አይ አበሻ! አበሻና ሆድ፤ ሁለት

መስፍን ወልደ ማርያም

ጥቅምት 2006

 

አበሻ ድግስ ይወዳል፤ ድግስ የሚወደው መብላትና ማብላት ስለሚወድ ነው፤ ለመብላት የአበሻ ምክንያቱ ብዙ ነው፤ ልጅ ተወለደ ብሎ መብላት ነው፤ ልጅ ክርስትና ተነሣ ብሎ መብላት ነው፤ ልጅ አገባ ብሎ መብላት ነው፤ ልጅ ሞተ ብሎ መብላት ነው፤ አበሻ ሰው ቀብሮ ሲመለስ በንፍሮ ይጀምርና ቀስ በቀስ ወደሌላው ይተላለፋል።

ሃይማኖትም ቢሆን ለመብላት ካልሆነ የነፍሱ ጉዳይማ በጣም ሩቅ ነው፤ ሕያዋን ለነገሥታት፣ ሙታን ለካህናት ይገብራሉ፤ በሚለው መመሪያ መሠረት
ግብር መቀበል ያለ ነው፤ ክርስቶስ ተወለደ መብላት ነው፤ ክርስቶስ ተጠመቀ መብላት ነው፤ ክርስቶስ ሞተና ተቀበረ መብላት ነው፤ ክርስቶስ ተነሣ መብላት ነው፤ ማርያም አረገች መብላት ነው።

ማኅበርም የሚጠጣው (የሚበላው ለማለት ነው፤) ለመብላት ነው፤ አምላክ በተለያዩ ስሞቹ፣ ቅድስት ማርያም በተለያዩ ስሞችዋ፣ መላእክት፣ ቅዱሳን፣ ሰማዕታት ሁሉ ለመብላትና ለማብላት ያገለግላሉ፤ ወደመንግሥተ ሰማያት ለመግባት አማላጅ ሊሆኑ የሚችሉ ሁሉ ማኅበር ለመብላት ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፤ የሌሎች አገሮች ክርስቲያኖች በመብል አይመለሱም፤ ገበያቸው በጠገራ ብር ነው፤ ስለዚህም አብሮ መብላት ብሎ ነገር የለም።

አበሻ የሚበላው የመጣውን ሲቀበል ብቻ አይደለም፤ የሚሄደውን ሲሰናበትም  መብላት ይወዳል፤ ሞትም ቢሆን ለመብላት ምክንያት ነው፤ ቀብር ብሎ እዝን እያቀረቡ መብላት ነው፤ ሠልስት ብሎ መብላት ነው፤ ለሰባት መብላት ነው፤ ለዓርባው መብላት ነው፤ የሙት-ዓመት ደግሶ መብላት ነው፤ በቀብር ላይም  ቢሆን ለቅሶውም ‹‹ሆዴ! ሆዴ!›› ነው።

ለአበሻ ጾምም ቢሆን ለመብላት ነው፤ የጾም ትልቁ ምሥጢሩ ምግብ እንዲናፍቅ ለማድረግ ነው፤ የፍስኩ የተትረፈረፈ ምግብና ጥጋብ ባይኖር ማን ይጾማል? የለየላቸው ጠጪዎች በሁዳዴ መለኪያውንና ብርጭቆውን አርግፍ አድርገው የሚተውት ሲፈሰክ በናፍቆት ዊስኪውንና ቢራውን ለመጋት ነውኮ! ይህ ባይሆን አንድ ጊዜ ሞጣ ያየሁትየበግ ሌባ ለምን ይጦም ነበር? ታሪኩ እንዲህ ነው፤ በሞጣ አውሮጵላን ማረፊያ አንድ የበግ ቆዳ የያዘ ሰውዬ በፖሊሶች ይጠበቃል፤ እንደሰማሁት በግ ሰርቆ ጫካ ይወስድና ቆዳውን ገፎ ለመሸጥ ወደገበያ ሲሄድ ተይዞ ነው፤ የሁዳዴ ጾም ስለነበረ ሥጋውን ለማይጾሙ አውሬዎች ጫካ ውስጥ ጥሎ ነው! አሁን ይህ ሰውዬ የሚጾመው ሲፈሰክ ደህና አድርጎ በናፍቆት ለመብላት ካልሆነ ለሌላ ለምንድን ነው ሊባል ነው?

ሥራም ቢሆን ለመብል ነው፤ ከመኝታው ሲነሣ ጀምሮ እስኪተኛ ቢበላ ደስታውን አይችለውም፤ለገና፣ ለፋሲካ፣ ለእንቁጣጣሽና ለመስቀል ለገናና ለፋሲካ፣ ለእንቁጣጣሽና ለመስቀልም ከሌሊት ጀምሮ ከአንዱ ቤት አንዱ ቤት እየተዘዋወሩ በመብላት ቀኑ ያልፍ የለም እንዴ! በእውነት አበሻ መብላት የሚወደውን ያህል ማብላትም ይወዳል፤ ስሞት! ስቀበር! አፈር ስገባ! … ወዘተ. እየተባባለ የጠገበውን ሰው በቁንጣን እንዲሰቃይ ማድረግ የአበሻ ልዩ የፍቅር መግለጫ ነው! መጎራረስም አለ፤ ፍቅርና ጉርሻ ሲያስጨንቅ ነው እየተባለ ፍቅርና ሆድን ያያይዛል፤ አነጋገሩ አበሻ ለመብላት ያለውን እንጂ ፍቅርን አይገልጽም፤ ማሰጨነቅንና ፍቅርን ምን አገናኛቸው! አበሻ ሌላም ተረት አለው፤ የወለዱትን ካልሳሙለትና የሠሩትን ካልበሉለት ደስ አይለውም ይባላል፤ የልጅ ፍቅር ከምግብ ፍቅር ጋር ተስተካክሎ የቀረበ ይመስላል፤ ደሞም ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል፤ ይላል፤ ጉድ ነው! ሲሞትም ተከተሉኝ የሚል ይመስላል!! ለነገሩማ ፍቅርምኮ አበሻ ዘንድ ምግብ ነው፤ ሆዴ! አንጀቴ! ጎንደሬዎች ሲያሳምሩት ደግሞ ራቴዋ! ይሉታል።

ዛሬ ዛሬ አበሻ ከማብላት ይልቅ ማጠጣት ይወዳል፤ እስቲ ሰዎች ሰብሰብ ብለው በሚጠጡበት ቦታ ብቅ በሉ፤ ያቺን የፈረደባትን ጉበት ለማቃጠል በአቦ፣ በሥላሴ የማይል የለም፤ ቸገረኝ ብሎ ገንዘብ የሚጠይቅ አይምጣ እንጂ ለማብላትና ለማጠጣት፣ ለአንድ ጥሪኝ ፈሳሽ አበሻ ቸር ነው፤ በላኤ ሰብስ በማርያም ስም አንድ ጥሪኝ ውሀ ሰጥቶ አይደለም እንዴ የበላው ሰው ሁሉ የተሰረዘለት? አበሻ በሆድ አይጨክንም።

ለአበሻ ምግብ ክቡር ነው፤ ስለዚህም ምንም ነገር ሲበላ ተቀምጦ ነው፤ ፈረንጅ ቂሉ በየመንገዱ እንደመጋዣ ያመነዥካል፤ በየመንገዱ ማመንዠክ ምግቡን ማዋረድ ነው፤ ከዚያም በላይ ቆመው ሲበሉ ወደጉልበት ይወርዳል ይላል፤ ለአበሻ ጨጉዋራና ጉልበት በቀጥታ የተገናኙ ናቸው፤ ሳይንሱ የሚለው ሌላ ቢሆንም አበሻ አበሻ ምን ቸገረው?

ለመሆኑ ከሆድ ጋር ያልተያያዘ ነገር አበሻ ምን አለው?  ነገርን በሆድህ ያዘው ምን ማለት ነው? ነገርን ማብላላት የማሰብ ምትክ መሆኑ ነው፤ ልጆች ሆነን አይጥ አበላሁት እንል ነበር፤ አሸነፍሁት ለማለት ነው፤ ዛሬም ቢሆን ቁማርተኞች በላሁ-ተበላሁ ይባላሉ፤ አይጥ ከማብላት ገንዘብ ወደማብላት ተለወጠ እንጂ ከሆድ አልወጣም፤

አበሻ በሆዱ የማይዘው ምን ነገር አለ? ፍቅርም፣ ጥላቻም በሆድ ነው፤ ቂምም በሆድ ነው፤ ምኞትም ፍላጎትም በሆድ ነው፤ ተስፋም በሆድ ነው፤ መጥኔ ይስጠው የአበሻ ሆድ! ሁሉን ከተናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል፤ አይ የአበሻ ሆድ! የነገር ስልቻ ከመሆኑ በላይ ነገር አልቆበት ‹‹ነገር እንዳይርበው(!)›› ጥንቃቄ ማድረግ አለበት! የአበሻ ሆድ እህል ቢያጣና ከእህል ባዶ ቢሆንም ከነገር ባዶ መሆን የለበትም፤ እህል ቢጠፋም ነገር አይጥፋ!

የአበሻና የሆድ ነገር በዚህ አያበቃም፤ አበሻ ሲያመው ቡዳ በልቶት ነው፤ ቆንጆውን ሁሉ ቡዳ ይበላዋል፤ ልብ በሉ ለአበሻ በዓይንም ይበላል ማለት ነው! አንዳንዴም ሲያመው መድኃኒቱ ምግብ ነው፤ ለሆድ ቁርጠት ብላበት፤ አበሻ ሲሞትም ለቅሶው ሁሉ ስለሆድ ነው፤ ‹‹የኔ ሆድ፣ ሆዴ እንዴት ይቻለው! ፋሲካን የት ልፈስክ?››

እስከናካቴው ‹‹ሆድ›› የሚባል ቃል ከአበሻ ቋንቋ ፈጽሞ ቢሰረዝ ቋንቋው ብቻ ሳይሆን አበሻም ጉድ ይፈላበታል፤ አእምሮ፣ ኅሊና የሚባሉትን ቃላት አበሻ አያውቃቸውም፤ ተግባራቸውንም ሁሉ ለሆድ ሰጥቶታል።

Advertisements
This entry was posted in አይ አበሻ!, አዲስ ጽሑፎች. Bookmark the permalink.

6 Responses to አይ አበሻ! አበሻና ሆድ፤ ሁለት

 1. Yibekal says:

  Selam Professor,
  Bemejemeria betam lameseginot ewedalew. Berso metsihaftina metatifoch betam bizu tetekimealew. Yemayakugn temariwo adrige erasen ekotiralew.
  Kelay betsafut lay andand neger libel biye new zare. Ye Abesha abiro mebilat bego new biye asibalew. Ye mihirabawiyan bahil endewim begilegninetu litech yichilal bezy reged. Bergit yemihirabawiyan bicha new lemalet yikebidal . Ke ketema silitane gar teyayizo be Ethiopia yeketema botawoch lay yitayal. Lemisale Addis Ababa lay abiro mebilatim hone metetat ejig kekenese kerarimual.
  Abesha migibin weyim hodun yemiagolaw band wegen ke dihinet gar liyayaz yichilal. Begile lemigib yemisetew waga ke gileseb gileseb ke geby dereja gar silewawet asitewuyalew. Yemitafit lemebilat rejim gize yetebeku yagerachin sewoch tiru neger bemebilat amet bahilin biakebiru yemigerim mehon yemigebaw ayimesilegnim. Yemayigegn neger bemagignet amet behal bemelaw alem yemikeber yimesilegnal. Be egna ager yemayigegnew tiru migib silehone yihewin bemakireb sewoch yakebiralu.

  Begile kasazenign negeroch wisit sewoch bemigib ende gubo sidelelu new. Neger gin yihew yemigib matatina dihinet enjy bahil new lemalet betam yikebidal.

  Akibariwo,
  Yibekal

 2. Pingback: አይ አበሻ! አበሻና ሆድ፤ ሁለት

 3. Bisrat says:

  Betam yemigirm ewenet nwe ! ke hodachin belay masib alben, yalfiwe alfuwal Kehodachin belay lelam kum nigir ale ! Professor bekild melk Yehodachwen nigirewenal, yekireta yelebachiwen nigirwenal. Ewenet nwe zare lay betam bizu akirare hodamoche lenafira yechalnwe bizehu asitesasibachen nwe.
  akirare hodamoch degmo agire eyeshetu yebilalu, swe eyegidelu yebilalu, Bahile eyeshetu yebilalu, Fitehe eyazabu yebilalu. Awo leakirare hodamoche HULUM NIGIRE MEBELA NWE !
  Rgime edme le Professor Mesfin W/Mariam yesitelgn. Amelak enderso yale swe ayasatan.

 4. Begashaw Debela says:

  አባቴ ሆይ፤ ማህበረሰባችን ከአመጋገብ ጋር አቆራኝቶ የዘረጋውን ማህበራዊ እና ባህላዊ ቁርኝት ማለፊያ አድርገህ አቅርበኸዋል፡፡ ይበል ይበል ብዬሀለው፡፡ መብል ያለውን/የነበረውን ፖለቲካዊ ፋይዳ ደግሞ ግዜ ካለህ ብትዳስሰው እጅግ የተሟላ ይሆን ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የታሪክ ምሁራን ሳይተነተኑ በቸልታ ከታለፉት ፅንሰ ሀሳቦች መሀከል ተስካር እና የቤተ-መንግስት ግብር የነበሯቸው የፖለቲካ አንድምታ ተጠቀሽ ናቸው፡፡ ታዲያ የቤተ-መንግስት ግብር (ደጅ ጥናትን ጨምሮ) ሆነ ተዝካር የተቆራኙት ከመብል ጋር ነው፡፡ አንተስ ምን ትላለህ?

 5. Flagot says:

  ፕሮፌሰር፤ ከላይ ካቀረቧቸው ነጥቦች በተወሰኑት ላይ እስማማለሁ፡፡ በተለይ እንደነ ወደጉልበት ይወርዳልና፣ አይን በልቶት ነው አይነት ምክንያቲያዊ ያልሆኑ የአበሻ እምነቶች ላይ የሰጡት አስተያየት እጋራለሁ፡፡
  ከዚህ ውጪ ነገሮችን የእኛ ስለሆኑ ብቻ የመንቀፍ ሁኔታን አልጋራም፡፡ አብሮ መብላትና መጠጣት፣ መተሳሰብን የመሳሰሉ የአንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ባህሎች የፈረንጅ ሆነው አበሻ ብቻዬን የሚል አባዜ ቢኖረውም የኛ በመሆኑ ብቻ ከመተቸት የምንላቀቅ አይመስለኝም፡፡ በአብሮነታችን ውስጥ ብዙ የህይወት ስንክሳሮቻችንን ተሻግረናል፡፡ በማህበራዊና ፖለቲካዊ ህይወታችን የተጋረጡብንን ሙዳ መከራዎች በአብሮነት ጫንቃችን ተሸክመናል፤ ታግለናልም፡፡እናም ፐሮፌሰር ነገሮችን የኛ በመሆናቸው ምክንያት ብቻ የመውቀስ ክፉ አበሻዊ አባዜ እርሶም ጋር እንዳጋባ አደራዎትን፡፡

 6. Pingback: አይ አበሻ! አበሻና ሆድ፤ ሁለት - EthioExplorer.com | EthioExplorer.com

Comments are closed.