ለግዛው ለገሰ፤ እንደመልስ

መስፍን ወልደ ማርያም
ኅዳር/2009

ግዛው ለገሰ በጣም መሠረታዊና አንገብጋቢ፣ ጊዜያዊም ጉዳዮችን አንሥቷል፤ በበኩሌ ጉዳዮቹን በማንሣቱ በጣም እያመሰገንሁት አስተያየቴን በአጭሩ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡
‹‹ህወሓት የተቁአቁአመው በአማራ ጥላቻ ነው:: ይህን ሀቅ ሳይቀበሉ ስለነፃነት ማታገል አይቻልም:: ነፃነት ደግሞ የዜግነት መበት እንጂ የወል መብት አይደለም:: ነፃነት በማንነት ትግል አይገኝም::›› ግዛው በጣም መሠረታዊ ነጥብና ሀሳብ አቅርበሃል፤ ነገር ግን ድብልቅልቁ ወጣብኝ!
መነሻ፡–‹‹ሕወሀት የተቋቋመው በአማራ ጥላቻ (ላይ?) ነው፤›› ከዚህ ትነሣና፡–
‹‹ይህንን ሀቅ ሳይቀበሉ ስለነጻነት ማታገል (መታገል?) አይቻልም፤›› ትላለህ፡፡
እንደምረዳው ግልጽ ያልሆነልኝ ግዛው ሁለቱን ዓረፍተ ነገሮች እርስበርሳቸውና እያንዳንዳቸውን ከነጻነት ጋር ያቆራኛቸው እንዴት ነው? የሚል ነው፤ በእኔ አስተሳሰብ ምንም ግንኙነት የላቸውም፤ የአማራን (በአንተው ቃል ለመጠቀም) ጥላቻም ሆነ በአማራ ላይ ያለውን ጥላቻ ይዞ ለነጻነት መታገልም ሆነ ማታገል የማይቻልበት ምክንያት አይታየኝም፤ ነጻነትን ‹‹አማራ›› ከምትለው ጋር አቆራኝተኸዋል! እንዴት ብሎ?
ሁለተኛው ዓረፍተ ነገርህ ለእኔ በጣም ፈር የለቀቀ ነው፤ ለእኔ ነጻነት ሰው ከመሆን የሚገኝ መብት ነው፤ ስለዚህም የሰው ልጆች ሁሉ መሠረታዊ የጋራ (የወል) መብት ነው፤ ከዜግነት ጋር ማያያዝህ በመሠረቱ ትክክል ቢሆንም ነጻነት የሌላቸው ዜጎች በያለበት ይገኛሉ፤ ከዚሁ ጋር አያይዘህ ‹‹ነጻነት በማንነት ትግል አይገኝም፤›› ስትልም በዝቅተኛ ደረጃ ያሉ ማንነቶችን (ለምሳሌ ባል/ሚስት መሆን፣ ክርስቲያን/እስላም መሆን፤ የዚህ/የዚያ ጎሣ አባል መሆን፣ …) ከሆነ ትክክል ትመስለኛለህ፤ በሰውነትና በዜግነት ደረጃ ካየኸው ግን እንለያያለን፤ ለእኔ መሠረታዊው ነጻነት የሚፈልቀው ማንነትን አንደኛ በሰውነት ደረጃ ሁለተኛ በዜግነት ደረጃ እያዩ በመታገል ነው፤ እኩልነት የነጻነት አካል ነው ለማለት የሚቻል ይመስለኛል፤ እኩልነትን ከነጻነት ጋር አቆራኝተህ ለመታገል የምትችለው በሰውነትና በዜግነት ደረጃ ብቻ ነው የምትል ከሆነ አብረን እንቆማለን፤ ሌሎች ዝቅተኞች ማንነቶች ለእኩልነት ቦታ የላቸውም፤ እንዲያውም አብዛኛውን ጊዜ ጸረ-እኩልነት ናቸው! የአንዳንድ ጎሣዎች አቀንቃኞች የጎሣቸው ሥርዓት ‹‹ዴሞክራሲያዊ›› ነው፤ ነጻነት አለበት ይላሉ፤ (በሴቶች ላይ የሚያሳድሩትን ክፉ ጭቆና ይረሱታል!) ይህ ወይ የማያውቁትን ለማሞኘት ነው፤ ወይም ስለዴሞክራሲና ስለእኩልነት፣ ስለነጻነት አለማወቅ ነው፡፡
ግዛው ያነሳኸው ዋና ነጥብ ሁሌም የሚረሳና በጎሠኛነት አረም የተሸፈነ ነው፤ ዜግነት! የአንድ አገርን ሰዎች በሕግ በነጻነትና በእኩልነት አዋኅዶና አዛምዶ የሚይዛቸው ዜግነት ነው፤ በጎሠኛነት ያለው መንገድ የወያኔ ብቻ ነው፤ የወያኔን መንገድ ተከትሎ ወደዜግነት መድረስ የሚቻል አይመስለኝም!
በመጨረሻ አንድ ያነሣኸው ነጥብ አለ፤ ጥላቻ በመሠረቱ ክፉ የአእምሮና የመንፈስ በሽታ ነው፤ በዚህም በሽታ ይበልጥ የሚጎዳው ማኅደሩ ነው፤ ስለዚህም ‹‹አማራን›› መውደድም ሆነ መጥላት፣ ‹‹በአማራ›› መወደድም ሆነ በጥላቻ መታየት ለዜግነት፣ ለአኩልነት፣ ለነጻነትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግዴታ አይደሉም! በተግባር ፍቅርና አብሮ የመኖር ልምዱ መኖሩን ከተለያዩ ጎሣዎች የወጡት ወጣቶች ተጨባጭ ማስረጃዎች ናቸው፤ እንኳን ሰው ነግሯቸውና አይተውም መረዳት የማይችሉ በሥልጣንና በሀብት በተለወሰ ጎሠኛነት የሰከሩትን ለማሳመን አይቻልም፤ በማየት መረዳት የሚቻል ቢሆንማ ኤርትራን አይቶ ልብ መግዛት ቀላል ነበር፤ በፖሊቲካ ጉዳይ ገና በሕጻንነት ደረጃ መሆናችን የሚረጋገጠው ጎሠኛነት በሃያ አምስት ዓመታት ውስጥ እያደገና እየሰፋ፤ ተምረናል የሚሉ ሰዎች የተሰለፉበት የእንጀራ እናት ሆኖ ማደጉና መስፋፋቱ ነው፡፡

Advertisements
Posted in አዲስ ጽሑፎች | 1 Comment

ዓለምነህና ጸጋዬ አራርሶ

መስፍን ወልደ ማርያም
ጥቅምት 2009

ዓለምነህ በአዋዜ ፐሮግራሙ ላይ ጸጋዬ አራርሳ ‹‹ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም›› ያለውን ይዞ በለዘበ ቋንቋና በለዘበ ድምጽ ደቁሶታል፤ ብዙ ሰዎች የገባቸው አልመሰለኝም፤ በጉዳዩ የተማረውና የተመራመረው ዶር. ጸጋዬ አራርሶም የገባው አይመስለኝም፤ እስቲ እኔ የገባኝን ልንገራችሁ፡፡
በመጀመሪያ በሁለቱ ሰዎች መሀከል ያለውን የትምህርት ደረጃ ልዩነት ዓለምነህ ራሱ እንዳለው እሱ ‹‹በትምህርት እጅግም አልገፋም፤›› ጸጋዬ ግን የትምህርቱን ደረጃ ጣራው ላይ አድርሶታል ተብሎ በስሙ ላይ ‹‹ዶክተር›› የሚል የትምህርት ማዕርግ እንዲጨምር አድርጓል፡፡
በትምህርት እጅግም ያልገፋው ሰው በትምህርት ጣራ ላይ በደረሰው ሰው አስተያየት ላይ የሰጠው ትችት የትምህርት ደረጃ የሚባለውንም ሆነ የሁለቱን ሰዎች እውቀትና ብስለት የሚለካ ነው፤ የዓለምነህ ትችት ስለቱ ያረፈው ጸጋዬ የሚልዮኖችን እምነት መካዱ ላይ ነው፤ ጸጋዬ እሱ ኢትዮጵያዊ ማንነት አንደሌለው ብቻ አልተናገረም፤ ማንም ቢሆን ኢትዮጵያዊ ማንነት የለውም በማለትም እምነቱን ለጥጦታል፤ (ምናልባትም ኢትዮጵያዊ ማንንት ባለመኖሩ ኢትዮጵያዊ ማንነት ያለው የለም ብሎ ‹‹ያስብ›› ይሆናል፤ ግን የባሰ ገደል ውስጥ ያስገባዋል!) በጸጋዬ ላይ ያረፈው የዓለምነህ የሀሳብ ጉማሬ ጸጋዬ አንድ ብቻውን ሆኖ የሚልዮኖችን እምነት በመካዱ ላይ ነው፤ አንድ የተማረ ሰው (ያውም ጸጋዬ የሚል ስም ይዞ) ‹‹ኢትዮጵያዊ ማንነት›› የለም ሲል እሱ የካደውን ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም ከሱ ጋር በክህደት የቆሙለት ያስመስላል፤ በሌላ በኩል ስናየው አንድ የተማረ ሰው ክርስቲያን የሚባል ሃይማኖት የለም ቢል፣ አንድ የተማረ ሰው እስልምና የሚባል ሃይማኖት የለም ቢል … አለማወቅ ብቻ ነው ብለን አናልፈውም፤ ተንኮልም ያለበት መሆኑን ማጋለጥ አስፈላጊ ይሆናል፤ ዓለምነህ እዚህ አልደረሰም፤ ወይም ሊደርስ አልፈለገም፤ ዓለምነህ የሚለው የጸጋዬ ንግግር ብዙ ኢትዮጵያውያንን አቁስሎአል፤ ስለዚህም ይቅርታ መጠየቅ አለበት ነው፡፡
ጸጋዬ ለኢትዮጵያዊ ማንነት የሞቱትን ሁሉ እንደሰደበ አያውቅም ለማለት ያስቸግራል፤ ጸጋዬ የሕግ ምሁር ነው፤ በተለይም በሰብአዊ መብቶች ላይ ያተኮረ ይመስለኛል፤ እሱ እንዳደረገው የራስን ስሜት በአጠቃላይ ሕዝቡ ላይ መጫን፣ ወይም የሱን ክህደት በሕዝብ ላይ መጫን ከባድ ጥፋት ነው፤ ወደዚህ ጥፋት ያደረሰው ሌላ የተሳሳተ እምነት ነው፤ የግለሰብ መብቶች የመብቶች ሁሉ የማዕዘን ድንጋይ ነው፤ ጎሠኞች ከራሳቸው በቀር ግለሰብ አያውቁም፤ ሌላው ሁሉ ጎሣው ነው፤ የጸጋዬ አስተሳሰብ ከጎሠኛነቱ ያገኘው ነው፤ በጎሠኛነት አስተሳሰብ ጎሣ እንጂ ግለሰብ የለም፤ ጸጋዬ ይህንን አስተሳሰብ ወደጎሣ ፖሊቲካ ሲመነዝረው ኢትዮጵያዊ ማንነትን እንዲክድ አደረገው፤ ዶር. ጸጋዬ አራርሳ በአንድ እጁ የኦሮሞን ሕዝብ በሙሉ ጨብጦ በሌላ እጁ ደግሞ የቀሩትን ኢትዮጵያውያን ጨብጦ በሁለቱም ላይ የራሱን የተለያዩና ተቃራኒ እምነቶች ሊጭንባቸው ይሞክራል፤ (ቅዠት እንዳይመስላችሁ!) እንኳን ከዚያ ታች (አንደሚባለው) ከአውስትራልያ ይቅርና ከአዲስ አበባም ቢሆን የእነዚህን ሰዎች አንድ ከመቶ ለማግኘት የሚችል አይመስለኝም፤ መንጠራራቱ ባልከፋ! ሲመለስ በምን ላይ ያርፋል አንጂ! ጸጋዬ የሕግ ምሁር በመሆኑ እንደሚያውቀው የግለሰቦችን መብቶች ይዞ ባልተነሣ ጥቅል እምነት ላይ ተመሥርቶ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ማንነት ላይ ፍርድ መስጠት ‹‹ይህን ያህል ያልተማረው›› ዓለምነህ እንዳለው ስሕተት ነው፤ ጥፋት ነው፡፡
እግዚአብሔር ለሁላችንም ብርሃኑን ያሳየን!

Posted in አዲስ ጽሑፎች | 1 Comment

ኢሰመጉ ከየት ወዴት?

መስፍን ወልደ ማርያም
ጥቅምት 2009
አምስት ዓረፍተ ነገሮች
ኢሰመጉ መንፈሳዊ ተልእኮ ያለው መንፈሳዊ ድርጅት ነው፤ ዓላማው በሰው ልጆች መሀከል የሚከተሉትን ተልእኮዎች መዝራት ነው፡–
1.1. እኩልነትንና ነጻነትን
1.2. ፍቅርንና ስምምነትን
1.3. ፍትሕንና ሕጋዊነትን
1.4. ሰላምንና ማኅበረሰባዊ እድገትን
1.5. የእውነትንና የእውቀትን ብርሃን ማስፋፋትን

ኢሰመጉ የተቋቋመው በሁለት ምክንያቶች ነው፤–
2.1. የደርግ አገዛዝ ወድቆ አዲስ መንግሥት በአዲስ ሥርዓት ይመሠረታል በሚል ተስፋ አዲሱ ሥርዓት የኢትዮጵያን ሕዝብ ወደትክክለኛ አቅጣጫ እንዲመራ ለመርዳት ነበር፤
2.2. የኢትዮጵያን ሕዝብ በመብት ጉዳይ ለማንቃትና ራሱን ከተገዢነት ወደገዢነት ደረጃ እንዲለውጥ ለማስቻል ነበር፡፡
ለትውልድ የሚተላለፍና ስምን ሲያስጠራ የሚኖር ሥራ ለመሥራት ሀበት ጥሩ መሣሪያ ነው፤ በሌሎች አገሮች እንደሚደረገው ሰዎች ለኢሰመጉ ሀብት ማውረስን ቢለምዱ የኢሰመጉ ዓላማዎችን ለማስፋፋትና ማኅበረሰባችንን ወደተሻለ አቅጣጫ ለመግፋት የተሻለ ኃይል ይኖር ነበር፤ ከውጭ ሰዎችም ጥገኛነት ለመውጣትና ራሳችንን ወደሰውነት ደረጃ ለመግፋት ያስችለን ነበር፡፡

እንዲያም ሆኖ በአለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ውስጥ ጠንካራ በጎ መንፈስን ብቻ በታጠቁ ጥቂት ሰዎች፣ በትንሽ ገንዘብ አዲስ የትውልድን አቅጣጫ የሚያመለክት ሥራ የሠራ ከኢሰመጉ ጋር የሚወዳደር ድርጅት የለም፤–

4.1. ከውጭም ከውስጥም የተሰነዘረበትን ዛቻና ግፊት ተቋቁሞ ቀጥ ብሎ ዓላማውን ሳይስት የቆየ
4..3. ቢከሳም ሕይወቱን ያላጣ ድርጅት ነው፤
4.4. የኢሰመጉ መክሳት የማኅበረሰቡን መክሳት የሚያመለክት ነው፤ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ማኅበረሰቡ ኢሰመጉን በሚገባ ባለመደገፉና እንዲከሳ በማድረጉ ራሱንም አከሳ፤ ራሱን ጎዳ፤ እስከዛሬ አንድም ባለሀብት ለኢሰመጉ ቀዋሚ ሀብት ያወረሰ አለመኖሩ አስተሳሰባችን ከግለሰብ ወደማኅበረሰብና ወደትውልድ አለመሸጋገሩን ያመለክታል፤
4.5. እስከዛሬም ድረስ ቢሆን ማኅበረሰቡ የኢሰመጉን መንፈሳዊ ተልእኮ በትክክል ተገንዝቦ ኢሰመጉን በመርዳት ራሱን ለመርዳት የሚያስችለው ደረጃ ላይ ገና አልደረሰም፡፡

በዚህ በዓል ላይ እኔ ያረቀቅሁትን የኢሰመጉን ደንብና ቃል ኪዳን ሁለት የሕግ ባለሙያዎች፣ ወርቁ ተፈራና ዓሥራት ገብሬ ብዙ ጊዜ አጥፍተውበት በማሻሻላቸውና የባለሙያ ሥራ በማድረጋቸው፣ በተጨማሪም የመጀመሪያው የኢሰመጉ ቢሮ በዓሥራት ገብሬ ቢሮ ውስጥ ሆኖ የሱ ጸሐፊም የኢሰመጉን ሥራ እንድትሠራ በማድረግ ያበረከተው እርዳታ ኢሰመጉ በራሱ እግር እስቲቆም ድረስ ደግፎታል፡፡

መደምደሚያ

የኔ ትውልድ አንድ በአንድ እያለ በመመናመን ላይ ነው፤ የእኔም ተራ እየደረሰ ነው፤ ለኢሰመጉ የማወርሰው መሬትና ቤት የለኝም፤ መጻሕፍት ሞልተውኛል፤ የአዋሳ ሕዝብ አሁን ኢሰመጉ ያለውን የመጻሕፍት ቤት ለሕዝብ የሚጠቅም ሊሆን በሚችልበት ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል ቤት ቢያገኝለት አብዛኛዎቹን ለአዋሳ ለማውረስ ወስኛለሁ፤ ቤትና አስተናባሪ ከአልተገኘለት ውርሱን ለማስፈጸም አስቸጋሪ ይሆናል፤ በአዲስ አበባ ብዙ አማራጭ የመጻሕፍት ቤቶች ስላሉ የአዋሳን ኢሰመጉ መጻሕፍት ቤት ማጠናከሩ የተሻለ ይመስለኛል፤ በተጨማሪም ከኢሰመጉ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ አዋሳ በጣም ልቆ የቆየ በመሆኑ ለማበረታታት ነው፤ ከአዋሳ ነዋሪዎች መሀከል አንድ ቤተ መጻሕፍቱን በስሙ ለማስጠራት የሚፈልግ ሰው ለኢሰመጉ አንድ ቤት የሚሰጥ ወይም የሚያወርስ እንዲገኝ ጥረት ሊደረግ ይገባል፡፡
በመጨረሻም ለዛሬ በዓል
በስደት ላሉት ለአበበ ወርቄና ለዓሥራት ገብሬ
በሕመም ምክንያት በመሀከላችን ላልተገኙት አንዳርጋቸው ተስፋዬና ለጌታቸው ተሰማ
በሕይወት ለሌለው አብረ-አደጌ ወርቁ ተፈራ፣ ነፍሱን ይማረው፤
ለቸርነቱ ወደር ለሌለው ጓደኛዬ አባተ የኔው — ኢሰመጉ ከስዊስ አምባሳደር ጋር ውዝግብ በተነሣበት ጊዜ መኪናዬንም ቢሆን ሸጬ አሥር ሺህ ዶላርህን እመልስልሃለሁ ያልሁትን በጋዜጣ እንብቦ፣ እቤቴ ድረስ መጥቶ የአሥር ሺህ ዶላር ቼክ ጽፎ ‹‹መኪናህን እንዳትሸጥ፤ ያውልህ አፍንጫው ላይ ወርውርለት!›› ያለኝ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ሰው ነው፤ ነፍሱን ይማረው፡፡

በነዚህ በስድስት ሰዎች ስም የአምስት ወር ጡረታዬን አውጥቼ የአምስት መቶውን ብር ቲኬት በስማቸው በመግዛት ላስታውሳቸው እፈልጋለሁ፡፡

ላስታውሳቸው እፈልጋለሁ፡፡

Posted in አዲስ ጽሑፎች | 2 Comments

አንድ ጉድ ልንገራችሁ!

አንድ ጉድ ልንገራችሁ!
ያለፈው እኁድ የዱሮው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ኢሰመጉ (ዛሬ በግድ ስምን ለውጦ ሰመጉ የተባለው) የሃያ አምስተኛ ዓመት በዓሉን ለማክበርና በዚያው እርዳታ ለመሰብሰብ በደሳለኝ ሆቴል የምሳ ግብዣ አዘጋጅቶ ነበር፤ ኢትዮጵያውያንም የውጭ አገር ሰዎችም ነበሩ፤ ፕሮግራሙ ሲካሄድ ቆይቶ አንድ ሰዓት ያህል ሲቀረው ፖሊሶች መጥተው ፕሮግራሙ እንዲቋረጥ አዘዙ፤ ተቋረጠና ወደየቤታችን ሄድን! ስብሰባው የተደረገው አስፈላጊው ፈቃድ ሁሉ በጽሑፍ ከተገኘ በኋላ ነበር፤ ምናልባት ፈቃጆቹና ከልካዮቹ አይተዋወቁም ይሆናል!
ይኸ በዶላር የሚገዛ የውሸት የትምህርት ማዕርግ ማሰብ አያስተምርም፤ በተፈጥሮም የማሰብ ችሎታ የሌላቸው በዚያ ሰፈር መጥፋታቸው ገና ብዙ ጥፋቶችን ያመጣል፤ በዚህ በግብዣው ጉዳይ፡
• አንደኛ ሰዓቱ አልቋል ‹‹መንግሥት ፈቅዶ ስብሰባው ተካሄደ፤›› ቢባል ‹‹መንግሥት ስብሰባውን ዘግቶ ሰው ተበተነ፤›› ከሚባል ሳይሻል አይቀርም፤
• ሁለተኛ ብዙ የውጭ አገር ሰዎች ነበሩ፤ ከልካዮች የእነዚህ የውጭ ሰዎች ታዛቢነት ጉዳትን አያስከትልም የሚል ግምት ነበራቸው ማለት ነው?

Posted in አዲስ ጽሑፎች

ደንቁሩ በአዋጅ

 

እግዚአብሔር ዓይንን ፈጠረና እዩበት አለ፤
እግዚአብሔር ጆሮን ፈጠረና ስሙበት አለ፤
እግዚአብሔር አእምሮን ፈጠረና አስቡበት አለ፤
እግዚአብሔር አንደበትን ፈጠረና ተናገሩበት አለ፤

ወያኔ አይሆንም አለ!
በዓይንህ አትይ፤
በጆሮህ አትስማ፤
በአእምሮህ አታስብ፤
በአንደበትህ አትናገር፤

አበሻ ተዋረደ!
ዓለም እየሰማ ድንቁርና ታወጀበት!

ማን ያሸንፋል?
እግዚአብሔር አለ፤
ወይስ ወያኔ አለ?

Posted in አዲስ ጽሑፎች | 1 Comment

መንፈሳዊ ወኔና ሥልጣን

መስፍን ወልደ ማርያም
ጥቅምት 2009

ባለሥልጣኖቻችን ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን በጣም የናቋቸው ይመስላል፤ ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቀውን ሁሉ ያውቃሉ፤ የኢትዮጵያን ቴሌቪዥን ያያሉ፤ የኢትዮጵያን ራድዮ ይሰማሉ፤ ባሎቻቸውና አባቶቻቸው የዛሬ ሳምንት የተናገሩትን ረስተው፣ ወይም ክደው፣ ወይም ዋሽተው ተቃራኒውን ሲናገሩ መሸማቀቃቸው አይቀርም፤ እንዲህ ያለው የንግግር መገለባበጥ የእምነት መገለባበጥን፣ የማሰብ ችግርን፣ የመንፈስ ልልነትን ያሳያል፤ ታዲያ ሚስቶችና ልጆች እየተሸማቀቁ አካላቸውም ነፍሳቸውም ሲያልቅ ለባለሥልጣኖቹ አይታወቃቸውም? ወይስ የቤተሰብ አባሎች ጠባይ እየሆነ ሽታዬ ሽታዬ እየተባባሉ ነው?
አንዳንዶች ባለሥልጣኖች ወንበሩ ላይ የወጡት እግዚአብሔርን ሳይይዙ ነው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ እግዚአብሔርን ይዘው ወንበሩ ላይ ይወጡና እግዚአብሔርን ከተቆናጠጡ በኋላ እግዚአብሔርን ከውስጣቸው የሚያስወጡት ይመስላል፤ የእግዚአብሔርን መንገድ ብዙ አናውቅምና ለሱ እንተውለት፡
ግን እኛም ሰዎቹ ባለሥልጣኖቻችን እውነተኞች ቢሆኑ፣ በትክክል ቢያስቡና የመንፈስ ልዕልና ቢኖራቸው እንኮራባቸው ነበር፤ አርአያም ይሆኑን ነበር፤ ልጆቻቸውም ከልጆቻችን ጋር ተግባብተው ያድጉ ነበር፤ ባለሥልጣኖቻችን ለቤተሰቦቻቸው ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ የመንፈስ ልዕልና አርአያ እንዲሆኑልን ኃላፊነት አለባቸው፤ ተደጋግሞ እንዳየነው በየዘመኑ የተሰየሙልን ባለሥልጣኖቻችን የኃላፊነት ግዴታ የሚጎድላቸው ናቸው፤ ለአምላካቸው የኃላፊነት ግዴታ አይታይባቸውም፤ ለቤተሰቦቻቸው የመንፈሳዊ ኃላፊነት ግዴታ አላደረባቸውም፤ ለአገራቸውና ለወገናቸው ደኅንነትና ብልጽግና ኃላፊነት አይሰማቸውም፤ የሥልጣን ወንበሩ የሚፈለገው ለሁለት ዓላማዎች ብቻ ነው፤ ለጉልበትና ለሀብት ብቻ!
በእኔ ዕድሜ ሥልጣንና የኃላፊነት ስሜት ሲጋጩና ነፍስን ሲገነጥሉ ‹‹በቃኝ!›› ብለው የመንፈስ ልዕልናቸውን መርጠው ሥልጣናቸውን ያስረከቡት ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ኃብተ ወልድ ናቸው፤ አጼ ኃይለ ሥላሴ ፊት ቀርበው፣ የማይደፈረውን ደፍረው፣ አሻፈረኝ! የማይባለውን አሻፈረኝ! ብለው ሥልጣን የሌለበትን የአገር ኃላፊነት በአጼ ኃይለ ሥላሴ እግር ስር አስቀምጠው ራሳቸውን ነጻ አወጡ! ትልቅ ድፍረት ነው፤ እንኳን በአገር ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትርን የሚያህል ሹመትና በትንሹ በአውራጃ አስተዳደሪ ደረጃም ቢሆን የጃንሆይን ትእዛዝ አልቀበልም ማለት ዋጋ ያስከፍላል፤ (እኔ በትንሹ ከፍያለሁ!)
ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ለአገራቸው ብዙ የደከሙ ሰው ናቸው፤ በታወቀው በፈረንሳዩ ሶርቦን ዩኒቨርሲቲ ተኮትኩተው ያደጉና በኢጣልያ ወረራ ጊዜ በአውሮፓ እየተዘዋወሩ ለኢትዮጵያ ነጻነት የታገሉ ሰው ናቸው፤ ከጦርነቱም በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተባበሩት መንግሥታት የአውሮፓውያን (የነጮች)ኃይል አክሊሉ በልበ-ሙሉነት ከምዕራባውያን ኃይሎች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በክርክር ሲተናነቁ ነበር፤ የምዕራባውያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጸሐፌ ትእዛዝን በጥቁርነታቸው ሊንቁ ሲቃጡ በአእምሮና በመንፈስ ልዕልናቸው እያሳፈሩ ልካቸውን አሳይተዋቸዋል፤ ነጮቹ በግዳቸው እንዲያከብሯቸው አደረጉ፤ እኝህ ሰው ናቸው በባህል ተጽእኖና በይሉኝታ ሥልጣን የሌለበትን ኃላፊነት ተቀብለውና ተሸክመው ለብዙ ዓመታት በጨዋ ደንብ የታገሉት፤ በመጨረሻም በቃኝ! አብዮታዊ እርምጃ ወሰዱና ለአጼ ኃይለ ሥላሴ ገበጣ መጫወቻ አልሆንም ሲሉ የኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ አቅጣጫን ያዘ፡፡
የዛሬው ጠቅላይ ሚኒስትር ከመጽሐፍ ቅዱስ ካልተማረ ከጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ ሊማር ይችላል፤ በመማርም ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ከአደጋ ሊያድን ይችል ይሆናል፤ አንድ ሰው ታሪክን ለመሥራት ይችላል፤ እግዚአብሔር መንፈሳዊ ወኔውን ይስጠው!

Posted in አዲስ ጽሑፎች | 2 Comments

የወያኔ አገዛዝና የኢትዮጵያ ወደፊት

ለማዳመጥ      http://bit.ly/2cIGTYM

Posted in አዲስ ጽሑፎች