የእናት ለቅሶ

 

እናት በፍቅር፣ ጽንስ ይዛ፣
ዘጠኝ ወር አርግዛ፣
ራስዋን ምግብ አድርጋ፣
በማኅጸንዋ ሸሽጋ፣
ሽሉን ወደሰውነት አሳድጋ፣
የፈጣሪን ባሕርይ ተጋርታ፣
ሰው ሆና ሰው ፈጣሪ የሕይወት አለኝታ፣
በጻዕር አምጣ ወልዳ፣ አቅፋ በፍቅር አጥብታ፣
ተጨንቃ አሳድጋ፣ እንቅልፍ አጥታ፣
ሲስቅ ሲያስቃት፣
ሲያለቅስ ሲያስለቅሳት፣
ስትቆጣው እንዲያድግላት እንዲማርላት፣
ክቡር ሰው ሆኖ እንዲያኮራት፣
ያላትን ሁሉ ከፍላ መስዋእት፣
በጉጉት ስትጠብቅ — ጨካኞች ሬሳውን ጣሉላት፡፡
ማኅጸንዋ ተኮማተረ፤
አንጀትዋ አረረ፤
አስፋልቱ ላይ የተንጣለለው ደም፣
ከልጅዋ አካል ጠብታም አልቀረም፤
ሙት አደረጋት በቁም፤
ከማኅጸንዋ እንደፈሰሰ ተሰማት፤
ተወልዶ ያደገ ልጅ አስወረዳት፤
በወጣት ልጅዋ የፈራረሰ አካል
እስዋም ፈራረሰች ወየው ልጄ! ስትል፤

አካልዋ ተፍረከረከ፤
ጉልበትዋ ተብረከረከ፤
ፍሬዋ ደረቀ
ተስፋዋ ደቀቀ፤

ቀስ ብላ በእጅዋ ተመርኩዛ መሬት ላይ ተቀመጠች፤
እንባዋን እያፈሰሰች፤
እንደምንም እጆችዋን ወደሰማይ ዘረጋች፤
መድኃኔ ዓለም! ግፌን – ለግፈኛው ስጠው አለች፡፡

Advertisements
This entry was posted in አዲስ ጽሑፎች. Bookmark the permalink.

2 Responses to የእናት ለቅሶ

  1. abebe says:

    God bless you prof

  2. Solomon Kebede says:

    Thank you Professor this a timely verse. Wish you all the best for the New year.
    Professor, the Father of Ethiopia, that is what you are.

Comments are closed.