የሥላሴዎች እርግማን (ሁለት)፤ አደህይቶ ማድከም

መስፍን ወልደ ማርያም

ሐምሌ 2005

       ከታትፎና ለያይቶ በማዳከም ቤቱን አፍርሶና መሬቱን ነጥቆ፣ ከሥራው አፈናቅሎና ሥራ አሳጥቶ ያለርኅራኄ ማደህየት በፕሮግራም የተያዘና በውጭ ኃይሎች የሚደገፍ ሥራ ነው፡፡

ለጥቂት ዓመታት በአሜሪካ ቆይቶ የመጣ አንድ ጓደኛዬ ራሱን በሁለት እጆቹ ይዞ ‹‹አዲስ አበባ በመሬት መናወጥ ፈራርሳ በመጠገን ላይ ያለች ከተማ ትመስል የለም እንዴ!›› አለኝ፤የመሬት አይደለም አንጂ የመናወጥ ነገር በእርግጥ አለ፤ የመሬት መናወጥ ባይደርስባትም የአእምሮ መናወጥ የመታት ከተማ ነች አልሁት፤ ቅንጅት ነፍሱን ይማረውና በፖሊቲካው መድረክ ብልጭ ብሎ ድርግም ካለበት ዓመት ጀምሮ በአዲስ አበባ ታይቶ የማይታወቅ የማፍረስና የመገንባት ሥራ በአንድ ላይ ጎን ለጎን ሲካሄድ እያየን ነው፤ ከጥንስሱ ጀምሮ የማሰብ ችግር ውላጅ መሆኑ በግልጽ ይታያል፤ ብዙ አገሮች አዳዲስ ከተማዎችን ሠርተዋል፤ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ሕንድ፣ ናይጂርያ፣ ብራዚል አሉበት፤ የወያኔ/ኢሕአዴግ ግን የተለየ ነው፤ አዲስ ከተማ እየሠራ ሳይሆን የጥንቱን እያፈረሰ ነው፤ ደርግ ሲጀምር ከጥንቱ ሥርዓት ጋር በመጣላት ነበር፤ ወያኔ ሲጀምር ግን ከማን ወይም ከምን ጋር ተጣልቶ አንደሆነ በግልጽ ባይታይም በጥላቻ መወራጨቱ ይታይ ነበር፤ ጎልቶ የወጣውም የችግረኛ ጉጉትና ምኞት፣ ሽሚያና ዝርፊያ የወያኔ ዓላማ ከራሱ የማያልፍ መሆኑን ያመለክት ነበር፤ በውጤቱም የሆነለት ያባትህ ቤት ሲዘረፍ እንደሚባለው ሆኖ ከውጭ ባንክ ተርፎ፣ ከአገር ውስጥ ባንክ ተርፎ፣ በጆንያና በጉድጓድ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያስቀመጠ ተደላድሎ እየሳቀ ይዝናናል፤ ያልሆነለትም በየሜዳው ያለቅሳል፤ ከተማው በሙሉ በማፍረስና በመገንባት ይታመሳል፤ ይተራመሳል፤ ዋናው ዓላማ ሕዝቡን ማዳከም ነው፤አዳክሞም ማደህየት ነው፡፡–

 • ይህ ሁሉ መንገድ የደሀውን ቤት ሁሉ እየመነጠረ ሲረዝምና ሲሰፋ፣
 • የደሀ ቤቶች ተመንጥረው መንገዱ ከረዘመና ከሰፋ በኋላ ባለሥልጣኖች በድንገት ስለባቡር የሚያስታውሳቸው አማካሪ ሲያገኙ፤
 • የድሆች ቤቶች እየተመነጠሩ የሰፋውን መንገድ እያፈረሱ ሲያጠቡት!
 • ቤቶች ሲፈርሱና መንገዶች ሲረዝሙ፣ መንገዶች ሲሰፉና ሲጠቡ፣
 • መንገዱ ለባቡሮች ሲቆፈርና ሲተራመስ፣
 • መንገዱ በደሀዎቹ ቤቶች ፍርስራሽ ተጨናንቆ በደሀ እንባ ሲጨቀይ፣
 • ለደሀዎች መኖሪያ ኮንዶሚንየም እየተባለ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሲገባና ሲወጣ፣
 • የመንገዱና የባቡሩ ወጪ ከኮንዶሚኒየሙ ሥራ ጋር ተዳብሎ በቢልዮን የሚቆጠር ብር እየተተራመሰ ከመንግሥት ኪስ ሲፈስ፣
 • ‹‹የመንግሥት ሌቦች›› የሚፈስሰውን እየለቀሙና እየተወዳደሩ ‹‹በምድር ላይ ሳንበተን ስማችንን እናስጠራ›› ብለው ግንበ-ሰናኦርን ሲክቡ፣
 • የሙስና ተከላካዮች ፈራ-ተባ እያሉ በእርሳስ ሲመዘግቡና ግንዱንና ስሩን ሳይነኩ በኢዮባዊ ትእግስትና በሰሎሞናዊ ፍርድ ቅጠሎቹን እየከረከሙ ሲያረግፉ፣
 • ሙስና ስሩ እየጠነከረ ግንዱም እንደግንበ-ሰናኦር ወደሰማይ እያደገ ሲሄድና ቅጠሉም ወዲያው ሲለመልም፤
 • ደሀነትም በጌትነት እየተጋጠ በሞትና በሕይወት መሀከል ሆኖ እያቃሰተ ሲያድግ፣
 • ለደሀነት መቀነሻ የሚባለው ሁሉ ደሀነትን ለማባባስ ሲውል፣

የደላው ይደሰታል፤ የተጎዳው እንባውን በየመንገዱና በየቤተክርስቲያኑ፣ በየቤተ መስጊዱ ይረጫል፤ የሚታዘብ ያንጎራጉራል፤

በቁንጣን፣ በስካር ጥቂቶች ሲንሩ፣

ብዙዎቹ ደግሞ በረሀብ መንምነው በቁንጫ ሲያርሩ፣

የደሀ እንባ ሲጎርፍ መሬቱ ሲሸበር፣

ዝብርቅርቁ ወጣ፤ ሕይወት ትርጉም አጣ፤

መንገዱ ጠበበ፤ ትርምስምሱ በዛ፤

እሪታው፣ ኡኡታው ቀለጠ እንደዋዛ፤

መሬቱም፣ ዓየሩም በክፋት ጠነዛ፤

ጥላቻና ቂሙ በሰፊው ተነዛ፤

እምቢልታው ሲጣራ ነጋሪት ሲያገሳ፣

የአለው ሁሉ ሞቶ የሞተው ሲነሣ፣

ምጽዓት መድረሱ ነው፤ ሊስተካከል ነው ፍርድ፤

በግና ፍየሉ ሊለዩ በገሀድ!

 

አፍርሶ መገንባት ዘለቄታ ያለው እድገትና መሻሻል ያስከትላል ብለው የሚያምኑ ከኋላቸውም ከፊታቸውም የሚያዩት ሁሉ ያከሸፋቸውና የከሸፉ ናቸው፤ ወደኋላ እንዳያዩ ታሪክ የላቸውም፤ ወደፊት እንዳያዩ ራእይ የላቸውም፤ የሥላሴዎች እርግማን!

Advertisements
This entry was posted in አዲስ ጽሑፎች. Bookmark the permalink.

7 Responses to የሥላሴዎች እርግማን (ሁለት)፤ አደህይቶ ማድከም

 1. Kidus says:

  ታላቁ ሰው ሁሌም ጆሮኣችን አይናችን አንደበታችን ነዎት፡፡ አዎ አ.አ አመት ሳይሞላው ሊያፈርሱ ከሚሰሩት አስፋልት በዚያም ስም ከሚቀራመቱት ብዙ ብር ትንሽ እንኳን ለቋሚ ነገር ቢያውሉት ስነት ነገር በለወጡ፡፡ ቅመው በመረቀ የማፈረስ ሰየጣናቸው እያገረሸ አገራችን ታሪካችን ፈርሶ አለቀ፤ እኛም ተሰነጣጠቅን. . . እረ ሰው. ጠፋ ሰው ጠፋ…

 2. gedeyon says:

  ye Ethiopian tensye endiasayot endmena tenna emgnalehu !!!!

 3. Kefale says:

  This is the result of doing with out planning. Performing what comes to the mind, with out checking whether it is important or not, is expensive, may be not timely, exposed for ongoing plan less destruction …

 4. tt says:

  የሙስና ተከላካዮች ፈራ-ተባ እያሉ በእርሳስ ሲመዘግቡና ግንዱንና ስሩን ሳይነኩ በኢዮባዊ ትእግስትና በሰሎሞናዊ ፍርድ ቅጠሎቹን እየከረከሙ ሲያረግፉ፣
  long live Prof.

 5. geezonline says:

  ይኽ በታሪክ-ወ-ራእይ-የለሾች የኛው ጉዶች “በፕሮግራም የተያዘና በውጭ ኃይሎች የሚደገፍ ሥራ”–ይኽ “የሥላሴዎች እርግማን”–እንዴት ይጠፋል?

  ራሱ እጥያቄው ውስጥ የሚገኘው መልስ፦ ብዑላነ-ታሪክ-ወ-ራእይ የኾኑ የኛው ወገኖች መርሐ ግብር ሲነድፉልን፤ የውጭ ኃይሎችም ሲታገሡልን።

  የለም የለም፤ ተስእሎውን እንዲኹ በተገብሮ ወይም በደንቦብ እንደሐውልት ከመጎለት ገቢራዊ ምላሽ በሚሻ መልኩ በግልጥ ለአካላዊ ባለቤት እንትከለውና እንዲኽ እንጠይቅ፦ ይኽንን… ፕሮግራም፥ ይኽንን… ሥራ–ይኽንን… ርግማን እንዴት እናጥፋው?

  የኛኑ ታሪክ-ወ-ራእይ-የለሾቹን ጉዶች ከነ የውጭ ደጋፊዎቻቸው እንቢ ብለን፤ ብዑላነ-ታሪክ-ወ-ራእይ በኾኑ ወገኖቻችን እንመራ። (“እንመራ” ሲል ተገብሯዊ ይመስላል። ቋንቋውማ ነው እንጂ። ነገር ግን በቅጥነተ ልብ ካስተዋልነው “እሺ፥ በጎ” ብሎ “መመራት” ገቢራዊ ነው እንጂ ተገብሯዊ አይደለም። የግብሮች ኹሉ መሠረት ፈቃድ አይደለምን? መፍቀድ የግብሮች ኹሉ ግብር ነውና፤ በታሪክ እና ራእይ የለሾች ለመመራት አንፍቀድ፤ ወይም በነሱ መመራትን እንቢ እንበል። በታሪክ ዐርበኞች እና በራእይ ባለቤቶች ለመመራት እንፍቀድ፤ ወይም እነሱን እሺ እንበል።)

  በእኔ እምነት (ደግሞ እምነቴን ብዙዎች እንደሚጋሩት አልጠራጠርም!) በታሪክ መሠረት ላይ ጸንቶ መጻእያትን እያየ የኢትዮጵያዊነትን ጎዳና ለማስተካከል ቀን ተሌት የሚጥረው አንዱ መሪ ፕሮፌሶር መስፍን ወልደ ማርያም ነው!!! ከርግማናችን ለመላቀቅ ርሱን እና መሰሎቹን እንስማ፤ እንከተላቸውም!!!

  ይኸው ነው፤ በቃ።

 6. Goytom says:

  ‹‹አዲስ አበባ በመሬት መናወጥ ፈራርሳ በመጠገን ላይ ያለች ከተማ ትመስል የለም እንዴ!›› This is what I have been feeling in Addis and always tell to my friends of this feeling.

 7. Amha Teresa says:

  well stated the way I see it

Comments are closed.