የሥላሴዎች እርግማን፤ አዳክሞ ማደህየት (አራት)

መስፍን ወልደ ማርያም

ሐምሌ 2005

አንዱ የኢትዮጵያን ሕዝብ የማዳከሚያና የማደህያ መሣሪያ ስደተኛው ነው፤ በአገር ውስጥ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሌለው ስደተኛው ሁለት ጉልበቶች አሉት፤ አንዱና ዋነኛው ስደተኛው የጠገራ ብር ባለቤት መሆኑ ነው፤ የጠገራ ብር ባለቤት መሆኑ በሁለት በኩል ጉልበት ይሰጠዋል፤ በአንድ በኩል በስደተኛው በኩል አገሪቱ ያላፈራችውን ሀብት ታገኛለች ማለት ነው፤ አገዛዙ ይህንን በደንብ ስለሚያውቅ ከመሬትም ሆነ ከሌላው የሀብት ድልድል ጋር እያያያዘ ይጠቀምበታል፤ በዚያ ላይ የአጠቃላይ ስግብግብነት ጠባይ ለአገዛዙ መሣሪያነቱን ይስለዋል።

ስደተኞች ጉልበት አላቸው፤ ብታምኑም ባታምኑም ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የበለጠ ጉልበት አላቸው፤ አንዱና ዋናው የስደተኞች ጉልበት የጠገራ ብራቸው ነው፤ የጠገራ ብሩ በሦስት መንገድ ወደኢትዮጵያ ይገባል፤ የኢትዮጵያ የዓየር መንገድና የአዲስ አበባ ሆቴሎች፣ የሌሊት መጨፈሪያዎች የጠገራ ብሩ ተቀባዮች ናቸው፤ በየወሩም ይሁን በተወሰኑ ጊዜዎች ለደካማ ዘመዶች የሚላክ ጠገራ ብር አለ፤ የሚላከው ጠገራ ብር በሁለት መንገድ ነው፤ በየወሩም ሆነ በየዓመቱ ለዘመዶች የሚላከው ገንዘብ በባንክ በኩል ከመጣ የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ ያሳድጋል፤ በማናቸውም መንገድ ቢመጣም ሀብት ከውጭ ወደሀገር ይገባል፤ ይህ በስደተኞች በተፈለገው መንገድ ወደአገር የሚገባው ገንዘብ አገሪቱ ያላፈራችው ስጦታ ነው፤ በጠገራ ብርም ሆነ በሌላ መንገድ ስደተኛው ወደአገር የሚያስገባው ሀብት ትልቅ ጉልበት አስገኝቶለታል።

ስደተኛው ሌላም ጉልበት አለው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታፍኖ ሲኖር በአንጻሩ ስደተኞች በሙሉ ነጻነት ዓለም-አቀፋዊ ግንኙነት ያላቸው ናቸው፤ ለውጭ መንግሥታት፣ ለውጭ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ለተባበሩት መንግሥታት፣ በተለያዩ አገሮች ለሚገኙ ለተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች፣ ለተለያዩ ሕዝቦች ኡኡታቸውን ያሰማሉ፤ የተፈለገውን ያህል የተቀነባበረ ባይሆንምና በጎሣና በስግብግብነት ቢከፋፈሉም ትልቅ ኃይል ትልቅ ጉልበት ናቸው፤ እየቆየም በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ የኢትዮጵያ ስደተኞች ዜግነታቸውን እየለወጡ በሚኖሩባቸው አገሮች የፖሊቲካ ትግል ውስጥ መግባት ሲጀምሩ በኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ የላቀ ተጽእኖ ማድረግ እንደሚችሉ ጥርጥር የለውም፤ በአሁኑ ጊዜ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሚኖሩት አንፈራጥጠው ነው፤ አንድ እግራቸው ብቻ በሚኖሩበት አገር ላይ የተተከለ ሲሆን አንደኛው ወደኢትዮጵያ ዞሮ በዓየር ላይ አንደተንጠለጠለ ነው፤ ይህንን በናፍቆት የተንጠለጠለ እግር አንዳንዴ ለማሳረፍ ጊዜያዊ ዜግነት በጠገራ ብር ይከራያሉ፤ ለአገዛዙም ጥሩ ገቢ ነው፤ አንድ ሚልዮን ያህል ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እያንዳንዳቸው ጊዜያዊ ዜግነት በተወሰነ የአሜሪካን ዶላር ቢከራዩ አገዛዙ ብዙ ሚልዮን ዶላር ያገኛል ማለት ነው፤ ከሌላው ጋር ተደማምሮ አገሪቱ በዓመት ከምታገኘው የቡና ሽያጭ ጋር የሚወዳደር ነው።

እሰካሁን የተነጋገርነው ስለልዩ ስደተኞች ነው፤ በአረብ አገሮች በኪራይ የሚሄዱ ደግሞ አሳዛኝ ስደተኞች አሉ፤ ከነሱ በኢትዮጵያ ዓየር መንገድም፣ በአገዛዙም በኩል ከፍተኛ ገቢ በጠገራ ብር ይገኛል፤ ከሱዳን፣ ከጂቡቲና ከኬንያ በኢትዮጵያ ሴቶች በኩል ወደአገር የሚገባ ጠገራ ብር ከፍተኛ ነው።

በተጨማሪም ከስደተኛው በተለያዩ መንገዶች የሚገባ የጠገራ ብር አለ፤ ስደተኞች የአገራቸውንና የወገናቸውን ናፍቆት የሚወጡት በአገር ምግብና በአገር ልብስ ነው፤ ብዙ ነገሮችን በተለያዩ መንገዶች ከአገር ውስጥ እየገዙ ይጠቀማሉ፤ ከስደተኞች መሀከል ጎላና ከፍ ብለው ለመታየት የሚፈልጉት ደግሞ ሠርጋቸውን በሸራተን፣ ወይም በሂልተን እየደገሱ ብዙ ገንዘብ ያወጣሉ።

እንግዲህ በብዙ መንገድ የስደተኞች ገንዘብ ወደኢትዮጵያ ይገባል፤ አገዛዙ ይህንን ስለሚያውቅ የተለያዩ አጋጣሚዎችን እየፈጠረ ስደተኞቹን ለማለብ ይፈልጋል፤ የአንዳንድ ስደተኞችን ስግብግብነት በማየትም በመሬትና በሥራ እየደለለ ወደግቢው ሊስባቸው ይጥራል፤ የገቡና ተደላድለው የሚኖሩ አሉ፤ ሌሎች ደግሞ ከገቡ በኋላ መውጫ አጥተው እየጎረበጣቸው የሚኖሩ አሉ፤ በቅርቡ ግን የአዲስ አበባ መሬት ለአገዛዙ ሰዎች እንዳያልቅ ተሰግቶ ለስደተኞች የሚሰጠው መሬት ከአዲስ አበባ ውጭ እንዲሆን በማድረጉ ብዙ ስደተኞች ሳይከፋቸው አልቀሩም።

ሆኖም ማላስ የለመዱና የሚችሉም ስደተኞች አሁንም በፈለጉበት ከተማ መሬት የማግኘት ዕድሉ አላቸው፤ ማላስ ሁሌም የተፈለገውን የበላይነትና የበታችነት ልዩነት እየጠበቀ አይቀጥልም፤ ላሾቹና አላሾቹ አብሮ በመብላትና አብሮ በመጠጣት፣ አብሮ በጥፋት በመተብተብና የወንጀል ወንድማማቾች በመሆን እየተመሳሰሉ ባሕርይ ይወራረሳሉ፤ ባለሀብቶች ባለሥልጣን ሲሆኑ ባለሥልጣኖች በበኩላቸው ባለሀብት ይሆናሉ፤ ሀብትና ሥልጣን አንድ ይሆናል፤ ሀብት ያለሥልጣን፣ ሥልጣንም ያለሀብት ዋጋቢስ መስሎ ይታያቸዋል፤ እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርሱ አወቅሁሽ ናቅሁሽ ይገባባቸውና ያመነቃቅራቸዋል፤ እየተጎራረሱ ለመቀጠል ይቸግራቸዋል፤ የሚልሱት በወፈሩና በጠነከሩ መጠን አላሾቹም የሥልጣን ኮርቻውን የማደላደል ኃይል ባገኙ መጠን ፍቅራቸው መሻከር ይጀምራል።

አንድ የሚያስገርም ነገር አለ፤ በውጭ አገር ለፍተው ያገኙትን ገንዘብ በስግብግብነት ወደአስከፊ የሙስና ተግባር ተሰማርተው ሀብታቸውንም ራሳቸውንም ማርከሳቸው ነው፤ በሥልጣን ላይ ሆነው የኢትዮጵያን ሀብት እየቸረቸሩ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከሚያደኸዩት ሰዎች ጋር እየተሻረኩ አስከፊውን የሙስና ተግባር ማደፋፈራቸውና የጥፋቱም ተካፋይ መሆናቸው ነው፤ የሁሉም ችግር የዛሬውን ሁኔታ በጣም ለጥጠው ከዕድሜያቸውም አስበልጠው ማየታቸው ነው፤ የሥላሴዎች እርግማን ነው!

 

 

 

Advertisements
This entry was posted in አዲስ ጽሑፎች. Bookmark the permalink.

One Response to የሥላሴዎች እርግማን፤ አዳክሞ ማደህየት (አራት)

  1. Pingback: የሥላሴዎች እርግማን፤ አዳክሞ ማደህየት (አራት) - Ethio News Monitoring | Ethio News Monitoring

Comments are closed.