሆን ይችላል:: አንዳንዴ በይሉኝታ ታስረንም ቢሆን ለፍቅር: ለአንድነት: ለመግባባትና ለመቻቻል ሲባል የምንዘላቸው ግድፈቶች ይኖራሉ:: ይሉኝታ ቢስነት: ለኢትዮጵያዊ ዕሴቶች ትልቅ ቦታ ከሚሰጥ እንደእርሶ ካለ ሰው የማይጠበቅ ነው:: ለምሳሌ ከላይ ያቀረብኩት የባንዳነት ጥያቄና አስተያየት ለጊዜው ትክክል አይደለም እንበልና: እርሶ እንደሚሉት በትክክል ባንዳ ነበር እንበልና: በምን አይነት አመክንዮ ነው “ባንዳነት ሲነሣ ኅሊናቸውን የሚቆረቁራቸውና የሚያፍሩ ባንዳዎችና የባንዳ ልጆች ከአሉ፣ ይቆርቁራቸው፤ ይፈሩ፤ የሚያሳፍር ሥራ ውጤት ነው” ሊሉ የቻሉት? እውነቱን ለመናገር እንኳንና እርሶን ከመሰለ የብዙዎች አርአያ የሆነ ሰው ቀርቶ: ከእንደኔ አይነቱ ተራ ሰው እንኳን የማይጠበቅ ይሉኝታና ህሊና ቢስነት ይመስለኛል ይሄ:: የእርሶን ህሊና ጥያቄ ውስጥ ማስገባቴ እንዳልሆነ መቼስ ይረዱልኛል:: ይህን ብል የራሴን ጤነኛነት ነው ሊያጠያይቅ የሚችለውና:: የዚህ አመለካከት ተቀጽላ የሆነውን የቅርብ ጊዜውን ክስተት: ማለትም አባት “ባጠፋው” ልጆቹ ሲቀጡ ያወገዙ ሰው እና ድርጊቱን ከህሊና ቢስነት ጋር ያያዙት ሰው: ይህን ይላሉ ብዬ እንዴት መጠበቅ ይቻለኛል? የባንዳ ልጆች በምን አመክንዮ ነው በአባታቸው ድርጊት መሸማቀቅ ይገባቸዋል ብለን የምንፈርድባቸው? አዩ ፕ/ር ትንሽ ይሉኝታ እዚች ላይ ትጠቅሞት ነበር:: ባንዶች አሉ: ባንዶቹና ልጆቻቸውም በማንኛውም መስፈርት ማፈር አለባቸው ብለው የሚያምኑ ቢሆን እንኳን: ትንሽ ኢትዮጵያዊ ይሉኝታ ቢኖሮት አውቀው እንዳላወቀ በማለፍ የባንዳ ልጆችን ከማራቅ ይቆጠቡ ነበር:: በዋናነት ደግሞ አመክንዮ የጎደለውና የተሳሳተ ፍርዶት በይሉኝታው ተሸፍኖ ለአደባባይ ሳይገለጥ ይቀር ነበር:: እና በኔ ዕይታ ትንሽ ይሉኝታ ለሁሉም በጎ ይመስለኛል::

  አክባሪዎ!

  (Pls you don’t have to post this; you can keep it as a dialogue between the two of us.)

  • haq says:

   አንድን ዜጋ አገሩ እንደ አንድ ዜጋ ልትቀበለው ካልቻለች: ራሱን ከአገሪቱ ነጥሎ ቢያይና ለራሱ ጥቅም መቆም ቢጀምር: ባንዳ የሚያስብለው ምክንያት ምንድን ነው??? Dan! ….በጣምመልካም እና በሳል አስተያየት ነው አዎ ክፉ የምንለው ያከፋነውን ነው፡፡ ርኩስ የምንለው ያረከስነውን ነው፡፡ ጠፋ የምንለው ያባረርነውን ነው፡፡ ባንዳ ከሀዲ የምንለው ያስካድነውን ነው፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ሰው ሸሽቶ ካልሆነ በቀር አብሮ ሆኖ ሕሊናውን መጠቀም አይችልም፡፡ ባይወድም ይከፋል፡፡ አቅም ባይኖረውም ይሸፍታል፡፡ ታዲያ እድሜ ሰጥቷችሁ ከዓመታት በኋላ ብትገናኙ ያ መልካምነት ሞቶ ተቀብሮአል፡፡ ያ ትህትና አፈር ትቢያ ሆኖአል፡፡ ያ ርኅራሄ ላይመለስ እርቆ ሄዶአል፡፡ ለልቡ ተጠግታችሁ “ምነው? ምን ገጠመህ?” ብትሉት ልክ እንደ ሙሾ አውራጅ እየተንሰቀሰቀ “ሰው አከፋኝ” ይላችኋል፡፡ታዲያ ይህኛው ሲከፋ ለመጪው ውርስ ሆኖ ይቀራል፡፡ስለዚህ የውርስ ቅብብሎሽ ለማቆም የሆነ ቦታ የሚጨክን ሰው ያስፈልጋል፡፡ ከአያት ከቅድመ አያት የመጣ ነገር ሁሉ ለልጅ ልጅ አይተላለፍም፡፡ እኛ የተጫነንን ሌሎች ላይ መጫን የለብንም፡፡ እኛ የመረረን ሌሎችንም እንዲመራቸው ቸልተኛነት ልናሳይም አይገባም፡፡ የከፉብንን በመክፋት፣ የጠሉንን በመጥላት፣ ያንገላቱንንም በማንገላታት ምድሪቱን በጨለማ ልንለውሳት አይገባም፡፡ ሰው የሚወልድበትን ዘር እና ቤተሰብ ወዶና መርጦ አዘጋጅቶ ወዲዚች ምድር አይመጣም ፕሮፌሰር ወንድም የፈለገ ቢበድል ወንድምነቱ አይካድም ያለ ምርጫቸው በሰው ምርጫ፣ ያለ ፍላጎታቸው በሰው ፍላጎት ክፉ የሆኑ ሰዎችን ቁስላቸውን በመንካት የበለጠ አናክፋቸው ይልቅስ ቁስላቸውን እንጠግን ያኔ የኛንም ችግርና ቁስል የሚያዩበት አይነ ልቦና ያገኛሉ!በዓለማችን ላይ ከተነሡ አያሌ ክፉ የሆኑ ሰዎች ዓላማቸውን የሳቱት፣ ከሕሊናቸው የተጣሉት፣ የማንነት መቃወስ የገጠማቸው ከእነርሱ ስህተት በላይ ሰው አክፍቷቸው ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ራሱን ፕሮፌሰርን ጨምሮ በእኔ ምክንያት የከፉ ሰዎች ይኖሩ ይሆን? ብሎ በመጠየቅ ለሚጽፋቼውም ሆነ ለሚናገራቼው ነገሮች ጥንቃቄ ሊያረግ ይገባል!betefikr

 3. smegn says:

  Dear prof. with all respect you don’t like Berhanu Nega and you think Berhanu did something for ESAT so you have to destroy ESAT. Nothing more nothing less. By the way I am your admirer but I also know your weak points too.

 4. Andinet says:

  በመጀመሪያ ለተሰጦት አስተያት ጊዜዎትን ወስደው አንብበው ምላሽ መስጠትዎ ለውይይት ምን ያህል ዝግጁ እንደሆኑ ያሳያሉ፡፡ ለዚህም ላመሰግኖት እወዳለሁ፡፡
  እኔ በሰጠሁት አስተያየት የሰጡትን ምላሽ ደጋግሜ አነበብኩት፡፡ እርስዎ “ ላንዳንዶች ሰዎች ይህ አገላለጼ የከረረ ይመስላቸው ይሆናል፤ በአውነት ይህ አገላለጽ ከበጎ መንፈስ የመነጨ ነው “ብለዋል፡፡ እንዲህ ከሆነ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ በስህተት ተረድቼዎት ሊሆን ይችላል እንጂ እርስዎ እንዳሉት ግን አውቄ ተኝቼ አይደለም፡፡በተጨማሪም እርስዎ ከጠቀሷቸው የኢሳት መክሽፍ መገለጫ አራት የሚሆኑ አጫፋሪ ሀሳቦች አንዱን ብቻ ላይ አተኩሬ (የጦርነት ጥሩንባ የሚነፉ) አስተያየት መስጠት ስለፈለኩ ነው እንጂ እርስዎ እንዳሉት ያሉትን ቆርጬ ለማውጣት ፍላጎት ኖሮኝ አይደለም፡፡
  እኔ የእርስዎ ጽሁፎች ላይ ስህተት ከታያኝ እርስዎን እንደ ፈጣሪ የማይሳሳቱ አድርጌ “የኔታ ፤ መሪ ጌታ……” .እያልኩ ስህተቶትን ሸፍኜ በማለፍ ማንቆላጰስ ባህርዬ ስላልሆነ አሁንም የታዩኝን ስህተቶች ደግሜ ልጠቁም፡-
  የእርስዎ አገላለጽ የከረረ ስለመሆኑ በተለይ በጠቀሱት አንቀጽ መረዳት ይቻላል፡፡ በአንቀጹ የኢሳትን መክሽፍ መገለጫ የሆኑ በርካታ ሰዎች ይታዩኛል፡፡ “ እላይ ቤት ታች ቤት የሚቀላውጡ ሰዎች ፤ አካላቸውን መንፈሳቸውን ያባለጉ፤ ደካሞች፤ የጦርነት ጥሩንባ የሚነፉ፤ የሚያቅራሩ፤ ……………………..” እነዚህን ሰዎች በኢሳት መድረክ አግኝተው ሃሳባቸውን ከገለጹ በኃላ ህዝቡ እርስዎ እንዳሉት ቢላቸው አንድ ነገር ነው፡፡ እነዚህን ሰዎች ለእርስዎ ስላልተመቹ አስቀድመው የኢሳትን መክሽፍ መገለጫ አድርገው ስለወሰዱ እንዴት የእርስዎን አስተያየት ለኢሳት በገለልተኝንት እንደተሰጠ አስተያየት መውሰድ ይቻላል?
  ሌላው እነደ ስህተት ያየሁት በዚህ ሁለት ገጽ በማትሞላ ጽሁፎ በርካታ ዘለፋዎችን ከእርስዎ ታዝቤያለሁ፡፡ ለምሳሌ “ የጭቃ እሾህ፤ አዋቂ ነኝ ባይ፤ ራሳቸውን ያሳበጡ ፤: መርዝ የሚረጩ ፤ አንጎላቸውን ያጠናገሩ ፤ መንፈሳቸውን ያባለጉ ፤ ራሳቸውን በመቃብር ውስጥ የከተቱ፤…………………” እንግዲህ እነዚህ ቃላት እየተጠቀምን እርስ በርስ በጨዋነት ለመወያየት እና ለመተራረም እንዴት ይቻላል? ከሌላው ወገን በጎ ምላሽስ እንዴት እንጠብቃለን? ለእርስዎ አትዮጵያዊ ጨዋነት እዚህ ላይ ለምን እንደማይሰራ አይገባኝም፡፡
  አሁንም ተሳስቼ ተረድቼዎት ከሆነ ለእርስዎ አስቂኝ ቢሆኑም በድጋሚ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡

 5. Deresse says:

  ውድ ፕሮፌሰር የሰጡት አስተያየት በተለይም ደግሞ አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት መች ይሰማል ያሉት በጣም ተስማምቶኛል፡፡ አስተያቶቹን በማንበብም ምላሽ በመስጠትዎ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡

  አንድነት በፅሁፋቸው ‹ከተሳሳትኩ ለመታረም ዝግጁ ነኝ›፣ ‹እርስ በርሳችን ገንቢ በሆነ መልኩ ካልተራረምን እንዴት ነው ከሌላኛው ወገን ጥሩ ነገር የምንጠብቀው› ብለዋል፡፡ በመሰረቱ ይህ ጥሩ ሃሳብ ነው፡፡ እስቲ ከሰጡት አስተያየት አንድ ሁለቱን እንይ፡፡ ‹ኢሳትን በቅንነት ለማጠናከር ከተፈለገ አሁን እየተደረገ ያለውን ጥረት አድንቆ የተሻለ ነገር መጠቆም አንድ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን እርሶ የማይወዱትን ነገር ጥላሸት እየቀቡ #ኢሳትን ለማሻሻል; በሚል ዓላማ መምከር የበለጠ ጎጅ ነው የሚሆነው› በማለት የነቀፋ አስተያየት አስፍረዋል፡፡

  በእውነቱ ምንም አይነት ምርምር ሳያስፈልግ የፕሮፌሰሩን ፅሁፍ በማንበብ ብቻ ከቀፈፋ (ልመና ይመስለኛል) የተሸለ ነገር እንደጠቆሙ ለመረዳት ይቻላል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን በፅሁፋቸው #ዓላማውን ሳይመታ እንዳይከሽፍ ኢሳት በቃልኪዳን መታሰር አለበት@ እንዴት? ቢባል፣ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ለኢሳት በአማካይ በወር አስር ዶላር ለመስጠት ቃል ኪዳን ቢገቡና የየዓመቱን ግዴታቸውን በአንዴ ቢወጡ፣ በወር አስር ሚሊዮን ዶላር (በአመት አንድ መቶ ሃያ ሚሊዮን ዶላር) ኢሳትን ኢትዮጵያዊነትን የሚያስከብር የሰላምና የፍቅር፣ የብልፅግናና የተስፋ መድረክ ሊያደርገው ይችል ነበር; ብለዋል፡፡ ጥያቄው ይህ በግልፅ የተፃፈ አማራጭና ውጤታማ ሃሳብ እንዴት አልታየዎትም? ነው፡፡

  ሌላው ጉዳይ ኢሳት ነፃ ሚዲያ እንዲሆን የምንሻ ከሆነ ከመርህ አኳያ ለሁሉም እኩል መድረክ መስጠት እንዳለበት በመግለፅ ፕሮፌሰሩ ይህ መንገድ ያልታያቸው የሚመስል አስተያየት አስፍረዋል፡፡ እንደገባኝ ከሆነ የፕሮፌሰር መስፍን ሃሳብ ከዚህም በላይ ይሄዳል፡፡ ሃሳቡንም በጥልቀት መረዳት ያስፈልጋል ያልኩትም ለዚህ ነው፡፡ ኢሳት ለሁሉም እኩል መድረክ መስጠት አለበት ብቻ ሳይሆን በዚህኛውም ሆነ በዚያኛው ጎራ ተሰልፈው ያሉትን አካላት እኩል መድረክ በመስጠትና በተጨማሪም እያከናወኑ ያሉት ተግባራት ምን ያህል ለኢትዮጵያ ህዝብ ጠቃሚ እንደሆነ ጠንከር ባለ ሁኔታ በመሞገት የኢትዮጵያ ህዝብ እውነቱን እንዲያውቅ የማድረግ ሃላፊነት አለባቸው ለማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ከተቃዋሚው ጎራም ቢሆን ላይ ታች እያሉ የሚያወሩ ደካሞች የመጫወቻ ሜዳው ሊሰፋላቸው አይገባም ለማለት ይመስለኛል፡፡

  አንድነት ይህ እንዲታይዎት ፈልጌ ነው፡፡

Comments are closed.