የሕይወት ዋጋ

በ2009 ዓ.ም. ቆሼ የሚባል ሰፈር ወይም መንደር ተፈጠረ፤ ቆሼ ማለት ቆሻሻን ማቆላመጫ ነው፤ ቆሻሽዬ ማለት ነው፤ ቆሼ የቆሻሻ ተራራ ነው፤ በዚያ የቆሻሻ ተራራ ዙሪያ መሄጃ የሌላቸው ሰፈሩበት፤ ጥንት ሴትዮዋ እንዳለችው፡-

እሾህ ብቻ ሆነ እግሬን ብዳብሰው
እንዴት መራመጃ መሄጃ ያጣል ሰው!

ሴትዮዋ ይህንን ያንጎራጎረችው ከብዙ ትውልዶች በፊት ነው፤ ጉልበተኞች የኢትዮጵያን ሰዓት ሰንገው ስለያዙት አይነቀነቅም! ባለህበት ሂድ! ነው፤ ዛሬም መሄጃ የለም፤ ቆሻሻንም የሙጢኝ ቢሉ ማምለጥ አይቻልም፡፡
እነዚህ አንድ መቶ አሥራ ሦስት ሟቾች በርግጥ ሰዎች ናቸው? በርግጥ ኢትዮጵያን ናቸው? የምናገረው ጠፍቶኛልና ጥያቄዎች ብቻ ልጠይቅ፡– ቤታቸውን ጉልበተኞች አፍርሰውባቸው፣ መሬታቸውን ሰማይ-ጠቀስ ወይም መንገድ ለመሥራት መሬታቸውን ወስደውባቸው የሚደርሱበት አጥተው፣ ባዶ ቦታ ፈልገው የፕላስቲክ መጠለያቸውን እየሠሩ ግፍን አሜን ብለው በሰላም ተቀብለው ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል እያሉ ቀኖችን ሲቆጥሩ ቆሻሻ መጣያው ደባል የሆነባቸው መቼ ነው? ወይስ ቆሻሻ መጣያው ቀድሞ እነሱ ደባል ሆነውት ነው? ጥያቄው ማን ቀደመ ሳይሆን ቆሻሻውና መጠለያ ፈላጊዎቹ አብረው አንዲኖሩ ፈቃድ የሰጣቸው ማን ነው የሚል ነው? የመጠለያ ፈላጊዎቹን ቤት ያፈረሰውና የቆሻሻውን ተራራ የሚክበው ጉልበተኛ ወይም ጉልበተኞች የተለያዩ ናቸው? ወይስ አንድ ነው? አንድ ከሆነ እውር-ደንቆሮ ሳይሆን አይቀርም፤ በማን-አለብኝነት ልባቸው ያበጠ ግዴለሾች ሳይሆኑ አይቀርም፡፡
አንድ መቶ አሥራ ሦስቱና ሌሎቹም ዜጎች ቢሆኑ፣ ማለት የአገሩን ባለቤትነት ከጉልበተኞች ጋር በእኩልነት የሚጋሩ ቢሆኑ፣ ሌሎች ዜጎች እነዚህ በቆሻሻ የተበሉት ወገኖቻቸው መሆናቸውን ቢገነዘቡ ቆሻሻና ዜግነት እንደተደባለቁ ማወቃቸው ይቀራል? ዋናው ችግራችንስ ይኸው ሳይሆን ይቀራል?
የሞቱትን ነፍሳቸውን ይማር ማለቱ አጉል ወግ ነው፤ አጥንታቸውን እሾህ ያርገው ማለቱ ሳይሻል አይቀርም!

Advertisements
This entry was posted in አዲስ ጽሑፎች. Bookmark the permalink.

One Response to የሕይወት ዋጋ

  1. solomon dejene says:

    ጤና ይስጥልኝ ፐሮፍ
    በቆሻሻ ናዳ የሞቱትም ሆኑ የተረፉት ሞት ከተፈረዳባቸው ቆይቷል፡፡ ከሞት በላይና ከመኖር በታቸ ሆነው ንዑሥ-ሰው ሆነው ኑሮን እየገፉ ነበር፡፡ የተረፉትና ዛሬ በጊዚያዊ መጠለያ ውስጥ ያሉትና አሁንም ቤታቸው ተርፎ እዚያው በፍርሐት እየኖሩ ያሉት፣ ገና መኖሪያቸውንና ለንግድም የሚሆን ቤትና ሕንፃ በመገንባት ላይ ያሉት በምን ዓይነት የከተማ አስተዳደር ዕቅድ ነው ያሉት? ዛሬ ሰዎች ካለቁ በኋላ እንዲነሡ ተነግሮአቸው ነበር ማለት ኃላፈነትን መሸሽ ነው፡፡ በጠራራ ፀሐይ ገሚሶቹ ቤታቸው ቤታቸው ተቀምጠው በግሬደር የፈረሰባቸው ሰንት ናቸው? ገሚሶቹ ደግሞ እነሱ ወደ ሥራ ገበታቸው ልጆቻቸው ወደ ትምህርት ቤት ሄደው ሲመለሱ ቤታቸው ከመሬት ተደባለቆ ያገኙትን ሆድ ይፍጀው፡፡ ሻል ሲል በወራት፣ ካለሆነም በሳምንታት ሲብስም በቀናት ማስጠንቀቂያ ቤታቸው በአፍራሽ ግብረኃይል የፈረሰባቸው አኀዝ በአዲስ አበባ ብቻ ለቁጥር አይታክትም፡፡ በስመ የጨረቃ ቤት ለአንዱ ፈቃድ ሲሰጥ ለሌለው ግን የአርባ ቀን ዕድሉ ሆኖ የአፍራሽ ግብረኃይል ሢሣይ ይሆናል፡፡ ታድያ እነኚህ ከቆሻሻ ጋር ተዳብለው የሚኖሩ ሰዎች ቦታው ልማት ለሚባለው ወዳጅ መሰል ባላንጣ የተፈለገ ባለመሆኑ ይሆን? ለሕይወታቸው አስጊ መሆኑ እየታወቀ ዝም መባሉ እንደሌሎቹ አካባቢዎች አፍራሽ ግብረኃይል አለመላኩ ቦታው ቢነሡም ባይነሡም ገንዘብ የሚያስገኝ ባለመሆኑ ይሆን? ይልቁንም እነሱን ማስነሣትና ምትክ መጠለያ መስጠት ወጪ ስላለው ይሆን? ዛሬ ኪራይ ሰብሳቢ እያለ የሚከሰን መንግሥት ለመናፈሻ፣ ለመኪና ማቆሚያ፣ ለስፖርት፣ ለትምህርት ቤት መሥሪያ እንኳን ሳይተው መሬትን እየቸበቸበ ስለሆነ ለእነኚህ ምስኪኖች መሬትና ቤት መስጠት ኪሱን የሚያሳሳበት ሆኖ ሳያገኘው አልቀረም፡፡
    ከሁሉ የሚያሳዝነው ለዚህ አሰቃቂ አደጋ አንድም አካል ኃላፊነት ለመውሰድ የሞራል ብቃት ማጣቱ ነው፡፡ የወረዳው አስተዳደር፣ የክፍለከትማው አስተዳደርና ከንቲባው እያዩት ለዓመታት እነኚህ ሰዎች ፡፡በዚያ ቦታ በዚህ ሁኔታ መኖራቸው የሚያስጠይቃቸው ጉዳይ ነበር፡፡ ስለዚህም እኔ የአዲስ አበባ ከንቱባ ኃላፊነቴን በብቃት ባለመወጣቴ ይህ አሰቃቂ አደጋ ተከስቷል ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ በገዛ ፈቃዴ ከሥልጣኔ ወረጃለሁ ቢሉ ባከበርናቸው፡፡ ይልቁንም የመንግሥትን ፈጥኖ ደራሽነት ደሰኮሩልን፡፡
    ሰላም ወሠናይ

Comments are closed.