ሰላማዊ ወይስ የትጥቅ ትግል ወይስ ማንፈራጠጥ

መስፍን ወልደ ማርያም

ጥር 2006

የተማረ ወይም የእውቀት ባለቤት እንደሆነ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ክፍል ከወያኔ ጋር የሚደረገው ትግል ሰላማዊ ይሁን ወይስ በትጥቅ ትግል የሚለውን የጦፈ ክርክር ሲያደርግ ሃያ ሁለት ዓመታት ሆነው፤ ዳኛ የሌለበት ክርክር ስለሆነ የመደማመጥ ግዴታ ታይቶበት አይታወቅም፤ ስለዚህም በሁለቱ መሀከል ያለው ልዩነት ግልጽ ሆኖ አያውቅም፤

አንድ፣ ከሁሉ በፊት ሰላማዊ ትግል በሀሳብ ደረጃ መሆኑንና የትጥቅ ትግል ደግሞ በተግባር መሆኑን ለይቶ ለመረዳት ችግር ሆኖ ቆይቶኣል፤ በሌላ አነጋገር ሰላማዊ ትግል በሀሳብ፣ በንግግር፣ በተለያዩ ሀሳብን ለማስለወጥ መቀስቀሻ በሚሆኑ መንገዶች ተቃውሞን መግለጽ ነው፤ በአንጻሩ የትጥቅ ትግል በጠመንጃ ወይም በጉልበት ያለውን የአገዛዝ ሥርዓት ለመለወጥ የሚደረግ ሙከራ ነው፤

ሁለት፣ እንዲህ ከሆነ በሰላማዊ ትግል ለሚያምኑ ሰዎች ያለምንም ጥርጥር በተለያዩ ዓላማዎችና ዘዴዎች ላይ መከራከርና ሀሳብን ማጥራት አስፈላጊ ነው፤ በሰላማዊ ትግል ተግባር አለ ቢባልም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የድጋፍ ወይም የተቃውሞ አቅዋሞችን ከማሳየት አያልፍም፤ አገዛዞች ጃዝ! ብለው ውሻና ፖሊስ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ሲለቁ የጉልበት ጥርስና ዱላ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያርፋል፤ ጉዳት ይደርሳል፤ ሰላም ይቃወሳል፤ በሕዝብና በአገዛዙ መሀከል ቂም ይጀመራል።

ሦስት፣  የትጥቅ ትግል ደግሞ በተዋረድ በሚተላለፍ ትእዛዝ የሚፈጸም ግዴታ ነው፤ በትጥቅ ትግል ጉልበተኛ ከጉልበተኛ ጋር፣ ብረት ከብረት ጋር ይጋጠማል፤ የሰው ልጅ ለእርድ ይቀርባል፤ በሕይወታቸው በልተው ያልጠገቡ ምስኪኖች ለጥቂት ሰዎች የሥልጣን ጉጉት ይታረዳሉ፤ ያለቀባሪ በጅብና በአሞራ ይበላሉ፤ ዕድለኞች የሚባሉት እጆቻቸው፣ ወይም እግሮቻቸው ተቆርጠው፣ ወይም ዓይኖቻቸው ጠፍተው፣ ወይም ከዚህ ሁሉ የባሰ ጉዳት ደርሶባቸው በሕይወት የሚቀሩት ናቸው፤ ከነዚህ በሕይወት በቀሩት የጦር ጉዳተኞችና በጦርነቱ ላይ በሞቱት መሀከል የትኛው የተሻለ አንደሆነ የሞቱት ባይናገሩም ጉዳተኞቹ ይናገራሉ፤ ‹የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ!› እያሉ።

አራት፣ ሁለቱ የትግል ስልት ዓይነቶች በባሕርይ የተለዩ ናቸው፤ አንዱ ሌላውን የሚደግፍ አይደለም፤ ሰላማዊ ትግል የትጥቅ ትግልን ለመደገፍ ሰላማዊ የሚለውን ስያሜ መጣል አለበት፤ የትጥቅ ትግልም ሰላማዊ ትግልን ለመደገፍ ትጥቅ የሚለውን ስያሜ መተው አለበት፤ ሰላማዊ ትግልና የትጥቅ ትግል አራማጆች ድል ቢያደርጉ ማን ወንበሩ ላይ እንደሚወጣ ሳይታለም የተፈታ ነው፤ ጠመንጃ የያዘው ሥልጣኑን ሲይዝ ሰላማዊ ትግሉ ይቀጥላል! ያውም ከተፈቀደለት!

በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ አርበኞች ሳይቀሩ በሩ ተዘግቶባቸው ለደጅ ጥናት እንደተዳረጉ አይተናል፤ መልኩን ለወጥ ቢያደርግም ደርግን ከተፋለሙት ውስጥ በአዲስ አበባና በአስመራ ወንበሮች ላይ ሲወጡ የተሸነፉት ወይ ለወያኔ ገብረው ሎሌነት ገቡ፤ ወይም በአሜሪካ መሽገው ያቅራራሉ፤ ዘመኑ እንዳለፈባቸውም ገና አልተረዱም።

አምስት፣ ሰላማዊ ትግልና የትጥቅ ትግል ሁለቱም ብርቱ ቃል ኪዳንን ይጠይቃሉ፤የቃል ኪዳናቸው ልዩነት አንዱ እስከሞት ለመታገል፣ ሌላው ደግሞ እስከመግደልና እስከመሞት ለመታገል መሆኑ ነው፤ ለሰላማዊው ትግል ከፍተኛ መንፈሳዊ ወኔ የሚያጎናጽፈው ለመግደል ያለው ተቃውሞ ነው፤ ሕይወትን ለማልማት ሕይወትን መቅጠፍ የአስተሳሰብም የመንፈስም ጉድፍ ያለበት ሥራ ነው።

የሰላማዊ ትግል ዋናውና ቀጥተኛው ተልእኮ ሕዝብን ለሥልጣን ባለቤትነት ማብቃት ነው፤ ሥልጣንን ለመያዝ አይደለም፤ ስለዚህም ኢላማው ሕዝብ ነው፤ በሥልጣን ወንበሩ ላይ ያሉት የሰላማዊ ትግሉን የሚቃወሙት በሕዝብ ዘንድ ተሰሚነትና ተቀባይነት እንዳያገኝ ለማድረግ ነው፤ ሰላማዊ ትግሉ የሚያተኩረው በሕዝቡ ጆሮ፣ አእምሮና ልብ ላይ ነው፤ አገዛዙ በበኩሉ ጸጥ-ለጥ ብሎ የሚገዛለት ሕዝብ እውቀቱ ዳብሮ፣ መብቶቹን ሁሉ ተገንዝቦ፣ በሕግ ለሕግ እንጂ ለሰው አልገዛም በማለት ልቡ እንዳይሸፍት አፈናውንና ማነቆውን በማጠናከር እያደነቆረ ለመግዛት ይፈልጋል፤ የሰብአዊ መብቶችን የሚያስተምሩና በአገዛዙ አካላት የሚፈጸሙትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የሚያጋልጡ ድርጅቶችን ማዳከም ወይም ማጥፋት ለአገዛዙ አስፈላጊ የሚሆነው ለዚህ ነው፤ ኢሳት የሚባለው የቴሌቪዥንና የራድዮ ፐሮግራም ለወያኔ የውስጥ እግር እሳት የሆነበት ለዚህ ነው፡፡ በሰውነት ደረጃ ሕዝቡ መብቶቹን ሁሉ እንዲያውቅና እንዲረዳ ማድረግ፣

በዜግነት ደረጃ ሕዝቡ ለሥልጣን የሚያበቃውን የዜግነትና የፖሊቲካ መብቶች እንዲያውቅና እንዲረዳ ማድረግ፣ ሕዝቡ የሰውነትና የዜግነት መብቶቹን ተገንዝቦ በአገዛዝ ስር አልተዳደርም የማለት መንፈሳዊ እምቢተኛነት እንዲያድርበት ማድረግ፣ በግልጽ ጭቆናን የሚጠላና ለመብቶቹና ለነጻነቱ በቆራጥነት የሚቆም ሕዝብ እንዲፈጠር ማበረታታት፣ መብቶቹንና የሥልጣን ባለቤትነቱን የተረዳና ከጭቆና ጋር የተጣላ ሕዝብ በፖሊቲካ መስመር ቡድኖችን እየፈጠረ እንዲደራጅ ማድረግ፣ ያወቀና የነቃ፣ በፖሊቲካ መስመር የተደራጀና ማናቸውንም ዓይነት ጭቆና የሚጠላ ሕዝብ ለማንም ጉልበተኛ የማይንበረከክ ሕዝባዊ ኃይል እንዲሆን መጣር፣

የትጥቅ ትግል ዋናውና ቀጥተኛው ተልእኮ በሥልጣን ላይ ያለውን አገዛዝ አውርዶ ወንበሩን ለራሱ ለመውሰድ ነው፤ ይህንን ሲያደርግ ሕዝቡን ወደጎን ትቶ ወይም ዘልሎ ነው፤ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ በጠመንጃ ሥልጣን የሚይዙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥልጣኑን ለሕዝብ እናስረክባለን፤ ትክክለኛ ምርጫ እናካሂዳለን በማለት ሕዝቡን በተስፋና በጠመንጃ ይዞ ነው፤ ነገር ግን ሥልጣንን ሕዝብ ለፈቀደው አስረክበው ከቤተ መንግሥት ሲወጡ አናይም፤ ሲሸሹ ወይም ሬሳቸው ሲወጣ እንጂ።

ብዙውን ጊዜ የማይታሰብ ወይም ብዙዎች የሚዘነጉት የሁለቱ ትግሎች የገንዘብ ወጪ በጣም ከፍተኛ ልዩነት ያለው መሆኑን ነው፤ ሰላማዊ ትግል በሕይወትም፣ በንብረትም፣ በመሣሪያም በዝግጅትም የሚያስከፍለው ዋጋ ከትጥቅ ትግል ጋር ሲወዳደር በጣም አነስተኛ ነው።

ስለዚህም በሁለቱ በተለያዩ ስልቶች አራማጆች መሀከል የሚደረግ ክርክር ምን ዓይነት ነው? የሰላማዊው የመጀመሪያ ደረጃ ኢላማው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፤ የትጥቅ ትግል የመጀመሪያ ደረጃ ኢላማው የወያኔ አገዛዝ ነው፤ በሌላ አነጋገር በሰላማዊ ትግል ሕዝቡ በሰላማዊ ትግል ትንሽም ቢሆን የነጻነትን አድማስ ለማስፋት እንዲችል ድፍረትን በማስተማር በኩል የማይናቅ አስተዋጽኦ ቢያደርግም አገዛዙን የመነቅነቅ ኃይል ገና አላዳበረም፤ አንድም ውጤት አላሳየም፤ የትጥቅ ትግሉ ከፉከራና ከሽለላ እስካሁንም አልወጣም፤ የሰላማዊ ትግል ዓላማ ሕዝቡ መብቶቹን እንዲያውቅ ለማንቃትና ለመብቶቹ እንዲታገል የሚያስችለውን ብቃት ለማስጨበጥ ነው፤ ስለዚህም ዘዴው በሕዝቡ ላይ ነው፤ የትጥቅ ትግሉ ዘዴ አገዛዙን በጉልበት ገልብጦ በዚያው ባልተለወጠ ሕዝብ ላይ ሌላ አገዛዝ ለመመሥረት ነው።

በኢትዮጵያ ለውጥ እናመጣለን የሚሉ ሁሉ የቆሙበትንና የቆሙለትን ዓላማና ዘዴ በግልጽ ተገንዝበው ካልተሰለፉ በተንፈራጠጠ አስተሳሰብ የተባበረ ተግባር ሊገኝ አይችልም።

Advertisements
This entry was posted in አዲስ ጽሑፎች, አፈናና ከአፈና መውጣት. Bookmark the permalink.

9 Responses to ሰላማዊ ወይስ የትጥቅ ትግል ወይስ ማንፈራጠጥ

 1. walelign5 says:

  መንግስት ለሰላማዊ ትግል ደንታ ቢስ ከሆነስ የመጨረሻዉ አማራጭ ምንድን ነው?

 2. Pingback: ሰላማዊ ወይስ የትጥቅ ትግል ወይስ ማንፈራጠጥ | THE ETHIOPIA OBSERVATORY

 3. saba says:

  professor i always print out your article and reads it with my family !!! your are our Nelson Mandela. we wish you long life !!

 4. Pingback: ሰላማዊ ወይስ የትጥቅ ትግል ወይስ ማንፈራጠጥ

 5. Sis Genta says:

  ኢሳት የዚህ ሰላማዊ ትግል መስፈርቱን ያላለፈ ይመስሎታልን?

 6. Pingback: ሰላማዊ ወይስ የትጥቅ ትግል ወይስ ማንፈራጠጥ | Helen Wame

 7. Pingback: ሰላማዊ ወይስ የትጥቅ ትግል ወይስ ማንፈራጠጥ | Helen Wame

 8. Gizachew Yohannes says:

  የትግል ስልት ከመመረጥ በፊት የምንታገልለት ነገርን እንስማማ
  ፕሮፌሰር ለእኔ የምንታገለውን የትግል ስልት የሚወስንልን ዋና ፓራሜትር ሆኖ የሚታየኝ የምንታገልልት ነገር ነው፡፡
  ከዚህ አንጻር ምን አልባት በባለፉት 20 አመታት ነፃነት እኩልነት በመረጥነው የመተዳደር ቋንቋን መሰረት ያደረገውን የፌደራሊዝም ስረዓትን የመገንጠል መብትን የዜጎች በብሄር መዳኘት መፈናቀል በኢትዮጵያዊነታቸው በፈለጉት ቦታ ተዘዋውሮ የመኖር እና የመስራት መብት መነፈጉን እንዲሁም የኤርትራ እና የአሰብ ጉዳይ ከዛም ሲጨመር ለምን መሬት ከትግራይ ወደ ኤርትራ ከጎንደር ወደ ትግራይ እና ወደ ሱዳን ተወሰደ አሊያም ከጋምቤላ ለምን ለባዕዳን የእርሻ መሬቱ ተነጥቆ ተቸበቸበበት የምንላቸው እና የምንታገልላቸው ጉዳዮች ነበሩን አሁንም አሉን፡፡
  ጉዳያችን እኒህ ሲሆኑ የትግሉን ስልት ለመመረጥ ቀላል ነው የእርሶም ድምዳሜ ያስማማኛል፡፡ ችግር የሚሆነው ችግራችን ከዚህ የዘለለ ሲሆን ነው፡፡
  ለእኔ በዚህች በጥቂት አመት ውስጥ ኢትዮጵያዊነት አደጋ ላይ ወድቆ እየተፈጠረች ያለችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ከላይ የጠቃቀስነቸውን ነገሮች ስላጡ የምንታገልላቸው አኩሪ ማንነት ያላቸው ህዝቦች ሳይሆኑ የእነርሱን ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር የምንታገላቸው አይነት እየሆነ ነው፡፡
  ትውልዱ በአደንዛዥ እጾች ቁጥጥር ስር ወድቋል
  ግብረ ሰዶማዊነት የትውልዱ መገለጫ እየሆነ ነው
  ሴተኛ አዳሪነት ከኢትዮጵያ አልፎ በአለም የምንታወቅበት የባህሪያችን መገለጫ እስከመሆን ደርሷል
  ዘረኝነት የተመሰረተን ትዳር የማፍረስ ሀይል ገንብቷል
  ያለሙስና ሲስተሞቻችን ፋክሽን አያደርጉም
  የእኛነታችን ምንጭ የሆኑት እምነቶቻችን ተቋሞቻችን ተንደው ከጫፍ ደርሰዋል
  ፕሮፌሰር እስቲ አሁን ባለው ላይ 10 አመት እንጨምር በእረግጠኝነት የትግል ስልት መርጠው የሚታገሉለት ሳይሆን ሀገሪቷን ጥለው የሚሸሹት አይነት ትውልድ እየፈራ ነው፡፡
  ይህን ሲያስቡት የትግል ስልቱ ምን ይሁን ይላሉ????

  ለልጄ እነደ እርሶ አይነት አባት ልሆንለት የምፈልግ የመንፈስ ልጅዎ!!!!

 9. Pingback: ሰላማዊ ወይስ የትጥቅ ትግል ወይስ ማንፈራጠጥ - EthioExplorer.com | EthioExplorer.com

Comments are closed.