ወልቃይት የማን ነው? የማይረባ ጥያቄ

 

 

መስፍን ወልደ ማርያም

ነሐሴ 2008

 

አንድ

በነገረ አስተሳሰብ ወይም በአስተሳሰብ ሕግ (ሎጂክ) ትምህርት ላይ አንድ የማስታውሰው ምሳሌ አለ፤ ‹‹ሚስትህን መደብደብ ትተሃል ወይ?›› የሚል ጥያቄ ነው፤ ጥያቄው የሚነሣው ጠያቂው አውቃለሁ ብሎ ከያዘው እውቀት ወይም እምነት ነው፤ ስለዚህም ጠያቂው የሚፈልገው ጥያቄ ለማስተላለፍና መልስ ለማግኘት አይደለም፤ ጠያቂው የሚፈልገው በጥያቄ መልክ የራሱን ‹‹እውቀት›› ወይም እምነት ለተጠያቂው ለማስተላለፍና ተጠያቂውን የጠያቂው ደቀ መዝሙር ለማድረግ ነው፡፡

ሚስትህን መደብደብ ትተሃል ወይ? መልስ የሌለው ጥያቄ ነው፤ ‹‹አዎ›› የሚል መልስ ሰውዬው ሚስቱን ሲደበድብ እንደነበረ አመነ ማለት ነው፤ ‹‹አልተውሁም›› ከአለ በራሱ ላይ መሰከረ፤ ሁለቱም መልሶች ተጠያቂውን የሚያስወነጅሉ ስለሆኑ መልስ አይደሉም፤ ከዚያም በላይ ጥያቄው ትክክል አይደለም፤ የማይረባ መጥፎ ጥያቄ ነው፡፡

‹‹ወልቃይት የማን ነው?›› የሚለው ጥያቄ ትክክል አይደለም፤ የማይረባና መጥፎ ጥያቄ ነው፤ ጠያቂው የሚፈልገው መልስ የአማራ ነው፤ የጎንደር ነው፤ የትግሬ አይደለም፤ የሚል ነው፤ ነገር የሚገባው ተጠያቂ ጥያቄውን ጠያቂው በፈልገው መልክ አይመልስለትም፤ ሊመልስለትም አይገባም፤ ወልቃይት የኢትዮጵያ ነው የሚል መልስ አይፈለግም፤ የማይፈለግበትም ምክንያት ‹‹ወልቃይት የኢትዮጵያ ነው፤›› ማለት ወልቃይትን ከጎሠኛነት አጥር ስለሚያወጣ ነው፤ የትግራይ አይደለም፤ የአማራ አይደለም፤ የኢትዮጵያ ነው፤ አሁን ትግራይና አማራ የኢትዮጵያ ናቸው፤ ይህ ከተባለ በኋላ ወልቃይት የትግራይ ነው? ወይስ የአማራ? የሚለውን ጥያቄ ማንሣት የጎሠኛነት ጥያቄ ነው፤ የኢትዮጵያዊነት ጥያቄ አይደለም፤ ጥያቄው የማይረባ የሚሆንበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው፤ ሁለተኛው ምክንያት የጎሠኛ ጥያቄ በመሆኑ የወያኔን የጎሠኛ መመሪያ የሚያከብር መሆኑ ነው፡፡

ትልቁና መሠረታዊው ጥያቄ በአማራ ክልል ስር የነበረው ወልቃይት በወያኔ አገዛዝ ወደትግራይ ክልል መግባቱ ነው፤ እዚህ ላይ ጥያቄው የወልቃይት ወረዳ ወይም አውራጃ ነው፤ በውስጡ የሚኖሩት ሰዎች የጎሣ ዓይነት ወይም የጎሣ ስብጥር አይደለም፤ የፈለገውን ዓይነት አንድ ጎሣ ወይም የብዙ የጎሣ ስብጥር ሊኖርበት ይችላል፤ ክርክሩ መሆን ያለበት የወልቃይት አውራጃ ከጎንደር ክልል ወጥቶ ወደትግራይ የገባበት መንገድ ትክክል አይደለም፤ የአስተዳደር ለውጡ የተፈጸመው የፌዴራል መዋቅሩን ሥርዓት በጣሰ መንገድ አንዱ ክልል (ትግራይ) በሌላው ክልል ላይ የጉልበተኛነት ወረራ አካሂዷል ነው፤ ይህ ወረራ ሕጋዊ አይደለም፤ ይህ ወረራ ሊቀለበስ ይገባል፤ ዋናው መቋጠሪያ ይኸው ነው፡፡

ግን ጉዳዩን የጀመርነው ከመሀሉ ነው፤ ሲጀመር ወያኔ ከኦሮሞ ቡድኖች ውስጥ ኦነግን መረጠና አማርኛ ተናጋሪውን አለ እያለ እንደሌለ ቆጠረው፤ በዚያን ጊዜ ኦሮሚኛ ተናጋሪዎቹም ኢፈትሐዊነቱን አልተናገሩም፤ ዋና የፖሊቲካ ጉዳይ አድርገው አላነሱትም፤ ለምን? እነሱ በሎሌነት በመመረጣቸው በደስታ ተውጠው ስለነበረ ጌቶቻቸውን ለማስቀየም ፍላጎት አልነበራቸውም፤ ግን ወያኔ በእጁ ያሉትን ምርኮኞች ከአደራጀ በኋላ ኦነግ ተባረረና በኦሕዴድ ተተካ፤ የኦነግ መሪዎች አገር ውስጥ ሆነው ለመታገል የሚያስከፍለውን ዋጋ ላለመክፈል በአሜሪካና በአውሮፓ ተቀምጠው በስልክ ‹‹ትግሉን›› መምራት መረጡ፤ ወያኔ አነግን በብዙ መንገድ ተጠቅሞበታል፤ አንደኛና ዋናው አማርኛ ተናጋሪውንና ኦሮምኛ ተናጋሪውን ለመለያየትና በቅራኔ ለማጋጠም፤ ሁለተኛ የኦሮሞ መሪዎች ነን የሚሉ ሁሉ ለወያኔ ትሑት አገልጋይ ከመሆን ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው አረጋገጠላቸው፤ ኦነግንና እስላማዊ ኦነግን አፋጅቶ በኦሕዴድ አጋዥነት ሁለቱንም ከትግል መድረኩ አስወጣቸው፡፡

አለ ተብሎ እንደሌለ የተቆጠረው አማርኛ ተናጋሪው በነታምራት ላይኔ፣ በነበረከት ስምዖን፣ በነህላዌ ዮሴፍ፣ በነተፈራ ዋልዋ፣ (ሁሉም ያለጥርጥር አማርኛ ተናጋሪዎች ናቸው፤ ነገር ግን ከየት ከየት እንደበቀሉ አጠራጣሪ ነው፤) ተወከለ፤ ከጎንደርም ይሁን ከጎጃም፣ ከወሎም ይሁን ከሸዋ የእነዚህን ሰዎች ውክልና የተቃወመ የለም፤ እንዲያውም ለአሽከርነቱ ውድድር ነበር፤ በሁለቱ ድርጅቶች — በብአዴንና በኦሕዴድ — አማካይነት ወያኔ ወደሰባ በመቶ የሚጠጋውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በቁጥጥሩ ስር አደረገ፤ ይሄ ሁሉ ሲሆን በአገር ውስጥ ያሉት የአማርኛ ተናጋሪውና የኦሮምኛ ተናጋሪው ወኪሎች ነን ባዮቹ ለፍርፋሪ ሲፎካከሩና ሲነታረኩ ወያኔ የራሱን ክልል በትምህርትና በልማት ለማሳደግ እየሞከረ ነበር፡፡

ለእኔ ፍሬ ነገሩ አማርኛ ተናጋሪውም ሆነ ኦሮምኛ ተናጋሪው ሃያ አምስት ዓመታት ሙሉ እየተፎካከሩ ወያኔን ከማገልገል ሌላ መብትና ሥልጣን ፈልገው አያውቁም፤ ስለዚህም ከማይናገር ከብቱን፣ ከማይራገጥ ወተቱን እንደተባለው ወያኔም በከብቱም በወተቱም ተጠቀመበት፡፡

 

ሁለት

በ1996 ዓ.ም. የክህደት ቁልቁለት በሚል ርእስ ትንሽ መጽሐፍ አሳትሜ ነበር፤ በዚያ መጽሐፍ ውስጥ በገጽ 96ና 97 መሀከል ካርታዎች አሉ፤ ከነዚህ ካርታዎች አንዱ የኢጣልያ ምሥራቅ አፍሪካ (AFRICA ORIENTALE ITALIANA) 1928-1933 ዓ.ም. የሚል ነው፤ በዚያ ካርታ ላይ ፋሺስት ኢጣልያ ትግራይን በሙሉና አፋርን በሙሉ በኤርትራ ክልል ውስጥ አድርጎት ነበር፤ በደቡብም የኢጣልያን ሶማልያ ወደሰሜን ገፍቶ ኦጋዴንን በሙሉና ግማሽ ባሌን ጨምሮበት ነበር፤ ምዕራቡን ክፍል — ወለጋን፣ ኢሉባቦርን፣ ጋሞ ጎፋን፣ ሲዳሞን በአንድ ላይ አስሮ ጋላና ሲዳማ የሚል ስያሜ ሰጥቶት ነበር፤ ሀረር ሰሜን ባሌንና አርሲን ጠቅልሎ ነበር፤ ወያኔም ከፋሺስት ኢጣልያ የወረሰውን አስተሳሰብ ይዞ የጎሣ ክልሎችን ፈጠረ፤ በዚያን ጊዜ ግማሹ እልል እያለ ግማሹ እያጉረመረመ ተቀበለ፤ በዚህም ሥርዓት አንድ ትውልድ በቀለና በጫትና በጋያ አደገ፡፡

ወያኔ የበቀለበትን ትግራይን ሲያይ አነሰችው፤ በዚያ ላይ በሰሜን በቂልነት ደም ከተቃባቸው ከኤርትራውያን ጋር በደቡብ ደግሞ የሥልጣን ችጋሩ ጠላት በአደረጋቸው ኢጣልያ ‹‹አማራ›› ብሎ በከለላቸው ሰዎች በጎንደርና በወሎ በኩል ታፍኗል፤ በዚያ ላይ በትግራይ ውስጥ ካለው የእርሻ መሬት የተሻለ በጎንደርና በወሎ አለ፤ ጉልበተኛ ሆኖ መቸገር አይበጅምና በጊዜ፣ በጠዋቱ ከጎንደርም ቀንጨብ፣ ከወሎም ቀንጨብ አደረገና አበጠ፤ ሲያብጡ ቦታ ይጠብባል፤ ስለዚህ ወደቤኒ ሻንጉልና ወደጋምቤላ በመዝለቅ ሁለት ዓላማዎችን ማሳካት ይቻላል፤ አንደኛ ትግራይ ሰፊ ይሆንና በእርሻ ልማት የሚከብርበት ተጨማሪ መሬት ያገኛል፤ ሁለተኛ ጠላት ብሎ የፈረጀውን አማርኛ ተናጋሪ ሕዝብ የውጭ ንክኪ እንዳይኖረው ያፍነዋል፤ ከሱዳንም ጋር ጊዜያዊ ወዳጅነትን በመሬት ይገዛል፤ የወያኔ የእውቀትና የብስለት እጥረት ከብዙ ትንሽም ትልቅም ኃይሎች ጋር ያላትማቸዋል፤ ሱዳንን በመሬት በማታለል ሱዳንን ከደቡብ ሱዳን፣ ከኤርትራ፣ ከግብጽ፣ ከሳኡዲ አረብያ፣ ከየመን፣ ከሶማልያ … መለየት የሚችሉ ይመስላቸዋል (ልክ አማርኛ ተናጋሪውንና ኦሮምኛ ተናጋሪውን እንደለዩት)፤ የተዘረዘሩት አገሮች ሁሉ በሱዳን ላይ ከወያኔ የበለጠ ጫና ማድረግ የሚችሉ ናቸው፤ አሜሪካን ለብቻው ብቻ ሳይሆን ከነዚህ አገሮች ጋር አብረን ስንገምተው የወያኔን ደካማ ሁኔታ ለመገንዘብ ቀላል ነው፤ በአካባቢያችን ከአሉት አገሮች ሁሉ ወረተኛ የውጭ አመራር ያለው ሱዳን ነው፤ ሱዳን የኤርትራን መገንጠል የደገፈው በአሜሪካ ጫና መሆኑን አንርሳ፤ ለማንኛውም አሁን በወልቃይት የተጀመረው ውጊያ ከቀጠለ የወያኔና የሱዳን የጓዳ ጨዋታ ያበቃለታል፡፡

ጉዳዩ ሰፊ ጥናት የሚያስፈልገው ነው፡፡

 

ሦስት

ወደየጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄ ስንመለስ፡– ጥያቄው በቁሙ የወልቃይት-ጸገዴ ተወላጆች እንዳቀረቡት ሲታይ የወያኔ አገዛዝ ሃያ አምስት ዓመታት የደከመበት የጎሠኛ ሥርዓት ቢያንስ በአስተሳብ ደረጃ የተሳካ መሆኑን ያረጋግጣል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም ከጎሠኛ አስተሳሰብ ገና እንዳልወጣ የሚያረጋግጥ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ወያኔ በጎሣ ሥርዓት እየገዛ በጎሣ ሥርዓት የሚሸነፍ መሆኑ በግልጽ እየታየ ነው፤ ወያኔ ይህንን አዲስ ክስተት ገና አልተገነዘበውም፡፡

ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት ከመለስ ዜናዊ ጋር ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ ተገናኝተን ስንከራከር አማራ የሚባል ጎሣ አሁን የለም፤ ግን አንተ ትፈጥረዋለህ ብዬው ነበር፤ ገና በሕጻንነት ነው እንጂ አሁን ተፈጥሮአል!

በደቡብ አፍሪካ ኔልሰን ማንዴላ በእስር ላይ በሚንገላታበት ጊዜ ደ ክለርክ የሚባለው የደቡብ አፍሪካ መሪ ማንዴላን ከእስር አስወጥቶ እንደአኩያው በጠረጴዛ ዙሪያ ተነጋግረው የሁለቱ ተቃራኒ መሪዎች መተማመን የደቡብ አፍሪካን ችግር ለጊዜው ፈታው፤ ማንዴላ በክብር ሞተ፤ ደ ክለርክ በክብር ይኖራል፤ የሚያሳዝነው በወያኔ አመራር ውስጥ እንደደቡብ አፍሪካዊው ደ ክለርክ ያለ ሰው እንኳን ሊኖር ሊታለምም አይቻልም፤ እንኳን በወያኔ ውስጥ በአገሩም እንዲህ ዓይነት ሰው እንዳይኖር አረጋግጠዋል፡፡

የተጀመረውን ግብግብ ኢትዮጵያ ካላሸነፈች ማንም አያሸንፍም!

ኢትዮጵያ የድንክዬዎች አገር ሆናለችና የገጠማትን ችግር እግዚአብሔር በጥበቡ ይፍታላት!

Advertisements
This entry was posted in አዲስ ጽሑፎች. Bookmark the permalink.

5 Responses to ወልቃይት የማን ነው? የማይረባ ጥያቄ

 1. Hiluf says:

  የወልቃይት “ጥያቄ” እና የፕሮፌሰር መስፍን ክሽፈት (✍ ጆሲ ሮማናት)
  ******************************
  ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ሰሞኑን ወልቃይትን በተመለከተ ኣንድ ጽሁፍ ለጥፈዋል፡፡ ጽሁፉ ኣጭር ቢሆንም እንደተለመደው ክህደትና ትእቢት የተቀላቀለበት ብቻ ሳይሆን እርስ በርስ የሚጋጩ ሃሳቦችንም ያካተተ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ወትሮው የሳቸውን ሃሳብ እንደወረደ ሲያራግቡ የነበሩ ተከታዮቻቸው ሲያራግቡት ኣልታየም፡፡

  ጽሁፉ “ወልቃይት የማን ነው? የሚለው ጥያቄ ትክከል ኣይደለም፣የማይረባና መጥፎ ጥያቄ ነው” ብሎ ይጀምርና ጥያቄው መጥፎ መሆኑን ለማስረዳት የቀረበው መከራከሪያ ደግሞ ወልቃይት የኣማራ ነው ወይም የትግሬ ነው ማለት ጎሰኝነት ነው፣ “ወልቃይት የኢትዮጵያ ነው” ይላሉ፡፡ በዚህ መከራከሪያ መሰረት ትግራይም ኣማራም ኢትዮጵያ ውስጥ እስከሆኑ ድረስ ወልቃይት በኣማራ ወይም በትግራይ ስር መሆኑ ለውጥ የለዉም የሚል መደምደምያ ላይ ሊያደርሰን ይችላል፡፡ ነገር ግን ፕሮፌሰሩ ብዙ ሳይርቁ በኣዲስ መስመር “ትልቁና መሰረታዊው ጥያቄ በኣማራ ክልል ስር የነበረው ወልቃይት በወያኔ ኣገዛዝ ወደ ትግራይ ክልል መግባቱ ነው” ይላሉ፡፡

  እስቲ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ዱቄት የሆኑ የፕሮፌሰሩ መከራከሪያዎችን ኣንድ በኣንድ እንያቸው፡፡

  ፕሮፌሰሩ “ትልቁና መሰረታዊው ጥያቄ በኣማራ ክልል ስር የነበረው ወልቃይት በወያኔ ኣገዛዝ ወደ ትግራይ ክልል መግባቱ ነው” ኣሉ፡፡
  ሲጀመር ከወያኔ ኣገዛዝ በፊት ኣማራ የሚባል ክልል ኣልነበረም፡፡ ኣሁን ያሉት ትግራይና ኣማራ ክልሎች የተፈጠሩት በወያኔ ጊዜ ነው (ኣሁን ያለው ትግራይ ከወያኔ በፊት ከነበረው የተለየ ነው – ለምሳሌ በድሮው ምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ትግራይ የነበሩ ቦታዎች ኣፋርኛ ተናጋሪ ህዝብ ስለሆኑ ወደ ኣፋር ተካለዋል)፡፡ ከመጀመርያው ኣማራና ትግራይ ክልሎች ሲፈጠሩ ወልቃይት ትግራይ ክልል ስር ሆኖ ነው፡፡ ስለዚህ ኣንድ ላይ የተፈጠሩ ክልሎች ሆነው ሳለ ኣንዱ ኣንዱን ወሰደብኝ ማለት ኣይችልም፡፡ ኣማራ የሚባል ክልል ባልነበረበት ሁኔታ ከኣማራ ክልል ተወሰደ ማለት የሚቻል ኣይመስለኝም- ሌላ መከራከርያ ነጥብ ያስፈልጋል፡፡ እንደዉም ሰውዬው በዚሁ ጽሁፋቸው በፊት ኣማራ የሚባል ጎሳ ኣልነበረም ኣማራን የፈጠረው መለስ ዜናዊ ነው ይሉናል፡፡ “ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት መለስ ዜናዊን “አማራ የሚባል ጎሣ አሁን የለም፤ ግን አንተ ትፈጥረዋለህ ብዬው ነበር፤ ገና በሕጻንነት ነው እንጂ አሁን ተፈጥሮአል” በማለት ያሉት ነገር እንዳልቀረ ይነግሩናል፡፡ በርግጥ እሳቸው እንደሚሉት ሳይሆን ኣማራ የሚባል ሕዝብ ነበረ ኣሁንም ኣለ፡፡ ትግራይና ኦሮሞ የሚባሉ ብሄሮች (በሳቸው ኣባባል ጎሳዎች) ከነበሩ ኣማራም የማይኖርበት ምክንያት ኣይኖርም፡፡

  ፕሮፌሰሩ ወረድ ብለው ደግሞ “ክርክሩ መሆን ያለበት የወልቃይት ኣውራጃ ከጎንደር ክልል ወጥቶ ወደ ትግራይ የገባበት መንገድ ትክክል ኣይደለም ፡፡ የኣስተዳደር ለውጡ የተፈፀመው የፌዴራል መዋቅሩን ሰርኣት በጣሰ መንገድ ኣንዱ ክልል (ትግራይ) በሌላው ክልል ላይ የጉልበተኛነት ኣካሂዷል” ይላሉ፡፡ እዚህ ላይ ፕሮፌሰሩ የፌዴራል ኣወቃቀሩን የሚያምኑበት ከሆነ የትኛው የፌዴራል ስርኣት እንደተጣሰ ኣይገልጹም፡፡ ኣንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት ወልቃይቶች ኣማርኛ ተናጋሪ ሆነው ሳለ በግድ ወደ ትግራይ ተካለሉ የሚል መከራከርያ ነው እንዳንል ደግሞ ፕሮፌሰሩ መልሰው “እዚህ ላይ ጥያቄው የወልቃይት ወረዳ ወይም ኣውራጃ ነው፣ በውስጡ የሚኖሩ ሰዎች የጎሳ ኣይነት የጎሳ ስብጥር ኣይደለም” ይላሉ፡፡ በርግጥ በፌዴራል ስርኣቱ ኣከላለል መሰረት ኣድርገን እንከራከር ካልን በመጀመርያ የሚመጣው የወልቃይቶች ማንነትና በተለይ ደግሞ ቋንቋ ምንድን ነው የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ሰውዬው ራሳቸውና የነበሩበት የትምህርት ክፍል እንዲሁም የደርግ ስርኣት ያወጡት የኣካባቢው የቋንቋ ስብጥር ካርታ ላይ ወልቃይት በዋናነት ትግርኛ ተናጋሪ ህዝብ መሆኑን ስለሚያሳይ (ኣማርኛ ተናጋሪዎች የሉም ማለት ኣይደለም) በዚህ ክርክር መቀጠል ኣልፈለጉም- እናም ውስጡ የፈለገ ኣይነት ጎሳ ይኑር ጉዳዩ የግዛት (በደርግ ጊዜ የነበረ ኣስተዳደር) የማስመለስ ጥያቄ ነው በማለት ጉዳዩን ይሸሹታል፡፡

  የሰውዬው ግራ መጋባት (ወይ ማምታታት ልበለው) በዚሁ ኣያበቃም፡፡
  ሰውዬው ይሄ ጎንደር ላይ በትግራይ ክልል የተካሄደው ወረራ (ወልቃይትን ከጎንደር ወደ ትግራይ የተካለለው) ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ መሆኑን በዚሁ መልኩ ለመግለጽ ይሞክራሉ … “ወያኔ የበቀለበትን ትግራይን ሲያይ አነሰችው፤ በዚያ ላይ በሰሜን በቂልነት ደም ከተቃባቸው ከኤርትራውያን ጋር በደቡብ ደግሞ የሥልጣን ችጋሩ ጠላት በአደረጋቸው ኢጣልያ ‹‹አማራ›› ብሎ በከለላቸው ሰዎች በጎንደርና በወሎ በኩል ታፍኗል፤ በዚያ ላይ በትግራይ ውስጥ ካለው የእርሻ መሬት የተሻለ በጎንደርና በወሎ አለ፤ ጉልበተኛ ሆኖ መቸገር አይበጅምና በጊዜ፣ በጠዋቱ ከጎንደርም ቀንጨብ፣ ከወሎም ቀንጨብ አደረገና አበጠ” ይሉናል፡፡ እዚህ ላይ ሰውዬው ኣርጅተዋል ብለን ከማለፍ ውጪ ባልሆነ ነገር ላይ መከራከር ከንቱ ልፋ ነው፡፡

  የወልቃይት ጉዳይን በተመለከተ ኣንድ ግልፅ ያልሆነ ነገር ኣለ፡፡ ጥያቄው የማንነት ጥያቄ ነው ወይስ የድሮ (በደርግ ጊዜ የነበረውን) ግዛት የማስመለስ ጥያቄ – “ኣረሱት የሁመራን መሬት” ???

  ኣንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት የወልቃይት ጥያቄ የማንነት ጥያቄ ከሆነና ወልቃይቶች ኣማራ ስለሆኑ ወደ ኣማራ መካለል ኣለባቸው የሚል ከሆነ ግልፅ ጥያቄ ነው መልሱም ቀላል ነው፡፡ መልሱ ያለው ደግሞ በወልቃይቶች እንጂ በኣማሮች ወይም በትግራዮች ኣይደለም (ሪፈረንደም ኣንድ መፍትሄ ነው)፡፡ እኛ ኣማራ ነን የሚሉ ከሆነና መልስ ኣጥተው ከሆነ እዛው ወልቃይት ውስጥ ራሳቸው ተነስተው መሰለፍና መታገል ኣለባቸው፡፡ ለምንድንው የጎንደር ወጣት ስለነሱ የሚሰለፈውና የሚሞተው? እነሱ መሰለፍ ኣይችሉም? ወይስ ኣልፈለጉም? ወልቃይት ውስጥ ኣልተፈቀደላቸዉም ከሆነ ጎንደር ላይ ያሉትም በራሳቸው እንጂ የተፈቀደላቸው ኣይመስለኝም፡፡

  በሌላ በኩል ጉዳዩ እነ ፕ/ር መስፍን እንደሚሉት የወልቃይት ጥያቄ ውስጣቸው የፈለገ ኣይነት ጎሳ ወይም የጎሳ ስብጥር ይኑር በደርግ ጊዜ የነበረ ግዛት የማስመለስ ጥያቄ ከሆነ (በርግጥ ጎንደርም፣ባህርዳርም፣ ዲሲም የሚነሱ ጥያቄዎች ይሄንን ያሳያሉ) ኣሁን ካለው ህገ-መንግስትና የክልሎች ኣወቃቀር ስርኣት (ማንነት ቋንቋ ላይ ያተኮረ) መያያዝና መቀላቀል የለበትም፡፡ በዚሁ መከራከርያ ከሄድን ደግሞ የድሮ ግዛቶችን ከትግራይ ብቻ ሳይሆን ከኣፋር (የድሮ ወሎና ሸዋ) ከቤኒሻንጉል (የድሮ የጎጃም ግዛት መተከል)፣ ከኦሮሚያና ደቡብ (የድሮ ሸዋ ክፍለሃገር) የተወሰዱ መሬቶች ውስጣቸው የፈለገ ኣይነት የጎሳ ስብጥር ይኑረው መመለስ ኣለባቸው ማለት ነው፡፡ ይሄንን ለማድረግ ደግሞ ብቸኛው መፍትሄ ኣሁን ያለውን ስርኣት ኣስወግዶ የክልሎችን ኣወቃቀር ወደ ድሮ መመለስ ነው፡፡

  ግራ የገባው የፕሮፌሰሩ ፅሁፍ እዚህ ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡

 2. Girma says:

  Dude you are swimming against the tide. Change is universal law, you cannot stop change you can only shape it or make the best of it. Bravo, you are saving the regime from itself. But i don’t think they will thank you for that. What I don’t understand– Ethiopians elites don’t hesitate to throw the nation under the bus just to prove that they are right. This is exactly what you are doing.

 3. በለው! says:

  የእኛ ቤት ጉድ!
  ” አለ ተብሎ እንደሌለ የተቆጠረው አማርኛ ተናጋሪው በነታምራት ላይኔ፣ በነበረከት ስምዖን፣ በነህላዌ ዮሴፍ፣ በነተፈራ ዋልዋ፣ (ሁሉም ያለጥርጥር አማርኛ ተናጋሪዎች ናቸው፤ ነገር ግን ከየት ከየት እንደበቀሉ አጠራጣሪ ነው፤) ተወከለ፤” አፍ ያለው ጥሬ ይቆላል!
  “ኢዴኃቅን ካጠፋን በኋላ ገብሬውን አማራ በፓለቲካው ያደራጀናቸውና ያነቃናቸው እኛ ነበርን የግድ የአማራ ብርሔር ባይሆኑም “በአመለካከቱ “የሚወክሉት መረጥንለት ብሎ ለገሠ መለሰ ዜናዊ ሲያናፋ አማራ አልነበረም !።
  ” ከጎንደርም ይሁን ከጎጃም፣ ከወሎም ይሁን ከሸዋ የእነዚህን ሰዎች ውክልና የተቃወመ የለም፤ እንዲያውም ለአሽከርነቱ ውድድር ነበር፤ “ታማኝ ጓዶች !”
  “ሰዶ ማሳደድ ሲያምርህ አገርህን በክልል ለውጥ ”
  *** በሁለቱ ድርጅቶች — በብአዴንና በኦሕዴድ — አማካይነት ወያኔ ወደሰባ በመቶ የሚጠጋውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በቁጥጥሩ ስር አደረገ፤ ይሄ ሁሉ ሲሆን በአገር ውስጥ ያሉት የአማርኛ ተናጋሪውና የኦሮምኛ ተናጋሪው ወኪሎች ነን ባዮቹ ለፍርፋሪ ሲፎካከሩና ሲነታረኩ ወያኔ የራሱን ክልል በትምህርትና በልማት ለማሳደግ እየሞከረ ነበር፡፡”
  እንደማጎብደድና ጭነት የመቻል አቅማቸው ልክ አዲስ ታሪክ እየፈጠረ ታሪክ ሰሪ (መሰሪ) በክልል አስሮ በጫካ ማኒፌስቶ አደንዝዞ በጡትና ወሸላ ሥር ባዶ ሆዱን ፡በባዶ እግሩ ባዶ ቂጡን እየመታ ሲያስጨፍረው በሕገ መንግሥታዊ ጥቅማጥቅም ልቡ ተደፍኖ ዓይኑ ታውሮ ፱፭ ዓመት ትውልድ መከነ ባከነ ።

  “ለእኔ ፍሬ ነገሩ አማርኛ ተናጋሪውም ሆነ ኦሮምኛ ተናጋሪው ሃያ አምስት ዓመታት ሙሉ እየተፎካከሩ ወያኔን ከማገልገል ሌላ መብትና ሥልጣን ፈልገው አያውቁም፤ ስለዚህም ከማይናገር ከብቱን፣ ከማይራገጥ ወተቱን እንደተባለው ወያኔም በከብቱም በወተቱም ተጠቀመበት!። “እያነቡ እስክስታ !”

  >> አሁን አማራ አለሁ እራሴን ወክዬ ሀገሬን ስጡኝ ቤተሰቤን ኦሮሞውን አትንኩ! አለ ኦሮሞ ቀበሌና መንደር የኔ(ኬኛ) ከማለት ጎንደር የእኔ ነው! አለ ውስጠ ወይራው “ኢትዮጵያ የእኔ ናት!” ማለቱ ነው ።አራት ነጥብ።

  = ኦሮሞ ከስህተቶቹ ተምሮ በሰላምና የዲሞክራሲ ግንባታ ቀዳሚውን ሥፍራ ይዞ ታሪካዊ ለውጥ እና የሕዝብን አመኔታን ያገኝ ይሆን ? ከእንግዲህ ኢትዮጵያ የኦሮሞ አደለችም የሚል ሻቢያ እና ህውሐት ይፈጥራሉን?
  ** አለሁ! ያለው አማራ በእርግጥም አንድ ሆኖ በዳግማዊ ብአዴን ሳይጠለፍ ይዘልቅ ይሆን ? ሞረሽ ወገኔ .. ቤተ ንፉጋን ..ቤተ አምሐራ የሚልም ዓርማው ምንም የኢትዮጵያ ሠንደቅ የሌለው ጭልፊት ይሁን ሲላ ወይም ንሥር ማንነቱንና ምንነቱን ያልተለየ በድረ ገፆች ላይ ሲያንዣብብ ይታያል :ያለው ከብዶናል ወንዝና ተራራ እየቆጠርን ጨርቅ በቀለም እየነከርን መንደራዊ ብሔርተኝነትን ቀፍቅፈን በጎጥ በነገድ ሻክላ እንዳንተባተብ አደራ በለው!

  የተማረ እያስተማረ ያልተማረ ይማራ
  ብርታትና ድል ለተገፋው አማራ!

 4. #ዳኛቸው says:

  “ሚስትህን መደብደብ ትተሃል ወይ?መልስ የሌለው ጥያቄ ነው፤ ‹‹አዎ›› የሚል መልስ ሰውዬው ሚስቱን ሲደበድብ እንደነበረ አመነ ማለት ነው፤‹‹አልተውሁም›› ከአለ በራሱ ላይ መሰከረ፤ ሁለቱም መልሶች ተጠያቂውን የሚያስወነጅሉ ስለሆኑ መልስ አይደሉም፤ ከዚያም በላይ ጥያቄውትክክል አይደለም፤ የማይረባ መጥፎ ጥያቄ ነው፡፡” በማይረባ ፖለቲካ፣ በማይረቡ ፖለቲከኞች፣ በማይረባ አስተዳደር ፣ በማይረባ ጊዜ፣ የሚረባ ጥያቄ፣ የማይረባ ግብረ መልስ። ኦ እግዚኦ ማለቱ ይሻላል ሁሉም በየእምነቱ። “ጊዜ የሰጠው ቅል፡ ድንጋይ ይሰብራል።” ሆኗልና ነገሩ።

 5. Goytom says:

  Amen.

Comments are closed.