አይ ስብሐት ነጋ!

መስፍን ወልደ ማርያም

ታኅሣሥ 2006

በኢትዮጵያ ውስጥ ሥልጣን ሳይኖረው ባለሙሉ ሥልጣን፣ እውቀት ሳይኖረው ባለሙሉ እውቀት የሆነ ሰው ስብሐት ነጋ ብቻ ነው፤ እንዲያውም ከዚያም አልፎ ራሱን የቻለ ሉዓላዊ ነጻነት ያለው ግለሰብ ነው ለማለት የሚቻል ይመስለኛል፤ በዚህ ግለሰብ ላይ የማደንቃቸው ሁለት ነገሮች ናቸው፤ በሉዓላዊነቱ የተጎናጸፈውን ሥልጣን ሙሉ በሙሉ ይጠቀምበታል፤ ይቆጣኛል ወይም ይቀጣኛል ብሎ የሚፈራው የለም፤ ስብሐት ነጋ የሚፈራው ምንም ነገር የለም፤ ሁለተኛ በሉዓላዊነቱ ያለውን ሙሉ ነጻነት በሙሉ ልብ ይጠቀምበታል፤ ናስ በላይ ከበደ እንዳለው ‹‹የቅብጠት መዘላበድ›› ሊሆን ይችላል፤ ስብሐት ነጋ የተናገረው ነገር ትክክል ይሁን አይሁን ጉዳዩ አይደለም፤ ዋናው ነገር መናገሩ ነው።

በቅርቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከጋዜጠኛነት ተማሪዎች ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ሁለት ሰዎች ጽፈው አይቻለሁ፤ ዶር. በድሉ ዋቅጅራ በፋክት ላይ፣ ናስ በላይ አበበ በኢትዮ-ምኅዳር ላይ፤ ሁለቱም ሰዎች አልወደዱለትም ማለት ያንሳል፤ የሚወዱለትና የሚያጨበጭቡለት መኖራቸውም ሳይታለም የተፈታ ነው፤ ነገር ግን ስብሐት ነጋም ሆነ ደጋፊዎቹ አደባባይ ወጥተው ለመከራከር አይችሉም፤ ናስ በላይ አበበ እንደሚነግረን ‹‹አቶ ስብሐት ነጋ የውጭ ሰው እንዳይገባ ከተማሪዎቹ ጋር ተደራድረው ነበር የመጡት፤ ስለሆነም ነበር ከፍተኛ ጥበቃ አልፈን የገባነው፤›› ብቻውን ተናግሮ በጭብጨባ የሚሸኝበት መድረክ በመፈለጉ በከባድ ጥያቄም ቢሆን የሚያጣድፉት ሰዎች እንዳይኖሩ ማረጋገጡ በተማሪዎቹም ቢሆን ውሎ አድሮ ትዝብት ላይ ይጥለዋል።

ዶር. በድሉ ዋቅጂራ ስለስብሐት ነጋ ከኢትዮጵያዊነት መውደቅ በሚል በጻፈው ላይ ዶር. ዳኛቸውን እንደሚከተለው ይጠቅሳል፤ ‹‹ከኢትዮጵያዊነት መውደቅ ማለት፤ በቃ በአጭሩ (ኢትዮጵያዊ ሆኖ) ኢትዮጵያዊ አለመሆን ነው፤›› በቅንፍ ውስጥ ያለው የኔ ነው፤ ልክ ነው፤ አንድ ግለሰብ በማናቸውም ምክንያት ከኢትዮጵያዊነት ቢወድቅ ኢትዮጵያዊነቱ የከሸፈ ነው ለማለት ይቻላል፤ ነገር ግን ከኢትዮጵያዊነት መውደቅንና ኢትዮጵያዊነትን መጣልን ለይተን ማየት ያስፈልጋል፤ አንድ ሰው በማናቸውም ምክንያት ከፍተኛውን የኢትዮጰያዊነት ባሕርይና ግዴታ መሸከም አቅቶት ቢወድቅ ለዚያ ሰው ኢትዮጵያዊነቱ ከሸፈ፤ ለስብሐት ነጋና ለጓደኞቹ ከከሸፈባቸው የቆየ ይመስለኛል፤ ከራሱ አልፎ የሌሎችን ኢትዮጵያዊነት ለማክሸፍ የሚሞክር ደሞ ከመክሸፍ አልፎአል፤ ከኢትዮጵያዊነት መውደቅ ማለት የከሸፈ ኢትዮጵያዊነት ነው ማለት ነው።

ስብሐት ነጋ ዋና ዓላማው በሙሉ ነጻነት የመጣለትን እንደመጣለት መናገር ነው፤ ምሳሌዎችን እንጥቀስ፤– ሀ) ‹‹ከኢትዮጵያ ሕዝብ በላይ የኤርትራ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነት አለው፤›› ስብሐት ነጋ ስለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ስለኤርትራ ሕዝብ፣ ስለኢትዮጵያዊነት ያለው እውቀት የሚባል ነገር እንዲህ ያለው መዘባረቅ ነው፤ ስብሐት ነጋ ጨረቃ ከጸሐይ የበለጠ ትሞቃለች ቢልም አይደንቀኝም፤ አልከራከረውም፤ ስብሐት ነጋም ብቻውን መናገር እንጂ መከራከር አይፈልግም፤ ለ) ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኤርትራ ሕዝብ የበለጠ የኤርትራን መሬት ይፈልጋል፤›› እንደምሳሌ ያነሣው አሰብን ነው፤ ባድመን አላነሣም!  እሱና ጓደኞቹ የኢትዮጵያን ወጣቶች በከሸፈ ጦርነት ውስጥ የማገዱት ባድመ ለሚባል መንደር ነው እንጂ አሰብ ለሚባል ወደብ አልነበረም፤ በዚያን ጊዜ ጦርነቱን በመቃወም ድምጼን ያሰማሁት ኢትዮጵያዊ ወይም ኤርትራዊ ሆኜ አልነበረም፤ ሰው ሆኜ ነው፤ ዛሬ ስብሐት ነጋ ሲዘላብድ ኢትዮጵያዊነት የማይታይበትን ያህል ኤርትራዊነትም አይታይበትም፤ በዚህም ጉዳይ ላይ መከራከር አይፈልግም፤ ሐ) ‹‹ለማንኛውም ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ መከልከላቸው የማውቀው ብዙ ነገር የለኝም፤ ይከልከሉም አልልም፤ አይከልከሉም አልልም፤ መብታቸው ነው፤›› ይህ መዘላበድ ካልሆነ ምንድን ነው? ምን ቁም-ነገር ይዞ ነው ይህንን የተናገረው? የገለባ ክምር ውስጥ አንድ ፍሬ መፈለግ ይቀላል።

አንድ ሌላ የስብሐት ነጋ ዘዴ (ዘዴ ካልነው!) ጉዳዩን በሚገባ ሳያጣራ እንደመጣለት ይናገርና ‹‹አላውቅም›› ይላል! የማያውቀውን መዘባረቅ ግን ይችላል፤ ሰማያዊ ፓርቲ ‹‹የምን ፓርቲ እንደሆነ አይታወቅም፤ የእስላም ፓርቲ ነው?›› ስብሐት ነጋ እውቀትን የሚሻ ቢሆን ለፓርቲዎች እውቅናን የሚሰጠውን መሥሪያ ቤት ያውቀዋል፤ ለምን ብሎ ይጠይቅ? ለምን ብሎ እውነቱን በማወቅ ይታሰር? ትክክለኛ መረጃ ባለማወቅ እንደልብ የመናገርን ነጻነት ይገድባልና ‹‹አላውቅም›› ማለት ለመዘላበድ ይጠቅማል፤ ምንም እንኳን የሰላዮች ሠራዊት እንዳለው ብናውቅም ስለእስላሞችና ስለሰማያዊ ፓርቲ የተናገረውን እንደፖሊቲካ ከወሰደው ደረጃውን ከማሳየት አያልፍም፤ ሰማያዊ ፓርቲን በሁሉም ዘንድ ለማስጠላት የሚከተለውን ይላል፤ ‹‹እስላሞች ወንድሞቻችን የሚሉት ደግሞ የት ያውቁናል? ሲቀጠቅጡን የነበሩ፤ ተራ ሕዝቡም አይወዳቸውም፤›› የጤፍ ቅንጣት የምታህል የማሰብ ተግባር ቢኖርበት ስብሐት የተናገረው ያልተጠረነፉትን እስላሞች በሙሉ የሰማያዊ ፓርቲ ደጋፊ የሚያደርግ መሆኑን መረዳት ይችል ነበር።

ስብሐት ነጋ አንድ መቶ ሃያ ዓመታት ያህል ወደኋላ ቢሄድ ኤርትራ የሚባል አገር አያገኝም፤ በዚያ መሬት ያሉ ሰዎች ላላቸው ወይም ለሌላቸው የኢትዮጵያዊነት ስሜት የስብሐት ነጋን ምስክርነት እንደማይፈልጉ በጣም እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል፤ ለሌሎቻችን ኢትዮጵያዊነትም ቢሆን የስብሐት ነጋ ምስክርነት አያሻንም፤ አሰብን አንሥቶ ብዙ ወጣቶች ያለቁበትን ባድመን ሳያነሣ መቅረቱ በአንድ በኩል፣ አሰብንም ሆነ ባድመን ከሚፈልጉ ወገኖች መሀል እሱ መውጣቱን በጣም ግልጽ አደረገ፤ ወዴት እንደገባ ግን ገና አልነገረንም!!!

 

Advertisements
This entry was posted in አዲስ ጽሑፎች. Bookmark the permalink.

2 Responses to አይ ስብሐት ነጋ!

 1. Pingback: አይ ስብሐት ነጋ!

 2. በለው! says:

  በኢትዮጵያ ውስጥ ሥልጣን ሳይኖረው ባለሙሉ ሥልጣን፣ እውቀት ሳይኖረው ባለሙሉ እውቀት የሆነ ሰው ስብሐት ነጋ ብቻ ነው፤ ስብሃት ነጋ አማርኛ፣ ታሪክ፣ ኅበረት ትምህርትና አልፎ አልፎ እስፖርት መምህር ሆነው ኢትዮጵያን ኢትዮጵያውያንን እና ኢትዮጵያዊነትን ሲሰልሉና ሲሰረስሩ የኖሩት ሞጃ ሀገር የደብረብርሃን ቁንዲፍቲ እየጠጡ ነበር። “ሀገር ማለት ህዝብ ነው” ‹‹ሀገር ማለት ህገ-መንግስት ነው›› ሻቢያህወአት/ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ፣ ባለስልጣናቱ እንደ ኢሊት ከ፲፱፹፫ዓ.ም ቀድሞ የነበረ ሁሉ ነገር እርኩስ፣ ከ፲፱፹፫ ዓ.ም ወዲህ ያመጡት ሁሉ ቅዱስ ይመስላቸዋል፡፡ ሕገመንግስቱ የሻቢአህወአት(ማኒፌስቶ ነው) ስንላቸው ፣አጃቢዎቻቸው ማኒፌስቶ ይተገበራል ህገ መንግሰት ይከበራል አሉን፡ እኛም ካልተተገበረ ይቀበራል! አልናቸው። አንዳንድ ግዜ ኢህ ሻቢያ ህወአት/ወያኔ/ኢህአዴግ የሚባልን የወሮ-ባላ በድን ነገር ለመረዳት ያስተችግራል ሀገርና ፓርቲ ጠፍቶባቸዋል!…እናንት ብሔር ብሄረሰቦች ሆይ፤ የተረሳችሁ! ማንነታችሁ ያልታወቀ! የፈጠርናችሁ ማንነታችሁን ያሳወቅናችሁ!ለእኛ በእኛ የምትኖሩ ያለ እኛ የምትጠፉ ድንቅዬ ተናጋሪ እንስሶች እያሉ ያስታጥቁታል።

  ዶር. በድሉ ዋቅጂራ ስለስብሐት ነጋ ከኢትዮጵያዊነት መውደቅ በሚል በጻፉት ላይ… ዶር.ዳኛቸው አሰፋን ትንታኔ ጠቅሰዋል” ህወአት ደርግን አሸንፎ መጣል፣ የቀደመውን እሴት ሁሉ የመጣል ጋራንቲ የሚመስላቸው፡፡ በዚህ አስተሳሰብ የተነሳ የተቻለው ሁሉ ተለውጧል፡፡ብሔር ብሔረሰብ ዜግነቱ በሀገሩ ሳይሆን በህገ-መንግስቱ እንዲቀረጽ ይፈለጋል፡፡ ህገ መንግስታዊ እንጂ ሀገራዊ ዜግነት አይፈቀድለትም፡፡ አይለወጤ የሆነው (ሆኖ ያስቸገረው) ዜግነታችን ነው – ኢትዮጵያዊነታችን!!፡፡
  ” ‹ከኢትዮጵያ ህዝብ በላይ የኤርትራ ህዝብ ኢትዮጵያዊነት አለው፡፡››”ከትጥቅ ትግል ጀምሮ አሁንም በኢህአዴግ በከፍተኛ አመራር ላይ ኤርትራውያንና ትውልደ ኤርትራውያን አሉ እኔም ኤርትራዊ ነኝ” የሚሉት ነፃ አውጭ ስብሃት ነጋ የሚናገሩ እንጂ የማይጠየቁ ምሁር!
  “ዘመንና አጋጣሚ የመረቃቸው ኤርትራውያን በሀገራቸው ጥሩ ኤርትራዊ፣ በሀገራችንም ጥሩ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ እኛ እዚህ ኢትዮጵያዊ እዚያም ኤርትራዊ አይደለንም፡፡ ከኤርትራ ንብረታችን ተዘርፎ ስንባረር፣ የኤርትራ መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያም መሪዎች ውሸት ብለው አላግጠውብናል፡፡ ለምን? እዚያ በኤርትራዊነት ስለሚበልጡን መሪዎቹ ዘርፈው አባረሩን፡፡ እዚህ በኢትዮጵያዊነት ስለሚበልጡን መሪዎቻችን አፊዘው ተቀበሉን፡፡ እውነቱን ብለዋል አቦይ ስብሀት! በመሪዎቻችን ሚዛን ኤርትራውያን በኢትዮጵያዊነት ይበልጡናል፡፡ ምን ኤርትራውያን ብቻ! ‹‹ለኤርትራ ብቻ ሳይሆን ለሶማሊያ፣ ለሱዳን፣ ለጅቡቲም፣ ለኤርትራም አትራፊ መሆን የእኛ የቤት ስራ ይመስላል፡፡›› ያሉት አቦይ ስብሀት ጅቡቲ፣ ሱዳንና ሱማሌስ በኢትዮጵያዊነት ስለሚበልጡን አይደል! እንግዲያማ በኮረንቲ በቀን አስሬ መጥፋት እቃችን እየተቃጠለ፣ ቋት የገባ እህል ሳይፈጭ እያደረ፣ በየቢሮው ያለስራ እየተዋለ፣ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሱዳን ድረስ፣ የኮረንቲ መስመር ዘርግተው ለምረቃ ይሄዱ ነበር!
  **ስብሀት ነጋ **ሕዝብ ከኤርትራ ሕዝብ የበለጠ የኤርትራን መሬት ይፈልጋል፤›› እንደምሳሌ ያነሣው አሰብን ነው፤ ባድመን አላነሣም! አስጨብጭቦ ጠፋብኝ አፋልጉኝ የሚሉት ሊቀ/ጠበብት መስፍን ወልደማርያም እሱና ጓደኞቹ የኢትዮጵያን ወጣቶች በከሸፈ ጦርነት ውስጥ የማገዱት ባድመ ለሚባል መንደር ነው። የስብሐት ነጋ ዘዴ (ዘዴ ካልነው!) ጉዳዩን በሚገባ ሳያጣራ እንደመጣለት ይናገርና ‹‹አላውቅም›› ይላል! የማያውቀውን መዘባረቅ ግን ይችላል፤ ይህ ኢህአዴጋዊ ሥልታዊ ከዕውቀት ማነስ የሚመጣ ማፈግፈግ ነው “ብለዋል። አቶ ስብሃት ግን ያልተማሩ ሠፈርተኞች አዳመቂ ናቸው ” መልስ ዜናዊ ኖረ አልኖረ! ፋጡማ (የኋላዊት እመቤት አዜብ) ኖረች አልኖረች ሕግመንግስታዊ ውርዓቱ ይቀጥላል። መለስ መሞቱ እነደተሰማ በሀለት ሰዓት በኃላ ኅያለማርያም ደስአለኝ ጠ/ሚኒስትር ሆነ… ግን ፴፬ ጄነራሎች መሾማቸውን መቼ እንደተሾሙ መረጃ የለኝም አልሰማሁም።
  “አንድ ሺሕ አራት መቶ ማይልስ የሚያህል የውኃ ጠረፍ ካስረከብን በኋላ አራት መቶ ኩንታል ድንች ለማያመርት ቦታ ከ፶ እስከ ፷ ሺሕ ወጣት በጦርነት ገብረናል።” ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ
  ” የሱዳን ሕዝብ የእኛን አትንካ የአንተን እንካፈል ሲባል ዝም ብሎ የኖረ ህዝብ ነው” መለሰ ለገሠ
  ***ዶር ዳኛቸው የጣሊያዊውን ፈላስፋ ምሳሌ “The easy way of being original” ማለት ብዙ አለማወቅ ነው። ብዙ አለማወቅ ደግሞ ታሪክን አለማንበብ ነው። ይሄ ደግሞ “Arrogance of Ignorance” ማለት ነው። ይህም ማለት አለማወቅ የራሱ የሆነ ‘Ignorance’ አለው። ስታውቅ ትሑት ትኾናለህ፤ ትሕትናን ታዳብራለኽ፤ ካላወቅኽ ግን ጣሊያናዊ ፈላስፋ በዚህ ዓለም ላይ አልፎ አልፎ ‘‘እኛ እስከመጣን ድረስ ዓለም ጨለማ ውስጥ ነበረች ዕድሜ ለእኛ ችቦ ብርሃን ታየ የሚሉ ጎበዞች ይመጣሉ’’ ብሏል።“በኢትዮጵያ ስንመጣ ብርሃን ሆነ” ማለት የተለመደ ነው። ስለህግ ሲወራ ኢትዮጵያ ከአሁን በፊት ምንም አይነት ሕግ ያልነበራት ትመስላለች። ጎበዞቹ ሲመጡ ሕግ እንዳመጡለት ነው የሚያወሩት። ጎበዞቹ [ኢህአዴጎቹ] ሁሌ ስንገዳደል አግኝተውን እነሱ ባመጡት ሕግ እንደ አዳኑን ይነግሩናል። ነገር ግን ይሄ አገር ስንት ሺህ አመት የኖረ ሕዝቡም ያልተፈራረመው ማኀበራዊ ውል (social contract) ያለው ሕዝብ ነው። ሕዝቡ ለዚህ ነው የማይፈርሰው። እንደአካፋው ብዛት ባለፉት ፳፩ ዓመታት ይሄ አገር (ስቴት) መናድ ነበረበት። ከመንግስት ውል በላይ በማኀበራዊ ውሉ የጠነከረ ሕዝብ ነው። የሶማሌ ሕዝብ ማኀበራዊ ውሉ በጎሳ የላላ ስለሆነ ቢሉት ቢሉት አንድ መሆን አልቻለም ብለዋል።ዶር ዳኛቸው። ለዜጋው የማይቆረቆር የሚንቅና የሚያዋርድ፣ የሀገርና የህዝብን ማንነት ለባዕድ የሚሸጥ የሚለውጥ፣ አሳልፎም የሚሰጥ፣ ወሮ- በላ፣ቅጥረኛ፣አድርባይ፣ ባንዳ፣ (ለጠላት ዶሮና እንቁላል አቅራቢ በአቶ ገብረመድህን አርዓያ አገላለጽ(ሹምባሽ) ፣በታኝ፣ ጎጠኛ፣ዘረኛ ቢባል እንደመንግስት ሻቢያህወአት/ ኢህአዴግ ከኢትዮጵያዊነት ወድቋል፤ እንደ ታላቅ ታጋይና የፖለቲካ ሰው ደግሞ አቦይ ስብሀት ነጋ፡፡ከኢትዮጵያዊነት መውደቅ ማለት፤ በቃ በአጭሩ ኢትዮጵያዊ አለመሆን ነው፡፡ ሌላ ማንነት መገንባት (IDENTITY DEVELOP) ማድረግ ነው፡፡››!!! ተው ተመለስ በለው!! በቸር ይግጠመን

Comments are closed.