የሥላሴዎች እርግማን (ሦስት) ፦ አዳክሞ ማደህየት

መስፍን ወልደ ማርያም

ሐምሌ 2005

አንድ በጣም የተገረመ ደቡብ አፍሪካዊ ይህንን ሁሉ መንገድና ሕንጻ በአንድ ጊዜ ለማሠራት ገንዘቡን ከየት ነው የምታገኙት? ብሎ ጠየቀኝና ከወርቅ-ቡና አልሁት፤ ሳቅ አለና እኔኮ ከልቤ ነው የምጠይቅህ አለኝ፤ እንግዲያው ዘክዝኬ ልንገርህ አልሁት፤ ለወትሮው ብዙ የምክር ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም ለመንግሥትህ እንዳትናገርና የዚሁ ዓይነት ሥራ በደቡብ አፍሪካ እንዳይጀመር ቃል ግባልኝ አልሁትና ቀጠልሁ፤ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በመንግሥት ባንኮች ደጃፍ ላይ የነበረውን መጨናነቅ አይተሃል ወይ? ብዬ ጠይቄው ማየቱን ካረጋገጥሁ በኋላ ጉዳዩን እንደሚከተለው አስረዳሁት፡፡

አገዛዙ መሬቱንም ሆነ ቤቶችን የራሱ ካደረገና ባለቤትነቱን ካረጋገጠ በኋላ በየመንገዱ ዳር እንጀራ፣ ዳቦ፣ ቆሎ፣ ጠላና ትናንሽ ነገር እየሸጡ ልጆቻቸውን የሚያሳድጉ ሴቶች፣ በየቤቱ እየሠሩ በነዚህ ቤቶች ተዳብለው ኪራይ እየከፈሉ የሚኖሩ ሴቶች በብዛት ነበሩ፤ በነዚህ ደሀዎች ላይ ቀበሌዎች በየጊዜው እየዘመቱ ቤቱ እንደሚፈርስባቸው እያስፈራሩ ደሀዎችን ያሸብራሉ፤ በዚህ ዓይነት ፍርሃትና ስጋት ውስጥ ለጥቂት ወራት ካቆዩአቸው በኋላ ክረምትን ጠብቀው በግድ ያስለቅቁአቸዋል፤ በዚህ ምክንያት በአዲስ አበባ ውስጥ የተፈናቃይ ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ በአንዲት ትንሽ ክፍል ውስጥ የሚኖረው ሰው ቁጥር እየበዛ ለጤንነት ክፉ ጠንቅ እየሆነ ነው፤ ይህ ችግርና ስቃይ ትልቅ የሀብት ምንጭ ሆኖአል፤ ደሀ የሚበላው አንጂ የሚከፍለው አያጣምነጭ ደሀ ነጭ ማር ይከፍላል፤ እነዚህ ባህላዊ አነጋገሮች ተጠንተው በተግባር ላይ እየዋሉ ነው።

እንዴት? ማለት ጥሩ ነው፤ እነዚህ (ቤቶቻቸው ከማለት ይልቅ) መጠለያዎቻቸው የፈረሱባቸው ሰዎች ከረሀቡ ሌላ በብርድና በጸሐይ በመጉላላታቸው የመጠለያ ችግራቸው በጣም ከባድ ስለሆነ በቀላሉ የሚበዘበዙ ናቸው፤ ችግሩን መፍቻ የሚመስል የደሀውን ነፍስ በጉጉት ሰንገው የሚይዙበት ኮንዶሚንየም የሚባል ማቁለጭለጫም አለ፤ ደሀ ሁሉ ኮንዶ አግኝቶ የሚያልፍለት ይመስለዋል፤ ስለዚህ ሁሉም ይፈልጋል፤ ስለዚህ የኮንዶ ፈላጊው ሰልፍ በጣም ረጅም ነው፤ ስለዚህ በመስገብገብ እየተተኮሰ ዋጋው በጣም ከፍ ያለ ነው።

ማፍረስ ከመገንባት የቀለለ ቢሆንም በአዲስ አበባ የሚካሄደው አብዛኛው የመገንባት ሥራም ከማፍረሱ ሥራ የተሻለ መሆኑ በጣም ያጠራጥራል፤ እንዲያውም የማፍረሱንም ሆነ የመገንባቱን ሥራ የሚመሩት የውጭ አገር (ምናልባትም የቻይና) ሰዎች ናቸው ለማለት ያስደፍራል፤ በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ነፍስ ውስጥ መሬት እንዳለ፣ በኢትዮጵያ የብዙ ሺህ ዓመታት ውስጥ መሬት እንዳለ፣ በኢትዮጵያ የተጋድሎ ጀግንነት ውስጥ መሬት እንዳለ፣ በኢትዮጵያ የአገር ፍቅር ውስጥ መሬት እንዳለ የውጩ አገር ሰው በምን መንገድ ሊያውቅ ይችላል? አንድ ኢትዮጵያዊ በአገሩ ውስጥ ባለው ቤት ውስጥ ምን ምን ይሠራል? አንዴት ይሠራል? በዚህ ጉዳይ ላይ የውጭ አገሩ ሰው ምንም ያህል አያውቅም፤

ስቱድዮ በወር አንድ መቶ ዘጠና አምስት ብር፣ ባለአንድ መኝታ ሁለት መቶ ሰባ አራት ብር፣ ባለሁለት መኝታ አምስት መቶ ብር እንደሚከፈል ተወስኖአል፤ ይህ ኪራይ ሁላችንም እንደምናውቀውና እንደለመድነው ዓይነት ያለ ኪራይ አይደለም፤ ልዩ ነው፤ አንዱ ልዩ የሚያደርገውም መጠለያዎቹን ሁሉ ያፈረሱትና ችግሩን የፈጠሩት ራሳቸው ኪራይ ሰብሳቢዎች መሆናቸው ነው፤ ዋናው ልዩ የሚያደርገው ግን ለኮንዶዎቹ ኪራይ መክፈል የሚጀመረው ሕንጻዎቹ ተሠርተውና አልቀው ተከራዮቹ ከገቡ በኋላ አይደለም፤ የሕንጻዎቹ ሥራ የሚጠናቀቀው ቢያነስ ከአምስት ዓመት በኋላ ሲሆን ኪራይ መክፈል የሚጀመረው ዛሬ ነው! ደሀዎች ለማይኖሩበት ቤት ኪራይ ይከፍላሉ! ማንም አላስገደዳቸውም፤ ያስገደዳቸው ደካማነታቸውና መናጢ ደሀነታቸው ነው፤ መስገብገባቸው ነው።

ከቀረበው መረጃ ተነሥተን እስቲ ትንሽ ስሌት እንሥራ፤ በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ውስጥ ስምንት መቶ ሺህ ያህል ሰዎች ለኮንዶ ተመዝግበዋል እንበል፤ በስቱድዮ፣ በአንድ መኝታ፣ በሁለት መኝታ፣ በሦስት መኝታ በእያንዳንዳቸው የቤት ደረጃዎች ሁለት መቶ ሺህ ሰዎች ቢመዘገቡ     ከነዚህ ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት በዝቅተኛ የደሀነት ደረጃ ላይ ቢሆኑ፣ ሢሶ የሚሆኑት ደግሞ የደሀነት መሀከለኛ ደረጃ ላይ ቢሆኑ፣ ሌሎቹ ማለትም አንድ አምስተኛ የሚሆኑት በተሻለ ደረጃ ላይ ያሉ ደሀዎች ቢሆኑ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በያመቱ የሚሰበሰበው ገንዘብ እንደሚከተለው ይሆናል፤

 

ደሀነት ሲበዘበዝ

ኮንዶ የተመዘገቡ   የወር ኪራይ በደሀነት ደረጃ የዓመት ኪራይ
ስቱድዮ

200 000

 200 000 x 195=  39 000 000

  468 000 000
1 መኝታ

200 000

200 000 x 274=  54 800 000

  657 600 000
2 መኝታ

200 000

200 000 x 500= 100 000 000

1 200 000 000
3 መኝታ

200 000

200 000 x 750= 150 000 000

1 800 000 000
ድምር 1 000 000                279 700 000 4 125 000 000

 

እንግዲህ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ከመጠለያ ማጣት ጭንቀት ለማምለጥና ያደረባቸውን የኮንዶ ጉጉት ለማሳካት ከአራት ቢልዮን ብር በላይ እየተራቡ ይገብራሉ፤ በአምስት ዓመታት ውስጥ ገና ኮንዶው ውስጥ ሳይገቡ ላባቸውን ያንጠፈጠፉበትን 20 625 000 000 ብር ይከፍላሉ ግፍ ሌላ ትርጉም የለውም።

ማፍረስም በጣም ትርፋማ ሥራ ሆነ።

በፈረሰው ላይ የሚገነባውስ? ስለኮንዶው ሕንጻ አንዳንድ ጥያቄዎችን ማንሣት በግድ ያስፈልጋል፤ አንደኛ የኮንዶው ሥራ መቼ ተጀምሮ መቼ ያልቃል? ያልቃል ሲባልስ ለመኖሪያ ብቁ የሆነ፣ በሮችና መስኮቶች ተገጥመውለት፣ ወለሉና ጣራው፣ የመታጠቢያ ቤቱ ሁሉ ተሟልቶ ነው ወይስ ባለቤት የሚሆኑት ሰዎች የሚጠብቃቸው ሥራ አለው? ሁለተኛ የኮንዶው ሕንጻ ስንት ክረምትና ስንት በጋ የሚችል ይሆናል? ሦስተኛ ኮንዶው ሰዎችን ወደከፍተኛው ፎቅ የሚያደርሳቸው ‹ሊፍት› አለ ወይስ ሰዎች በእግራቸው በደረጃ ሊወጡ ነው? ይህ ከሆነ ለሽማግሌዎችና አሮጊቶች ምን ዝግጅት ተደርጎላቸዋል? ሽማግሌዎችንና አሮጊቶችን ወደምድር ቤቱ አካባቢ ለመደልደል ታስቦአል ወይ? አራተኛ የውሀ አቅርቦቱ ምን ያህል አስተማማኝ ነው? ውሀ በሚጠፋበት ጊዜ ነዋሪዎቹ ሊጠቀሙበት የሚችሉበት የመጸዳጃ ቦታ ካልተዘጋጀ በጥቂት ጊዜ ውስጥ አካባቢው ለጤና ጠንቅ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፤ ‹‹የአበሻ ኑሮ›› የሚባል ነገር ያለ ይመስለኛል፤ ቡናና ጌሾ መውቀጡ፣ ብቅልና በርበሬ ማስጣቱ፣ ዶሮና በግ ማረዱ፣ አንጀራ መጋገሩ፣ ማኅበሩ፣ ለቅሶው — እነዚህና ሌሎችም ማኅበራዊ ግዴታዎች ኮንዶው ሲሠራ ታስበው ነበር ወይ?

ደሀው ራሱን በማፈራረስ፣ ይበልጡኑ በሚደኸይበት ሥራ እንዲጠመድ፣ በፍርስራሽ እንዲነግድ በምናምን ተይዞአል! የሥላሴዎች እርግማን!

 

Advertisements
This entry was posted in አዲስ ጽሑፎች. Bookmark the permalink.

2 Responses to የሥላሴዎች እርግማን (ሦስት) ፦ አዳክሞ ማደህየት

  1. tt says:

    wow ,touching. long live prof

  2. samson says:

    thank you professor, could you pleas tell me how can I get the book title <>.PLS,PLS.PLS
    AKBARIWO…..

Comments are closed.